የቻይና መንግሥት ጋዜጣ የአሜሪካው ፕሬዝንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) በጀት እንዲቋረጥ መወሰናቸውን አወደሰ።
የአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) እና ራድዮ ፍሪ እስያ (አርኤፍኤ) በቻይና መንግሥት ዙሪያ ለዓመታት ሲዘግቡ የቆዩ ሲሆን ትራምፕ የጣቢያዎቹ በጀት እንዲቀነስ ወስነዋል።
ውሳኔው የተላለፈው ባለፈው አርብ ነው። 1300 የቪኦኤ ሠራተኞች በግዴታ እረፍት እንዲወጡ ተነግሯቸዋል።
ተቺዎች ውሳኔው ዲሞክራሲን ወደኋላ የሚጎትት ነው ቢሉም ግሎባል ታይምስ የተባለው የቻይና መንግሥት ጋዜጣ ቪኦኤ አሁን "እንደ አሮጌ ምንጣፍ ተጥሏል" ብሏል።
ዋይት ሐውስ የትራምፕን ውሳኔ በተለመከተ በሰጠው መግለጫ "ግብር ከፋዮች ከዚህ በኋላ ለፕሮፖጋንዳ ገንዘብ አይከፍሉም" የሚል አስተያየት።
ትራምፕ ያስተላለፉት ውሳኔ በኮንግረሱ ድጋፍ ያገኘ ሲሆን ዩኤስ ኤጀንሲ ፎር ግሎባልድ ሚድያ የተባለውን ድርጅት ዒላማ ያደረገ ነው። ይህ ኤጀንሲ ቮኦኤ፣ ራድዮ ፍሪ እስያ እና ራድዮ ፍሪ አውሮፓ የተባሉትን ጣቢያዎች ያስተዳድራል።
እኒህ ጣቢያዎች የፕረስ ነፃነት የላቸውም በሚባሉ ሥፍራዎች በሚሠሯቸው ዘገባዎች ይታወቃሉ። ቻይና፣ ካምቦዲያ፣ ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ከእኒዚህ ሥፍራዎች መካከል ይመደባሉ።
ቪኦኤ ቻይና ውስጥ እንዳይሰራጭ ቢታገድም አድማጮች በአጭር ሞገድ ራድዮ አሊያም 'ቪፒኤን' ተጠቅመው ማግኘት ይችላሉ።
አርኤፍኤ በተለይ በካምቦዲያ ስላለው የመብት ጥሰት በመዘገብ የሚታወቅ ሲሆን የቀድመው የሀገሪቱ አምባገነን መሪ ሁን ሴን የትራምፕን ውሳኔ "ለሐሰተኛ ዜና ትልቅ አስተዋፅዖ የሚያበረክት" ሲሉ አሞግሰውታል።
በቻይና ዢንግጂያንግ ግዛት በሚገኙ ካምፖች የቻይና መንግሥት የኡጉር ሙስሊሞችን አፍኖ ማስቀመጡን ቀድመው ከዘገቡት መካከል አንዱ አርኤፍኤ ነበር።
ቤይጂንግ ይህን ወቀሳ የማትቀበለው ሲሆን ሙስሊሞች በፍላጎታቸው "ትምህርት ለመቅሰም" ነው የገቡት፤ የካምፖቹ ዓላማ ደግሞ "ሽብርተኝነት እና ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነትን" መከላከል ነው ትላለች።
ቪኦኤ ከሰሜን ኮሪያ ጠፍተው ስለሚወጡ ዜጎች እንዲሁም የቻይናው ኮሚዩኒስት ፓርቲ በኮቪድ ወረርሽኝ የሞቱ ሰዎችን ለመደበቅ ስላደረገው ሙከራ በሠራው ዘገባ ሽልማት ተበርክቶለታል።
በዋነኛነት በራድዮ የሚተላለፈው የአሜሪካ ድምፅ በአማርኛ እና በማንድሪን እንዲሁም በበርካታ ቋንቋዎች በተለያዩ ሀገራት ይተላለፋል።
የቻይና መንግሥት ሚድያ የሆነው ግሎባል ታይምስ ጋዜጣ የቪኦኤን መዘጋት አወድሶ ጣቢያው "የውሸት መፈብረኪያ ነው" ብሏል።
የቀድሞ የቢቢሲ ጋዜጠኛ የነበረችው እና በቪኦኤ መዘጋት ምክንያት ሥራዋን ያጣችው ቫልድያ ባራፑትሪ የቻይናው ጋዜጣ ያወጣው ዘገባ "የሚያስደንቅ አይደለም" ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የናዚ ፕሮፖጋንዳንድ ለመገዳደር የተቋቋመው ቪኦኤ በ50 ቋንቋዎች የሚተላለፍ እና ከ360 ሚሊዯን በላይ ሳምንታዊ አድማጮች ያሉት ጣቢያ ነው።
በቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ፣ በኮሚዩኒስት ኩባ እና በቀድሞው ሶቪዬት ሕብረት ተላልፏል። በርካታ ቻይናዊያን እንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲለምዱም አስተዋፅዖ አድርጓል።
የቪኦኤ ዳይሬክተር ማይክል አብራሞዊትዝ የትራምፕ ውሳኔ ቪኦኤን ነቅንቆታል ብለው "በተቃራኒው እንደ ኢራን፣ ቻይና እና ሩሲያ ያሉ ሀገራት ቢሊዮን ዶላሮች እያፈሰሱ የአሜሪካን ስም እያጠለሹ ነው" መሆኑን ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment