ለሰውነታችን ጠቃሚ የሆነው ቫይታሚን ዲ የሚገኘው በፀሐይ ጨረር አማካኝነት በተፈጥሮ ሂደት ነው። ኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት የምታገኝ ሀገር ብትሆንም በቅርቡ የወጣ መረጃ ብዙዎች የቫይታሚን ዲ እጥረት እንዳለባቸው ያመለክታል። ለምን ይሆን?
ቫይታሚን ዲ
የቫይታሚን ዲ እጥረት በመላው ዓለም ሰዎች ላይ ስለሚታይ አሳሳቢ መሆኑ ይነገራል። በተለይ በዓመት ውስጥ የፀሐይ ብርሃንም ሆነ ሙቀቷን በውስን ወራት ብቻ በሚያገኙ የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ሃገራት ሰዎች በተለያየ መልኩ በሚዘጋጁ ተጨማሪ የመድኃኒት ምግቦች ካላካካሱት ዘርፈ ብዙ የጤና ችግር እንደሚያስከትል ሀኪሞች ይመክራሉ።
በአብዛኛው በእነዚህ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የቫይታሚን ዲ እጥረት እንዳለባቸው በምርመራ እንደተደረሰበት ሲናገሩ ሲሰማ ያሉበት ሀገር የፀሐይ ብርሃን እንደልብ ስለማይገኝ ነው ሊባል ይችላል። ይኽ ችግር ግን ኢትዮጵያም ውስጥ እንዳለ መነገሩ ግን መንስኤው ምን ይሆን የሚል ጥያቄን ያስከትላል።
የውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ንብረት ገዳሙ በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህርና በደብረ ታቦር ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ይሰጣሉ። ለሰውነታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ቫይታሚን ዲ 90 በመቶ የሚሆነው የሚመረተው ከፀሐይ በሚገኝ ጨረር በቆዳችን አማካኝነት በተፈጥሮ እንደሚገኝ ነው የሚያስረዱት።
«ቫይታሚን ዲ ምንድነው የሚለውን ስናይ ለሰውነታችን በጣም አስፈላጊ ከሆኑትና ብዙ የሰውነታችንን እንቅስቃሴ ከሚቆጣጠሩ ቫይታሚኖች አንዱ ነው፤ ቫይታሚን ዲ 90 በመቶ የሚሆነው ከቆዳ የሚመረት ሲሆን ከቆዳ ለመመረት ደግሞ አልትራቫዮሌት ቢ የተባለ የፀሐይ ጨረር ያስፈልገዋል።»
ዶክተር ንብረት እንደገለጹት ቫይታሚን ዲ በዋናነት በሰውነታችን ውስጥ ካልሲየም የተባለውን ንጥረነገር እንቅስቃሴ ይወስናል። ካልሲየም ደግሞ በተለይ ለአጥንት ጥንካሬ ያለው ጠቀሜታ ወሳኝ ነው።
የውስጥ ደዌ ህክምና ባለሙያው እንደገለጹልን ቆዳችን ቫይታሚን ዲ እንዲያመርት የፀሐይ ጨረር ይፈልጋል። ይኽ በሌለበት እንዴት ነው በየቀኑ የሚያስፈልገንን ቫይታሚን ዲ ሰውነታችን የሚያገኘው የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ዶክተር ንብረት፤ እንደሚሉት ከፀሐይ ጨረር በተጨማሪ ከተለያዩ የዓሣ ዓይነቶች እንዲሁም ከእንቁላል አስኳል ቫይታሚን Dን ማግኘት ይቻላል። በመድኃኒት መልክ የተዘጋጁ የቫይታሚን ዲ እንክብሎችን በተጨማሪ ምግብነት መውሰድም ሊረዳ እንደሚችል ጠቁመዋል። በዋናነት ግን እነዚህ በገንዘብ የሚገዙ እና እንደልብ የማይገኙ ምግቦች በሌሉበት ያለምንም ወጪ የፀሐይን ጨረር መጠቀሙ በተፈጥሮ ቫይታሚን ዲን ለማግኘት እንደሚረዳ ነው የህክምና ባለሙያው አጽንኦት የሰጡት።
የቫይታሚን ዲ እጥረት መረጃ
የኢትዮጵያ የ13 ወር ፀጋ የሚለው የቱሪዝም መሪ ቃል በዋነኝነት የፀሐይን ብርሃን እና ሙቀት መነሻ ያደረገ መሆኑ ነው የሚገለጸው። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ ይፋ የወጣ መረጃ ዓመቱን ሙሉ ፀሐይ በምታገኘው ሀገር በርካቶች ለቫይታሚን ዲ እጥረት መጋለጣቸውን ያመለክታል። እንዴት ሊሆን ቻለ?
ዶክተር ንብረት ኢትዮጵያ ውስጥ ለጤና እጅግ አስፈላጊ የሆነው ቫይታሚን ዲ ለማግኘት በነጻ እና እንደልብ ተፈጥሮ ያቀረበችውን የፀሐይ ጨረር መጠቀም አማራጭ የለውም። ሆኖም ግን ዓመቱን ሙሉ ፀሐይ እንደልብ በምትገኝበት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙዎች ለቫይታሚን ዲ እጥረት መጋለጣቸውን የምርመራ ውጤት አሳይቷል። በጥናቱ መሠረትም ከገጠር ነዋሪዎች ይልቅ የከተማ ነዋሪዎች በይበልጥ ለቫይታሚን ዲ እጥረት የተጋለጡ ናቸው።
ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው የቆዳ ቀለማችን ጥቁር እንደመሆኑ ረዘም ላለ ጊዜ ፀሐይ መሞቅ ሊኖርብን ነው። ግን በየትኛው ሰዓት ይሆን ለዚህ የሚትጠቅመንን ፀሐይ የምናገኘው? ዶክተር ንብረት እንደሚሉት በኢትዮጵያ አቆጣደር ከጠዋቱ አራት ሰዓት እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ ከ20 ደቂቃ ጀምሮ ረዘም ላለ ጊዜ ሰውነታችን በቂ የፀሐይ ጨረር እንዲያገኝ ማድረግ ይኖርብናል። የፀሐይ ጨረር ማግኘት ያለበት ደግሞ በተለይ ፊታችን እና የእጃችን ክንድ መሆን እንዳለበትም ነው የመከሩት።
እርግጥ ነው በተጠቀሰው ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ጃንጥላ ይዞ መሄድ፤ አለያም ጥላ ባለበት አካባቢ መቀመጥን የመሳሰለ ልማድ አለ። ዶክተር ንብረትም በተለይ በከተማ አካባቢ ይህንኑ ታዝበዋል። በዚያ ላይ የኢትዮጵያን የቆዳ ቀለም ረዘም ላለ ጊዜ የፀሐይ ከሚያስፈልጋቸው ወገን ነው። ብዙውን ጊዜ ጃንጥላን ለፀሐይ መከላከያ መጠቀሙ ወገኖችም ሰውነታቸው የሚያስፈልገውን ቫይታሚን ዲ እንዳያገኝ እንቅፋት እየሆኑ መሆኑን አመልክተዋል።
No comments:
Post a Comment