Saturday, June 29, 2024

በአማራ ክልል በዚህ ሳምንት ከ27 በላይ የሚሆኑ ‘ሰላማዊ ሰዎች’ “በመንግሥት ኃይሎች” መገደላቸው ተነገረ

 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ሰሜን ጎጃም ዞኖች በቀናት ልዩነት “የመንግሥት ኃይሎች” ቤት ለቤትና መንገድ ላይ ‘ሰላማዊ ሰዎችን’ መግደላቸውን የዐይን እማኞችና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የደብረሲና ከተማ


ጥቃቶቹ ሰኞ ሰኔ 17 እና ረቡዕ ሰኔ 19፤ 2016 ዓ/ም መፈጸማቸው የተነገረ ሲሆን፤ በጥቃቶቹም ከ27 በላይ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ ከደብረ ሲና ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ ሾላ ሜዳ በተባለች አነስተኛ የገጠር ከተማ ሰኔ 19 በመንግሥት ኃይሎች ደርሷል በተባለ ጥቃት ቢያንስ 15 ሰዎች መገደላቸውን እና አራት የሚሆኑ ሰዎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በከተማዋ ‘አጋም በር መገንጠያ’ በተባለ ሰፈር ጥቃቱ 11፡30 አካባቢ እንደተፈጸመ ለቢቢሲ የተናገሩ አንድ ከጥቃቱ የተረፉ እማኝ፤ በጥቃቱ በአብዛኛው ማዳበሪያ ለመውሰድ ከተለያዩ ቀበሌዎች የመጡ አርሶ አደሮች እንደተገደሉ ገልጸዋል።

ከዘጠኝ እስከ 12 የሚሆኑ ወታደሮች “ቀጥታ መጥተው ሱቅ ላይ የተኩስ እሩምታ ጀመሩ” ያሉት የዐይን እማኙ፤ እሳቸውን ጨምሮ ማዳበሪያ ለመጫን በመጠባበቅ ላይ የነበሩ አርሶ አደሮች የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን ተናግረዋል።

“የመንግሥት ኃይሎች” ማሙሽ በተባለ ሻይ ቤት ‘ሻይ ቡና’ እያሉ ነበር የተባሉ ስምንት የሚሆኑ ሰዎችን ቤቱ ውስጥ ገብተው እንደገደሏቸው ተናግረዋል።

“ማዳበሪያ ለመጫን እዛው አካባቢ ላይ ነበርን። ስምንት ሰዎች የወደቁት እዛው ሻይ ቤት ነው” ያሉት እማኙ፤ እሳቸውና ጥቂት ሰዎች በጓዳ ዘለው ማምለጣቸውን ገልጸዋል።

“ድንገት መጥተው ጨርሰውን ሄዱ” ሲሉ ጥቃቱን የገለጹ ሌላ የዐይን እማኝ እሳቸውም ጥቃቱ የተፈጸመበት ቤት ውስጥ እንደነበሩ ተናግረዋል።

“እኔ ምን እንዳዩ እንጃ። ማታ ነው፤ ሰዓት እላፊ እንኳ መጥተው አያውቁም ነበር። 12፡00 ላይ መጥተው አጋም በር መገንጠያ የምትባል መስመር አለች፤ እዛ ላይ ተኩስ ጀመሩ። አንድ አምስት ስድስት ሰዎች መንገድ ላይ ጣሉ [ገደሉ]። ከዚህ የተረፉትን ደግሞ ሻይ ቤት እየገቡ በተቀመጡበት እርፍርፍ ነው ያደረጓቸው” ሲሉ ጥቃቱን ገልጸዋል።

እርሳቸው ከነበሩበት ሻይ ቤት ብቻ 11 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን የተናገሩት እማኙ፤ ሦስት ከሚሆኑ ሰዎች ጋር በጓዳ በር አምልጠው ሕይወታቸውን መታደግ ቢችሉም፤ በ20ዎቹ እድሜ ላይ ይገኛል ያሉት ወንድማቸው መንገድ ላይ ተገድሎ እንዳገኙት ተናግረዋል።

በጥቃቱ ከአያቶቹ ጋር የሚኖር የ14 ዓመት ታዳጊ ልጃቸው ቤታቸው አጠገብ ከሚገኝ መንገድ ላይ መገደሉን የተናገሩ አንድ አባት፤ በደብረ ሲና ሀዘን መቀመጣቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተኩስ ድምጽ መስማታቸውን የተናገሩ አንድ የአካባቢው ነዋሪ እሳቸው የሚያውቁት 11 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጠው፤ ቁስለኞች ሾላ ሜዳ እና ደብረ ብርሃን ሆስፒታል መግባታቸውን ተናግረዋል።

የ11ዱ ሟቾችን ስም ዝርዝር መሰብሰብ እንደቻሉ የተናገሩ ሌላ እማኝ፤ በማግስቱ ሰኔ 20 አራት ተጨማሪ አስከሬን ተገኝቷል ሲሉ የሟቾቹ ቁጥር 15 ነው ብለዋል።

“. . . አብዲላቅ፣ ማኔ አምባ፣ አራጨለንቆ፣ ወይን ውሃ፣ ሸንኮርጌ፣ እንዶዴ፣ ዶቃይት፣ ድብ አምባ ቀበሌዎች ትናንት [ሰኔ 20] ወደ ስምንት ደብር ቀብረን ነበር” ብለዋል።

በአካባቢው ለለቅሶ መጥተዋል የተባሉ ሦስት የፋኖ ታጣቂዎችን ተከትለው ሳይመጡ አልቀረም የተባሉት “የመንግሥት ኃይሎች ስለ ታጣቂዎቹ መረጃ በመፈለግ ግድያውን ፈጽመዋል” ብለዋል።

ጥቃት አድራሾቹ “መከላከያ ሰራዊት” ለመሆናቸው በለበሱት የደንብ ልብስና በአካባቢው በቅርብ ርቀት ሲና በተባለ ስፍራ ካምፕ በመመስረታቸው እንዳረጋገጡ ገልጸዋል።

በሌላ ተመሳሳይ ጥቃት በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ አዴት ከተማ በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ሰኔ 17፤ 2016 ዓ.ም. ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በጥቃቱ 11 ንጹሃን ሰዎች በመንግሥት ኃይሎች መገደላቸውን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ድርጊቱን ከበቀል ጋር አያይዘውታል።

በእለቱ የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግሥት ኃይሎች ለሰዓታት የዘለቀ “ከባድ ውጊያ” ማድረጋቸውን ተከትሎ ከሰዓት 9፡00 አካባቢ ጥቃቱ መፈጸሙን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ አንድ ሴትና 10 ወንዶች እንደተገደሉ ገልጸዋል።

ግድያው የፋኖ ታጣቂዎች ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ 02 ቀበሌ እርሻ ሰብል በተባለ ሰፈር መንገድ ላይ እና ቤት ለቤት መፈጸሙን የጠቆሙት ነዋሪዎች፤ “ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ” በሚል ግድያው ተፈጽሟል ብለዋል።

“ፋኖ ከተማውን ተቆጣጥሮ ውሎ በወጣበት ሰዓት ብዙ ኃይል ስለተመታባቸው በዛ ብስጭት ያገኙትን ሁሉ ነበር እየመቱ የነበረው” ሲሉ ስለ ግድያው የተናገሩ አንድ የአዴት ከተማ ነዋሪ፤ በጉልበት ስራ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ 11 ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።

“ሁለት ልጆች ናቸው ውጭ ላይ [መንገድ ላይ] የተመቱት እንጂ ሌላውን ከቤት እያወጡ ነው የገደሉት” ሲሉ ስለ ጥቃቱ የተናገሩ ሌላ ነዋሪ፤ 18 ዓመት ያልሞላውን ታዳጊ ጨምሮ ሟቾቹ አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው ብለዋል።

የ11 ሰዎች ግድያ በተፈጸመ በማግስቱ ሰኔ 18 ደግሞ ከከተማው መውጫ ባለ ርብርብ በተባለ አካባቢ ተጨማሪ አራት ሰዎች ተገድለዋል በማለት የሟቾቹ ቁጥር ከፍ እንደሚል የጠቆሙ ሌላ ነዋሪ፤ ከሟቾቹ ውስጥ አባትና ልጅ እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

የሟቾቹ ቀብር ያኑ ቀንና በማግስቱ ‘ቀለሞ ገብርኤል’ በተባለ ቤተ-ክርስቲያን መፈጸሙን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ግድያውን ተከትሎ ከክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር በ43 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው አዴት ከተማ “በሀዘን ተውጣለች” ብለዋል።

“[ከተማው] በጣም በሀዘን ተውጧል። የእያንዳንዱን ሰው ፊት ስታይው ለቅሶ፤ እንባ ነው። ትናንት ለቅሶ ነበረ፤ ማነው የእነዚህ ልጆች ቤተሰብ ብለሽ መለየት አትችይም [ነበር]” ሲሉ ማሕበረሰቡ በከባድ ሀዘን ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ግድያውን ተከትሎ በአዴት ከተማ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ገደብን ጨምሮ የንግድ ተቋማትም ዝግ እንደሆኑ የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ ከዚህ በፊትም እንደዚህ አይነት ጥቃቶች ደርሰው እንደሚያውቁ ጠቁመዋል።

“ሆቴሎች ዝግ ናቸው፤ ማንኛውም የስራ እንቅስቃሴ የለም፤ የመኪና መንገድ ዝግ ነው፤ ባጃጅ ሳይቀር ዝግ ነው [የለም]” ሲሉ በከተማዋ ውጥረት እንዳለ የጠቆሙት አንድ ነዋሪ፤ በቤተ-ክርስቲያን ከማክሰኞ እለት ጀምሮ ለሰባት ቀናት የጸሎትና የፍትሃት መርሃ ግብር ታውጇል” ሲሉ ሌላ ነዋሪ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ግድያዎቹን አስመልክቶ የክልሉን የመንግሥት ባለስልጣናት ለማናገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በአማራ ክልል በሰኔ ወር መጀመሪያ ቀናት በምዕራብ ጎጃም እና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች “በመንግሥት ኃይሎች” ተፈጽሟል በተባለ ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በጀመረው የክልሉ “የትጥቅ ግጭት” የፋኖን እና የመንግሥት ኃይሎችን ውጊያ ተከትሎ ‘ሰላማዊ ሰዎች’ የጥቃት ሰለባ እንደሚሆኑ ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ አስታውቀዋል።

Source: https://www.bbc.com/amharic/articles/cley9eeyxv0o

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time