Monday, May 14, 2018

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከእስር ለመፍታት ተወስነ

በእስርና እንግልት ላይ የነበረውን የአርበኞች ግንቦት ስባት ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ከእስር ለመፍታት ተወስኖ በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የተመራ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አመለከቱ።
መረጃውን ለዋዜማ ያደረሱና ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደነገሩን አቶ አንዳርጋቸው እንዲፈታ ውሳኔ ከተላለፈ በርካታ ቀናት ተቆጥረዋል። በቅርቡ ከእስር ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል።
አንድ የፍትሕ ሚንስቴር ባልደረባ ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ ጉዳዩ በመስሪያ ቤታቸው አካባቢ መነጋገሪያ እንደነበርና ጉዳዩ በከፍተኛ ባለሥልጣናት በኩል በምስጢር ተይዞ ቆይቷል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። አቶ አንዳርጋቸው ሲፈታ በቀጣይ በሚኖራቸው የፖለቲካ ሚና ላይ ንግግር መደረግ አለበት ብለው የሚያምኑ ወገኖች እንዳሉ የነገሩን እኚሁ ግለሰብ በማረሚያ ቤቶች፣ በደኅንነት መሥሪያ ቤቱ፣ ግንባሩ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ብድኖች እና በጠቅላይ ሚንስትሩ ጽሕፈት ቤት መካከል መግባባት ለመፍጠር እየተሞከረ መሆኑን መስማታቸውን ነግረውናል። በአንዳርጋቸው ጉዳይ በአራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች መካከል ስለነበረ ውይይት ብዙ የተሰማ ነገር የለም። ይሁንና ብአዴን የሚደርስበትን የሕዝብ ጫና ለማስታገስ የአንዳርጋቸውን መለቀቅ ሳይገፋፋ እንዳልቀረ ይገመታል።
ስለጉዳዩ ከአንዳርጋቸው ቤተሰቦችም ሆነ ከአርበኞች ግንቦት 7 እስካሁን የተባለ ነገር የለም። ወሬው ባለፉት 3 ቀናት በስፋት መሰማት የጀመረው ውሳኔውን በተለያየ ደረጃ ያሉ ሰዎች እንዲያውቁት በመደረጉ ሊሆን እንደሚችል የዋዜማ ምንጮች ተናግረዋል። የአቶ አንዳርጋቸው መፈታት በድርጅታቸው፣ አልፎም በአገሪቱ ፖለቲካ አቅጣጫ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተጽእኖ ብዙዎች በቅርበት የሚከታተሉት ጉዳይ ይሆናል።
አቶ አንዳርጋቸው ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓም ከሰንአ አውሮፕላን ጣቢያ በየመን እና በኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ ሰራተኞች ታፍኖ መወሰዱ ይታወሳል። በእስር ላይም የተለያዩ ግፍና ማሰቃየት እንደተፈጸመበት ቤተሰቦቹ እና የትግል ጓዶቹ ይናገራሉ። በተቃራኒው፣ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ላይ ቀርበው አንዳርጋቸው በጥሩ ሁኔታ መያዙን እንዲያውም “ከተማ ይጎበኛል፣ ላብቶፕ ተሰጥቶች መጽሐፍ እየጻፈ ነው” ብለው መናገራቸው ይታወሳል። ተመድ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የእንግሊዝ መንግሥት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አንዳርጋቸው እንዲፈታ ሲጎተጉቱ መቆየታቸው ይታወቃል።

ዋዜማ ራዲዎ

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time