Tuesday, December 26, 2017

መረጋጋት ያልቻሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት

ትምህርት ሚኒስቴር
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተማሪዎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች የትምህርት መቋረጥን በተደጋጋሚ ከማስከተላቸው በተጨማሪ ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ ሥጋት ፈጥረዋል።
በተለይም በተማሪዎች መካከል ማንነትን መሰረት አድርገው የሚነሱ ግጭቶችን ተከትሎ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የአካል ጉዳት ከመድረሱም በተጨማሪ ንብረትም ወድሟል።
ይህ ክስተትም የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማስተጓጎሉም ባሻገር ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች ለደህንነታቸው በመስጋት ወደየመጡበት ለመመለስ ሲገደዱ፤ ሌሎች ደግሞ ስጋት ዉስጥ ሆነው በየዩኒቨርሲቲዎቹ ባለተረጋጋ መንፈስ ይገኛሉ።
መንግሥት ነገሩን ለማረጋጋት በትምህርት ተቋማቱ ውስጥ የፀጥታ ኃይሎችን ከማሰማራቱ በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲዎቹ የሰዓት እላፊ ገደብ ለመጣልም ተገዷል።
በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች ከመንግሥት ተጠሪዎች ጋር በመሆን ከተማሪዎች ጋር ውይይት እያደረጉ መሆናቸዉንና የተማሪዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ነገር እያደረጉ መሆኑን ቢገልፁም ተማሪዎች፣ መምህራንምና ወላጆች አሁንም ስጋታቸው አልተቀረፈም።
"ሰግተናል"
በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የነበሩ በርካታ ተማሪዎች በየተቋሞቻቸው ባጋጠሙ ግጭቶች ሳቢያ ለደህንነታቸው በመስጋት የጀመሩትን ትምህርት አቋርጠው ወደየመጡበት አካባቢ ለመመለስ እንደተገደዱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸዉ ሲከታተሉ የነበሩ በርካታ ተማሪዎች በአዲስ አበባ ማደሪያ አጥተዉ ሲንገላቱ ቆይተው ብዙዎቹ ወደ ትዉልድ ቦታቸዉ መመለሳቸውን አብረዋቸው የነበሩ ተማሪዎች ተናግረዋል።
እነዚህን ተማሪዎች የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጉዳዮች ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ያናገሯቸዉ ቢሆንም ተገቢውን ምላሽ እንዳላገኙ ተማሪዎቹ ይናገራሉ።
ከተማሪዎቹ መካከልም አንዱ "አሁን ባለዉ ሁኔታ ወደመጣንበት ዩኒቨርሲቲ ተመልሰን መሄድ ስለማንችል፤ በአካባቢያችን ወደ ሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲመድቡን ጠይቀን ነበር። ትምህርት ሚኒስቴር ግን አግባብ ያለው ምላሽ አልሰጠንም" ብሏል።
"የዓመቱ ትምህርት ሲጀመር አንስቶ የተረጋጋ ሁኔታ አልነበረም" የሚለውና ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የምህንድስና ተማሪው ''ሁሌ አንድ የሚረብሽ ነገር አይታጣም። ወደ ግጭት ደረጃ ሲደርስ ደግሞ እራሴን ማትረፍ ስለነበረብኝ ከግቢ ወጥቻለዉ" ሲል ይናገራል።
የተለያዩ ተማሪዎች እንደሚሉት በዩኒቨሲቲዎቹ የሚነሱት ግጭቶችና ጥቃቶች በቀላል አጋጣሚ የሚጀመሩ ቢሆንም እንኳን የሚያስከትሉት ጉዳት ቀላል የሚባል አይደለም። የሚደርሰውን ጉዳትም ለመከላከል ተቀናጅቶ በአንድነት የሚሰራ አካል ባለመኖሩ የከፋ ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
እንዴት ተጀመረ?
በምንማርባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚከሰቱ ግጭቶችና ጥቃቶች ሳቢያ ደህንነት ተሰምቶን ትምህርታችንን መከታተል አልቻልንም ያሉ ተማሪዎች በሩን ያንኳኩበት የትምህርት ሚኒስቴር፤ ችግሩ የሃገሪቷን ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች የፈጠሩት እንጂ የህዝቡም ሆነ የተማሪዎቹ ችግር አይደለም ብሎ ያምናል።
ነገር ግን ባጋጠሙት ነገሮች ምክንያት ተማሪዎቹን በየክልላቸዉ መመደብ ግን እንደማይቻል፤ ዩኒቨርሲቲዎችም የፌደራል መንግሥት ተቋማት እንጂ የክልሎች አይደሉም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በሁሉም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች፤ ጥያቄያቸዉን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ ይገባቸዋል የሚሉት የትምህርት ሚኒስቴር የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሃረጓ ማሞ፤ አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት ጉዳዩን በተለይ የሚከታተል ክፍል እንደተደራጀ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈ ግን ችግሩ የአስተሳሰብ ክፍተት የፈጠረዉ በመሆኑ በቀጣይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ የተማሪዎቹ ስሜት ከዚህ የተለየ ነዉ። መንግሥት የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ስለሚሰራቸዉ ሥራዎች እርግጠኞች ስላልሆኑ አሁንም ስጋታቸውን የሚቀርፍ እርምጃ አላየንም ባይ ናቸዉ።
ከዚህ በተቃራኒ ሌሎች ደግሞ በየዩኒቨርስቲዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን ለማብረድና ለማረጋጋት የተሰማሩ የፀጥታ ኃይሎች ስጋት እንደሆኑባቸው የሚናገሩ ተማሪዎችም አሉ።
ካለመረጋጋቱ በኋላ ወደሚማርበት የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተመለሰው ሌላኛው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ተማሪ እንደሚለው እርሱና ጓደኞቹ ወደ ትምህርታቸው የተመለሱት ጥያቄያቸው ተመልሶ ሳይሆን በሁኔታዎች ተገደን ነው ይላል።
ተማሪዎቹ አሁንም ቢሆን በግቢው የጦር መሳሪያ የያዙ ሃይሎች መገኘት ፍርሃት እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።
ከሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ያናገርናቸው ተማሪዎችም ግቢዉ በጸጥታ ኃይሎች መወረሩን ይናገራሉ።
ወደ ትምህርት የተመለሱ ቢሆንም ያለው ሁኔታ መረጋጋትን የሚያመለክት ስላልሆነ ትምህርታቸው ላይ ማተኮር በሚችሉበት የሥነ-ልቦና ሁኔታ ላይ አለመሆናቸውን የገለፁ ተማሪዎችም አሉ።
የትምህርት ሚኒስቴር አርማImage copyrightMMINISTRY OF EDUCATION
የወላጆች ጭንቀት
ልጆቻቸውን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለይም ግጭቶች ወደ ጎሉባቸው የላኩ ቤተሰቦች ከባድ ችግር ውስጥ እንደሚሆኑ አያጠራጥርም። የልጆቻቸው በተቋማቱ መገኘት ለደህንነታቸው እንዲሰጉ ያደርጋቸዋል።
በሌላ በኩል ልጆቻቸውን ከቤት እንዲቀሩ ማድረግ ደግሞ በቀጣይ ትምህርታቸው እንዴት ይሆናል በማለት ያስጨንቃቸዋል።
ሴት ልጃቸውን ከአዲስ አበባ ባለፈው ዓመት ወደ ዩኒቨርሰቲ የላኩት አቶ መኮንን በየጊዜው በፍርሃት የተዋጠ ድምጿንና የብሄር ግጭቶችን ወሬ መስማት ጭንቀት ውስጥ እንደከተታቸው ይናገራሉ።
"አምኜ የላኳት አንድ ፍሬ ልጄ መማሩ ቀርቶ በሰላም ስለመኖር ስትጨነቅ ስሰማ በጣም ያሳዝነኛል፤ ሁሉ ቀርቶብኝ እንድትመለስልኝ ብፈልግም መግባት መውጣት አይቻልም ብላኝ ይኸው በጭንቀት ውስጥ ነኝ" ይላሉ።
ልጆቻቸው ያሉበትን ሁኔታ በትክክል የሚያስረዳና መረጃ የሚሰጥ አካል አለመኖሩ ደግሞ ስጋታቸውን እንደጨመረው ይናገራሉ አቶ መኮንን።
"ምነው እንደምንም ተቸግሬ እዚሁ ባስተምራትስ? በምን ክፉ ቀን ነው የላኳት እያልኩ እጸጸታለሁ፤ ብቻ ይሄ ቀን አልፎ በሰላም ትመለስልኝ እንጂ ዋስትና ሳላገኝ ልጄን አልካትም።''
ልጃቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ትምህርት ቤት እያስተማሩ ያሉ ሌላኛው አባትም ነገሩ ለወላጆች እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን ይናገራሉ።
የእርሳቸው ልጅ በሚማርበት የትምህርት ተቋም እስካሁን ምንም ዓይነት ግጭት ባለመፈጠሩ ልጃቸው ትምህርቱን እየተከታተለ ቢሆንም፤ የቅርብ ዘመዶችና ጎረቤቶቻቸው ልጆቻቸውን በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እያስመጡ እንደሆነ ይናገራሉ።
"የማውቃቸው ወላጆች ከተለያዩ ክልሎች ልጆቻቸውን እያስመጡ ነው። የእኔ ልጅ ባለበት ነገሮች ደህና ቢሆኑም የሌሎች ወላጆች ችግር በጣም ይሰማኛል "ይላሉ።
ባለፍው ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የነበረውን አለመረጋጋት በማሰብ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ጨርሶ ልጆቻቸውን ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርሲቲዎች ያልላኩ ቤተሰቦችንም ያውቃሉ።
እነዚህ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን አዲስ አባባ ውስጥ በተለያዩ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለማስተማር የወሰኑ ናቸው።
ነገሮች ተስተካክለው ዩኒቨርሲቲዎችም ወደ መደበኛው የመማር ማስተማር ሂደት እንዲመለሱም "በዩኒቨርሲቲዎች የሚታየው ነገር በማህበረሰቡ ያለው ፖለቲካ ትኩሳት ነፀብራቅ ነው። ስለዚህ በዩኒቨርሲቲዎች ያለውን ነገር ለመፍታት መጀመሪያ የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት" በማለት እኚህ አባት ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ።
''በዚህ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ስለሚከሰቱ ነገሮች እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ዛሬ ሰላም ቢሆን ነገ ሌላ ይሆናል። ለዚህም ነው ከእኔ ርቆ የሚገኘው ልጄ ደህንነት ዘወትር የሚያሳስበኝ። መረጋጋት አልቻልኩም'' ይላሉ ሌላ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ እናት።
ላለፉት ሳምንታት ካለበት ዩኒቨርሲቲ ተመልሶ ነገሮች እስኪረጋጉ ልጃቸው ከእርሳቸው ጋር እንዲቆይ እንዳደረጉ የሚናገሩት እናት በየዕለቱ የልጃቸውን ውሎ ይከታተላሉ። ''ምንም እንኳን ያለበት ቦታ እሩቅ ቢሆንም ዘወትር እደውልለታለሁ፤ ስልክ አልሰራ ሲለኝ በጣም እጨነቃለሁ''ይላሉ።
እኚህ እናት ስለልጃቸው ደህንነት መጨነቃቸው የሚያበቃበትን ጊዜ ይናፍቃሉ፤ ''መንግሥት ሕዝቡ የሚለውን መስማት አለበት። ካልሆነ ግን ነገሮች ከቁጥጥር እየወጡ ነው። ወደከፋ አቅጣጫ እያመራን እንደሆነ መገመት አይከብድም'' በማለት ያክላሉ።
የባህር ዳር ነዋሪ የሆኑትና ልጃቸው የሁለተኛ ዓመት የኢኮኖሚክስ ተማሪ እንደሆነች የሚናገሩት አቶ ይላቅም መፍትሄው በመንግሥት እጅ መሆኑን ጠቅሰው፤ እርሳቸውም የልጃቸው ደህንነት እንደሚያሰጋቸው ተናግረዋል።
''ይህ አሁን የምናየው ችግር ፖለቲካው ለዓመታት ሃገሪቱን የወሰደበት መንገድ ውጤት በመሆኑ አዝናለሁ። በቀደመው ዘመን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለጭቁኑ ሲጮሁና ሲንገላቱ ነበር የምናውቀው፤ አሁን ግን እርስ በርስ የጎሪጥ መተያየታቸው የተጓዝንበት መንገድን አደገኝነት የሚያሳይ ነው'' በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል።
ልጃቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህክምና እያጠና ያለው አባትም የአቶ ይላቅን ሃሳብ ይጋራሉ። በዩኒቨርሲቲዎች ዛሬ እየታየ ያለው ነገር ኢህአዴግ ላለፉት ዓመታት ያራመደው ፖለቲካ ውጤት እንደሆነ ያስረዳሉ።
ተኽላይ ገብረንስአ የተሰኘው ወላጅ ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ ከገጠር አምጥቶ ያስተማረው ወንድሙ ይማርበት ከነበረው ዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ኣቋርጦ እንዲመለስ አድርጓል። ትምህርቱ ቢቋረጥም ወንድሙ በህይወት በመመለሱ ብቻ ደስተኛ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ጎበዝ ተማሪ ስለነበር ትምህርቱን ጨርሶ ታናናሾቹን ይጠቅማል የሚል እምነት ነበረኝ። ይሁን እንጂ አሁን ወንድሜ ሥነ-ልቦናው እጅግ ተጎድቷል። ከመጣ ጀምሮም ከቤት አይወጣም። ነገሩ ለታናሽ ወንደሞቹም ተስፋ አስቆራጭ ነው" ይላል።
ትምህርት ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ
እየተስተዋሉ ባሉት ክስተቶች ተጨንቀው የሚገኙት ተማሪዎችና ወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ሁኔታው በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራንም ስጋት አላቸው።
ስማቸውና የሚያስተምሩበት ተቋም እንዳይጠቀስ የጠየቁት መምህር እንደሚሉት አሁን እየታዩ ያሉት ግጭቶችና ጥቃቶች ድንገት የተከሰቱ ነገሮች አይደሉም።
''ትምህርት ከፖለቲካ ሥርዓቱ ጋር ተጣብቆ ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ ለዓመታት ሲዘራ የነበረው የጥላቻ ፖለቲካ ውጤት ነው'' ይላሉ።
ይህ ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች በክፍል ውስጥ ሲያጋጥም እንደታዘቡ የሚናገሩት መምህር ''አሁን ገንፍሎ ይፋ የወጣው ሃገሪቱ ውስጥ ያለውን ፖለቲካዊ ውጥረት ተከትሎ ነው።''
በአዲስ አበባ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ እስራኤል ተሰማ ደግሞ ክስተቶቹ በትምህርት ሂደቱ ላይ ከባድ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ ይናገራሉ።
በተማሪዎች ላይ የሚፈጠረው ስጋት የትምህርት ፍላጎታቸውንና ዝግጁነታቸውን ይቀንሰዋል። ትምህርት የተቋረጠባቸውን ጊዜያት ለማካካስ የሚደረገው ጥረትም በተማሪዎችና በመምህራን ውጤታማነት ላይ ተፅዕኖ አለው ይላሉ።
አቶ እስራኤል ''እንዲህ አይነት የእቅድ መዛባቶች በትምህርት ተቋማቱ ፕሮግራም ላይ መስተጓጎልን ከማስከተል በተጨማሪ በትምህርት ጥራት ላይ ችግር ያስከትላሉ'' ይላሉ።
ነገሮች ተረጋግተው ተማሪዎችም ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እየተመለሱ እንደሆነ ሲገለፅ የነበረ ቢሆንም የተለያዩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ከቀናት በፊት በመቱ እንዲሁም በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት መቋረጡን ዘግበዋል። Read more here

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time