መሐመድ አብዱላሂ ሞሐሙድ 35 ዓመቱ ነው።
ከጂቡቲ ወደ የመን በጀልባ ያደረገውን የስደት ጉዞ አይረሳውም። በ20ዎቹ ዕድሜ ሳለ ነበር የተሰደደው።
ሶማሊያን ጥሎ የወጣው የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ነበር።
ከአፍሪካ ወደ የመን የሚደረገው ስደተኞች የሚጓዙበት መንገድ 'ምሥራቃዊው ኮሪደር' በሚል ይታወቃል።
በብዛት ስደተኞች ከሚጓዙባቸው መንገዶች አንደኛው ነው። እምብዛም ግን ትኩረት አላገኘም።
ይህ መንገድ በጣም አደገኛው እንደሆነም መሐመድ ይናገራል።
"መንገድ ጀምረን 30 ደቂቃ ሳይሞላ ጀልባው ይዋዥቅ ጀመረ። የየመን ሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች በአረብኛ ማውራት ጀመሩ። ስደተኞችን ከጀልባው ለመወርወር ነበር የሚመካከሩት። ከዚያም ሰባት ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አስገድደው ወደ ባሕሩ ጣሏቸው" ሲል ያስታውሳል።
መንገዱ አደገኛ ቢሆንም በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በዚህ መንገድ ይጓዛሉ።
ሚክስድ ማይግሬሽን ሴንተር እንደሚለው በየዓመቱ ከአፍሪካ ወደ የመን የሚገቡ ሰዎች 100 ሺህ ይደርሳሉ።
ስደተኞቹ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ናቸው። እንደ ሶማሊያ እና ጂቡቲ ካሉ የተቀሩት የምሥራቅ አፍሪካ አገራትም ዜጎች ይሰደዳሉ።
መሐመድ በተጓዘበት ጀልባ 47 ኢትዮጵያውያን፣ 5 ሶማሌያውየን እና 2 የየመን ሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ነበሩ።
"በጣም አስጨናቂ ነበር። ውሃ ወደ ጀልባው ይገባል። ውሃውን ለማስወጣት ስንሞክር ነበር። በሕይወት መትረፋችንን እርግጠኛ አልነበርንም" ይላል።
ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ የመን በእርስ በርስ ጦርነት እየተናጠች ነው። ስደተኞች ወደ ሳዑዲ አረቢያ መግባት ነው የሚፈልጉት። በሳዑዲ የሚፈለጉ ሠራተኞች ቁጥር ከፍተኛ ነው።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም (አይኦኤም) እንደሚለው፣ አብዛኞቹ ስደተኞች ጥያቄያቸው የኢኮኖሚ ቢሆንም በተለይ ከአማራ ክልል እና ከኦሮሚያ ክልሎች የሚሰደዱት ወጣቶች ግጭት እና እስራትን በመሸሽ ነው ከኢትዮጵያ የሚወጡት።
'ምሥራቃዊው መንገድ'
ሕገ ወጥ ስደተኞቹ ጂቡቲ በሚገኘው ኦቦክ በኩል አድርገው ደቡብ ምዕራብ የመን ወደሚገኘው ላሂጅ ይገባሉ።
ከሶማሊያ ቦሳሶ የሚነሱት ስደተኞች ደግሞ በየመን ደቡብ ምሥራቅ በሚገኘው ሻብዋህ የባሕር ዳርቻ ይደርሳሉ።
መሐመድ በሁለቱም መንገድ ተጉዟል። ከጂቡቲ ላሂጅ ለመድረስ አምስት ሰዓታት ወስዶበታል።
በአውሮፓውያኑ 2014 ወደ ሶማሊያ ከተመለሰ በኋላ በሶማሊያዋ ቦሳሶ በኩል ወደ የመን ገብቷል።
"በሁለተኛው ጉዞ አልፈራሁም። የመጀመሪያው ከጂቡቲ ያደረግኩት ጉዞ ረዥም ነበር። የመን ለመግባት 24 ሰዓት ወስዶብናል" ይላል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም እንደሚለው፣ ወደ የመን ለመሄድ ዋነኛው መንገድ ጂቡቲ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2023 ብቻ 106 ሺህ ኢትዮጵያውያን ጂቡቲ ገብተዋል። ከአገራቸው ተነስተው የጂቡቲ ድንበር ለመድረስ ሳምንታት ይጓዛሉ።
ከአማራ ክልል የሚነሱ ስደተኞች ኦቦክ ለመድረስ 400 ኪሎሜትር ይጓዛሉ።
በመኪና፣ በአውቶብስ ወይም በእግር ነው ጉዞውን የሚያደርጉት። በጋ ላይ ሙቀቱ እስከ 50 ሴንቲግሬድ ይደርሳል።
ባሕር ዳርቻ ላይ ለሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች 300 ዶላር ከፍለው የኤደን ባሕረ ሰላጤን ለመሻገር ይሞክራሉ።
የሚክስድ ማይግሬሽን ሴንተር ቀጣናዊ ዳይሬክተር አይላ ቦንፊግሎ እንደሚሉት፣ ሕገ ወጥ የሰው ዝውውር ብዙዎች የተሰማሩበት ንግድ ነው።
"100 ሺህ ስደተኞች 300 ዶላር ቢከፍሉ 30 ሚሊዮን ዶላር የሚገኝበት ሥራ ነው ማለት ነው" ይላሉ።
በየመን የተዋቀረ መንግሥት አለመኖሩ ለሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም እንደሚለው፣ ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ 1,400 ስደተኞች በጉዞ ላይ ሳሉ ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሞተዋል።
አይላ በበኩላቸው ቁጥሩ ከዚህም እንደሚበልጥ ይገምታሉ።
"ይህ ምሥራቃዊው የስደተኞች መንገድ በአህጉሪቱ በጣም አደገኛው ነው። በሕገ ወጥ መንገድ ባሕር ሲያቋርጡ የሚጠቀሙት የተበላሹ ጀልባዎች ነው" በማለት ለሚደርሰው አደጋ አንዱን ምክንያት ጥጠቅሳሉ።
ምን ያህል ስደተኞች እንደሞቱ በትክክል እንደማይታወቅ ያስረዳሉ።
ስደተኞች መንገድ ላይ ከሚገጥማቸው ፈተና ባሻገር በሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ብዝበዛም ይደርስባቸዋል።
"አምና 350 ስደተኞች አነጋግረን ነበር። ሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ስለ ጉዞው የተዛባ መረጃ ሰጥተው እንዳሳሳቷቸው ይናገራሉ" ይላሉ አይላ።
"ሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎቹ ናቸው ለብዝበዛ የሚያጋልጧቸው። አካላዊ ጥቃት፣ ዝርፊያ እና ስቃይ ይደርስባቸዋል" ሲሉም ዳይሬክተሯ ያክላሉ።
አፍሪካውያን ስደተኞች ባሕሩን ከተሸገሩ በኋላም በሚደርሱባቸው አገራትም ለብዝበዛ ይጋለጣሉ።
በግጭት የምትናጠውን የመን ካለፉ በኋላ ሳዑዲ አረቢያ ቢገቡም ብዝበዛው ይቀጥላል።
"ጦርነቱ ጉዟችንን የበለጠ ከባድ አድርጎታል" ይላል መሐመድ።
ከየመን ሳዑዲ ለ11 ቀናት በእግር መጓዛቸውን ያስታውሳል። ያለ በቂ ምግብ እና ውሃ ነበር ድንበር የተሻገሩት።
"አንድ አብራን ትጓዝ የነበረች ሴት በረሃብ እና በውሃ ጥም ሞታለች" ይላል።
ሳዑዲም ስደተኞች ድንበሯን አቋርጠው እንዳይገቡ ትከላከላለች።
No comments:
Post a Comment