Thursday, May 8, 2025

ሐኪም በመሆኔ ያተረፍኩት ድኅነትን ነው" የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች እሮሮ እና ጥያቄ

 የደሞዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ያነሱ የጤና ባለሙያዎች መንግሥት ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚመቱ ተናገሩ።

ባለሙያዎቹ ጥያቄዎቻቸውን ለመንግሥት ማቅረባቸውን የተናገሩ ሲሆን፤ ምላሽ እንዲሰጣቸውም የ30 ቀናት ቀነ ገደብ ከሰጡ ሳምንታት ተቆጥረዋል።



የጤና ባለሙያዎቹ "መኖር አቅቶናል" ያሉ ሲሆን፤ በተለያዩ መንገዶች ድምፃቸውን እያሰሙ ነው።

ሐኪም ለመሆን 23 ዓመታትን በትምህርት እንዳሳለፉ ለቢቢሲ የተናገሩት ዶ/ር ይማም እንድሪስ ጠቅላላ ሐኪም ሲሆኑ፤ በቅርቡ የማኅበራዊ የትስስር ገፅ አነጋጋሪ የሆነ የኑሮ ሁኔታቸውን የሚያሳይ መልዕክት ከምስሎች ጋር አጋርተዋል።

"ቤተሰቤ ብዙ [ገንዘብ] እንደማገኝ [ያስባሉ]፤ ሐኪም ልጅ ስላላቸው የሚኮሩ ናቸው" የሚሉት ዶ/ር ይማም፤ ለቤተሰባቸው ችግር አለመድረሳቸው ልባቸውን እንደሰበረው ተናግረዋል።

"23 ዓመት መስዋዕትነት ለከፈለልኝ ቤተሰብ በወር አንድ ኪሎ ቡና መሸፈን የማልችል ሐኪም ነው የሆንኩት። በጣም ነው የሚሰማው" ይላሉ።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በአዲስ አበባ የሚሰሩ የጤና ባለሙያ በበኩላቸው "መብላት አልቻልንም፤ ልጆቻችንን ማስተማር አልቻልንም፤ ቤት ኪራይ መክፈል አልቻልንም" ሲሉ ጥያቄያቸው የሚያድር እንዳልሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"መጀመሪያ ባለሙያው ጤነኛ መሆን አለበት እኮ ሌላ ሰው ለማከም። እርሱ በአካል፤ በአእምሮ ጤነኛ መሆን አለበት። አሁን ያለው ባለሙያ እንደዛ [ጤነኛ] አይደለም" የሚሉት ዶ/ር ይማም፤ "አብዛኛው ሐኪም በሕይወቱ ደስተኛ አይደለም። በማማረር፤ ጠዋት ቁርስ በልቶ ስለሚበላው ምሳ የሚያስብ ሐኪም ነው ያለው" ብለዋል።

"እኔ ነኝ ለእነርሱ [ለቤተሰቦቼ] መሆን ያልቻልኩት። . . . ሐኪም በመሆኔ ያተረፍኩት ድኅነትን ነው። ሰው ሰርቶ ሲቀየር አይተናል። ነገ የተሻለ ቀን ይመጣል በሚል ነው [የቆየነው]" ሲሉም አክለዋል።

ዶ/ር ይማም በዚህ ምክንያት የጤና ባለሞያዎች ሙያውን ጥለው እየወጡ እና እየተሰደዱ እንደሆነም ተናግረዋል።

ስፔሻሊት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ማህሌት ጉዑሽ መንግሥት ለጤና ባለሞያዎች ያለው እይታ እና አያያዝ ወደ ሌላ አገር ተሰድደው እንዲሰሩ እንደገፋፋቸው ይናገራሉ።

በተሻለ ክፍያ እና አያያዝ ሶማሌላንድ ሰርተው እንደተመለሱ የተናገሩት ዶ/ር ማህሌት፤ መኖር የሚያስችል ክፍያ ይከፈለን ሲሉ ይጠይቃሉ።

"የሥነ አዕምሮ መረጋጋት፤ እርካታ የለንም" የሚሉት ሐኪሟ፤ የጤና ባለሙያዎች ተረጋግተው እንዲሰሩ መንገዱ መመቻቸት አለበት ሲሉም ጠይቀዋል።

"መንግሥት ትንሽ ልክፈልሽ፤ በግል እንደፈለግሽ እያካካስሽ ነው ይላል። ስለተገደድኩ እንጂ እንደዚህ አልፈልግም" የሚሉት ዶ/ር ማህሌት፤ የጤና ባለሙያዎችም የግል ሕይወት እንዳላቸው በመጠቆም "አታግቡ አትውለዱ ልንባል አንችልም" ብለዋል።

በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ያሰሙት ባለሙያዎቹ፤ የአሁኑ ጥያቄ ሲንከባለል የመጣ እና በኑሮ ውድነት እና ዋጋ ግሽበት ምክንያት የኅልውና ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከእንቅስቃሴው አስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆኑ ባለሙያ ከክፍያ ባለፈ "የጤና መድኅን የለንም። ብንታመም መታከም አንችልም። ስጋት ባለበት አካባቢ ነው እየሰራን ያለነው፤ እንደ አደጋ ተጋላጭነታችን አስፈላጊ የሆኑ ክፍያዎችን እያገኘን አይደለም። ለእነዚህ ጥያቄዎቻችን ምላሽ ይሰጠን የሚል እንቅስቃሴ ነው እያደረግን ያለነው" ብለዋል።

ጥያቄውን "ትክክለኛ እና ወሳኝ" የሚለው የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኅበር፤ "የጤና ባለሙያው ተረጋግቶ ማኅበረሰቡን እንዲያገለግል ራሱ የተረጋጋ ሕይወት ሊኖረው ይገባል" ይላል።

የማኅበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ መለሰ ባዕታ የጤና ባለሙያዎች የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው ደረጃ መከፈል እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ "[የጤና ባለሙያ] ስለሚበላው፣ ስለሚለብሰው እየተጨነቀ አንድን ማኅበረሰብ ስለ አመጋገብ ስርዓት ማስተማር እና ማከም በጣም የሚከብድ ነገር ነው" ብለዋል።

"አንቺ እየሞትሽ፤ ሌላውን እንዴት አድርገሽ ልታድኝው ትችያለሽ? በቅንነት እና በታማኝነት ማገልግል እንዳለ ሆኖ ለማገልገለም ቢያንስ መሠረታዊ [ፍላጎቶች] ሊሟሉለት ይገባል" ሲሉ አስረድተዋል።

ድምፃቸውን እያሰሙ ያሉ ባለሙያዎች እስራትን ጨምሮ ጫናዎች እየደረሱባቸው እንደሆነ ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፤ ማኅበሩ ይህን እርምጃ "ጥያቄ ለማዳፈን" የሚደረግ እና "አላስፈላጊ" ብሎታል።

'የመንግሥት አመራሮች ጥያቄዎቻችን ፖለቲካዊ ስም እየሰጧቸው ነው' የሚሉት የእንቅስቃሴው አስተባባሪ፤ "ፖለቲካዊ ፍላጎት የለንም፤ ፍላጎታችን በልተን ማደር ነው፤ ያስተማረንን ማኅበረሰብ አገልግለን መኖር ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

መንግሥት ለጥያቄዎቻቸው መልስ ካልሰጠ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚመቱ የተናገሩት የጤና ባለሞያዎች እና የእንቅስቃሴው አስተባባሪዎች፤ እስካሁን ከመንግሥት ተስፋ ሰጪ ምላሽ እንዳላገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለሥራ ማቆም አድማው በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀሩ ሲሆን፤ በአድማው ወቅት ታካሚዎች እና ማኅበረሰቡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይደርስ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

ቢቢሲ የጤና ሚኒስቴርን የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ባይሳካም የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ኃላፊ ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ ምልልስ ጥያቄዎቹን "ተገቢ" ብለዋቸዋል።

ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው፤ በቅርቡ የፀደቀው የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ በርካታ ችግሮችን እንደሚፈቱ ጠቁመዋል።

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time