Monday, November 28, 2016

በአማራና በትግራይ ክልሎች የወሰንና የማንነት ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱ ዳግም ጥያቄ አስነሳ

Tigrai Region after 1991
Click here for image source
ከዓመታት ንትርክ በኋላ ለግጭት መንስዔ የሆነው የአማራና የትግራይ ክልሎች የጋራ አዋሳኝ ሥፍራዎችን የመከለልና የማንነት ጉዳይ፣ የመጨረሻ ዕልባት አለማግኘት አሁንም ጥያቄ አስነሳ፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት የችግሩን መንስዔ በተመለከተ ግምገማ ተካሂዶ ሁለቱ ክልሎች የጋራ መግባባት መድረሳቸውንና ችግሩን ለመፍታት መስማማታቸውን ገልጿል፡፡ ችግሩ መቼና እንዴት እንደሚፈታ ግን የሰጠው ዝርዝር ማብራሪያ የለም፡፡
ማክሰኞ ኅዳር 13 ቀን 2006 ዓ.ም. የአማራ ክልል ምክር ቤት ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ጉባዔውን ዋና መቀመጫው በሆነችው ባህር ዳር ከተማ ሲያካሂድ በበርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ድንበር ነክ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በስብሰባው ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው  ከምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በዕለቱ በምክር ቤቱ አባላት ተነስተው ከነበሩ ጥያቄዎች ውስጥ የልማት፣ የፖለቲካ፣ የአካባቢውን ፀጥታና ደኅንነትን የተመለከቱ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች ይገኙበታል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ የድንበር ጉዳይን በተመለከተ ክልሉ ለሚዲያ ግብዓት እንዲሆን ሲናገረውና ቃል ሲገባ ከሚደመጠው በተጨማሪ፣ ተግባራዊ ሆኖ መሬት ላይ አለመታየቱና ሌሎችም ያልተፈቱ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
ለአብነትም ያህል ካለፈው ዓመት ጀምሮ መፍትሔ ይሰጠዋል ተብሎ ሲነገርለት ቆይቶ ነገር ግን ዕልባት ባላገኘው ክልሉን ከትግራይ ክልል የማዋሰን ጉዳይ ተነስቷል፡፡ አንድ የምክር ቤት ኃላፊ እንዲህ ሲሉ ጥያቄ አቅርበው ነበር ‹‹ከዚህ ከድንበሩ ጭቅጭቅ ጋር ባለው ችግር ርዕስ መስተዳድሩ (አቶ ገዱ) እንፈታዋለን ነበር ያሉን፡፡ ነገር ግን እንፈታዋለን ማለት ሳይሆን ተግባር ነው ዋናው ሥራው፤›› በማለት ጉዳዩ በአግባቡ ትኩረት እንዳልተሰጠው በመተቸት ለአቶ ገዱ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ እኚሁ ጠያቂም አስከትለውም፣ ‹‹ካልተተገበረ ለፖለቲከኞች መጠቀሚያ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ኅብረተሰቡንም መሬትህ ተነጥቆ ሄደ በማለት እንዲቀጥሉ የመጫወቻና የማደናገሪያ ሜዳ ሆኖላቸዋል፤›› ሲሉም በማሳሰብ ተችተዋል፡፡
በሌሎች የምክር ቤት አባላት ተመሳሳይ ጥያቄዎች ለርዕስ መስተዳድሩ ቀርበውም ነበር፡፡ በተለይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሲያነታርክና በኋላም በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች ግጭት ተስፋፍቶ ለሰው ሕይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት መንስዔ የሆነው፣ የወልቃይትና የአጎራባች ሥፍራዎች ወደ ትግራይ ክልል መካለል ከተነሱት ውስጥ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
‹‹ከትግራይ ጋር ባለን የወሰን ክርክር በተመለከተ የሁለቱም ክልል አመራሮች፣ እንዲሁም የፌደራል መንግሥት ተወካዮች በተገኙበት ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በዝርዝር ያሉት ችግሮች ላይ ግምገማ አካሂደናል፡፡ ድክመቱም የት ላይ እንዳለ ተመልክተነዋል፡፡ በዚህ ረገድ ይህ ችግር በሁለቱ ክልሎች መካከል እስካሁን ድረስ የንትርክ አጀንዳ ሆኖ መቆየቱ ተገቢ እንዳልነበር፣ አሁንም በፍጥነት መፈታት ያለበት ጉዳይ መሆኑን፣ ይህንን ደግሞ ለመፍታት ሁለቱም ክልሎች መተማመን የደረሱበት ጉዳይ ነው፤›› ሲሉ አቶ ገዱ ገልጸዋል፡፡
በማስከተልም ማብራሪያቸውን የሰጡት አቶ ገዱ፣ ‹‹መተማመን ብቻ ሳይሆን ችግሩን ፈትተን በሌሎች የልማት ጉዳዮች ላይ በመተጋገዝ የሁለቱ ክልሎችና  ሕዝቦች ዝምድናና ግንኙነቶች ላይ አብረን መሥራት እንዳለብን ሁሉ መግባባት ተፈጥሯል፤›› በማለት ነበር ምላሽ የሰጡት፡፡
በዕለቱም የወጣት ሥራ ፈጠራን በተመለከተ በመንግሥት በተደጋጋሚ ቃል ሲገባ እንጂ መሬት ጠብ ያለ ነገር አልታየም፣ በተለያዩ ወረዳዎችና የገጠር ክልሎች የአገናኝ መንገዶች፣ የኤሌክትሪክና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ቃል በተገባው መሠረት አልተከናወነም ወይም በጅምር ቀርተዋል የሚሉ ቅሬታዎችም በጉባዔው ላይ ተነስተውም ነበር፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩም በኅብረተሰቡ የቀረቡላቸው ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸው መሆናቸውን ገልጸው፣ የተነሱት የልማት ጥያቄዎች ለምን በተባለላቸው ጊዜያት እንዳልተከናወኑና ተግባራዊ ሊሆኑ ስለታቀዱትና አሁን በመተግበር ላይ ስላሉ ሥራዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡       
በተያያዘም አቶ ገዱ ረቡዕ ኅዳር 14 ቀን 2009 ዓ.ም. አዲሱን ካቢኔ ሥራ በክልሉ ምክር ቤት አቅርበው አፅድቀዋል፡፡ ከነባር ካቢኔያቸው 12 አስቀርተው፣ ቀሪዎቹን አሥሩን አባላት በአዲስ መተካታቸውም ታውቋል፡፡ አምስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራንም በአዲሱ ካቢኔ መካተታቸው ተገልጿል፡፡

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time