Monday, November 28, 2016

ቂሊንጦ ማረሚያ ቤትን በማቃጠል ለ23 ታራሚዎች ሞት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ተከሰሱ

 በቃጠሎው ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል ተባለ
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ በፌዴራል ማረሚያ ቤት ቂሊንጦ የእስረኞች ማቆያ ቤትን በማቃጠል፣ የ23 ታራሚዎች ሕይወት እንዲጠፋና ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት አውድመዋል የተባሉ 38 ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀእናለ)ን፣ አንቀጽ 38ን፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ (1፣2፣4 እና 6)ን ተላልፈው መገኘታቸውን በመግለጽ ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡ ተከሳሾቹ የኦነግ፣ የግንቦት ሰባትና የአልሸባብ ድርጅቶችን ዓላማና ተልዕኮ በመቀበል በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር የዋሉና በማረሚያ ቤት የሚገኙ መሆናቸውን በክሱ ላይ ገልጿል፡፡
በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አመፅና ሁከት በኃይል በማስነሳትና ከእስር በማምለጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት በተፈረጁት ኦነግ፣ ግንቦት ሰባትና አልሸባብ ድርጅቶችን ለመቀላቀል በማሰብ፣ ተከሳሾቹ ከጥር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ አባላት በመመልመል ከተለያዩ ዞኖች በማሰባሰብና በማደራጀት ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው በክሱ ተጠቁሟል፡፡
በውጭና በአገር ውስጥ ከሚገኙ ታራሚዎች ገንዘብ በማሰባሰብ የአመፁን ድርጊት በኃይል ይመራሉ ያሉዋቸውን በከባድ ወንጀልና በውንብድና የተከሰሱትን ታራሚዎች በመመልመል፣ ‹‹የሽብርና የዱርዬው ቡድን›› የሚል ስያሜ በመስጠት ሲመካከሩ መክረማቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡
የ66 ዓመት ዕድሜ ያላቸውና በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጋር ተከሰው በአራት ዓመታት ከስምንት ወራት የእስራት ቅጣት የተጣለባቸው የአዲስ ካርዲያክ የሕክምና ማዕከል ባለድርሻ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ፣ ለ‹‹ሽብርና ዱርዬው ቡድን›› 70,000 ብር የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ አመፁ እንዲፈጸም ተልዕኮ መስጠታቸውንና እሳቸውም በክሱ መካተታቸውን ያስረዳል፡፡
‹‹የሽብርና ዱርዬው ቡድን›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ቡድን ተከሳሾችን በሴል በማደራጀት፣ ስለሽብር እንቅስቃሴ በማስረዳትና በመግለጽ ከመለመለ በኋላ በሚስጥር ኮድ መረጃ በመለዋወጥ አመፁን በመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም. ለመፈጸም የተዘጋጀ ቢሆንም፣ ከውጭ ይመጣሉ ብለው ያሰቧቸው የግንቦት ሰባትና የኦነግ ታጣቂዎች በመቅረታቸው ለሌላ ጊዜ ማስተላለፋቸውንም ክሱ ይገልጻል፡፡
ተከሳሾቹ ለማረሚያ ቤቱ መረጃ ይሰጣሉ በማለት የጠረጠሯቸውን ታራሚዎች መግደል እንዳለባቸው በመመካከር በፌሮና በዱላ በመቀጥቀጥ መግደላቸውን፣ ፖሊስ ለቆጠራ ሲገባ አፍነው በመያዝ መሣሪያውን ቀምተው ታራሚዎች እንዲወጡ በማድረግ መኝታ ቤቱን በእሳት ማቃጠላቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ከማረሚያ ቤቱ አምልጠው ለመውጣት ዕቅድ በመያዝ ‹‹የሽብርና የዱርዬው ቡድን›› በማደራጀት ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በማረሚያ ቤቱ ላይ በፈጸሙት የእሳት ቃጠሎ ወንጀል ድርጊት፣ የ23 ታራሚዎች ሕይወት እንዲጠፋ ወይም እንዲቃጠሉ በማድረግና ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንዲወድም አድርገው የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን ተላልፈዋል በማለት፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ Read more here

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time