የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ተጠርጥረው ከታሰሩበት የሙስና ወንጀል እንዲፈቱ የዋስትና መብት ተጠበቀላቸው፡፡
አቶ ኤፍሬም በባንኩ የዕቃ አቅርቦትና አስተዳደር ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ፣ እ.ኤ.አ. ለ2012/13 በጀት ዓመት ለግዢ አፅዳቂ ኮሚቴ 500,000 ማርከር እንዲገዛ ጥያቄ ማቅረባቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡ ጥያቄውን ያቀረቡት ግን ቀደም ብሎ ተገዝቶ የቀረበውን 1,000 ማርከር መሠረት አድርገው ሳይሆን የሥሌት መነሻ ሳይኖራቸው በራሳቸው ውሳኔ በመሆኑ፣ በባንኩ ላይ 6,962,090 ብር ኪሳራ ማድረሳቸውን ገልጾ ነበር ፖሊስ ለፍርድ ቤት ያስረዳው፡፡ ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት የጠየቀ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ አሥር ቀናትን ብቻ ፈቅዶለት ነበር፡፡
ፖሊስ በቀጣይ ቀጠሮ ሲቀርብ ምርመራውን መጨረሱን ለፍርድ ቤት በማስረዳት ለዓቃቤ ሕግ ማስረከቡን የገለጸ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር (38ሐ) መሠረት መጣራት አለባቸው ያላቸውን ሰባት ነጥቦች በመጥቀስ በድጋሚ እንዲያጣራ ለፖሊስ መዝገቡን መልሶለት ነበር፡፡ ለማጣሪያ ጊዜም ስምንት ቀናት ሰጥቶት ነበር፡፡ ፖሊስ ከስምንት ቀናት በኋላ በድጋሚ ምርመራውን መጨረሱን ገልጾ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ ቢመልስለትም፣ ዓቃቤ ሕግ ግን በባንኩ ላይ ጉዳት መድረስ አለመድረሱን፣ ማርከሩ መሥራት አለመሥራቱንና ግዢው የፀደቀው በኮሚቴው ወይም በተጠርጣሪው መሆን አለመሆኑን አጣርቶ እንዲያመጣ በድጋሚ መልሶታል፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ተጠርጣሪው መቃወሚያ አቅርበው ነበር፡፡ ያቀረቡት መቃወሚያም ማርከሩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ፋኩሊቲ ተመርምሮ ከተገዛ ሁለት ዓመታት ቢሆነውም፣ እንደሚሠራ መረጋገጡንና በአማካይ 7,190 ኖቶችን (ዶላር ወይም ብር) ፎርጂድ መሆን አለመሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስችል ምላሽ እንደሰጥ አስረድተዋል፡፡
ተጠርጣሪው አቶ ኤፍሬም በወቅቱ ለኮሚቴው ግዢ እንዲፈጸም ሲቀርብ እሳቸው የነበሩት ቴክኒካዊ ግምገማ እስከሚደረግበት ጊዜ እንጂ ጨረታ ሲከፈት ወደሌላ ሥራ በመዛወራቸው እንዳልነበሩ በመግለጽ፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ጥያቄው የቀረበለት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በ40,000 ብር ዋስትና እንዲፈቱ ፈቅዶ የነበረ ቢሆንም ፖሊስ ይግባኝ ብሎባቸዋል፡፡
ይግባኙን የመረመረው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ለጊዜው ዋስትናውን ያገደው ቢሆንም፣ ጉዳዩን መርምሮ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሰጠውን ዋስትና በማፅናት ይግባኙን ውድቅ አድርጎ ዓርብ የካቲት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በዋስ እንዲፈቱ ፈቅዷል፡፡ Read more here
No comments:
Post a Comment