Monday, October 31, 2016

‹‹ለእኔ የተሳካለት መሪ የምለው የተሳካላቸው ተተኪዎችን ማፍራት የቻለን ነው›› ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ጥቅምት 25፣ 26 እና 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡ ጉባዔው ከመደበኛው አጀንዳ በተጨማሪ ለቀጣዩ አራት ዓመት ፌዴሬሽኑን የሚያስተዳድሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ያደርጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚወክሏቸው ዕጩዎች እየታወቀ ይገኛል፡፡ የዘንድሮው ከወትሮው ለየት የሚያደርገው ነባርና ታዋቂ አትሌቶች ለምርጫ መቅረባቸው እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡ ከነዚህ አትሌቶች መካከል አዲስ አበባን በመወከል ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትነት የሚቀርበው ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ይጠቀሳል፡፡ ኃይሌ ከዓመታት የሩጫና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በኋላ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን በኃላፊነት ለማገልገል ምን አነሳሳው? የሚለውንና በወቅታዊ የአትሌቲክሱ ጉዳይ ደረጀ ጠገናው አነጋግሮታል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከቀናት በኋላ በሚያደርገው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ያከናውናል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ  ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ አድርጎ አቅርቧል፤ መሥፈርቱ ምንድን ነው?
ኃይሌ፡- እንደሚታወቀው እኔን ጨምሮ የቀድሞና የአሁን አትሌቶች የአገሪቱ የአትሌቲክስ ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ ደረጃ መገኘቱና ይህንኑ አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አባላት ጋር ቀደም ሲል ጀምሮ መፍትሔ ለማምጣት ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ አሁንም እያደረግን እንገኛለን፡፡ ከቀናት በኋላ ለሚደረገው ምርጫ የአዲስ አበባን ውክልና እንዴት ልታገኝ ቻልክ? ለሚለው አንዱና የመጀመርያው ነገር የአዲስ አበባ ነዋሪ በመሆኔ ለምርጫው ብወከል እመጥናለሁ በሚል መነሻ ነው፡፡ ሌላውና ሁለተኛው ነገር የውክልና ጥያቄው ከመምጣቱ በፊት እኔ ለዚህ ኃላፊነት እመጥናለሁ የሚል ተነሳሽነት ስላደረብኝ ጠይቄ ያገኘሁት ውክልና ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩም እንኳን መጣህልን ብሎ ነው ጥያቄዬን በደስታ የተቀበለው፡፡ ምክንያቱም አትሌቲክስ ለእኔ ከሁሉ ነገር በላይ ነው፡፡ በመሆኑም እስከዚህ ድረስ ያለው ጊዜ ባለው የሕግ አግባብ መጥቻለሁ በቀጣይ እንዴት ይሆናል? የምርጫ ሒደቱ የሚለየው ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ ወቅት ክልሎች የዕጩዎቻቸውን ማንነት በውል ባላሳወቁበት አንተ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ቀርበህ ራስህን ማስተዋወቅ ጀምረሃል፡፡ አካሄዱ ለሌሎች ዕጩ ተወዳዳሪዎች ተፅዕኖ የለውም?
ኃይሌ፡- ተፅዕኖ አለው የለውም የሚለውን ብዙ አልሄድበትም፡፡ ምክንያቱም የምንነጋገርበት አትሌክስ ምንም ድብቅ ነገር የለውም፡፡ እያንዳንዱ እቅንስቃሴ በምትሠራው የሥራ አቅምና መጠን የሚወሰን ነው፡፡ ሌላው እኔም ሆንኩ ሌሎች የሙያ ባልደረቦቼ ቀደም ሲል ጀምሮ የተነሳንለት ነገር በዋናነት አትሌቲክሱን መታደግ ነው፡፡ ውጤት ማምጣት ነው፡፡ ውጤት ሲባል በለንደንና በሪዮ ያስመዘገብናቸው ሜዳሊያዎች ብለን ራሳችንን ከራሳችን ጋር የምናደርገውን ንጽጽር ወደ ጎን ትተን ከተወዳዳሪዎቻችን አኳያ ራሳችንን በመፈተሽ የተሻለ የአሠራር ሥርዓት ለመፍጠር ቁርጠኝነቱ ስላለን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ባለው ተሞክሮ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ኃላፊነቱን እስኪረከቡ  ድረስ ‹‹ከነበረው የተሻለ ነገር መሥራት›› የሚለው የተለመደ አባባል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አትሌቲክሱን መታደግ ስትል መነሻህ ምንድነው?
ኃይሌ፡- በዚህ ረገድ እርግጠኛ ሆኜ ልናገር የምችለው በአትሌቲክሱ ኅብረተሰባችን የሚያምንበትን ውጤት ለማምጣት በትንሹ ሦስት ዓመት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ ይኽም ለመነሻ ካልሆነ የረዥም ጊዜ ብለን በልበ ሙሉነት የምናወራበት አይደለም፡፡ ከተመረጥን የመጀመርያ አድርገን የምንሠራው በሁሉም ክልሎቻችን የተሰጥኦ ምንጭ ተብለው የሚታመኑ ቦታዎችን በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብና በትግራይ ላይ የተቋቋሙ የወጣት ማዕከላትን በመመልከት ምን እንደሚያስፈልጋቸው መፈተሽ ነው፡፡ በቀጣይነት ደግሞ አትሌቲክስ ሲባል ሩጫ ብቻ እንዳልሆነ፣ በሩጫም ለምን በረዥም ርቀትና ማራቶን ብቻ ተንጠልጥለን ቀረን? በውርወራና ዝላይስ የሚለው ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ደቡብ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል የመሳሰሉትን ክልሎቻችንን እስካሁን ባለው ሁኔታ አልተጠቀምንባቸውም፡፡ በአጫጭር ርቀት ውጤት አይደለም ተሳትፎ የለንም፡፡ የዝላይ ስፖርትን እንደ ምሳሌ ወስደን ብንመለከት፣ በአገሪቱ በተለይም በደቡብ አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከብቶችን ደርድረው መዝለል የሚችሉ፣ ይህንኑ ባህል አድርገው የሚያዘወትሩ አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚገኝበት ማራቶን ለሩጫ ተብሎ የተገኘ የውድድር ዓይነት እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ከብቶችን ወደ ጎን ደርድረው በመዝለል የሚታወቁት እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአብዛኛው ወጣቶች ትዳር ለመመሥረት ሲያቅዱ የሚተገብሩት የባህል ጨዋታ ነው፡፡ እስካሁን ባለው አንዱንም ለዘመናዊ ስፖርት እንጠቀምበታለን ብለን ለመመልከት አልቻልንም፡፡ ብመረጥ አንዱ የአትሌቲክሱ ዕቅድ አድርጌ የምጀምረው ከዚህ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አንተን ጨምሮ የቀድሞና የአሁን አትሌቶች ከአደረጃጀትና ከአሠራር እንዲሁም ከሙያተኛ ምደባና አትሌት ምልመላ ጋር በተያያዘ ከፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር ሰፊ ልዩነት እንደነበራችሁ ይታወቃል፡፡ አሁን ደግሞ አንዳንዶቻችሁ የተቋሙን የአመራርነት ኃላፊነት ለመውሰድ ዕጩ ሆናችሁ የቀረባችሁ አላችሁ፡፡ አመጣጣችሁን የብቀላ ዓይነት አድርገው የሚወስዱ ወገኖች አሉ፡፡ እንዴት ታየዋለህ?
ኃይሌ፡- እኔም ሆንኩ የተቀሩት የሙያ ባልደረቦቼ ከተመረጥን በፌዴሬሽን ደረጃ የመጀመርያ ሥራችን የሚሆነው በተቋሙ በየደረጃው የሚገኙ ዲፓርትመንቶች ሙያና ባለሙያተኞችን ያማከሉ መሆን አለመሆናቸውን ለይተን ማስተካከያ ማድረግ ነው፡፡ የምናወራው ስለዝላይ ከሆነ ለዚያ የሚመጥን ማን ነው? በአጭርና ረዥም ርቀት እንዲሁም ማራቶን ማን ምን ዓይነት አቅም አለው? የሚለውን ፍፁም ሙያዊ በሆነ ሥነ ምግባር ኃላፊነትን ቆጥሮ መስጠትን እናስቀድማለን፡፡ በቢሮ ደረጃም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መሥራቹ ኃይሌ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሥራው በእነማን እንደሚሠራ ለማንም ሰው ግልጽ ነው፡፡ ሁሉም ሊያውቀው የሚገባውና መመዘኛው ሥራና ሥራ ብቻ መሆኑን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአገሪቱ አንተን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ዝናና ክብር ያላቸው አትሌቶች አሉ፡፡ አገሪቱ ልክ እንደ ኬንያና ሌሎችም አገሮች በእነዚህ አትሌቶች መጠቀም ያለባትን ያህል ተጠቅማለች ማለት ይቻላል?
ኃይሌ፡- የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከሻምበል አበበ ቢቂላ ጊዜ ጀምሮ በፈሩ ታዋቂ አትሌቶች ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ይኼ ሁሉ ታዋቂ አትሌት ባለበት አገር በአህጉራዊም ይሁን ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ስለአገሪቱና የአትሌቲክሷ እንቅስቃሴ መናገር የሚችል ተወካይ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ፌዴሬሽኑን እንዲወክሉ የሚደረጉ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ በስፖርቱ የሚታወቁ አይደለም፡፡ እነሱም ይህንኑ ስለሚያውቁ በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ካልሆነ አገራዊ ፋይዳ ስላለው የአትሌቲክሱ ጉዳይ ለማውራት ጊዜ አይኖራቸውም፡፡ ይህ ባይሆንማ ኖሮ ቀነኒሳ፣ ጥሩነሽ፣ መሠረት፣ አልማዝ፣ ገንዘቤና ሌሎችንም ይዘን ከአንድ አዲዳስ ውጪ ስፖሰር ባላጠን ነበር፡፡ ይኼ በጣም የሚገርም ነው፡፡ የዓለም የተከበሩ አዳዲስ ክብረ ወሰኖች ቢደመሩ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ቀጥሎ ያለውን ቦታ ማግኘት እንደምትችል እገምታለሁ፡፡ አገሪቱ ባላት ውጤትና የአትሌት መጠን ተጠቃሚ አይደለችም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቀደም ሲል እንደተናገርኩት፣ በሚገኙ አጋጣሚዎች የሚናገር ሰው ማጣታችን ነው፡፡ እንግሊዛዊው ሰባስቲያን ኮ የዓለም አቀፉን አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) መምራት የቻለው በውጤቱ አይደለም፡፡ የሚናገርለት ስላለው ብቻ ነው፡፡ በደንብ እንተዋወቃለን፡፡ ልዩነታችን ኢትዮጵያውያን እንደነሰባስቲያን ኮና ሌሎችም መድረኮችን ተጠቅመው የሚናገሩበት አጋጣሚ አላገኙም፡፡ አሁንም እነዚህ አጋጣሚዎች እንዳያመልጡን መንቃትና ማሰብ ያስፈለጋል፡፡
ሪፖርተር፡- በአትሌቲክሱ አገሪቱ በአበረታች ንጥረ ነገር ከሚጠረጠሩ አገሮች ተርታ እንድትጠራ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ ረገድ ያለህ አስተያየት ምንድን ነው?
ኃይሌ፡- ይኼ ጉዳይ ለአገሪቱም ሆነ ለአትሌቶቹ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ ምርመራውን ከምናደርግበት በጀት ጀምሮ ከባድ ሆኗል፡፡ ይህንን በጋራ ሆነን የምንከላከልበትን አማራጭ መሻት ይኖርብናል፡፡ በዓመት አራትና አምስት መቶ ሺሕ ዶላር ይጠይቁናል፡፡ ይኼ የሆነው ካለፈው ዓመት ጀምሮ ነው፡፡ ከዚያ በፊት አገሮችን የሚመለከት አልነበረም፡፡ በዚህ ጉዳይ ከዋዳም ሆነ ከአይኤኤኤፍ ጋር መነጋገር ይኖርብናል፡፡ እንደቀደሙት ዓመታት በራሳቸው የፋይናንስ አቅም እንዲያከናውኑ ግፊት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ በጣም ብዙ የቤት ሥራ እንደሚጠበቅብን ነው የማስበው፡፡
ሪፖርተር፡- የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) የፋይናንስ ድጎማ ቀርቶ በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ሲያከናውነው የቆየውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከነጭራሹ ለመሰረዙ ዕቅድ እንዳለው ይሰማል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ውጤቱ የጥቂት አገሮች በተለይም የምሥራቅ አፍሪካውያኑ ኢትዮጵያና ኬንያ በመሆኑ እንደሆነ ተደርጎ ነው የሚሰማው?
ኃይሌ፡- የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ብቻ ሳይሆን አሥርና አምስት ሺሕ ሜትር ለጊዜው እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ ስለመጣ ጉዳዩን አቀዘቀዘው እንጂ እሱ ባይኖር ኖሮ እስካሁን በተሰረዘ ነበር፡፡ እኛ ደግሞ በእነዚህ የሩጫ መስኮች በርካቶችን እያፈራን ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከባድ የቤት ሥራ ነው የሚጠብቀው፡፡ ቀደም ሲል እንደተነጋገርነው ኃይሌ የራሱ አጀንዳ አለው የሚሉ ወገኖች እንዳሉ እሰማለሁ፡፡  ስህተት ነው፡፡ እውነቱን ለመነጋገር የእኔ አነሳስ የአጀንዳ ጉዳይ ከሆነ በተለይ በዚህ ወቅት የአይኤኤኤፍ ፕሬዚዳንት ትሆናለህ ብባል አልቀበልም፡፡ መጀመር የምፈልገው ከዚሁ ነው፡፡ መጀመርያ በቤቴ ውስጥ ያለውን ችግር መፍታት እፈልጋለሁ፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሆኜ አትሌቲክሱ ያጣውን ነገር በስፖንሰር ረገድም ይሁን ከዓለም አቀፍ ማኅበራት ጋር መሥራት ያለብኝን ያህል ከመሥራትና ተፅዕኖ ከመፍጠር የሚከለክለኝ የለም፡፡ ነገሩን መድገም ካልሆነብኝ የአይኤኤኤፍ ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ ለምርጫ ቅስቀሳ ከተጠቀማቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ከኬንያ ዴቪድ ሩዲሽያ፣ ከሩሲያ ኢሴባይቫ፣ ከእንግሊዝ ፓውላ ራዲክሊፍ ይጠቀሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቀጣይ በሚኖረው ምርጫ የክልሎቻችን አጀንዳ ሊሆን የሚገባው ኃይሌን በኃይሌነቱ ወደ ጎን ትተው ለአገሪቱ አትሌቲክስ የሚጠቅመውን እንዲመርጡ ነው የምጠይቀው፡፡ ብመረጥ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ ከአይኤኤኤፍ ጋር የመብት ጥያቄና ልመናን እንዴት እንደምንጠቀምበት እናውቅበታለን፡፡
ሪፖርተር፡- በግንኙነትና ትውውቅ ብቻ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያጣቸው በርካታ ጥቅሞች አሉ ብለን እንውሰድ?
ኃይሌ፡- ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በሺሕ የሚቆጠር ጥቅም አጥተናል፡፡ እያጣንም ነው፡፡ ኬንያዊው ፖልቴርጋት በአይኤኤኤፍ ባለው ቦታ ኬንያውያን እያገኙት ያለውን ጥቅም መመልከት ይቻላል፡፡ ለጊዜውም ቢሆን በዚህ የሚገኘውን ጥቅም እንተወውና በሪዮ ኦሊምፒክ በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተወከለችው ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ በሪዮ የሽልማት መድረኮች ሸላሚ መሆኗ የአገሪቱን መልካም ገጽታ ከመገንባት አኳያ ያለውን ፋይዳ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ብዙዎቻችን ወ/ሮ ዳግማዊትን ላናነሳት እንችል ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ለሁላችንም እኩል ነች፡፡ ስሟና ማንነቷ ሲታወቅና ሲጠራ ደስ ሊለን  ይገባል፡፡ መመልከት ያለብን በዳግማዊት ውስጥ የምትወከለውን ኢትዮጵያን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአትሌቲክሱ በተለይ ከዲሲፕሊን ጋር ተያይዞ ቀድሞ የነበረውና አሁን ያለው ሁኔታ ፈጽሞ የተለያየ ነው፡፡ ብትመረጡ በዚህ ረገድ ችግር አይገጥማችሁም?
ኃይሌ፡- ማን ምን እንደሆነ በሚገባ ስለምንተዋወቅ ችግር ይገጥመናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በቀላሉ በዓለም ካሉ ማራቶኖች የቱ ከየትኛው እንደሚያንስና እንደሚሻል እናውቃለን፣ እንተዋወቃለን፡፡ ይኼ ደግሞ አሠራሩን አንዱ ሌላውን ስለሚወደውና ስለሚጠላው ከሚለው አሉባልታ የፀዳ እንዲሆን ምቹ ያደርገዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከነባሮቹ አትሌቶች አንዱ እንደመሆንህ ከዚህ በፊት የአሁኑ ዓይነት ማለት በፌዴሬሽኑ በአመራርነት ለማገልገል ፍላጎት አልነበረህም፡፡ ምክንያት ይኖርሃል?
ኃይሌ፡- አንዱና ዋናው ምክንያት የአትሌቲክሱ የውጤት ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ቀደም ባሉት ዓመታት ተወዳዳሪ ስለነበርኩ ኃላፊነቱ ስለሚከብድ ነው፡፡ አሁን ግን ማሸነፍ እንደቻልኩባቸው ዓመታት ሁሉ በአመራርም ማሸነፍ የሚችሉ አትሌቶች መጥተው መመልከት እፈልጋለሁ፡፡ ሌላው አሁን አሁን እየተበለጥን ያለነው ከሜዳሊያ አንፃር ብቻ ሳይሆን በምናገኘው የሜዳሊያ መጠን በስፖንሰር ገቢያችንም ጭምር ነው፡፡ ከዚህ ባልተናነሰ ልናተኩርበት የሚገባው የዶፒንግ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአምስቱ ተጠርጣሪ አገሮች አንዷ ስትሆን ኃይሌስ ማን ነው? መባሉ አይቀርም፡፡ በዚህ ጉዳይ ከዋዳም ሆነ ከአይኤኤኤፍ ጋር የምንነጋገርበት ወቅት ቢኖር አሁን ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ኢትዮጵያን በዚህ መልክ ለይተው ሲያወጡ ከሌሎች አገሮች አትሌቶች አንፃር እንዴት ለይተዋት ነው፡፡ ምክንያቱም በውስጡ የምናውቃቸው ጨዋታዎች ያሉ መሆኑም ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ በአገር ውስጥም ከአትሌቶችና ማናጀሮች ጋር የምንሠራቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ የሚገርመው ከወራት በፊት ከኢትዮጵያ በባሰ ሁኔታ ውስጥ የነበረችው ኬንያ በአሁኑ ወቅት ስሟን እያደሰች ነው፡፡ እንዴት የሚሉ ካሉ መልሱ ትኩረት ሰጥተው ስለሠሩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እንደዚያ ከሆነ ወደ ፌዴሬሽን ለመምጣት አልዘገያችሁም?
ኃይሌ፡- በእርግጥ ዘግይተናል፡፡ ግን ከተጠቀምንበት አልመሸም፡፡ ምክንያቱም ሥራችንን የምንጀምረው ከመሠረቱ ነው፡፡ ለእኔ የተሳካለት መሪ የምለው የተሳካላቸው ተተኪዎችን ማፍራት የቻለን ነው፡፡ ኃይሌ ውጤታማ ሥራ ሠርቷል እንዲባል የምፈልግ ከሆነ፣ የሚያስቀጥሉትን ማፍራት ከቻልኩ ብቻ ነው፡፡ ይኼ ካልሆነ እኔም ከቀደሙት የምለይበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ከዚህ ለመነሳት ዓለም አቀፍ ደንቦችና መመርያዎችን ከአገራችን ነባራዊ እውነታ ጋር በማጣጣም የምንሄድበት ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ረገድ ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ በመነሳት በምንቀሳቀስበት ጊዜ የሚገጥሙን ፈተናዎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያውያን ታዋቂ አትሌቶች ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ ልምምድ እንጦጦ ሠርተው መኖሪያቸው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ውጤት ከፈለግን ለዚህ ነገር መፍትሔ ማበጀት ይኖርብናል፡፡ የአዲስ አበባ አየር ተበክሏል፡፡ የአብዛኛው አትሌት ሳምባ ወንፊት ሆኗል፡፡ ጎረቤት ኬንያን ብንወስድ ውድድር ያቆሙት እነ ፖልቴርጋት ሳይቀር በዋና ከተማዋ ናይሮቢ የሚኖር አትሌት የለም፡፡ የሚገርመው ወጣ ብላ የምትገኘው ኤልዶሬት ሳይቀር ፈተና እየሆነችባቸው መምጣቷን የሚናገሩ ኬንያውያን ገጥመውኛል፡፡ ችፕቾጌ በአሁኑ ወቅት ዓለም ላይ በቁጥር አንድ ከሚጠቀሱ አትሌቶች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ አትሌቱ ኤልዶሬት ውስጥ ቤተመንግሥት አለው፣ ሄዶ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በዚያ ቤት ውስጥ ከሚስቱና ልጆቹ በስተቀር የእሱ ኑሮ ጫካ ውስጥ ነው፡፡ ለምንም ብሎ ሳይሆን ለውጤቱ ነው፡፡ እኛም ይህን ተሞክሮ መልመድ ይኖርብናል፡፡ ይህን የማናደርግ ከሆነ በእጃችን እንዳለ የምንቆጥረው አምስትና ሥር ሺሕ ሜትር እንዲሁም ማራቶንን ጨምሮ የምናጣበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም፡፡ አሁንም እየጠፋ ነው፡፡ አልማዝ አያና ተሠርቶባት እንዳልመጣች እናውቃለን፡፡ እዚህ የደረሰችው በግል ጥረቷ ነው፡፡ ለመለወጥ ከሆነ መተማመንና ከዚህ ድክመታችን መጀመር ይኖርብናል፡፡
ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ በአገሪቱ ካሉት የስፖርት ተቋማት የራሱን የገቢ ምንጭ ከመፍጠር ጀምሮ የተሻለ መሆኑ የሚናገሩ አሉ ትቀበለዋለህ?
ኃይሌ፡- እያልኩ ያለሁት እስካሁን የነበረው አመራር ሙሉ ለሙሉ እየሠራ አይደለም ሳይሆን፣ ያልተሠራ የሚቀር ሥራ አለ ነው፡፡ ሁሉም የሚችሉትን ሠርተዋል፡፡ ነገር ግን ይቀረናል፣ ተጠናክረን እንሂድበት ነው፡፡ በአትሌቲክስ ውስጥ ሩጫ፣ ውርወራና ዝላይ የሚባሉ የውድድር ዓይነቶች አሉ፡፡ የምናዘወትረውና ውጤት ጠፋ እያልን የምንከራከርበት ስንቱን ነው? የሚለው ነው መታየት ያለበት፡፡ ኬንያ በጦር ውርወራ ከኢትዮጵያ አጠገብ ከሚገኝ ቦታ አትሌት መልምላ የዓለም ሻምፒዮን ሆናለች፡፡ እኛስ? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ የመንግሥት አካሉም በዚህ ጉዳይ የራሱን ሚና መጫወት አለበት፡፡ ምክንያቱም ለስፖርቱ በሚሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ መጠን እያፈሰሰ ነው፡፡ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ፀበል ቅመሱ ዓይነት አካሄድ እንዲቀር የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡- ከዓመታት በፊት ኃይሌ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር መሆን እንደሚፈልግ ሲነገር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ወደ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መውረዱ ለምን የሚሉ ወገኖች አሉ እንዴት ታየዋለህ?
ኃይሌ፡- መማር ስለምፈልግ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኃይሌ የፌዴሬሽኑ ኃላፊነቱ ቢሰጠው የጊዜ እጥረት ስላለበት ይቸገራል የሚሉ አሉ?
ኃይሌ፡- ይህን ጥያቄ ከሠራተኞቼም ይቀርብልኛል፡፡ የመለስኩላቸው በደሜ ያለው አትሌቲክስ ደሜ ካልተቀየረ በስተቀር በምንም እንደማልተካው ነው፡፡ የሚሰማኝና እምነቴም ይሆናል ብዬ የምጀምረው ይሆናል፤ አይሆንልኝም የምለው ደግሞ አይሆንም፡፡ በተለይ በአትሌቲክሱ ይህን ለማለት የምደፍረው እኛ ተፈጥሮ የሰጠን ‹‹ዶፒንግ›› አለን፡፡ የአየር ፀባያችን ከሠራንበት ውጤታማ እንደሚያደርገን እምነት አለኝ፡፡ ችግራችን ያላየናቸውን ሀብቶቻችንን ለማየት ፍላጎት የለንም፡፡ Read more here

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time