Tuesday, June 18, 2024

በአማራ ክልል ሁለት የጎጃም ዞኖች በቀናት ልዩነት “በመንግሥት ኃይሎች” ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

 

Bahir Dar

በአማራ ክልል ምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች ባለፈው ሳምንት በቀናት ልዩነት ውስጥ ተፈጽሟል በተባሉ ጥቃቶች ከ20 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጥቃቶቹ ባለፈው ሳምንት ሰኔ 7 እና 9 ቀራኒዮ እና ጂጋ በተባሉ ከተሞች እንደተፈጸሙ የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ሁለቱም ጥቃቶች የመንግሥት ኃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ውጊያ ካደረጉ በኋላ ስለመፈጸማቸው ገልጸዋል።

እሁድ ሰኔ 9 በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢጠህና ወረዳ ጂጋ ከተማ በተፈጸመው ጥቃት መምህራን እና የባንክ ቤት ሠራተኞችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች “መረሸናቸውን” ሁለት የዐይን እማኞች እና ከተማዋን ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቡት አቶ አበባው ደሳለው ተናግረዋል።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የዐይን እማኝ ከግድያው በፊት በከተማዋ ደምበጫ በር የሚባል ሰፈር አካባቢ ለ20 ደቂቃ ያህል የቆየ ውጊያ በፋኖ እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል መደረጉን ጠቁመዋል።

ሌላ የዐይን እማኝም እንዲሁ፤ “ከደንበጫ ወደ ጂጋ የሚመጣ ሦስት ፓትሮል ነበር። የፋኖ አባላት ጥቁር ውሃ ከሚባል አካባቢ የደፈጣ ጥቃት አደረሱ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሃያ ደቂቃ ከቆየው የተኩስ ልውውጥ በኋላ የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸውን የተናገሩት ነዋሪው፤ ከፋኖ ማፈግፈግ በኋላ “የመከላከያ ሠራዊት አባላት በበቀል” ነዋሪዎችን መግደላቸውን አክለዋል።

ግድያው ከተፈጸመበት ቦታ በቅርብ ርቀት ላይ እንደነበሩ የተናገሩ የዐይን እማኝ፤ “ጎህ የሚባል ሆቴል ላይ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የባንክ ሠራተኞችን [እና] መምህራንን [በድምሩ] 12 ሰዎችን አውጥተው በሕዝብ ፊት በአስቃቂ ሁኔታ ገደሏቸው” ሲሉ የተመለከቱትን ክስተት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ሁለተኛው የአካባቢ ነዋሪም በተመሳሳይ “የመከላከያ ሠራዊት መስመር ላይ ያገኘውን ጎህ የሚባል ሆቴል እራት ለመብላት የገቡትን ባንክ ቤት ሠራተኞች፤ መምህራን ያገኙት በሙሉ ረሸኑ” ብለዋል።

ሁለቱም ነዋሪዎቹ በጂጋ ከተማ የምትኖር አንዲት የአዕምሮ ህመምተኛን ጨምሮ “12 ሰዎች በመከላከያ ሠራዊት ሲገደሉ” መመልከታቸውን እና ከተመለከቱትን ጨምሮ በድምሩ 23 ሰዎች ተገድለዋል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሌሎች ሁለት ግለሰቦች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከምዕራብ ጎጃም ዞን ጂጋ ምርጫ ክልልን ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አበባው ደሳለው በበኩላቸው፤ “እስካሁን ስም ዝርዝራቸው እና ሥራቸው በእጃችን የደረሰ 13 ሟቾች አሉ፤ ሁለት ደግሞ የቆሰሉ ናቸው” ሲሉ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የምክር ቤት አባሉ አክለውም “ተጨማሪ የሟቾች ዝርዝር ይመጣል ብለን ነው የምንጠብቀው፤ የተረጋገጠ ግን የ13 ሟቾች እና የሁለት ቁስለኞች ዝርዝር አለን” ብለዋል።

“ተዋጊ ኃይሎች እርስ በእርስ ሊገዳደሉ ይችላሉ። አምነው የገቡበት ነው። የጦርነት ጨዋታ ነው እሱ። ነገር ግን ምንም ያልታጠቁ ንጹሃንን ከቤታቸው እያወጡ መረሸን አግባብነት የለውም” ብለዋል የምክር ቤት አባሉ።

አቶ አበባው አክለውም እሁድ ዕለት የተፈጸመውን ክስተት በተመለከት ለሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለኤምባሲዎች በደብዳቤ እንደሚያሳውቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሁለት እጁ እነሴ ወረዳም አርብ ሰኔ 7/2016 ዓ.ም. “በመንግሥት ኃይሎች” ተፈጽሟል በተባለ ጥቃት የሰባት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ሁለት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ነዋሪዎች እና የዐይን እማኞች ተናግረዋል።

ጥቃቱ ከወረዳው ዋና ከተማ ሞጣ በ16 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ቀራኒዮ አነስተኛ ከተማ ‘ደብረ ቀራኒዮ መድኃኒያለም ቤተ-ክርስቲያን’ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለቀብር ጉድጓድ ሲቆፍሩ ነበሩ የተባሉ እድርተኞች ላይ መፈጸሙን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቱ ከመፈጸሙ አስቀድሞ በአካባቢው የመንግሥት ኃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች የተኩስ ልውውጥ እያደረጉ እንደነበር የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ጥቃቱ ተኩሱ ጋብ ማለቱን ተከትሎ ጠዋት 3፡00 ላይ መፈጸሙን አመልክተዋል።

የቤተ-ክርስቲያኒቷ አገልጋይ የሆኑ አንድ የዐይን እማኝ ተፋላሚ ኃይሎቹ ተኩስ ልውውጥ ማድረግ ሲጀምሩ ወደ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ መግባታቸውን ገልጸው፤ መቃብር ሲቆፍሩ የነበሩ እድርተኞች ግን ቁፋሮ ላይ እያሉ እርሳቸው “መከላከያ” ባሏቸው ኃይሎች ስለመገደላቸው ገልጸዋል።

የመንግሥት ኃይሎች መጠጋታቸውን ተከትሎ “የሥላሴ ቅዳሴ” ላይ የነበረው ምዕመን ወደ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ እንዲገባ ማድረጋቸውን የተናገሩት አገልጋዩ፤ መቃብር ቆፋሪዎቹ ግን “‘እኛ መቃብር ነው የምንቆፍረው ንጹሃን ነን፤ ምንም አንሆንም’ ብለው ሲቆፍሩ” የጥቃቱ ሰለባ እንደሆኑ እማኝነታቸውን ተናግረዋል።

“የሆነች ሴትዮ ሞታ ኑሯል፤ ሕዝቡ ተሰባስቦ የባለእግዚያብሔር እድር ነበር የእሷን መቃብር እየቆፈሩ ነው [ጥቃቱ የደረሰው]። እንዲያ ሲታኮሱ ቆይተው መጥተው ሲያያቸው [መቃብር ቆፋሪዎቹን] ምን እንዳሰቡ እንጃ እዳሪ [ከመቃብር ቤት ውጭ] ያሉትንም፤ ቤት ያሉትንም ገድለዋቸው ነው የሄዱት” ሲሉ ስለ ግድያው ተናግረዋል።

ሌላ ነዋሪም አንድ በእድሜ የገፉ መነኩሴን ለመቅበር መቃብር እየቆፈሩ የነበሩ እድርተኞች ላይ ጥቃቱ መፈጸሙን ገልጸዋል።

አምስቱ ሰዎች ወዲያውኑ ሕይታቸው ሲያልፍ፤ አንዱ ሆስፒታል ከሄደ በኋላ እንዲሁም አንድ የቆሎ ተማሪ ደግሞ ከቤተ-ክርስቲያን ወጣ ባለ አካባቢ ተገድሎ መገኘቱን ተናግረዋል።

ጥቃቱን “አሰቃቂ ጭፍጨፋ” ሲሉ የገለጹት የአካባቢው ነዋሪ፤ አስከሬን ለማንሳት ወዲያው ወደ ቤተ-ክርስቲያኒቷ ቅጥር ጊቢ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

“ስንሄድ አምስት ሰዎች አንድ ላይ ተገድለዋል። ስድስተኛው የሞተው በኋላ ላይ ነው። ጭንቅላቱ አካባቢ ላይ ነው የተመታው። ስለዚህ ነፍስ ስለነበረው እሱን ለማዳን ቅድሚያ ለእሱ ትኩረት ሰጥተን አነሳነው” ብለዋል።

ሦስት ሰዎች ቆስለው ቀራኒዮ ጤና ጣቢያ ለህክምና መግባታቸውን ለቢቢሲ ያረጋገጡ አንድ የህክምና ባለሙያ፤ ጭንቅላቱ ላይ የቆሰለው ታካሚ ሕይወቱ ከሰዓት በኋላ ማለፉን ገልጸዋል።

“ሁለቱ እጃቸውን፤ አንዱ ጭንቅላቱን ነው የተመታው። ለሞጣ ሪፈር ብለነው [ጭንቅላቱን የተመታው] ሞጣ ሲደርስ ሕይወቱ አለፈ” ሲሉ የህክምና ተቋም ምንጩ ተናግረዋል።

የጥቃቱ ሰለባዎች በጉልበት ሥራ ይተዳደሩ የነበሩ ሰዎች መሆናቸውን የተናገሩት ነዋሪዎች እድርተኛ በመሆናቸው ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቁፋሮ ላይ የነበሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

“በአብዛኛው ደካማ [ኑሮ የሚኖሩ]፣ እንጨት የሚፈልጡ፣ ረዳት ሆነው ቋጠሮ የሚሸከሙ፣ ጭቃ የሚያቦኩ ሰዎች ናቸው የተገደሉት” ሲሉ አንድ ነዋሪ ስለ ሟቾቹ ማንነት ተናግረዋል።

የመንግሥት ኃይሎች “ምሽግ ትቆፍራላችሁ” በሚል ጥርጣሬ ግድያውን እንደተፈጸሙ አስከሬን ተጭኗቸው በሕይወት መትረፍ ከቻሉ ሰዎች መረዳታቸውን የደብሩ አገልጋይ ተናግረዋል።

ጥቃት አድራሹ “መከላከያ” ለመሆኑ በምን እርግጠኛ እንደሆኑ ለቢቢሲ የተናገሩት ነዋሪዎች፤ በለበሱት የደንብ ልብስ፣ በሚያሽከረክሩት መኪና እንዲሁም በአካባቢው ሲንቀሳሰቀሱ የሚያውቋቸው በመሆናቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

የሟቾቹ ቀብር የዚያኑ ቀን መፈጸሙን ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን፤ አምስቱ ሰዎች በአንድ ጉድጓድ ውስጥ መቀበራቸውን ተናግረዋል።

“. . . ተመልሰው መጥተው ይመቱናል የሚል ስጋት ነበር። ‘ይመለሳሉ፤ አሁን መጡ’ የሚል ስጋትም ነበር” በማለት በአንድ ጉድጓድ ለመቅበር መገደዳቸውን ገልጸዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ በአካባቢው ስጋት ማደሩን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ በቀራኒዮ የገበያ ቀን የሆነውን ቅዳሜን ጨምሮ ግብይትና እንቅስቃሴ እንደሌለ ተናግረዋል።

አንድ ዓመት ሊሞላው በተቃረበው የአማራ ክልል አለመረጋጋት፣ በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በሚካሄዱ ግጭቶች ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተቋማት የሚያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

Source: https://www.bbc.com/amharic/articles/cg33wypl722o

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time