Friday, September 23, 2016

የውጭ ኩባንያዎች የነገሡበት የቢራ ኢንዱስትሪና እንግዳው ቢራ

በኢትዮጵያ የመጀመርያው የቢራ ፋብሪካ ተገንብቶ ሥራ የጀመረው ከ90 ከዓመታት በፊት ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የቢራ ፋብሪካ በወቅቱ ሥራ ሲጀምር በባለቤትነት የተመዘገበው በውጭ ሰዎች ነበር፡፡ ኋላ ላይ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተይዞ መቀጠሉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የአስመራው ሜሎቲ ቢራ ፋብሪካ በሁለተኛው የአገሪቱ ፋብሪካ እንደነበር ይጠቀሳል፡፡ ሌሎች ፋብሪካዎች መመሥረት የጀመሩት እነዚህ ገበያውን ከተቀላቀሉ በኋላ ነው፡፡
ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ በ1956 ዓ.ም. ሲቋቋም ወደ ሥራ የገባው በዓመት 150 ሔክቶ ሊትር የማምረት አቅም ይዞ ነበር፡፡ ቀጥሎ የተቋቋመው ሐረር ቢራ ፋብሪካ በ1972 ዓ.ም.  ሲመሠረት፣ በደሌ ደግሞ በ1976 ዓ.ም. ሥራ መጀመሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እስከ ደርግ ውድቀት ድረስም እነዚህ ፋብሪካዎች የአገሪቱን የቢራ ፍላጎት ሲያሟሉ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በተለያዩ ኩባንያዎች ይተዳደሩ እንጂ የቢራ ፋብሪካዎች ቁጥር አሥራ አንድ ደርሷል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመጠጥ ኢንዱስትሪዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ከፍያለው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በቢራ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉት 11 ፋብሪካዎች ውስጥ በሰባት የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ባለቤትነትና ባለድርሻነት የተያዙ ናቸው፡፡ በሚቀጥለው ወር አጋማሽ ወደ ሥራ ይገባል የተባለው ዛቢዳር ቢራ ሲጨመርበት  የፋብሪካዎቹ ቁጥር ወደ 12 ይደርሳል፡፡ ፋብሪካዎቹን ኩባንያዎቹም ስምንት እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
የቀጣዩ ጊዜ የቢራ ምርት
በገበያው ውስጥ ያሉት የቢራ ፋብሪካዎች ዓመታዊ የምርት መጠናቸው በዓመት ከ10.5 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር በላይ እንደደረሰ ይታመናል፡፡ እንደ አቶ አክሊሉ ገለጻ ግን በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የቢራ ፋብሪካዎች የማምረት አቅም 11.7 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ደርሷል፡፡ተደጋግሞ እንደሚነገረው ይህ ዓመታዊ የቢራ ምርት በአገሪቱ ውስጥ አለ ከሚባለው ፍላጎት ጋር ሲመሳከር በቂ አይደለም፡፡
በርካቶቹ የቢራ ፋብሪካዎች የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ያላቸው በመሆኑ፣ በ2009 በጀት ዓመት የማስፋፊያ ሥራቸውን የሚያጠናቅቁ የቢራ ፋብሪካዎች እንዳሉ የገለጹት አቶ አክሊሉ፣ ሐይኒከንና ሐበሻ ቢራ ፋብሪካዎች ያላቸው የማስፋፊያ ሥራና የዛቢዳር ቢራ ምርት ሲታከል በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የአገሪቱ የቢራ ምርት 13.5 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ይሆናል፡፡ 
በቅርቡ ገበያውን ይቀላቀላል ተብሎ የሚጠበቀው ዛቢዳር ቢራ፣ ይህንኑ የገበያ ፍላጎት ታሳቢ አድርጎ ሥራ ለመጀመር እየተዘጋጀ ነው፡፡ ገበያው እንዳለ፣ በአገሪቱ የቢራ ምርትና ፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት ሌሎች ተጨማሪ ቢራ ፋብሪካዎችን ለማምጣት ያስችላል የሚል ትንታኔ የተሰጠበት ነበር፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ግን የኢትዮጵያ ዓመታዊ የቢራ ምርት በነፍስ ወከፍ ሲታሰብ ከሌሎች አፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡
ለአብነትም የኬንያ ዓመታዊ የቢራ ምርት በነፍስ ወከፍ ሲሰላ 12 ሊትር ደርሷል፡፡ የኢትዮጵያ ገና አምስት ሊትር ላይ የሚገኝ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካውያን ፍጆታ በነፍስ ወከፍ 58 ሊትር ደርሷል፡፡ ይሁን እንጂ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በቢራ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተካሄዱ ኢንቨስትመንቶች የአገሪቱን ዓመታዊ የቢራ ምርት መጠን እያሳደጉ መጥተዋል፡፡ ከአሥሩ ቀዳሚ የቢራ አምራች አገሮች መካከልም ኢትዮጵያ አንዷ ለመሆን እንደበቃች መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አኅጉራዊውን የቢራ ምርት በተመለከተ ከአኃዛዊ መረጃዎች መረዳት እንደሚቻለው እ.ኤ.አ. በ2005 የአፍሪካ ዓመታዊ የቢራ የምርት መጠን 141.9 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ሲደርስ፣ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ቢራ አምራች የሆነችው ደቡብ አፍሪካ መሆኗን ያሳያል፡፡ ከዚያም ናይጄሪያና አንጎላ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ይከተላሉ፡፡ ኢትዮጵያ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
 ቅዱስ ጊዮጊስ ቢራ ፋብሪካ ከ90 ዓመታት በፊት የምርት ተግባሩን ሲጀምር በቀን ይመረት የነበረው ቢራ መጠን 200 ጠርሙሶች ብቻ ነበር፡፡ በዓመት ወደ 53 ሺሕ ጠርሙሶች ብቻ እንደ ማለት ነው፡፡ በዚህ መጠን የተጀመረው የቢራ ምርት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ቁጥሩን በጠርሙዝ ሳይሆን በሔክቶ ሊትር ወደ መለካት የሚያስችል ደረጃ ሊያድግ ችሏል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ በአዲስ አበባ፣ በኮምቦልቻና በሐዋሳ ያቋቋማቸው ሦስቱ ፋብሪካዎች በዓመት ከሦስት ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር በላይ የማምረት አቅም አላቸው፡፡ ከቢጂአይ ያገኘነው መረጃ ይህንኑ ያሳያል፡፡
እንደ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ሁሉ ዳሸን ቢራ ፋብሪካም ጎንደር ከሚገኘው የመጀመርያ ፋብሪካ በተጨማሪ በደብረ ብርሃን አዲስ ፋብሪካ ገንብቶ ሥራ አስጀምሯል፡፡ ሁለቱ የዳሸን ቢራ ፋብሪካዎች በዓመት ከሁለት ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር በላይ የማምረት አቅም አላቸው፡፡ በደሌና ሐረር ቢራ ፋብሪካዎችን በመግዛት የኢትዮጵያን የቢራ ኢንዱስትሪ የተቀላቀለው ሐይኒይከን፣ ከመንግሥት በግዥ ከተረከባቸው ከበደሌና ከሐረር ቢራ ፋብሪካዎች በተጨማሪ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቂሊንጦ አካባቢ አዲስ ያስገነባው ፋብሪካ ሲታከልበት በሐይኒከን ሥር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ምርቶቻቸውን የሚያሠራጩ የሦስት ቢራ ፋብሪካዎች ባለቤት በመሆን እየንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ሦስቱ የቢራ ፋብሪካዎች በዓመት ከ2.5 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር በላይ የማምረት አቅም እንዳላቸው ይታወቃል፡፡
በእንግሊዙ ዲያጅዮ ኩባንያ የተገዛው ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካም በአሁኑ ወቅት የማምረት አቅሙ አንድ ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር በላይ ደርሷል፡፡
እነዚህ የቢራ አምራች ኩባንያዎች ባሻገር ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ገበያውን ከተቀላቀሉት አንዱ የሆነው ራያ ቢራ የማምረት አቅሙ ግማሽ ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ሲሆን፣ ሐበሻ ቢራ በኩሉ 350 ሺሕ ሔክቶ ሊትር የማምረት አቅም አለው፡፡ ይህም አጠቃላይ የአገሪቱ የቢራ ፋብሪካዎች ዓመታዊ የማምረት አቅም ከአሥር ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር በላይ መሆኑን ያለክታል፡፡ በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባው ዛቢዳር ቢራ ፋብሪካ  ደግሞ ወደ ሥራ የሚገባው 300 ሺሕ ሔክቶ ሊትር የማምረት አቅም ይዞ ኢንዱስትሪውን ስለሚቀላቀል የአገሪቱ ዓመታዊ የቢራ ጠመቃ አቅም እየጨመረ ይቀጥላል፡፡ በተለይ አዳዲሶቹ የቢራ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ከእጥፍ በላይ ለማሳደግ በሚያስችል የግንባታ ሥልት የተገነቡ በመሆኑ፣ አሁን ካለው የበለጠ ምርት ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያውያንን ባለቤትነት እያከሰመ የሄደው ቢራ
የአገሪቱ የቢራ ፋብሪካዎች የባለቤትነት ጉዳይ ሲታይ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ለውጦች የታዩበት መስክ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ከመጀመርያው የአገሪቱ ቢራ ፋብሪካ ጀምሮ አሁን ገበያውን ለመቀላቀል ዝግጅት እያደረገ እስካለው ዛቢዳር ቢራ ፋብሪካ ድረስ ሙሉ በሙሉ ወይም በአብላጫው የኩባንያዎች የባሌትነት ድርሻ በውጭ ኩባንያዎች የተያዙ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
የቢራ ኢንዱስትሪ ከ20 ዓመታት ወዲህ የሄደበትን ጉዞ ብንመለከት፣ የቢራ ፋብሪካዎች ባለቤትነት ከኢትዮጵያውያን እየሸሸ ወደ ውጭ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ያመራ እንደሚገኝ እናያለን፡፡ ሌላው ቀርቶ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት ተቋቁመው ወደ ሥራ ይገባሉ ተብለው አክሲዮኖችን ሲሸጡ የነበሩ አዳዲሶቹ የቢራ ፋብሪካዎች ዕውን ለመሆን የውጭ ኩባንያዎችን ፋይናንስ ለመደገፍ ተገደዋል፡፡ ከአክሲዮኖቻቸው ውስጥ ከፍተኛውን የባለቤትነት ድርሻ የውጭ ኩባንያዎች እንዲይዙት አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት ይያዛሉ የተባሉት የቢራ ፋብሪካዎች ብልጫ ያለውን የአክሲዮን ድርሻ ለውጭዎቹ የለቀቁት በተለያየ ምክንያት ነው፡፡ ዋናው ግን ለኢንቨስትመንት የሚፈለገውን ገንዘብ በአገር ውስጥ የአክሲዮን ሽያጭ ማሰባሰብ ባለመቻሉና በቢራ ጠመቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልምድ ያላቸውን ኩባንያዎች ማስገባቱ ኢንቨስትመንቱን የበለጠ ያዋጣል በሚል ምክንያት ነው፡፡ በተለይ ኩባንያዎቹ ልምዳቸውን ይዘው ስለሚቀርቡ የውጭ የቢራ አምራች ኩባንያዎች በነባሮቹም ሆነ በመቋቋም ላይ ባሉት የአገሪቱ የቢራ ፋብሪካዎች ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ እንዲይዙ አስችሏቸዋል፡፡
የውጮቹ በመንግሥት እጅ የነበሩትንም ሙሉ ለሙሉ ለመግዛት ችለዋል፡፡፡ አብዛኛዎቹ የቢራ ፋብሪካዎች በቀደምው መንግሥት የተቋቋሙ፣ ባለቤትነታቸውም የመንግሥት ነበር፡፡ ደርግ እስከወደቀበት እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስም የአገሪቱ የቢራ ገበያ ውስጥ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሐረር፣ በደሌና ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪዎች የሚያስገኙት ዓመታዊ ትርፍ ለመንግሥት ሁነኛ የገቢ ምንጭ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ደርግ በባለቤትነት ሲያስተዳድራቸው የነበሩት አራቱ የቢራ ፋብሪካዎች ከደርግ ውድቀት በኋላም ባለቤትነታቸው በመንግሥት እጅ እስከቅርብ ጊዜ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት እነዚህን ፋብሪካዎች ይዞ ለመቆየት የማይፈልግና ወደ ግል ይዞታ እንዲዛወሩ ለማድረግ በመነሳቱ፣ ፋብሪካዎቹን ለመሸጥ በተደጋጋሚ ጨረታ በማውጣት ገዥ ሲያፈላልግ ቢቆይም ቀድሞ መሸጥ የቻለው ቅዱስ ጊዮርፊስ ቢራ ፋብሪካን ብቻ ነበር፡፡ በወቅቱ እነዚህን የቢራ ፋብሪካዎች ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በጥምረት ለመግዛት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካን የገዛው ቢጂአይ የተባለው የፈረንሣይ ኩባንያ ነው፡፡ በወቅቱ ይህ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ በአሥር ሚሊዮን ዶላር መሸጡ ይታወሳል፡፡ ቀሪዎቹን ፋብሪካዎችም ቢሆን በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያውያን ሊገዟቸው አልቻሉም፡፡ ዶላር ይዘው የመጡት የውጭ ኩባንያዎች ለዓመታት በኢትዮጵያ መንግሥት በባለቤትነት የቆዩትን ፋብሪካዎች ተራ በተራ ተረከበዋል፡፡ ሐይኒከንና ዲያጅዮ በባለቤትነት ወስደዋቸዋል፡፡ በዚህ አኳኋን መንግሥት ከቢራ ንግድ ሥራ ራሱን አስወጥቷል፡፡
በዚህ መካከል ግን ኢትዮጵያውያን በባለቤትነት የሚያስተዳድሯቸው፣ በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ የሚቋቋሙ የቢራ ፋብሪካዎችን ለመገንባት የአክሲዮን ሽያጭ መጀመሩም ይታወሳል፡፡ ከአክሲዮን ኩባንያዎቹ አነሳስ መረዳት የሚቻለውም ባለቤቶቻቸው ኢትዮጵያውያን ይሆናሉ የሚል መነሻ እንደነበር ነው፡፡ ራያ፣ ሐበሻና ዛቢዳር የተባሉ የቢራ ፋብሪካዎችን ለመመሥረት አክሲዮን ሽያጭ ማካሄድ ጀምረው ነበር፡፡ ነገር ግን እንደታሰበው አልሆነም፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ከጠቅላላ አክሲዮኖች ውስጥ አብዛኛውን አለያም ትልቁን የባለቤትነት ድርሻ የውጭ ኩባንያዎች ወሰዱ፡፡ የውጭ ኩባንያዎች የባለቤትነት ድርሻ እየጎላ ስለመምጣቱ ማሳያ ይሆናል የተባለው የዳሸን ቢራ 51 በመቶ ድርሻ ወደ እንግሊዙ ዱዌት ኩባንያ በሽያጭ መተላለፉ ሲሰማ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ በደሌና ሐረር ቢራን ሐይኒከን በ163 ሚሊዮን ዶላር ገዛ፡፡ ዲያጆም ሜታን በ225 ሚሊዮን ዶላር ገዛ፡፡
ዳሸን ቢራ ፋብሪካ እ.ኤ.አ. 2000 ሲቋቋም በባለቤትነት የያዘው የአማራ ኢደውመንት ድርጅት (ጥረት) ነበር፡፡ ይህም ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ድርሻ መያዙን ያመለክት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. 2012 ግን የእንግሊዙ ድዌት ኩባንያ 51 በመቶውን ሲገዛ፣ የጥረት ወደ ድርሻ 49 በመቶ በመውረዱ፣ ብልጫ ያለውን የባለቤትነት ድርሻ ድዌት ወሰደ፡፡
በቅርቡ ተቋቁመው ወደ ሥራ ከገቡት ውስጥ ራያ ቢራ ከኩባንያው ጠቅላላ አክሲዮኖች ውስጥ 42 በመቶውን፣ ለፈረንሣዩ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሸጧል፡፡ ሐበሻ ቢራ በበኩሉ 70 በመቶውን ድርሻ የሆላንዱ ባቫሪያ በመሸጥ በዚሁ ኩባንያ ሊጠቅለል ችሏል፡፡
በጥቅምት አጋማሽ ገበያውን የሚቀላቀለው ዛቢዳር ቢራ ደግሞ 60 በመቶ የሚሆነውን የባለቤትንት ድርሻውን የቤልጄሙ ዩኒብራ ኩባንያ ገዛው፡፡ በጥቅሉ ሁሉም የቢራ ፋብሪካዎች የኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የአምበሳውን ድርሻ የልያዙበት ሊሆኑ ችለዋል፡፡ ውድድሩም በዓለም አቀፎቹ የቢራ ጠማቂዎች መካከል እንደሆነ እየተነገረለት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቢራ የወጭ ገበያዎችን መቆጣጠር ስለመቻሉ ግን ገና ወደፊት የሚታይ ነው፡፡ ይሁንና ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ግን በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪው መፎካከር ይዘዋል፡፡
የቢራ ኢንቨስትመንትና የባንክ ብድር
የቢራ ጠመቃ አዋጭ እንደሆነ ያነጋገርናቸው የቢራ ፋብሪካ ኃላፊዎች ያረጋግጣሉ፡፡ የበለጠ አትራፊ ለመሆንና ገበያ ውስጥ የተሻለ ተቀባይነት ለማግኘት ግን የእርስ በርሱ ፉክክር እየጠነከረ ስለመምጣቱም ይስማማሉ፡፡ በተለይ የውጭ ቢራ ፋብሪካዎች የአገሪቱን የቢራ ገበያ ከመቀላቀላቸው ቀደም ብሎ ከነበረው በተለየ የውድድር መንፈስ ተፈጥሯል ይላሉ፡፡
የውጭ ኩባንያዎች ወደ ቢራ ምርት የገቡት ቢዝነሱ አዋጭ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለማስፋፊያ ሥራዎቻቸውም ቢሆን የአገሪቱን ባንኮች ድጋፍ በማግኘታቸው ጭምር ነው፡፡ አዳዲስ ቢራ ፋብሪካዎች እንዲገነቡ ነባሮችም የማስፋፊያ ግንባታ እንዲያከናውኑ የፋይናንስ አቅርቦት ዕድል በመሰጠቱ ጭምር ነው፡፡
የራሳቸውን መዋዕለ ንዋይ ያፈሳሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩት የውጭ ኩባንያዎች  ሳይቀሩ ከአገሪቱ ባንኮች ብድር በብዛት ማግኘት ችለዋል፡፡ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ለአዲስ ቢራ ፋብሪካ ግንባታና የማስፋፊያ ሥራ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ፈሷል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ብልጫ ያለውን የኢንቨስትመንት ወጪ መሸፈን የተቻለው ከባንክ በተገኘ ብድር እንደሆነ ይነገራል፡፡ እንደምሳሌ ሊጠቀስ የሚችለው ሐይኒከን ቢራ ፋብሪካ ቂሊንጦ አካባቢ የገነባው አዲስ ፋብሪካ ከ1.4 ቢሊዮን ብር ብላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ ወጪውን ከልማት ባንክ ባገኘው ብድር ሊሸፍን ችሏል፡፡
የራያ ቢራ ከ910 ሚሊዮን ብር በላይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር ተለቆለታል፡፡ ሐበሻ ቢራ ደግሞ ከ500 ሚሊዮን ብር ከልማት ባንክ አግኝቷል፡፡ በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባውም ዛቢዳር 610 ሚሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ወጪው የተሸፈነው በባንክ ብድር ነው፡፡ እንደ ሌሎቹ ከፍተኛ አይሁን እንጂ ቅዱስ ጊዮርጊስና ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካዎችም ለማስፋፊያ ግንባታቸው የባንክ ብድር አግኝተዋል፡፡
በተለይ አዳዲሶቹ የቢራ ፋብሪካዎች ግንባታቸውን ለማጠናቀቅ ከሚያስፈልጋቸው ኢንቨስትመንት ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ከባንክ ብድር መሸፈን ከተቻለ የውጭዎቹ ኩባንያዎች ድርብ ዕድል እንዲያገኙ ያስቻላቸው ሆኗል፡፡
የቢራ ዓይነቶችና ምርት
ሰባቱ የቢራ ፋብሪካዎች ለገበያ የሚያቀርቧቸው የተለያዩ ምርቶች አሏቸው፡፡ በአልኮል መጠናቸውና ቅመማቸው የተለያዩ መሆናቸው የሚነገርላቸው የምርት ዓይነቶች ቁጥር ከ13 ይበልጣል፡፡
ቢጂአይ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አምበርና ካስትል የተባሉ ምርቶችን ያቀርባል፡፡ በሐይኒከን ሥር ያሉ ሦስቱ ፋብሪካዎች ደግሞ በደሌና ፕሪሚየም፣ ዋልያና ሐረር የተባሉ ቢራዎችን ያመርታል፡፡ ከዚህ ምርት ሌላ ሐረር ሶፊ የተባለ ከአልኮል ነፃ መጠጥ ለገበያ አብቅቷል፡፡
ሜታ ቢራ ሜታ ፕሪሚየም የተባሉ ምርቶችን ይዟል፡፡ ከቀሪዎቹ ፋብሪካዎች ግን የሚታወቁበት ዳሸን፣ ሐበሻና ራያ ቢራዎቻቸውን ያሠራጫሉ፡፡ ሁሉም ፋብሪካዎች የድራፍት ቢራም ያቀርባሉ፡፡ ኢንዱስትሪ ውስጥ ገብተው የወጡም የምርት ዓይነቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የቢጂአይ ምርት የነበረው ባቲ ቢራና በቅርቡ ዘመን ስያሜ ተሰጥቶት የነበረው የሜታ ምርቶች በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡
የጦዘው ፉክክርና እንግዳው ቢራ
የቢራ ፋብሪካዎች ባለቤትነት በውጭ ኩባንያዎች እጅ ከመውደቁ በፊት ገበያው ብዙ ውጥረት ያልነበረበት እንደነበር በዘርፉ የቆዩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
አሁን ውድድሩ ጦፏል፡፡ የገበያ ውድድሩ የተደበላለቀ ስሜትም ያለው ነው፡፡ አንዱ ፋብሪካ የሌላው ሠራተኛ ከመንጠቅ አንስቶ የተሻለ ገበያና ስም ለማግኘት ሁሉም የየራሱን ብልኃት ይጠቀማል፡፡ በተለያዩ የማኅበራዊ ተሳትፎዎች ውስጥ በመግባትም የደንበኞቻቸውን ቀልብ ለመሳብ የሚያደርጉት ጥረት የዚሁ የገበያ ውድድር አካል ሆኗል፡፡ በመጪው ወር አጋማሽ ላይ ገበያውን የሚቀላቀለው ዛቢዳር ቢራም የውድድር አካል ይሆናል፡፡
ከአዲስ አበባ 158 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጉብሬ ከተማ የፋብሪካ ግንባታው መጠናቀቁ የተነገረለት ዛቢዳር ቢራ ፋብሪካ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ እንደ ዛቢዳር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገብሩ ሐብተ ወልድ ማብራሪያ፣ ፋብሪካው እስከ 670 ሺሕ ሔክቶ ሊትር ቢራ የማምረት አቅም እንዲኖረው የተገነባ ቢሆንም አሁን  በዓመት 300 ሺሕ ሔክቶ ሊትር በማምረት ወደ ሥራ ይገባል፡፡
እንደ መረጃው ከሆነ ከጠቅላላ ኢንቨስትመንቱ ውስጥ 610 ሚሊዮን ብር የሚሆነው በባንክ ብድር የተሸፈነ ሲሆን፣ ቀሪው ደግሞ በዩኒብራልና ዛቢዳር ቢራ ለመመሥረት የተቋቋመው ጃሚር ሁለገብ አክሲዮን ማኅበር ነው፡፡ Read more here

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time