Tuesday, October 10, 2017

የኦሮሚያና የሶማሌ ግጭት ሙሉ በሙሉ እንዳልቆመ መንግሥት አስታወቀ

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ከወር በፊት ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ እንዳልቆመ መንግሥት አስታወቀ፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ዓርብ መስከረም 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል የከፋ ግጭት ባይኖርም በየቀኑ አልፎ አልፎ ግጭት መከሰቱ ቀጥሏል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በኩል እስካሁን ድረስ እየሞቱና እየተፈናቀሉ ያሉ ሰዎች በየቀኑ ሪፖርት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ድረስም ጉዳቶች እንዳሉ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ደግሞ የታጠቀ ኃይል ሰርጎ እየገባና ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ነው ብለዋል፡፡
በሁለቱ ክልሎች መካከል ተቀስቅሶ የነበረውን ግጭት በተመለከተ ለመገምገምና አዳዲስ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ሲባል ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሁለቱን ክልሎች አመራሮች አግኝተው እንዳነጋገሯቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ውይይት ላይ ከኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ከሶማሌ ክልል ደግሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ግጭቱ የዜጎችን በሕይወት የመኖርና ንብረት የማፍራት መብቶች የጣሰ እንደሆነ መግለጻቸውን ጠቁመዋል፡፡ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦችን የማይወክሉ ኃይሎች ባደረሱት ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት መጥፋት ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ማስተላለፋቸውንም ተናግረዋል፡፡
ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጎች ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ክልል ባቀረበው ሪፖርት መሠረት ከ75 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የኦሮሚያ ተወላጆች ከሶማሌ ክልል መፈናቀላቸውን፣ ከኦሮሚያ ክልል ግን 392 የሶማሌ ተወላጆች መፈናቀላቸውን እንዳስታወቀ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ከአወዳይ አካባቢ ምሥራቅ ሐረርጌ የተፈናቀሉና ወደ ጅግጅጋ የሄዱ እንዳሉም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ኦሮሞዎች የሶማሌ ሕዝብ እንዳላፈናቀላቸው፣ አንዳንዶቹ በተለያዩ አካላት ተገፍተው፣ ሌሎቹ ደግሞ በአመራሩና በፀጥታ አካሉ ላይ እምነት ስላልነበራቸው ከሶማሌ ክልል መፈናቀላቸውን እንደገለጹም ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉት ምናልባት 400 ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ በኦሮሚያ በኩል የተገለጸው ይህ ነው፡፡ እንዲያውም አወዳይ አካባቢ የደረሰውን ጥቃት የከፋ እንዳይሆን ያደረገው የኦሮሞ ሕዝብ እነዚህን ተፈናቃዮች ደብቋቸው ወደ ሐረር እንዲሄዱ በማድረጉ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በሕዝቡ መሀል ችግር ከሌለ ይህ ግጭት ለምንድነው የተከሰተው ለሚባለው አመራሩ ራሱን እንዲፈትሽ የሚያስገድድ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውንም ተናግረዋል፡፡
‹‹በዚህ ግጭት እስካሁን ድረስ ምን ያህል ሰው እንደሞተ ሁለቱም ክልሎች የሚገልጹት እንዳለ ሆኖ፣ በአሁኑ ወቅት እየተጠና ስለሆነ ወደፊት ለሕዝቡ ይፋ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም በግጭቱ ምክንያት የደረሰውን ጉዳትና የሞተውን የሰው ቁጥር ለማወቅ በአሁኑ ወቅት እያጠና መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹በቅርብ ጊዜ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ያቀርባል፤›› ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ከሁለቱ ክልሎች ወንጀል የፈጸሙትንና ለግጭቱ መንስዔ የሆኑትን የፌዴራል ፖሊስ እያጣራና በቁጥጥር ሥር እያዋለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ግጭቱን ለማስቆም ሲባልም የሁለቱ ክልሎች የፀጥታ አካላት ከአዋሳኝ አካባቢዎች እንዲርቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አቅጣጫ መስጠታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በዚህ መሠረትም የሁለቱም ክልሎች ሚሊሻዎች ከወሰን አካባቢ አምስት ኪሎ ሜትር እንዲርቁ፣ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል እየተባለ የሚጠራው ፖሊስና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስም ከአዋሳኝ አካባቢዎች ከአሥር እስከ 20 ኪሎ ሜትሮች መራቅ እንዳለበት አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግሥት በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ ታጣቂዎችን ትጥቅ እያስፈታ ነው እየተባለ በተለያዩ ሚዲያዎች እየተገለጸ እንደሆነ ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ይህ ውሸት እንደሆነና የተከለከለውን ዞን ጥሰው የሚገቡ አካላት በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ ግን እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሁለቱ ክልሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት የወጪ ንግድ መስተጓጎል እያስከተለ እንደሆነ መንግሥት መገምገሙን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በምሥራቅ በኩል ጫትና ሌሎች ምርቶች እንዲቆሙና እንዲቃጠሉ በመደረጉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት ያስቀመጡትን አቅጣጫና መመርያ የጣሰ መሆኑ ታውቆ ለወደፊቱ እንዲስተካከል አቅጣጫ መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡
ለጫትና ለሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች መስተጓጎል ምክንያቱ ደግሞ በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ያለው ኬላ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱም ክልሎች በገቢና በወጪ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ኬላ ማቆም እንደሌለባቸው፣ ወደፊት በፌዴራል መንግሥት ሥር ሆነው መሥራት እንደሚገባቸው መናገራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በተመለከተም በጊዜያዊነት የሚያስፈልጋቸው ድጋፍ በአፋጣኝ እንዲደረግላቸው፣ የተጎዱት ንብረታቸው የሚመለስበትና ለወደመባቸው ደግሞ ካሳ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሳሰባቸውን ተናግረዋል፡፡
የሶማሌ ክልል መንግሥትና የአገር ሽማግሌዎች ባለፈው ሳምንት ያወጡትን መግለጫ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አይተው እንዳዘኑና እንደዚህ ዓይነት መግለጫ ለወደፊት መውጣት እንደሌለበት ጥብቅ ማሳሰቢያ መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡
የሶማሌ ክልል መንግሥትና የአገር ሽማግሌዎች ማክሰኞ መስከረም 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የጋራ መግለጫ ያወጡ ሲሆን፣ መግለጫው የሶማሌ ሕዝብ የቀድሞውን የደርግ ሥርዓት ለማስወገድ በተደረገው ትግል ሕዝቡ መስዋዕትነት እንደከፈለ አስታውሷል፡፡ መግለጫው በሁለቱ ክልሎች መካከል ለተቀሰቀሰው ግጭት ዋነኛ ተጠያቂ የኦሮሚያ ክልልን አድርጓል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time