“የፖሊሲ ለውጥ ከሌለ የግለሰቦች መቀያየር ለውጥ አያመጣም”
• ተቃዋሚዎችና ፖለቲከኞች በሹም ሽሩ ደስተኞች አይደሉም
• የህዝቡን ጥያቄዎች መለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል ተባለ
ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተቀሰቀሰው ታይቶ የማይታወቅ ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በአጠቃላይ ወደ አንድ ሺ የሚጠጉ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በብዙ ሺዎች የሚገመቱ በእስር ላይ እንደሚገኙ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ የሟቾች ቁጥር ተጋንኗል የሚለው መንግስት በበኩሉ፤የጸጥታ ሃይሎችን ጨምሮ ከ500 በላይ ሰዎች መሞታቸውን አልካደም፡፡ በተቃውሞው በርካታ የመንግስትና የግል ባለሃብቶች ንብረትም እንደተቃጠለና እንደወደመ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ይሄን የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ ነው በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት፤የከፍተኛ ባለስልጣናትን ሹም ሽር የሚያካትት “ጥልቅ ተሃድሶ” በማድረግ የህዝቡን ጥያቄዎች እንደሚመልስ በ2008 መጠናቀቂያ ላይ ቃል የገባው፡፡ በዚህ መሃል በኦሮሞ ባህላዊ የምስጋና ቀን “እሬቻ” በዓል ላይ በተከሰተው አስደንጋጭ የበርካታ ዜጎች ህልፈት ሳቢያ ህዝባዊ ቁጣ ተቀሰቀሰ፡፡ በቀጣዮቹ ቀናትም በተለይ የውጭ ባለሃብቶችን ክፉኛ ያስደነገጠ ውድመትና ዘረፋ በፋብሪካዎቻቸው፣በእርሻቸው፣በአጠቃላይ በንብረቶቻቸው ላይ ተፈጸመ፡፡ ይሄን ተከትሎም የዛሬ ሦስት ሳምንት መንግስት አገሪቱን ለማረጋጋትና የህዝቦችን ሰላም ለማስጠበቅ በሚል ለ6 ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን አስታወቀ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በግንቦት 200ገ ምርጫ ማግስት ራሳቸው ያቋቋሙትን የሚኒስትሮች ካቢኔት በመበተን፣ከወትሮው በተለየ መንገድ በምሁራን የተዋቀረ አዲስ ካቢኔ የመሰረቱ ሲሆን 9 ሚኒስትሮች ብቻ ባሉበት ሲቀሩ 16 አዳዲስ ሚኒስትሮችን ሾመዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 5 የሚሆኑት የፓርቲ አባል አይደሉም ተብሏል፡፡ ሹመቱ የተከናወነው በዋናነት የትምህርት ዝግጅትና ብቃትን መሰረት አድርጎ መሆኑን ለተወካዮች ም/ቤት የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፤አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ አቅሙና ብቃቱ ያላቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ፖለቲከኞች ግን በአዲሱ ካቢኔ ደስተኛ አይደሉም፡፡ በምሁራን በተዋቀረው አዲስ ካቢኔም እምብዛም የተደመሙ አይመስሉም፡፡ ጠንከር ያለ ሂስ የሰነዘሩም አልጠፉም። ሁሉም በአንድ ድምጽ የሚስማሙበት ግን የፖሊሲ ለውጥ አስፈላጊነት ላይ ነው፡፡ የፖሊሲ ለውጥ ሳይደረግ ግለሰቦች መለዋወጥ ብቻውን ውጤት አያመጣም ባይ ናቸው፡፡ የህዝቡም ጥያቄዎች በዚህ መንገድ መልስ ያገኛሉ ብለው እንደማያምኑ አበክረው ይናገራሉ፡፡ አንጋፋዎቹን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ፖለቲከኞች በአዲሱ ሹም ሽር ዙሪያ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡
****
“ዋናው መሰረታዊ ጉዳይ የፖሊሲ ለውጥ ነው”
ዶ/ር መረራ ጉዲና
(የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የተቃዋሚ መሪ
*የሰሞኑን የሚኒስትሮች ሹመት እንዴት አገኙት? እንደጠበቁት ነው ወይስ ----?
“ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” እንደሚባለው ነው የሆነው፡፡ ህዝብ እየጠየቀ ያለው መሰረታዊ ለውጥ ነው፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ ቀባብቶ ለማለፍ እየሞከረ ነው፡፡ ከኋላ የነበሩትን ወደፊት በማምጣት “ይኸው እየተሻሻልኩ ነው፤እየተለወጥኩ ነው፤ እየታደስኩ ነው” እያለ ነው፡፡ ህዝብ ግን የጠየቀው፡- ነፃ ምርጫ ቦርድ፣ ነፃ ፍርድ ቤት፣ ነፃ ሚዲያ፣ ነፃ የሲቪክ ተቋማትና ሌሎች ብዙ ጉዳዮችን ነው። ራስን በራስ ማስተዳደር ሌላው የህዝብ ጥያቄ ነው፡፡ ኢህአዴግ ግን “እኔ ራሴ እየተለወጥኩ ነው እመኑኝ፤ ጥያቄያችሁን እየመለስኩላችሁ ነው” አይነት ነገር ነው እያለ ያለው፡፡
*ሹመቶቹ የትምህርት ዝግጅትንና ብቃትን መሰረት አድርገው የተሰጡ ናቸው ተብሏል፡፡ ከዚህ አንጻር ከቀድሞው የተሻለ ውጤት መጠበቅ አይቻልም?
ኢህአዴግ አሁን ከገባበት አጣብቂኝ ውስጥ ግለሰቦችን በመለዋወጥ የሚወጣ አይመስለኝም። ለህዝቡም ጥያቄ አጥጋቢ መልስ አይመስለኝም። ለምሳሌ ብዙ የእውቀት ሰርተፍኬት ያላቸው ሰዎች ገብተዋል ነው የተባለው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ያለው ችግር ግን የእውቀት ብቻ አይደለም፤ መሰረታዊ የፖሊሲ ችግር አለ፡፡ የአሰራር ችግር አለ፡፡ ያንን የሚለውጥ ነገር መፈጠር ነው ያለበት። ግለሰቦች ብቻ መለዋወጡ፣ “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም” ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ ተሾሙ የተባሉ ምሁራኖችም ቢሆኑ በኢህአዴግ አካባቢ የነበሩ ናቸው፡፡ አዳዲሶች አይደሉም፡፡ በተለያየ ደረጃ ኢህአዴግን ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው፡፡ ምን ውጤት እንደሚያመጡ ለወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡
*በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የሚሉትን ጨምሮ የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪነት ሹመቶች እንዲቀሩ ተደርገዋል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
እነዚህ የስልጣን እርከኖች ከህገ መንግስቱ ውጪ የነበሩ ናቸው፡፡ አንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንጂ በርካታ ምክትል ጠ/ሚኒስትሮችና አማካሪዎች ይኖራሉ የሚል አንቀፅ ህገ መንግስቱ ላይ የለም። ስልጣንን ለማደላደል የተደረገ እንጂ ህጋዊ አልነበረም፡፡ ዞሮ ዞሮ ያመጡትም የወሰዱትም እነሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህን በማስቀረታቸው የሚመጣ ብዙ ለውጥ የለም፡፡ እንዳልኩት ዋናው መሰረታዊ ጉዳይ የፖሊሲ ለውጥ ነው፡፡ ፖሊሲው ከተለወጠ በኋላ የተሻለ ስራ መስራት ያስችላል፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት ተሞክሮ አሁን ያለውን ቀውስ ያስከተለውን ፖሊሲ ሳይለውጡ፣ ባለስልጣናትን ወደ ፊትና ወደ ኋላ በማድረግ ምንም ውጤት ሊመጣ አይችልም፡፡ እንደ አንድ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር፣ በዚህ በኩል ምንም የሚታየኝ ነገር የለም፡፡
አዲሱ ካቢኔ በዚህ መልኩ በምሁራን ይዋቀራል ብለው ጠብቀው ነበር?
ምን መጠበቅ ያስፈልጋል! ተሃድሶ እናደርጋለን እያሉን አልነበር እንዴ፡፡ እኔ ግን ይሄን አልነበረም የጠበቅሁት፡፡ የፖሊሲ ለውጥ ነበር የምጠብቀው። “እኔ ማስተዳደር አቅቶኛል፤ከሌሎች ኃይሎች ጋር መግባባት ፈጥሬ፣ከምሁራን ጭምር ተቀናጅቼ ለውጥ አመጣለሁ” ቢል ነበር መልካም የሚሆነው። የሠለጠነ ሃገር ቢሆን ኖሮ፣ ይሄ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠይቆ ከስልጣን መውረድ ነበረበት፡፡ ብዙ ቃል የገባቸውን ነገሮች መፈፀም ስላቃተው፣ ”ስልጣን ወይም ሞት” ማለቱን ትቶ፣ ቢሆን ከስልጣን መውረድ ካልሆነ ደግሞ ከኢትዮጵያ ምሁራን ጋር ተቀናጅቶ፣የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ለመጀመር ቁርጠኝነቱን ማሳየት ነበረበት፡፡
የፖሊሲ ለውጥ የሚሉትን ሊያብራሩልኝ ይችላሉ?
የፖሊሲ ለውጥ ሲባል ለምሳሌ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አንዱ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት ነፃነት፣ ለምሳሌ የሚዲያ ነጻነት፣ የፍርድ ቤት ነጻነት፣ የፓርላማ ነፃነት ---- ሌላው ነው፡፡ ይሄ ሲሆን ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል፡፡ የስልጣን ክፍፍል ማድረግም አንድ የፖሊሲ ለውጥ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ህዝቡ በመረጣቸው የአካባቢ አስተዳደሮች እንዲመራ ማድረግ ነው፡፡
መሬትን በተመለከተ “መድረክ” መሬት ይሸጥ የሚል አቋም የለውም፤ ነገር ግን ለምሳሌ መንግስት መሬቱን ሲሸጥ ከሚያገኘው ገንዘብ ላይ ለገበሬው በተገቢው መልኩ ማካፈል አለበት፡፡ እነሡ አሁን 50 ሺህ ብር ካሳ ከፍለው ወዲያው ያንን ቦታ 50 ሚሊዮን ብር ይሸጡታል፡፡ ነገር ግን ከ50 ሚሊዮኑ ለገበሬው 10 ሚሊዮኑን መስጠት ይቻል ነበር፡፡ በቦታው ላይ 50 መኖሪያ ቤቶች ከተሰሩ ደግሞ 10ሩን ለባለ መሬቱ ሰጥቶ፣ እያከራየ ህይወቱን እንዲለውጥ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህም ገበሬው የተሻለ ህይወት ሊመራ ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ኢኮኖሚውንም የዲሞክራሲ ጨዋታ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የምርጫ ስርአቱ ይሻሻላል ተብሏል፡፡ ስርአቱ መሻሻሉ ምን የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል?
በፊት ከነበረው ይሻላል እንጂ መሠረታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ ባለፉት 16 እና 17 አመታት የአንድ ፓርቲ የበላይነት እንዲቀንስ ስንጠይቅ ነበር። አሁን ኦሮሚያ ውስጥ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ቢደረግ ኢህአዴግ በዝረራ ይሸነፋል፡፡ የሆኖ ሆኖ የምርጫ ሥርዓቱ መሻሻሉ አይጠላም፡፡ እኛም ስንጠይቀው የነበረ ነው፡፡ ግን መሠረታዊ መፍትሄ አይደለም። አሁን ህዝብ እየጠየቀ ያለው ከዚያም የላቀ ነው፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳይ አንዱ ጥያቄ ነው፡፡
==============================
“በምሁራን የተዋቀረ የመጀመሪያው ካቢኔ ነው”
አቶ ልደቱ አያሌው (ፖለቲከኛ)
የካቢኔ ሹም ሽረቱን እንዴት ገመገሙት? ለውጥ የሚያመጣ ይመስልዎታል?
እኔ እንደጠበቅሁት አላገኘሁትም፡፡ ትንሽ ወጣ ብሎ ለህብረተሰቡ ጥሩ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ የሚችሉ ግለሰቦችን ሊያካትት ይችላል የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ግን ያ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ አንደኛ የተቋቋመውን ካቢኔ “የምሁራን ካቢኔ” ልንለው እንችላለን፡፡ አሁንም በዋናነት የታየው አንደኛ የፓርቲ ታማኝነት ነው፤ ሁለተኛ የትምህርት ደረጃ ነው፡፡ እኔ ሁለቱም ብቻቸውን ውጤታማ የሆነ የህዝብ አስተዳደር ለማምጣት ያስችላሉ ብዬ አላምንም፡፡ የስራ ልምዳቸው ሲዘረዘር፣ ከአንድ ወይም ሁለት ሰው በስተቀር አብዛኞቹ በኢህአዴግ መዋቅር ውስጥ ባለፉት 15 ዓመታት የነበሩ ናቸው። አዲስ አመለካከት፤ አዲስ እይታ ያለው ሰው አልተቀላቀለም፡፡ ሁለተኛ፤ አንድ ሰው ሚኒስትር እንዲሆን የሚፈለገው ቴክኒካል የሆነ ምርምር እንዲሰራ አይደለም፡፡ ሚኒስትር ለመሆን በአንድ ነገር ላይ የረቀቀ እውቀት አይፈልግም። ሚኒስትርነት የበለጠ የፖለቲካ አመራር ብቃትን ይጠይቃል። ብዙ ጊዜ በኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በዓለም ሁኔታ የምናውቀው፣ የአካዳሚ ሰዎች የአመራርነት ሚናቸው በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ነው፡፡ በምሁርነት የቆዩ ሰዎች ወደ አመራርነት ሲመጡ፣ እውቀታቸውን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ነው የሚሆኑት፡፡
ምናልባት አሁን በሚሉት ጉዳይ ላይ አለማቀፍ ተሞክሮ ይኖር ይሆን?
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ በዚህ ደረጃ ከተዋቀረ በኋላ የተለያዩ የመረጃ አማራጮችን በመጠቀም አለማቀፍ ተሞክሮዎችን ለማየት ሞክሬያለሁ። የደረስኩበት መረጃ፣ አዲሱ ካቢኔ በዓለም ላይ በምሁራን የተዋቀረ የመጀመሪያው ካቢኔ መሆኑን ነው፡፡ ይህ የካቢኔ አደረጃጀት በዓለም ላይ የመጀመሪያዎቹ ሊያደርገን ይችላል፡፡ ሌሎች ሃገሮች ያልተደረገ ነው፡፡ ሚኒስትርነት ፖለቲካን የማስተዳደር፣ ውሳኔ የመስጠት ብቃትን የሚጠይቅ እንጂ ሙያን የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ግለሰቡ በአንድ ጉዳይ ላይ ምርምርና ጥናት ማድረጉ አይደለም መታየት ያለበት፡፡
ዋናው የሚኒስትር መስሪያ ቤቱን የተለያዩ ዲፓርትመንቶች አስተባብሮ አቀናጅቶ መምራት መቻሉ ነው፡፡ ዶክተሮችና ምሁራንን መመደብ ብቻውን ለውጥ ያመጣል ብዬ አላምንም። አንድ ሁለት ሰዎችን ነው ወጣ ያለ የስራ ልምድ ያየሁባቸው፡፡ ሌሎቹ በአጠቃላይ በኢህአዴግ ውስጥ የኖሩ ናቸው፡፡ አዲስ አቀራረብና አሰራር ይዘው ለመጡ የሚችሉ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ አንፃር ካቢኔው የሚፈለገውን ውጤት ያመጣል ብዬ አላምንም፡፡ ምናልባት አሁን ከተፈጠረው ቀውስ አንፃር ብሄረሰባዊ ተዋፅኦውን ጎላ አድርጎ በመሾም ሁኔታዎችን ለማርገብ የተፈለገ ይመስላል፡፡ ይሄ ግን አጉል ጨዋታ ነው የሚሆነው፡፡
ህብረተሰቡም እየጠየቀ ያለው ይሄን አይደለም። አቶ እገሌ ወርዶ፣ ዶ/ር እገሌ ይሾምልኝ አይደለም ያለው፡፡ የፖለቲካ ለውጥ ነው እየጠየቀ ያለው። ከዚህ አንፃር በቂ የሆነ ጥናትና ግምገማ ተካሂዶ፣ ለወቅቱ ችግር አስተዋፅኦ ሊያደርግ የሚችል ካቢኔ፣ በቅጡ ታስቦበት የተቋቋመ አልመሰለኝም። ቢቻል ከኢህአዴግ ወጣ ብሎ የሌላ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትም ቢሆኑ፣ ህብረተሰቡን ለማገልገል ፍቃደኝነቱ እስካላቸው ድረስ ማካተት ቢቻል ጥሩ ነበር፡፡ ያ ባይሆን እንኳ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ ሰዎችን ከንግዱ ማህበረሰብ፣ በሲቪል ተቋማት ከሚገኙ ምሁራን ማካተት ይቻል ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ አላየናቸውም። ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ጀምሮ በወረዳ መዋቅር ውስጥ የነበሩና የሚያውቋቸውን ሰዎች ነው ለሹመት ያቀረቡት፡፡
አንዳንድ ፖለቲከኞች “የሚያስፈልገው የፖሊሲ ለውጥ ነው” ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
አንዱ የስርአቱ ችግር የወቅቱን የህዝብ ተቃውሞና የብሶት እንቅስቃሴ ከአፈፃፀም ችግር ጋር አያይዞ ማየቱ ነው፡፡ ተቃውሞው በመልካም አስተዳደርና በኢኮኖሚ አፈፃፀም ጉድለት ሳቢያ ብቻ የመጣ አድርጎ ነው የሚመለከተው፡፡ የተቃውሞውን መሰረታዊ ምንጭ በደንብ ከመረመርነው ግን ችግሩ ፖለቲካዊም ነው፡፡ ስለዚህ ፖለቲካዊ መፍትሄ ካልመጣ በስተቀር ይሄን ችግር መፍታት አይቻልም፡፡ ለጊዜው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ችግሩን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ግን በዘላቂነት ችግሩን መቆጣጠር ያዳግታል፡፡ ስለዚህ መለስ ብሎ የችግሩን ምንጭ በጥልቀት መመርመር ያስፈልጋል። በዚህ ከተማመንን የችግሩን ምንጭ የማወቅ ጉዳይ ለኢህአዴግ ብቻ መተው የለበትም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ህዝቡ መወያየት አለባቸው፡፡
ኢህአዴግ ብቻውን ለምንድን ነው የሚወስነው? የችግሩ ምንጭ ላይ መተማመን ካልተቻለ፣ በመፍትሄው ላይ መተማመን ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ ኢህአዴግ የችግሩ ምንጭ ይህ ነው ብሎ በራሱ አይን አይቶ ከወሰነ በኋላ፣ ያንን ለማስፈፀም ነው ጥረት የሚያደርገው፡፡ ይሄ ግን ችግሩን አይፈታውም፡፡
የችግሩ ምንጭ ምንድን ነው? ብለን ከመረመርን፣ መሰረታዊ የሆኑ የፖለቲካ ችግሮች መኖራቸውን እንገነዘባለን፡፡ ያንን መፍታት የሚቻለው የአፈፃፀም አቅምን በማጎልበት ብቻ አይደለም፤ የፖሊሲ ለውጥ በማምጣት ነው፡፡ ከህገ መንግስቱ ጀምሮ የፌደራል አደረጃጀቱ የየራሳቸው ችግሮች አሉባቸው፤ እነሱ መሻሻል ይገባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በህገ መንግስቱም ሆነ በሌላ ህጎችም የተቀመጡ ጥሩ ጥሩ ህጎች መሬት ላይ መውረድ አለባቸው፡፡ ከወረቀት አልፈው ተግባር ላይ ሊውሉ ይገባል፡፡ የችግሮቹ መነሻ እነዚህ ነገሮች ናቸው፤ መፍትሄውም የሚገኘው ከእነዚህ ነው፡፡
ገዥው ፓርቲ ግን በጣም ቅንጭብጫቢ የሆኑ ከሙስና፣ ከመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመፍታት ብቻ ለውጥ አመጣለሁ እያለ ነው፡፡ ይሄ ግን ብቻውን መፍትሄ አይሆንም፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በተለያዩ የመዋቅር ማሻሻያዎች ለመፍታት ተሞክሮ የከሸፈ ነው፡፡ የችግሩ ምንጭ ያለው የፖለቲካ ሙስና ውስጥ ነው፤ የፖለቲካ ሙስና ሳይፈታ የኢኮኖሚ ሙስና ሊፈታ አይችልም፡፡ ኢህአዴግ የችግሩን መሰረታዊ ምንጭ አላወቀም ወይም ለማወቅ አልፈለገም፡፡
ተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ፤ ”ኢህአዴግ ምሁራንን አያሳትፍም፤ ሙያን ለሙያተኛ አይለቅም” የሚል ትችት ሲሰነዝሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይሄ ከእርስዎ አስተያየት ጋር እንዴት ይታረቃል?
ሚኒስትርነት የፖለቲካ ሹመት ነው፡፡ የሚፈለገው ውጤትም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያሉ የተለያዩ ዲፓርትመንቶችን አቀናጅቶ መምራት ነው። ከስራው ጋር ቀጥተኛ ሙያዊ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ምክትል ሆነው ሊሰሩ ወይም የዲፓርትመንት ኃላፊ ሆነው ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ ትችቱ ከዚህ አንፃር ነው መታየት ያለበት፡፡ ለምሳሌ የማህፀን ሃኪም ናቸው ብሎ ማብራሪያ መስጠት ከሚኒስትርነት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ለመሆን በአንድ ውስን ሙያ ላይ ኤክስፐርት መሆን አይፈልግም፡፡ የሚኒስትርነት ቦታው ሙያዊ አይደለም፤ ፖለቲካዊ ነው፡፡ የሚፈለገው የአመራር ብቃት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር የግድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ወይም የህግ ምሁር መሆን አይጠበቅበትም፤ ዋናው የአመራር ክህሎቱ ነው፡፡ ሙያተኞች ምክትል ሆነው ሊሰሩ ይችላሉ፡፡
===============================
“ዋናው ጥያቄ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የመመስረት ነው”
ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም (ዓለማቀፍ የህግ ባለሙያ)
ጠቅላይ ሚ/ሩ ያዋቀሩትን አዲስ ካቢኔ እንዴት አዩት?
እኔ ብዙም ለውጥ የሚያመጣ አይመስለኝም። ምክንያቱም የሰው ችሎታ ማነስ አይደለም የችግሩ ምንጭ፡፡ ዋናው ጥያቄ የፖሊሲ ጥያቄ ነው እንጂ በግለሰቦች ያለመርካት አይደለም። ዋናው መሰረቱ ፖሊሲ ነው፡፡ የፖሊሲ ለውጥ እስካልመጣ ድረስ በአዕምሮ ምጡቅ ነው የተባለ ሰው እንኳ ስልጣን ላይ ቢቀመጥ ለውጥ ላያመጣ ይችላል። ህዝቡ በተደጋጋሚ ሲጠይቃቸው ከነበሩት ጥያቄዎች መረዳት የሚቻለው፣ የፖሊሲ ጉዳዮችን የሚያስፈትሹ መሆናቸውን ነው። ዋናው ሲጠየቅ የነበረው ዲሞክራሲን የማስፈን ጉዳይ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ከተተገበረ ሌሎቹ ጥያቄዎች በዚያ አግባብ ምላሽ ያገኛሉ፡፡ የምርጫ ስርአቱ ስለሚሻሻል በህዝብ የተመረጠው ግለሰብ በሙስና ቢጨማለቅ፣ ህዝቡ በድምፁ መልሶ እንደሚያባርረው ያውቃል፡፡ ስለዚህ ዋናው ጥያቄ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የመመስረት ነው፡፡ የሚዲያዎች ነፃነት፣ የፍርድ ቤቶች ነፃነት፣ የሲቪክ ተቋማት ነፃነት ጥያቄ ነው፡፡ የግለሰቦች ለውጥ አይደለም ጥያቄው፡፡ የግለሰቦች መቀያየር ያን ያህል ለውጥ የሚያመጣ አይመስለኝም፡፡
የፖሊሲ ለውጥ ሲሉ ለምሳሌ--ይጥቀሱልኝ?
ነፃ ምርጫ፣ የፓርቲዎች ነፃነት፣ የጋዜጦችና የሚዲያ ነፃነት፣ የፍ/ቤቶች ነፃነት ---- በተለይ ለህግና ለህሊናቸው እንዲገዙ ማድረግ የመሳሰሉ መሰረታዊ የፖሊሲ ማሻሻያዎች መደረግ አለባቸው። እነዚህ አሁን በሀገራችን እንደሌሉ ይታወቃል። እነዚህ መሰረታዊ ለውጦች እስካልተደረጉ ድረስ የሰዎች መለዋወጥ ትርጉም የለውም፡፡ ይህን ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ኢህአዴግ ዝግጁ አይመስለኝም፡፡
ምሁራን ወደ ሚኒስትርነት መምጣታቸው አስተዳደራዊ መዋቅሮችን በእውቀት ለመግራት አስተዋፅኦ አይኖራቸውም?
እርግጥ ነው ምሁራን የተሻሉ ናቸው፡፡ እውቀቱ ከሌላቸው ሰዎች እውቀቱ ያላቸው የተሻለ እንደሚሰሩ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ወሳኙ ግን የሚሰሩት ስራ ምንድን ነው የሚለው ነው? አምባገነንነትን ለማጠናከርም ምሁራን ይሻላሉ፡፡ በዚያው ልክም ዲሞክራሲን ለማምጣት ምሁራን ይመረጣሉ፡፡
የፖለቲካ ምህዳሩ እስካልሰፋ ድረስ ግን የምሁራን መሾም ምንም ዋጋ የለውም፡፡ ምሁርነታቸውንና እውቀታቸውን በአግባቡ አውጥተውም ሊጠቀሙ አይችሉም፡፡
==============================
“ሹም ሽረቱን በበጎ አይን ነው የምመለከተው”
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (ፖለቲከኛ)
የህዝቡ ጥያቄ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ይፈቱልን የሚል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የተሾሙት ምሁራን የበለጠ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት ሊሰጡ ስለሚችሉ ሹመታቸው መልካም ነው፡፡ በሌላ በኩል እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ጠቅላላ ስርአቱ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ብቃቱና ዝግጁነቱ አለው ወይ? የሚለውን በደንብ ፈትሾ፣ የምሁራኑ እውቀት ተጨምሮበት ከተሰራ ጥሩ ነው፡፡ ያ ካልሆነ ግን ምሁራን በተለያዩ ዘርፎች መቀመጣቸው ብቻ የህዝብን ጥያቄ አይመልስም፡፡
ከዚህ በፊት “የፖለቲካ ስልጣኑ እውቀትና ብቃት ባላቸው ሰዎች ሳይሆን በታማኝ ፖለቲከኞች ብቻ ነው የሚያዘው” የሚለውን ሲያነሱ የነበሩት ራሳቸው ምሁራኑና የፖለቲካ ድርጅቶች ነበሩ። ህዝቡ ይሄን ጥያቄ ያነሳ አይመስለኝም፡፡ ህዝቡ በዋናነት የሚፈልገው ያነሳቸው ጥያቄዎቹ መመለሳቸውን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኢህአዴግ ምሁራንን መሾሙ ምናልባት “ሰዎች በታማኝነት እንጂ በእውቀት አይመደቡም” ለሚለው መልስ ሊሰጥ ይችላል፡፡ እንደኔ ግን እነዚህ የተሾሙ ሰዎች፤ ዶክተሮች ፕሮፌሰሮችና ምሁራን ቢሆኑም ባይሆኑም ቴክኒካሊ የሚሰጣቸውን ስራ እውቀት ላይ ተመስርተው ይሰራሉ የሚል እምነት አለኝ። ግን እነዚህ ምሁራን የህዝቡን ፖለቲካዊ ችግሮች ይመልሳሉ ወይ ነው ጥያቄው፡፡
ይህን ለመመለስ መንግስትን የሚመራው ድርጅት የሚከተለው ርዕዮተ አለምና ከዚያም በመነሳት የሚያወጣው ፖሊሲ የህዝብን ጥያቄዎች ምን ያህል ይመልሳል የሚለውም መታየት አለበት፡፡ ትልቁ መሰረታዊ ጉዳይ ያለው ፖሊሲው ላይ ነው፡፡
የፓርቲ አባል ያልሆኑ ሰዎችንም የመሾም ሁኔታ እያየሁ ነው፡፡ የአንድ ፓርቲ የበላይነትና ልማታዊ ዲሞክራሲ የሚባለው ርዕዮተ ዓለም፣ የሀገሪቱን ህዝቦች ጥያቄ እየመለሰ ነው ወይ የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ። ነባሮቹ እየለቀቁ አዳዲስ ሰዎች ማምጣቱ ጥሩ ነገር ነው፡፡ በአንድ በኩል ይህ ሲደረግ መንግስትና ፓርቲን የመለየት ነገር እየመጣ ነው ማለት ነው፡፡ ግን ሂደቱ በጣም አዝጋሚ ነው። መንግስትና ፓርቲ የተለያዩ መሆናቸውን የበለጠ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ማለት ካድሬ መሆን ብቻውን ለሚኒስትርነት እንደማያበቃ ማሳየት ማለት ነው፡፡ እኔ መልካም አካሄድ ነው ብዬ በበጎ አይን ነው የምመለከተው። በሌላ በኩል የብሄር ተዋፅኦን ከፍ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ይህ ለህዝቡ ጥያቄ ምን ያህል ምላሽ ሊሰጥ ይችላል የሚለውም በጥልቀት መታየትና መገምገም ይኖርበታል፡፡ Read more here
No comments:
Post a Comment