Tuesday, October 11, 2016

በተቃውሞ በቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል


“ለደህንነታችን ዋስትና የሚሰጠን አካል የለም” ባለሀብቶች
- “ቢሻን ጋሪ ሎጅ” ላይ በደረሰው ዘረፋና ቃጠሎ ፖሊስ ጥቃቱ እንዳይደርስ ከመከላከል ተቆጥቧል
- ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ፍርድ ቤቶች፣ ማዘጋጃ ቤቶችና የመንግስት ተቋማት ወድመዋል

በኢሬቻ በዓል አከባበር ወቅት የተከሰተውን የበርካቶች ህልፈተ ህይወት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ተቃውሞና አመፅ እያደረሰ ያለው የንብረት ውድመት ከመንግስት ጥበቃና ቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው፡፡ 
ባለፈው ሳምንት በክልሉ የተለያዩ ስፍራዎች በተቀሰቀሰው ተቃውሞና አመፅ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ንብረት ወድሟል ተብሏል፡፡ 
ሰሞኑን በቡራዩ፣ በሰበታ፣ በአዋሽ መልካሳ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በአለምገና እና ሌሎች የኦሮሚያ ክልሎች በተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ በሚሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ የተቋቋሙ ፋብሪካዎች፣ የህዝብና የጭነት ማመላለሻ መኪኖች፣ የመንግስት ተቋማት፣ ፖሊስ ጣቢያዎችና የአበባ እርሻዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ 
በላንጋኖ አካባቢ በ100ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በተገነባው ቢሻን ጋሪ ሎጅ ባለፈው እሮብ በደረሰበት ዘረፋና ቃጠሎ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋትም ሆነ ንብረቱን ከአደጋ ለመከላከል የተደረገ ሙከራ አለመኖሩ ተስፋ እንዳስቆረጣቸው የድርጅቱ ባለቤት አቶ ዑመር ባገርሽ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡ 
ሎጁ ላለፉት 17 ዓመታት የአካባቢ ጥበቃን ባማከለ መንገድ ለውጪ አገርና ለአገር ወስጥ ቱሪስቶች አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደነበር የገለፁት ባለሀብቱ፤ ‹‹ምንም በማናውቀውና ፈፅሞ ባልገመትነው ሁኔታ በሎጁ ላይ በተፈፀመው ዘረፋና የቃጠሎ አደጋ ከፍተኛ ሀዘን ተሰምቶናል ብለዋል፡፡ የድርጅቱ ኦፕሬሽን ክፍል ሃላፊ አቶ ዘለዓለም ቤኩማ በወቅቱ ስለተፈጠረው ሁኔታ ሲገልፁ፤ “ማንነታቸውን የማናውቃቸው በርከት ያሉ ወጣቶች እየጨፈሩ ወደ ግቢው ለመግባት ያደረጉትን ተደጋጋሚ ሙከራ በአካባቢው ሽማግሌዎች ልመናና ውትወታ ለመከላከል ሞክረናል፡፡ ሁኔታው እየተባባሰና የሰዎቹም ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ለአሩሲ ነጌሌ ፖሊስ ጣቢያ ደውለን፣ አሣወቅን” ያገኘነው ምላሽ ግን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ብለዋል፡፡ እኛ ወደ እናንተ መምጣት አንችልም፤ ጉዳዩን እዛው በሽምግልና ለመፍታት ሞክሩ ነው ያሉን ሲሉ ገልፀዋል - አቶ ዘልዓለም፡፡  “ሁኔታው ከአቅማችን በላይ ስለነበር፣ ዓይናችን እያየ ሎጁን እሳት ለኮሱበት፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሎጁ ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡ በሰው ህይወት ላይ ግን የደረሰ አደጋ የለም›› ብለዋል፡፡ በዚህ ዘረፋና ቃጠሎ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንደወደመባቸውም የሎጁ ባለቤት አቶ ዑመር ባገርሸ ተናግረዋል፡፡ 
‹‹ደህንነታችን ባልተረጋገጠበትና ፖሊስ ሊደርስልን በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ እንሆናለን ብለን ፈፅሞ አልጠረጠርንም፡፡ የደረሰብን ጉዳት እጅግ አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ ነው›› ብለዋል፡፡ 
ባለፈው ረቡዕ በኦሮሚያ ክልል አዋሽ መልካሳ በተቀሰቀሰ አመፅ በአካባቢው በሚገኘው ብስራት የጠጠር ማምረቻ ድርጅት ላይ የተከሰተው ቃጠሎም ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ አዳዲስ ማሽኖች ወድመዋል ተብሏል፡፡ 
ውድመቱ በደረሰባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው ባለሃብቶች፤ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሥጋት ላይ እንደሚገኙና በማንኛውም ጊዜና ሰዓት በንብረታቸውም ሆነ በህይወታቸው ላይ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ገልፀው፤ ለደህንነታችን ዋስትና የሚሰጠንና አደጋ ቢደርስብን ፈጥኖ የሚደርስልን አካል የለም ብለዋል፡፡ ሁኔታው ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ እየሆነ መምጣቱ ከፍተኛ ሥጋት አሳድሮብናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ 
በዝዋይ ከተማ ውስጥ በአበባ እርሻ ልማት ላይ የተሰማሩ አንድ ባለሃብት ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው በተቀሰቀሰው ተቃውሞና አመፅ ሳቢያ በንብረት ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት እጅግ እንዳሳሰባቸው ጠቁመው፤ ዋስትና በሌለበትና ምን እንደሚከሰት መገመት በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ መሆን እጅግ አስፈሪ ነው ብለዋል፡፡ 
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እየተባባሰ በሄደው ተቃውሞና አመፅ በርካታ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ፍርድ ቤቶች፣ ማዘጋጃ ቤቶች፣ የመንግስት ሴክተር መ/ቤቶች የመንግስትና የግለሰቦች ተሽከርካሪዎች በእሳት ወድመዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በሳምንቱ ውስጥ በርካታ የመንግስትና የግል ንብረቶች ወድመዋል፡፡ በሰበታ ከተማ ብቻ የኤሌክትሪክ ኬብል ማምረቻ፣ የጨርቃ ጨርቅና የፕላስቲክ ፋብሪካዎችን ጨምሮ 11 ልዩ ልዩ ፋብሪካዎች የተቃጠሉ ሲሆን ከ62 በላይ አውቶብሶችና ሌሎች ተሽከርካሪዎች በቃጠሎው ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡  

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time