Tuesday, October 11, 2016

‹‹የተሰበረ ፖለቲካ እንዴት ይጠገናል?››

አሁን የምንገኝበት ዘመን በየሐገሩ ልዩ ልዩ ቀውስ ተንሰራፍቶ የሚታይበት ዘመን ነው፡፡ አሁን የምነገኘው፤ በሶሻሊዝም ተስፋና በካፒታሊዝም ረድዔት መጽናናት ባልቻለች ዓለም ውስጥ ነው፡፡ አሁን እንደ ካርል ማርክስ፣ እንደ ሲግሞንድ ፍሮይድ ወይም እንደ አንስታይን ያሉ ‹‹ፀያህያነ ፍኖት›› በእጅጉ የሚያስፈልጉበት ዘመን ነው፡፡ አሁን ዓለም የምትታመስበት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ወዘተ ቀውስ፤ የዘመኑን እንቆቅልሽ በደንብ ተረድቶና አፍታቶ ምላሽ ማቅረብ የሚችል ፈላስፋን የሚጠይቅ ውስብስብ ችግር ነው፡፡ ነቢይ የሚያስፈልገው ዘመን ነው፡፡ ሆኖም፤ አንድ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ከችግር ለመውጣት በጣም ከባድ ቀውስ አስፈላጊ መሆኑን ሊያስረዳን እየሞከረ ነው፡፡  
ይህ ጋዜጠኛ ‹‹የፎሪን አፌርስ›› (Foreign Affairs) ማኔጅንግ ኤዲተር ዮናታን ቴፐርማን (Jonathan Tepperman) ነው፡፡ ቴፐርማን፤ በተለይ በበለጸጉት ሐገራት የሚታየው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ችግር፤ ዜጎች በመንግስታት ላይ ተስፋ የሚቆርጡበት ዘመን መቃረቡን የሚያመላክቱ መሆናቸውን ይናገራል፡፡ ከሣምንት በፊት ታትሞ በወጣ ‹‹የፎሪን አፌርስ›› መጽሔት እትም፤ ‹‹የተሰበረ ፖለቲካ እንዴት ይጠገናል?›› (How to Fix Broken Politics) በሚል ርዕስ የቀረበው ቃለ ምልልስ ይህን ችግር ይዘክራል፡፡ 
ይህ ቃለ ምልልስ፤ ሁለት የመጽሔቱ አዘጋጆች የሚነጋገሩበት ቃለ ምልልስ ነው፡፡ ማኔጅንግ ኤዲተሩ ዮናታን ቴፐርማን ተጠያቂ፤ ምክትል ማኔጂንግ ኤዲተሩ ጀስቲን ቮት (Justin Vogt) ጠያቂ የሆኑበት ቃለ ምልልስ ነው፡፡ ሰበቡ፤ ቴፐርማን፤ ‹‹The Fix: How Nations Survive and Thrive in a Decline›› በሚል ርዕስ አንድ መጽሐፍ ማሳተሙ ነው፡፡ መጽሐፉ አስር የዓለም ሐገራትን ባለታሪክ አድርጎ አቅርቧል፡፡ በመጽሐፉ የቀረቡት ሐገራት፤ መውጫ የሌለው ይመስል ከነበረ ችግር (ለምሣሌ፣ ሙስና - በሲንጋፖር፤ የከፋ ድህነት - በብራዚል፤ የስደተኞች ጉዳይ - በካናዳ) ውስጥ ተዘፍቀው፤ ከዚያ ከባድ ችግር መውጣት የቻሉ ሐገሮች ናቸው፡፡
ዮናታን ቴፐርማን፤ ባለጉዳዮቹን ሁሉ በያሉበት ሄዶ አነጋግሮ፤ ከእነርሱ ጋር ያደረጋቸውን ቃል ምልልሶችና ኤክስፐርት የሚሰጡትን ትንታኔ መሠረት አድርጎ ባዘጋጀው በዚህ መጽሐፍ፤ ውጤት ማምጣት የሞት ሽረት ጉዳይ ሆኖ የታያቸው መሪዎች፤ ፖለቲካዊ አደጋን ሊጋብዝ የሚችል ደፋር የተሐድሶ እርምጃ በመውሰድ ከችግራቸው እንዴት እንደወጡ የሚተርክበት መጽሐፍ ነው፡፡ 
እናም ይህን መጽሐፍ መነሻ በማድረግ የመጽሔቱ ምክትል ማኔጂንግ ኤዲተር ጀስቲን ቮት (Justin Vogt) ለባልደረባው በመጀመሪያ ያነሳላት ጥያቄ፤ 
‹‹ይህ መጽሐፍ በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከባድ ተግዳሮት ገጥሟቸው፤ በፖለቲካዊ ሂደት መፍትሔ ማግኘት የቻሉ መንግስታትን ታሪክ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ በአሁኑ ወቅት በመንግስትና በፖለቲካ ጉዳይ ትንታኔ የሚያቀርቡና አስተያየት የሚሰጡ በርካታ ወገኖች ከሚያቀርቡት እውነት ጋር የሚያጋጭ  ይዘት ያለው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በስፋት እየተነገረ የሚገኘው፤ ስለ መንግስት ተቋማት ውጤት አልባነት፣ ሙስና፣ ብቃት ማጣትና ውድቀት ነው፡፡ ሰው ሁሉ መንግስትና ፖለቲካ በተባሉ ጉዳዮች የተንገሸገሸ ይመስላል፡፡ አንተ ይህን መጽሐፍ በዚህ ጊዜ የጻፍከው መንግስትና ፖለቲካን ከጥቃት ለመጠበቅ ፈልገህ ነው እንዴ?››
ቴፐርማን እንዲህ ሲል መለሰ፤
‹‹በዚህ መጽሐፍ ማድረግ የፈለግሁት ሁለት ነገሮችን ማፍረስ ወይም መቃወም ነው፡፡ ወይም ለሁለት ነገሮች ምላሽ መስጠት ነው፡፡ በመጀመሪያ፤ አሁን የምንገኝበት ጊዜ ዓለም በመጥፎ የማሽቆልቆል ጉዞ ውስጥ የገባችበት ጊዜ ነው የሚል ሰፊ የጋራ መግባባት የተያዘበት አስተያየት አለ፡፡ ይህን ጉዳይ በሚዲያዎች እናየዋለን፡፡ ከምሁራንና ከፖለቲከኞች አንደበት ሲነገርም እንሰማዋለን። እርግጥ ነው፤ እንዲህ ያለ ድምዳሜ ለመያዝ የሚያበቁ በቂ ምክንያቶች አሉ፡፡ ነገር ግን እኔ ይህ አስተሳሰብ ትክክል ሆኖ ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ ነገሩን በልቤ ስገመግመው (on intuitive level) ይህን አስተያየት መቀበል ያስቸግረኛል፡፡ ስለዚህ፤ ይህ ብዙ ሰዎች የሚጋሩት ስሜት ወይም አስተያየት መስሎ የሚታየው ሐሳብ የተሳሳተ ነው ከሚል መነሻ መጽሐፉን መጻፍ ጀመርኩ፡፡ እናም ለልቤ ወይም ለስሜቴ እውነተኛ ምስክር የሚሆን ምክንያታዊ ሐሳብ ለመፈለግ ተነሳሁ፡፡ በፍለጋው ዕድለኛ ነበርኩ፡፡ የልቤን ሐሳብ የሚደግፉ ብዙ-ብዙ ማስረጃዎችን ማግኘት ችያለሁ፡፡ 
‹‹ለጥያቄህ የሰጠሁት የመጀመሪያው መልስ፤ ወደ ሁለተኛው ምላሼ የሚመራኝ ነው፡፡ እኔ ራሴን፤ ‹‹ነገሮች ሁሉ በፍጻሜው ጥሩ አቅጣጫ ይይዛሉ›› ብሎ የሚያስብ ተምኔተኛ ሰው አድርጌ አልቆጥረውም። ሆኖም፤ በእኛ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎች፣ መጥፎውን ነገር ብቻ የመመልከት ዝንባሌአቸው ሁሌም ያበሳጨኛል፡፡ በእርግጥ፤ ጋዜጠኞች ክፉ ነገር አነፍናፊ መሆናቸውን የሚያሳይና ‹‹If it bleeds it leads›› የሚል የጨረተ ብሂል አለ፡፡ ይህ ብሂል በዜና ዘገባ ዘርፍ ዘወትር እውነት ሆኖ የሚታይ ብሂል ነው፡፡ ሆኖም ይህ ነገር በዜና ዘገባ ብቻ ሳይሆን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በፖሊሲ ትንተና ሥራ በተሰማሩ ሰዎችም ዘንድ ይታያል፡፡  በሌላ አገላለጽ ከመፍትሔ ይልቅ በችግርና በትችት ላይ የማትኮር ሰፊ ዝንባሌ ይታያል ማለት እንችላለን፡፡ ሆኖም ይህ ዝንባሌ ለምን እንደሚፈጠር በትክክል አላውቅም›› የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ 
ጀስቲን ቮት ለሌላ ጥያቄ የተንደረደረው የጓደኛውን ሐሳብ የሚደግፍ ተጨማሪ አስተያየት በማቅረብ ነበር፡፡ ‹‹አዎ፤ ይህ ነገር በእኛ የሙያ መስክ በተሰማሩ ሰዎች ዘንድ የሚታይ ዝንባሌ ይመስለኛል” የሚለው ቮት፤ ጋዜጠኞች የዚህን ችግር ትክክለኛ ምንጭ በዝርዝር ልነግራችሁ ነው›› በሚል ዝንባሌ እንደሚሰሩ ጠቅሶ፤ ሆኖም ‹እውነተኛውን ምክንያት ስታውቁ የምትደርሱበት የመፍትሔ ሐሳብ ይህ ነው› የሚል ነገር ሲያስከትሉ የምንመለከተው በጣም አልፎ - አልፎ ነው›› ሲል የጓደኛውን ሐሳብ ያጠናክራል፡፡ 
ውይይቱ ይቀጥላል፡፡ 
ዮናታን ቴፐርማን መልስ መፈለግ ከባድ ነገር መሆኑንና የመልስ ፍለጋ ቀጣና በጣም አስቸጋሪ እንደሆነና መልስ ፍለጋ ለብዙ ጸሐፊዎች የማይመች ሥራ መሆኑን በማስታወስ፤ ለመልስና ለመፍትሔ ጥቆማ የሚሰንፍ የአሰራር ባህል እንደሚጠላ ይገልጻል፡፡ አክሎም፤ አንዳንዴ መልስ ለማቅረብ ሙከራ የሚደረግ ቢሆንም፤ ሙከራው ለተግባር የማይረዳ የማይጨበጥ አርቅቆት (very high level of abstraction) እንደሚሆን ያትታል፡፡ ‹‹ችግሮች ተጋፍጠው የሚገኙትን የዓለም መንግስታት እንቆቅልሽ የሚፈታ ምስጢር ከመጽሐፉ አይገኝም” የሚለው ቴፐርማን፤“እኔ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ብሆን ምን ላደርግ እችላለሁ?›› የሚል ጥያቄ በማንሳት፤ ራሱን ከግብዝነት ችግር ለመጠበቅና ለራሱ ታማኝ ለመሆን ጥረት እንደሚያደርግ ይናገራል፡፡ 
ልዩ ባህርያት ወይም የብቻ መልክ የሚይዙ ልዩ ልዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመጽሐፉ እንደሚያነሳ የሚገልጸው ቴፐርማን፤ ‹‹በውጤታማነት የላቀ የመንግስት አስተዳደር ለመፍጠር የሚያስችሉ ሰባቱ ባህርያት›› (The Seven Habits of Highly Effective Governments) በሚል የሚያቀርበው ሐሳብ አይኑረው እንጂ፤ በመጽሐፉ ከተነሱ ታሪኮች ውስጥ ሁሉን ገዢ የሆኑ አጠቃላይ ህጎችን ማውጣት እንደሚቻል ግን ያምናል፡፡ 
ከቀረቡት የተለያዩ የመንግስታት ወይም መሪዎች ታሪክ ውስጥ ከታዩ የጋራ ባህርያት መካከል፤ የመሪዎች ወይም የባለስልጣናት ለሁኔታዎች ተገዢ የሆነ (pragmatic) ውሳኔ የማድረግ ጠንካራ ዝንባሌ አንዱ መሆኑን ቴፐርማን ገልጾ፤ መንግስታት መፍትሔ አድርገው የሚወስዱት ሐሳብ ወይም አሰራር ምንጩ የት መሆኑ ሳያስጨንቃቸው፤ ሐሳብ ወይም አሰራሩ ከሚከተሉት ርዕዮተ ዓለምና ከፓርቲያቸው አቋም መስማማት - አለመስማማቱ ግድ ሳይሰጣቸው፤የተገኘውን መፍትሔ የተባለ ነገር አንጠልጠሎ የመሮጥ ፍላጎት እንደሚታይባቸው አስረድቷል፡፡ 
በቴፐርማን መጽሐፍ ታሪካቸው ከተጠቀሰላቸው ባለስልጣናት መካከል፤ የቀድሞው የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ማይክል ብሉምበርግ አንዱ ናቸው። ማይክል ብሉምበርግ፤ ከ9/11 የአሜሪካ የሽብር ጥቃት በኋላ የፌደራሉ መንግስት የከተማዋን ደህንነት በማስከበር ረገድ ድክመት በማሳየቱ ከንቲባው የራሳቸውን እርምጃ መውሰዳቸውንና ‹‹እናንተ ትክክል የሆነውን ነገር አድርጉ፡፡ ከዚያ በኋላ በሚሆነው ነገርም ምንም አትጨነቁ›› ሲሉ መናገራቸውን ቴፐርማን ጠቅሷል። አክሎም፤ ‹‹በመጽሐፉ ታሪካቸው የተወሳው የሐገር መሪዎች በሙሉ የሚያደርጉትም ይህንኑ ነው›› የሚለው ቴፐርማን፤ የሐገር መሪነት የፈላስፋ ንጉስ (a philosopher king) ባህርይን የሚጠይቅ ሥራ መሆኑን አመልክቷል፡፡
መሪው በአንድ በኩል የቴክኖክራት ባህርይ፤ በሌላ በኩል ፖለቲካዊ ሂደቱን ይዞት ለተነሳው ዓላማ ተፈጻሚነት የመጠቀም ጥበብ ሊኖረው ይገባል። ሆኖም አንድ መሪ የፖለቲካ ሂደቱን ለዓላማው ተፈጻሚነት ምቹ እንዲሆን የማድረግ ብቃት ሳይኖረው፤ ቴክኖክራት የመሆን ብቃት ሊኖረው እንደማይችል የሚያወሳው ቴፐርማን፤ ‹‹ይህን ለማድረግ የሚችለው የፈላስፋን ብቃት የታደለ የፖለቲካ ሰው ብቻ ነው›› ይላል፡፡ እናም ቴፐርማን በመጽሐፉ ለማስተላለፍ የሞከረው መልዕክት፤ አንድ መሪ ርዕዮተ ዓለማዊ ንጽህናውን ለመጠበቅ ከሚጣጣር ይልቅ፤ ጊዜው ምን እንደሚጠይቅ አውቆና ተረድቶ፤ ከእውነታው ጋር የተጣጣመ የአፈጻጸም ብቃት መያዝ፣እንዲሁም ለማመቻመች (compromise) ዝግጁ መሆንና ቴክኖክራቲክ ጥበብ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ 
ከደራሲው ጋር ቃለ ምልልስ የሚያደርገው የመጽሔቱ ምክትል ማኔጅግ ኤዲተር ጀስቲን ቮት፤ ‹‹አሁን የምንገኝበት ጊዜ ህዝበኝነት (Populist - የህዝብን ድጋፍ ለማግኘት ሲባል የሙያ ብቃትን የሚጠይቁ ጉዳዮችን ጭምር በህዝብ ፈቃድና ውሳኔ ለማስፈጸም የመሻት መጥፎ ዝንባሌ) የነገሰበት ጊዜ ነው፡፡ የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል ያላቸው ሐገሮች ዜጎች፣ ነባር የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ተቋማት ሲያብጠለጥሉ ይታያሉ፡፡ ይህም በሆነ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ለመድረስ የሚያበቃ የዜጎች ድጋፍ ማግኘትን አስቸጋሪ እያደረገው ነው ለማለት ነው የፈለግኸው?›› ሲል ጠይቆት ነበር፡፡     
ቴፐርማን ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ፤ ‹‹እንዲህ ያለ አስተያየት በመስጠት እኔ የመጀመሪያ ሰው አይደለሁም›› ሲል ይጀምራል፡፡ በማያያዝም ‹‹ዜጎች የህዝበኝነት ዝንባሌ መያዝ የጀመሩት፤ መንግስታት ተራ ዜጎች የሚገጥማቸውን ችግር መፍታት ባለመቻላቸውና በምርጫ ዘመቻ ወቅት የገቡትን ቃል መፈጸም ባለመቻላቸው የተነሳ ነው፡፡ ስለዚህ፤  በሁኔታዎች ላይ በተመሰረተ ውሳኔ ችግር የመፍታት አካሄድ (lack of pragmatic problem solving) አለመኖሩ፤ ሰዎች በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል ማለት ይቻላል›› ብሏል፡፡ 
ለሁለተኛ ጊዜ የመመረጥ ዕድል ለማግኘት የሚሹ፤ ምቾት ወይም ሥልጣን የሚያስገኘውን ጥቅም ማጣት የማይሹ የመንግስት ባለስልጣናት፤ መራጩን ህዝብ ላለማስቀየም ሲሉ፤ ትክክለኛውን ነገር ሳይሆን ህዝብ የሚወድላቸውን ውሳኔ ለመወሰን ጥረት እንደሚያደርጉና ይህም ህዝበኛ እንደሚያደርጋቸው ዮናታን ቴፐርማን ያስረዳል፡፡ የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ማይክል ብሉምበርግ፤ ‹‹ትክክለኛውን ነገር አድርጉ፤ ከዚያ በኋላ አዳሜ ያሻውን ይበል›› የማለት ድፍረት ያገኙትም፤ የኑሮ ጣጣ የማያስጨንቃቸው ከበርቴ መሆናቸው የኢኮኖሚ ነጻነት ስለሰጣቸው ነው የሚለውን የባልደረባውን አስተያየት ይጋራል፡፡ እንዲህ ያሉ ድክመቶችም ነገሮች ከመሻሻል ይልቅ የሚባባሱበትን ሁኔታ እንደሚፈጥሩ አመልክቷል፡፡ 
ደራሲው እንደሚለው መንግስታት ችግር ፈቺ ውሳኔዎችን የሚያሳልፉት ህልውናቸውን የሚፈታተን አደገኛ ችግር ውስጥ ሲገቡ ነው። መንግስታት ድርስ ከሆነ አደጋ ጋር ሲጋፈጡ፤ በአዘቦቱ ይደረጋሉ ተብለው የማይታሰቡ የለውጥ እርምጃዎችን ይወስዳሉ፡፡ በአንድ በኩል፤ እነዚህ ህልውናን የሚፈታተኑ አደጋዎች፤ ችግሮችን በከፍተኛ የትኩረት ኃይል ለማሰብ፣ ዳተኝነትን ለማስወገድና በእውነተኛ ስሜት መፍትሔ ለመፈለግ የሚያነሳሱን ይሆናሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የችግሩ አደገኛነት የተሐድሶ ጥረት እንዳናደርግ መሰናክል የሚሆኑ ችግሮችን ሁሉ ጠራርጎ በመጣል፤ ለእውነተኛ ተሐድሶ መንገድ ያመቻቻል፡፡ በመሆኑም፤ በደህናው ጊዜ ወይም በአገር አማን ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣትና የርዕዮተ ዓለም አጥርን  ጥሶ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛነት የሚጎድላቸው ፖለቲከኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ሌላው ቀርቶ ህዝብ ራሱ)፤ በተስፋ መቁረጥ ጫና የሚፈጠረውን ዳተኝነት በማስወገድ፣ትክክለኛ ሆኖ የተገኘን ማናቸውንም ውሳኔ ለመወሰን ያደፋፍራሉ፡፡ ስለዚህ በቴፐርማን አስተያየት፤ የእውነተኛ መፍትሔዎች ምንጭ ቀውስ (crisis ) ነው፡፡ 
በመጨረሻም፤ የጻፍከውን መጽሐፍ ሊያነብ ይገባል የምትለው ርዕሰ ብሔር ማነው? የሚል ጥያቄ አቅርቦለት ነበር፡፡ ከዚያም ጥያቄውን በማሻሻል፤ ‹‹ቀደም ሲል የተነሳው ጥያቄ በሌላ መንገድ ይቅረብ ቢባል፤ ‹በአሁኑ ወቅት ከባድ ፈተናን የተጋፈጠ ሆኖ ሳለ፤ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የተጣመመ (pragmatic )፣ ፈጠራ የታከለበት (creative) እና ተጣጣፊ (flexible) የችግር አፈታት ስልትን በመከተል ከችግሩ የመውጣት ሰፊ ዕድል ያለው አንድ ሐገር ጥቀስ ብትባል የትኛውን ሐገር ትጠቅሳለህ?› ተብሎ ሊቀርብ ይችላል›› ሲል ጠየቀ፡፡ 
ቴፐርማን ሲመልስ፤ ‹‹የፎሪን አፌርስ መጽሔት አዘጋጅ ሆኜ ለዚህ ጥያቄ በአደባባይ ምላሽ መስጠት ተገቢ ባይሆንም፤ ከባድ ፈተና የተጋረጠባት ሆና ሳለ፤ መፍትሔ ሊገኝለት የሚችል ችግር ይዛ የምትሰቃይ ሐገር አሜሪካ ናት›› በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ፀሐፊው፤ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በመጽሐፉ የተገለጹ በርካታ ችግሮችን የተሸከመች ሐገር መሆኗን አመልክቶ፤ የአሜሪካ ችግር በገዛ እጅ የተጎተተ ችግር መሆኑን ጠቅሷል፡፡ አሜሪካ በመጥፎ ሁኔታ ላይ የምትገኝ ሐገር ብትሆንም፤ ሌሎች ሐገራት ተስለው የማያገኙት በርካታ አጓጊ እሴቶች ያላት ሐገር ነች የሚለው ቴፐርማን፤ አሜሪካ በጣም የተማረ ህዝብ፤ በዓለም ምርጥ የሚባሉ ዩኒቨርሲቲዎች፤ እንዲሁም ከማንኛውም የዓለም ሐገር የላቀ በፈጠራ የተደራጀ (innovative ) ኢኮኖሚ ያላት፤ የኃያል ወታደራዊ ኃይል ባለቤት፣ በግራ በቀኝ በውቂያኖስ የተከበበችና የሰላም ጠንቅ የማይሆኑ ጥሩ ጎረቤቶች ያላት ሐገር ናት - በሰሜን ካናዳ፣ በደቡብ ሜክሲኮ - ይላል፡፡ የጀርመኑ ቢስ ማርክ ‹‹እግዚአብሔር ለሰካራሞችና ለአሜሪካኖች ይስቅላቸዋል›› (God smiles on drunkards and Americans) የሚል ዝነኛ ብሂል እንዳለው ያስታወሰው ደራሲው፤ ሆኖም በአሁኑ ሰዓት መንግስታችን ዓለምን የሚያስቀኑ ድንቅ እሴቶቻችንን ሁሉ ለማውደም የሚችለውን እያደረገ ይገኛል ሲል ይከሳል፡፡ እናም ይህን መጽሐፍ በግድ የማስነበብ መብት ቢሰጠኝ፤ በአሜሪካ የሚገኙትን የፖለቲካ መደብ አባላት በሙሉ (ቢያንስ ቢያንስ) የአንዳንድ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በግድ እንዲያነቡት አደርግ ነበር›› የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ 
‹‹ሆኖም አሁን እኔን በጣም እያስጨነቀኝ ያለው ነገር›› ይላል ፀሐፊው፤ ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ የፖለቲካ አመራሩ ሐገሪቱ ወደ ትክክለኛው ጎዳና የመመለስ ዕድሏ ይበልጥ እንዲጠብብ የሚያደርጉ ተከታታይ ውሳኔዎችን የሚወስን መሆኑ ነው፡፡ …..…ስንቱን ሐገር ትቼ አሜሪካ ላይ ማትኮር የፈልግሁት፤አሜሪካ የመፍትሔ እርምጃዎች በትክክል ተፈጻሚ ሊሆኑ የሚችሉባት ሐገር ስለሆነች ነው፡፡ ይህች ሐገር እስከ ዛሬ ድረስ በስኬት ጎዳና ስትጓዝ የነበረችና አሁንም ተመልሳ በስኬት ጎዳና ለመራመድ የምትችል ሐገር ስለሆነች፤ በገዛ እጃችን ራሳችንን የማቁሰሉ ተግባር መቆም ይኖርበታል›› ሲል ያጠቃልላል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ትንታኔ የምትማረው ቁምነገር ይኖር ይሆን?  Read more here

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time