Tuesday, October 11, 2016

“አገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት”


* የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሟል፤አዲስ ሃኪምና መድሃኒት ይፈልጋል
* ኢህአዴግ ውስጥ ካለው ምሁር በተቃዋሚው ጎራ ያለው በእጅጉ ይልቃል
* ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ውለታ እንዲውል እጠይቀዋለሁ

    ለ3 ወራት ገደማ አሜሪካ ቆይተው የተመለሱት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ በወቅታዊ አገራዊ ችግሮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ
ጋር ቃለምልልስ አድርገዋል፡; በተጨማሪ በአሜሪካ በነበራቸው ቆይታ ምን እንዳከናወኑ፣ የዳያስፖራው ፖለቲካ ምን እንደሚመስልና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል - ዶ/ር መረራ ጉዲና፡፡

እስቲ የአሜሪካ ጉብኝትዎ አላማ ምን እንደነበር በዝርዝር ይንገሩኝ?
በሶስት ምክንያቶች ነበር ወደ አሜሪካ የተጓዝኩት። አንደኛው የዲፕሎማቲክ ስራ ነው። ይሄን ሃገር እንግዲህ ቅኝ እየገዙ ነው የሚባሉት አሜሪካኖች ናቸው፡፡ በማይሆን ግንኙነት እንዳይጎዱን፤ በኢትዮጵያ ላይ ያለውን ፖሊሲ እንዲመረምሩ፤ ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል እንዲያግዙ…ወዘተ መጠየቅ አንዱ አላማ ነበር፡፡ በሁለተኛነት፣በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኦሮሞ ማህበረሰብ ጋር ለመወያየት ነው፡፡ በሶስተኝነት፣ ለድርጅታችን ድጋፍ ለማሰባሰብ ነው። 
ከአሜሪካ ባለስልጣናትም ጋር ተገናኝተዋል፡፡  ውይይታችሁ በምን ላይ ያተኮረ ነበር?
የሃገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት የሴኔት አባላት፣ በተለይ የህግ ጉዳዮችን ከሚያዘጋጁት ጋር ተነጋግሬያለሁ፡፡ ከ‹‹ሠማያዊ›› ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ይልቃል ጌትነት ጋር ‹‹አትላንቲክ ካውንስል›› ከሚባል የአሜሪካ የሃሣብ አመንጭዎች ቡድን ጋር ተወያይተናል፡፡ እዚያ ውስጥ ከነበሩትና አስቀድሞ ከማውቃቸው መካከል፣ በ1983 ለንደን ላይ ኢህአዴግ ሃገር እንዲረከብ፣ ምርቃት የሰጠው፣ ሄርማን ኮኽ የሚባለው ሰው ነበር፡፡ የቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺል የሚባለውም ነበር፡፡ እንዲሁም ከሌሎች የአሜሪካ ባለ ራዕዮችና ሃሳብ አመንጪዎች ጋር 2 ሰዓት የፈጀ ውይይት አድርገናል፡፡ በአብዛኛውም አሁን በሃገሪቱ ባሉ የህዝብ ተቃውሞዎች ላይ አተኩረን ነው የተወያየነው፡፡
በሃገሪቱ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ምን አስተያየት አላቸው? የተሟላ መረጃስ ያገኛሉ?
እነሱ ሁሉንም ያወቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታና የሚደረገውን ነገር በተመለከተ በቂ መረጃ አላቸው፡፡ የራሳቸው መንግስት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲም ችግር እንዳለው ያውቃሉ፡፡  በተደጋጋሚ፣‹‹ተቃዋሚው አንድ ሆኖ አልወጣም፤ አንድ ላይ ሆናችሁ ለማየት እንፈልጋለን›› የሚል ሀሳብ ነበር የሚሰነዝሩት፡፡ 
ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ያደረጋችሁት ውይይትስ----ምን ይመስላል?
ስለ ዳያስፖራው ፖለቲካ፣በመፅሐፌ ላይ ገልጬዋለሁ፡፡ ዳያስፖራው እንደ ማናችንም በሃገር ጉዳይ የሚጨነቅ ነው፡፡ ክፍፍሉ እዚህም እንዳለው፣ እዚያም ይንፀባረቃል፡፡ ምናልባት እዚህ ካለው ጎልቶ ይታይ ይሆናል፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የማክረር ዝንባሌ ይታያል፡፡ ጎንደር ላይ በተደረገው ሰልፍ፣ህዝቡ የኦሮሞን ህዝብ ደግፎ እንደሚቆም ከገለጸ በኋላ፣ በዳያስፖራው ዘንድ ቀድሞ የነበረውን አመለካከት የቀየረው ይመስላል፡፡ በአገር ውስጥ የተፈጠረው አንድነት፣ የዳያስፖራውን ክፍፍል ማስቀረት ብቻ ሳይሆን አዲስ አይነት ግንኙነት እንዲጀመርም አድርጓል፡፡ አንድ ላይ ሠላማዊ ሠልፍ የመውጣት፤ በጋራ የመሠብሠብ ነገር መፈጠሩን ለማየት ችያለሁ፡፡ አሁን በዳያስፖራው የእርስ በእርስ ግንኙነት ላይ ለውጥ አለ ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡  
በሃገር ውስጥ ያለው ተቃውሞና ግጭት የተለያየ መልክና ቅርፅ እየያዘ ወደ አንድ አመት ገደማ ሊያስቆጥር ነው፡፡ ተቃውሞው ከቀጠለ ሁኔታዎች ወዴት የሚያመራ ይመስልዎታል?
እኔ ደጋግሜ እንደምለው፣ ሃገሪቱ አሁን መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት፡፡ የኢህአዴግ መሪዎች ልቦና ገዝተው፣ ሃገሪቷንና ህዝቦቿን ወደተሻለ የጋራ የፖለቲካ ስርአት… ማለትም መነጋገርና መደራደር ወደሚቻልበት መስመር ካልገቡ፣ ቻይኖች፤ ‹‹ቀውስ የተሻለ ሁኔታን ይዞ ይመጣል›› እንደሚሉት፣ያ እድል ሊመጣ ይችላል፡፡ ወደ እርስ በእርስ ግጭት ሊያመራ የሚችልበት ዕድልም አለ፡፡  
መንግስት ችግሮች ለመፍታት ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡ ከዚህ በተረፈ የሚፈጠሩ ሁከቶች ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ጠቁሞ፣በሃይል እርምጃ ህግና ስርዓት አስከብራለሁ ብሏል፡፡ ከእነዚህ የመፍትሄ መንገዶች ምን ውጤት ይጠብቃሉ?
ተሃድሶና የሃይል እርምጃ ከዚህ በፊትም ውጤት እንዳላመጡ ታይቷል፡፡ እኛ ከዚህ ቀደም መሬት ዘረፋን በሚመለከት፣በተለይ ማስተር ፕላን ብለው ባወጡት ጉዳይ ላይ መንግስትን ለመምከር ሞክረን ነበር፤አልሠሙንም፡፡ እንደፈራነውም ችግር ተፈጠረ፡፡ ከዚያ በኋላም በየደረጃው እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱ፤ መንግስት ያልተመጣጠነ ሃይል መጠቀሙ መፍትሄ እንደማይሆን ተናግረናል። ህዝብ ለውጥ እየፈለገ ነው፤መሠረታዊ ለውጥ ነው የሚያስፈልገው፤ እርምጃዎች ውሰዱ ብለን በተደጋጋሚ ወትውተናል፡፡ ነገር ግን ሃሳባችን ቸል በመባሉ የበለጠ ቀውስና ደም መፋሰስ ተከስቷል። አሁንም ቢሆን በፖሊሲዎቻቸው ላይ ደጋግመው ካላሰቡና ወሳኝ እርምጃዎችን ካልወሰዱ አሳሳቢ ነው፡፡ ተሃድሶ የሚባለው ጨዋታ ነው፡፡ ኢህአዴግ ችግር በገጠመው ቁጥር  ተሃድሶ ይላል፡፡ ውጤቱ ግን ጉልቻ መቀያየር ነው የሚሆነው፡፡ ፊት ያለውን ባለስልጣን ወደ ኋላ ወስደው፣ ኋላ የነበረውን ወደፊት ያመጣሉ፤በቃ የእነሡ ተሃድሶ ይሄው ነው። አዲስ ፖሊሲ፣ አዲስ አስተሳሰብ የላቸውም። በተለይ ዲሞክራሲያዊ አሰራር አልታየም፡፡ በኔ እምነት፣ ከዚህ በኋላ ምንም የቀራቸው የሚታደስ ነገር የለም፡፡ ህዝብም ተሃድሶ አይደለም እየጠየቀ ያለው፤ መሠረታዊ ለውጥን ነው፡፡ 
በብዙዎች ዘንድ ኢህአዴግ ስልጣን ቢለቅ፣ሃገርን ተረክቦ ማስተዳደር የሚችል ሃይል የለም የሚል ስጋት አለ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው? ስጋቱስ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
በዋናነት መሰረታዊ ችግሩን የሚፈጥረው ኢህአዴግ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ተቃዋሚዎች እንዳይፈጠሩ ትንሽ ብቅ የሚሉትን እጅና እግራቸውን አስሮ፤ ቢሮ እንዳይከፍቱ እየከለከለና እንዳይንቀሳቀሱ እያደረገ ያለው ኢህአዴግ ነው፡፡ ለዚህ ተጠያቂ መሆን ያለበትም ተቃዋሚው ሳይሆን ኢህአዴግ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን በተግባር ላይ አላዋለም፡፡ ህገ መንግስቱ፣ነፃ ሚዲያ ይላል፤ ይሄ በተግባር የለም፡፡ ነፃ የዲሞክራሲ ተቋማትን ህገመንግስቱ ይፈቅዳል፤ በተግባር ግን የሉም፡፡ ተቃዋሚም በሚፈለገው ደረጃ እንዳይወጣ አድርጎ የፖለቲካ ምህዳሩን ያበላሸው ኢህአዴግ ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ሽብርተኛ ተብለው ይታሠራሉ፡፡ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ተቃዋሚ ጠንክሮ እንዳይወጣ ሆኗል። ከ97 በኋላ በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዴት እንደተፈለጡና እንደተቆረጡ ከማንም የተሠወረ አይደለም፡፡ በአንድ በኩል ይሄን እያደረገ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹እኔ ከሌለው ሃገሪቱ አትኖርም›› እያለ ፕሮፓጋንዳ ያሠራጫል፡፡ አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ ካለው ምሁር በተቃዋሚው ጎራ ያለው በእጅጉ ይልቃል፡፡ ይሄ በገሃድ የሚታይ ሃቅ ነው፡፡
በልምድም በእውቀትም ኢህአዴግ ውስጥ ካሉት ሰዎች በተቃዋሚ ደጋፊነት ያሉት ይልቃሉ። ስለዚህ አንዳንዶች እንደሚሉት፤እኔ በዚህ በኩል ስጋት የለኝም፤ በርካታ ይህቺን ሀገር ለማስተዳደር የሚመጥኑ ሰዎች አሉ፡፡ ተቃዋሚው ምሁራንን አስተባብሮ ለመምራት ሰፊ አቅምና ተቀባይነት አለው፡፡ ስለዚህ ጭንቀቱ በዋናነት የኢህአዴግ ነው፡፡ “እኔ ከሌለው ሀገር ይፈርሳል፣ መአት ይወርዳል›› እያለ የሚያስወራው ኢህአዴግ ነው፤ ስጋቱም የኢህአዴግ ነው፡፡ በእውቀትም በልምድም ብዙ ምሁራን የመስራት እድል አላገኙም፡፡ ስንት ኢኮኖሚስቶች ናቸው ያሉት? ተቃዋሚው ጋ ስንመጣ፣ በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር የሚያስተምሩ፣ አለም ያከበራቸውና እውቅና የሰጣቸው ሰዎች አሉ፡፡ ስንት ፖለቲካል ሳይንቲስቶች ናቸው ከኢህአዴግ ጋር የሚሰሩት? በአጠቃላይ ሀገሪቷን መምራት የሚችል በእውቀትና በልምድ የዳበረ የሰው ኃይል ያለው በተቃዋሚው ወገን ነው፡፡ ተቃዋሚው እድሉን ቢያገኝ፣እነዚህን የእውቀት ሀብቶች በአግባቡ ተጠቅሞ ሀገሪቱን ይታደጋት ነበር፡፡ 
አሁን በአገሪቱ ለተከሰቱት ቀውሶች መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
እኔ ኢህአዴግ አንድ ውለታ እንዲውል የምጠይቀው፣ ብሄራዊ የአንድነት መንግስት እንዲቋቋም እድል እንዲፈጥር ነው፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ከፍቶ፣ ጉዳዩ ያገባናል ከሚሉ እውነተኛ የህዝብ ተወካዮች ጋር ውይይት መጀመር አለበት። ‹‹ታድሻለሁ›› ብሎ ተቀባብቶ መቅረብ የትም አያደርስም፡፡ መሰረታዊ የሆነ የፖሊሲ፣ የአሰራርና የአመራር ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ አንድ መድኀኒት አልሰራም ካለ፣ ሀኪም ያንኑ መድኃኒት መልሶ አያዝም፤ መድኃኒቱን ይቀይራል፡፡ የኢህአዴግም ተሃድሶ ተደጋግሞ ታይቶ፣ ተፈትኗል፤ የመጣ ለውጥ የለም፡፡ ተፈትኖ የወደቀ መድኃኒትን በህዝብ ላይ ደጋግሞ መሞከር ለውጥ አያመጣም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሟል፡፡ ለህመሙ አዲስ ሃኪምና መድኃኒት ያስፈልገዋል፡፡ የሚለዋወጡት ሹመኞች እኮ ከካድሬ ትምህርት ያለፈ እውቀት የሌላቸው፣ ተቀባብተው የሚቀርቡ ሰዎች ናቸው፡፡ 
‹‹የብሄራዊ አንድነት መንግስት›› ይቋቋም ሲሉ፣ ይሄን ማን ነው ኃላፊነት ወስዶ ማስተባበር የሚችለው?
ሁሉም አካል አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይችላል። ነገር ግን ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ፣ ከስልጣን እስካልወረደና የደህንነትና ሌሎች ኃይሎችን እስከተቆጣጠረ ድረስ ለዚህ ሃሳብ መንገድ መክፈት ያለበት እሱ ነው፡፡  ይሄ ካልሆነ አስቸጋሪ ነው። ለዚህ ነው ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ መልኩ ውለታ ይዋል ያልኩት፡፡ አፈና ከሌለ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ሰዎች ወደፊት ለመውጣትና የሂደቱ አካል ለመሆን አይቸገሩም፡፡  
በኦሮሞ የኢሬቻ በአል ላይ በደረሰው አስከፊ እልቂት፣ መንግስትና ተቃዋሚዎች በመንስኤውና  በሞቱ ሰዎች ቁጥር ዙሪያ እየተወዛገቡ ነው፡፡ ህዝቡ ሃቁን እንዲያውቅ ምን መደረግ አለበት?
ይሄ ግልፅ ነው፡፡ ገለልተኛ አካል ጉዳዩን መመርመር አለበት፡፡ የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን ያሉበት አካል፣ጉዳዩን እንዲያጣራ እንፈልጋለን፡፡ የሟቾችን ቁጥር መደበቅ ምንም የፖለቲካ ትርፍ አያመጣም፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በተሰበሰበበት አስለቃሽ ጭስ ከተለቀቀና ሰዎቹ ታፍነው ጉዳት እንዲደርስ ከተደረገ በኋላ፣ ‹‹የለም እኔ ጥይት አልተኮስኩም›› ማለት አያዋጣም፡፡ ወጣቶቹ በወቅቱ ከተቃውሞ ጩኸት በላይ ያደረጉት ነገር የለም፡፡ በጥፊ እንኳ የተመታ የመንግስት ባለስልጣን የለም፡፡ ገና ለገና የሆነ ነገር ይፈጠራል በሚል ነው እርምጃው የተወሰደው፡፡ ለመቃወም ፈቃድ አያስፈልገውም። ሰዎች ለምን ተቃወሙ አይባልም፡፡ እስከ 3፡30 ሁሉም ነገር በሰላም ይከናወን ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ከመንግስት ጋር የተለየ ግንኙነት አላቸው ተብለው የሚታሰቡ የቀድሞ አባ ገዳን አምጥተው ንግግር እንዲያደርግ ማድረጋቸው አግባብ አልነበረም፡፡ ሌላው ህዝብ መተላለፊያ እንደሌለው እየታወቀ፣ ከባድ ድምፅ የሚያወጣ ጭስ መተኮስ ምን ማለት ነው? ባለስልጣን ባልተነካበት፣ የመንግስትና የህዝብ ንብረት ባልወደመበት… ለምን ጭስም ሆነ የፕላስቲክ ጥይት ይተኮሳል? ይሄ አሳዛኝ ነው፡፡ 
መንግስት በደረሰው አደጋ ማዘኑን ገልፆ፤የ3 ቀን ብሄራዊ የሃዘን ቀን አውጇል …. 
እኔ ይሄን እንደ ፌዝ ነው የቆጠርኩት፡፡ ከዚያ በኋላም ሰላማዊ ሰልፈኞች ተገድለዋል፡፡ ሰሞኑን በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ፍጥጫዎች ነበሩ። ከልብ ቢታዘን ኖሮ፣ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቆ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ አይደገምም፤የፀጥታ ኃይሉ የወሰደው እርምጃ ትክክል አይደለም›› ተብሎ ይነገራል። ከዚያ ይልቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ለፀጥታ ኃይሉ ምስጋና ነው ያቀረቡት፡፡ ሃዘኔታው ከልብ መሆኑ የሚያጠራጥረው እዚያ ላይ ነው፡፡  Read more here

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time