Monday, August 6, 2018

አብዲ ሞሃመድ ኡመር ከስልጣናቸው ተነሱ


የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዝድንት የነበሩት አብዲ ሞሃመድ ኡመር ከስልጣናቸው መነሳታቸውን የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊው ኢድሪስ ኢስማኤል ለቢቢሲ ሶማልኛ አረጋግጠዋል።
ከኢድሪስ ኢስማኤል መረዳት እንደተቻለው፤ አብዲ ሞሃመድ ኡመር ከክልሉ ፕሬዝደንትነታቸው ይነሱ እንጂ የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሪ ሆነው ይቆያሉ ብለዋል።
ኢድሪስ ኢስማኤል ጨምረው እንደተናገሩት አህመድ አብዲ ሞሃመድ የቀድሞውን ፕሬዝደንት በመተካት ተሹመዋል።
አዲሱ የክልሉ ፕሬዝደንት አህመድ አብዲ ሞሃመድ የሶማሌ ክልል ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ በሞሆን አገልግለዋል።
ከቅዳሜ አንስቶ በጂግጂጋ እና በክልሉ ሌሎች ከተሞች የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ የሃገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ወደ ክልሉ ገብቶ ሰላም እንዲያስከብር መታዘዙ ከሰዓታት በፊት ይፋ ተደርጎ ነበር።
በስፋት ''አብዲ ኢሌ'' በመባል የሚታወቁ አብዲ ሞሃመድ ኡምር ሰልጣን በፍቃደቸው ወይም ተገደው ስለመልቀቃቸው የታወቀ ነገር የለም።
ባለፉት ቀናት በክልሉ በተከሰተው ሁከት የሰው ህይወት ጠፍቷል እንዲሁም ንብረት መውደሙ ተነግሯል።

BBC

Sunday, August 5, 2018

ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው በእውቀትና በትእግስት መስራት ያስፈልጋል- አቶ ለማ መገርሳ

ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው በእውቀትና በትእግስት መስራት ያስፈልጋል- አቶ ለማ መገርሳ

አሁን የተገኘው ድል በበርካታ ዜጎች ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘ በመሆኑ በዚሁ ለማስቀጠል በእውቀትና በትዕግስት መስራት እንደሚያስፈልግ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ገልጸዋል፡፡
አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ /ኦኤምኤን/ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱን ለማስመረቅ በተዘጋጀው ስነ ስርዓት ላይ እንደተናገሩት ከአሁን በኋላ የወጣቱ ዋንኛ ዓላማም ለልማትና ለብልጽግና መስራት መሆን አለበት፡፡
ጃዋር መሃመድን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ዜጎት ለህዝቡ ነጻነትና መብት ሲሉ በስደት ከሚኖሩበት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ከክልሉ ጋር ለመስራት በመወሰናቸው ምስጋና እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
የህዝቡ ትግል ፍሬያማ እንዲሆን ጃዋር መሃመድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ ግለሰቦች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ በመሆኑ ልናመሰግነው ይገባል ነው ያሉት፡፡
ኦኤምኤን ትልቅ ስራ ሲያከናውን እንደነበር እና የኦሮሚያ ህዝብ ያገኘውን የተስፋ ብርሃን ይበልጥ እንዲፈካ ለማድረግ ከሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ጋር እንደሚሰራ ተስፋ አለኝ ብለዋል አቶ ለማ መገርሳ፡፡
እንደ አቶ ለማ መገርሳ ገለጻ ከአሁን በኋላ በፖለቲካ ምክንያት ህዝቡ መጋጨት እና መበጣበጥ የለበትም፤ ይህ ደግሞ እንዳይሆን የፖለቲካ አመራሮች የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ ግድ ይላቸዋል፡፡
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ /ኦኤምኤን/ ዳይሬክተርና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ጃዋር መሃመድ በበኩሉ ኦሮሚያን ማልማት፤ የሰላም ምድር ማድረግ፤ የዲሞክራሲ ድርዓት እንዲስፋፋ በአንድነት፤ በመስማማት መስራት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በመሆኑም በአንድነትና በፍቅር ጠንክሮ በመስራት የህዝቡን ሰላምና ብልጽግና የማይፈልጉትን ሃይሎች በንቃት መጠበቅ እንሚገባም ተናግሯል፡፡
በመሆኑም ማንኛውም አካል ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ይጠበቅበታል ነው ያለው፡፡
ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችም ወደ ሀገራቸው በመመለስ በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን እንዲያካሄዱና የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የአማራ እና የኦሮሚያን ህዝብ አንድነት እና ወንድማማችነትን በማጠናከር ረገድ ኦኤምኤን ትልቅ እስታዋጽኦ ነበረው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል የኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ናቸው፡፡
አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ አንድነትን፤ ፍቅርን፤ መተባበርን፤ ይቅርታን በህዝቡ ዘንድ በማስፋት ቂም በቀል፤ ጭቆናና በደልን ቦታ ያሳጣ ነው ብለዋል፡፡

የፌደራሉ መንግስት አብዲ ኢሌን ከስልጣን እንዲያስወግድ የሚፈቅደው የህግ አዋጅ!

የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት በዛሬው ዕለት በጅጅጋ ከተማ ገብቶ ስለ ወሰደው እርምጃ ህጋችን ምን ይላል? በክልሎች ጉዳይ የፌዴራሉ መንግስት ጣልቃ-ገብነትስ እስከ ምን ድረስ ነው?

በታደሰ ተክሌ የቀረበ ምልከታ፡፡
በኢትዮ-ሶማሌ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የሰብአዊ መብት ጥሰትና መፈናቀል በክልሉ አስተደደር በኩል መፍትሔ ተሰጥቶት እንዲስተካከል በፌዴራል መንግሥት በኩል የተለያዩ ጫናዎችና የሽምግልና መድረኮች ላይ የእርቅ ስምምነቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ግን የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ሲብስበት እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ነገሮችን በቸልታ እንዳያይ የሚያደርገውና ቀጥተኛ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለው የህግ ማዕቀፍ አው፡፡ ይኸውም የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገባበትን ሁኔታ የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 359/2003(95) ሲሆን በዚህ አዋጅ መሰረት የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ወሰኑ እስከ ምን ድረስ እንደሆነ በግልፅ ይደነግጋል፡፡
የፌደራል መንግሥት በክልሎች የሚፈፀሙ ህገመንግስታዊም ሆነ ሰብአዊ መብት
ጥሰተቶች ሲያጋጥሙ ከሚወስዳቸው እርምጃዎች ውስጥ አንዱ ዛሬ ያየነው የመከላከያ ሰራዊት ጣልቃ ገብነት አንዱ ነው፡፡ “ከዚህ ቀጥሎ ሊወሰዱ የሚችሉ ተግባራትስ በምን አግባብ ወደ ህጋዊነት ሊመጡ ይችላሉ?” የሚለው የዚህ ፅሁፍ ዋናውና አንኳሩ ነጥብ ነው፡፡ “የመከላከያ ሰራዊት ጣልቃ ገብቶ ያረጋጋውን ሰላምና ደህንነት ለማን አስረክቦ ይወጣል?” የሚለውም ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ የሚዳኝ ይሆናል፡፡ ለክልሉ ፖሊስ ያስረክብ የሚባል ከሆነ ከከዚህ ቀደሙ የከፋ ቀውስ ሊያጋጥመን ይችላል፡፡ እንዲሁም “ክልሉንስ ማን ያስተዳድረው?” የሚለው ሌላው መታየት ያለበት ነጥብ ነው
በአዋጁ አንቀፅ 14(2)(ለ) ስር እንደተደነገገው የፌዴራሉ መንግሥት የክልሉን ምክር ቤትና የክልሉን ከፍተኛ የህግ አስፈፃሚ አካል በማገድ ለፌዴራል መንግስቱ ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም የመወሰን ስልጣን አለው፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩም ክልሉን በበላይነት ከመምራት ጀምሮ በስልጣን ላይ የነበሩ የአስተዳደር አካላትንና የፀጥታ ክፍል ኃላፊዎችን ለፍርድ እስከማቅረብ የሚደርስ ስልጣን የሚኖረው ይሆናል፡፡ ስለሆነም የዛሬው የመከላከያ ሰራዊት ተልዕኮ ግቡን መምታቱ ሲረጋገጥ በቀጣይ የሚደረገው ተግባር ክልሉን ለጊዜያዊ አስተዳደር የማስረከብ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡
እነዚህ የሽግግር ሂደቶች ህጋዊነታቸውን ጠብቀው በመሄድ ለክልሉ ሰላም መደፍረስ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል የክልሉን ሰላምና መረጋጋት የማስቀጠል ኃላፊነት ለፌዴራል መንግስቱ የተሰጠ ስለሆነ በአንዳንድ ወገኖች እየተነሳ ያለው ትችት ህጋዊ መሰረት የለውም፡፡ የፌዴራል መንግሥት የዛሬውን እርምጃ ለመውሰድ በመዘግየቱ ቢወቀስ እንጂ አብዲ ኢሌን ጠምዝዞ ከስልጣን በማውረዱ ተጠያቂ መሆን አይችልም፡፡ የክልሉ ምክር ቤትም ቢሆን ክልሉን የማስተዳደር አቅሙ ከተሽመደመደ ከህዝብ የተሰጠውን ውክልና እስከመነጠቅ የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድብት እንደሚችል በተጠቀሰው አዋጅ ተደንግጏል፡፡
በጋምቤላ ክልል ከአስራ ሶስት አመታት በፊት ተከስቶ የነበረውን የእርስበርስ ግጭት ለማስቆም በማሰብ የወጣው አዋጅ ዛሬ ለሌላ ተግባር ተመዞ የወጣበትን ሁኔታ እያየን ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ በፌዴራል መንግስቱ የሶህዴፓን ወክለው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ ክልሉን በጊዜያዊነት ሊመሩ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ መሆኑን አንዳንድ ሹክሹክታዎች እየተሰሙ ነው፡፡

ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ገለፀ

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የህዝቦችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ገለፀ። ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደሆነች አንስታል።
ለውጡም መላ የኢትየጵያ ህዝቦችን ባሳተፈ እና ባለቤት ባደረገ መልኩ እየተካሄደ ይገኛል ያለው ሚኒስቴሩ፥ እየተካሄደ ካለው የለውጥ እንቅስቃሴም መላው የሀገሪቱ ህዝቦች ተጠቃሚ በመሆናቸው ተሳትፏቸውን በማጠናከር ላይ ይገኛሉ ብሏል።
ሆኖም በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች አልፎ አልፎ የብጥብጥና የሁከት ድርጊቶች እንደሚስተዋሉ አስታውቋል።
እነዚህ ህገወጥ ድርጊቶች በሚስተዋሉባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ሃይሉ ከህዝቡ ጋር ሆኖ የማረጋጋት ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ነው የገለፀው።
በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በጂግጂጋ ከተማ የተከሰተው ብጥብጥ፣ ቀጥሎም ወደ ሌሎች አንዳንድ የክልሉ ከተሞች የተዛመተው ሁከት በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለውና በፍጥነት ሊገታ እና ሊታረም የሚገባው ድርጊት መሆኑን አስታውቋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊታችን ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን የተከሰተውን ሁከት በቅርበት ሲከታተል፣ ሁኔታውን ለመቆጣጠርና ህብረተሰቡን ለማረጋጋት ጥረት እያደረገ የነበረ ቢሆንም ብጥብጡ በተፈለገው ፍጥነት ሊቆም አልቻለም ብሏል።
በመሆኑም በክልሉ የህዝቦቻችን ሰላም እና ደህንነት አደጋ ውስጥ እየገባ ያለበት ሁኔታ በመፈጠሩ የመከላከያ ሃይላችን ሁከትና ብጥብጡን በዝምታ የማይመለከት መሆኑንና የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን በጥብቅ እንደሚያሳስብ ነው የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በመግለጫው ያስታወቀው።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል
ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ
አገራችን ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደሆነች ይታወቃል። ለውጡም መላ የኢትየጵያ ህዝቦችን ባሳተፈ እና ባለቤት ባደረገ መልኩ እየተካሄደ ይገኛል። እየተካሄደ ካለው የለውጥ እንቅስቃሴም መላው የአገራችን ህዝቦች ተጠቃሚ በመሆናቸው ተሳትፏቸውን በማጠናከር ላይ ይገኛሉ።
ሆኖም በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች አልፎ አልፎ የብጥብጥና የሁከት ድርጊቶች ይስተዋላሉ። እነዚህ ህገወጥ ድርጊቶች በሚስተዋሉባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ሃይሉ ከህዝቡ ጋር ሆኖ የማረጋጋት ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል።
በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በጂግጂጋ ከተማ የተከሰተው ብጥብጥ፣ ቀጥሎም ወደ ሌሎች አንዳንድ የክልሉ ከተሞች የተዛመተው ሁከት በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለውና በፍጥነት ሊገታ እና ሊታረም የሚገባው ድርጊት ነው።
የአገር መከላከያ ሠራዊታችን ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን የተከሰተውን ሁከት በቅርበት ሲከታተል፣ ሁኔታውን ለመቆጣጠርና ህብረተሰቡን ለማረጋጋት ጥረት እያደረገ የነበረ ቢሆንም ብጥብጡ በተፈለገው ፍጥነት ሊቆም አልቻለም።
በመሆኑም በክልሉ የህዝቦቻችን ሰላም እና ደህንነት አደጋ ውስጥ እየገባ ያለበት ሁኔታ በመፈጠሩ የመከላከያ ሃይላችን ሁከትና ብጥብጡን በዝምታ የማይመለከት መሆኑንና የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን በጥብቅ ያሳስባል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር
ሃምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም.

የሶማሌ ክልል ከኢትዮጵያ ዘጠኝ ክልሎች አንዱ ነው

የሶማሌ ክልል (ክልል 5) ከኢትዮጵያ ዘጠኝ ክልሎች አንዱ ነው። ዋና ከተማው ጅጅጋ ነው። 279,252 ካሬ ኪ.ሜ. ቦታ ሲሸፍን በ1991 የሕዝብ ብዛቱ 3,602,000 ነበር። ባሁኑ ስአት የሕዝብ ብዛት በአጠቃላይ 5,148,989 በላይ ተብሎ ይገመታል። ክልሉ በጣም ብዙ የሶማሌ ብሔረሰቦች ይገኙበታል። በ1970ዎቹ እ.ኤ.አ. ሶማሊያ ቦታውን በወውረር ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት አስነስታ ነበር። ከነዚህም ዋነኛው የኦጋዴን ጦርነት ነው። ርዕሰ ከተማ ጅጅጋ ሲሆን ጅጅጋ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኝ ከተማ ነው። ከተማው ከሐረር 80 ኪ.ሜ. ይርቃል። በቀድሞው ሐረርጌ ክፍለ-ሀገር የሚገኝ ከተማ ሲሆን አሁን የሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ነው። በ1994 እ.ኤ.አ. ከተማው 56,821 ሰዎች ነበሩት። በ1998 ማዕከላዊ የስታትስቲችስ ባለስልጣን እንደተመነው ጅጅጋ የ98,076 ሰው መኖሪያ ስትሆን ከነሱም 50,355 ወንዶችና 47,721 ሴቶች ይገኙበታል። ከተማው በ9°10' ሰሜን ኬክሮስ እና 42°48' ምስራቅ ኬክሮስ ይገኛል። የሶማሌ ፕሬዚዳንት ሞሐሙድ አብዲ ኦማር («አብዲ ኢለይ») ይባላሉ። በክልሉ የሱማሌ ብሔር ሲገኙ የሶማሌ ብሔር ከኢትዮጵያ ሱማሎ ውጭም በአፍሪካ ቀንድ ይገኛሉ። ሱማሊኛ ቋንቋቸው ነው። ጠቅላላ ብዛታቸው ከ10 እስከ 20 ሚሊዮን የሚገመት ሲሆን እነዚህም በሶማሊያ (ከ8 ሚሊዮን በላይ)፣ ኢትዮጵያ ሱማሌ (ከ3 እስከ 5 ሚሊዮን)፣ ጅቡቲ (250,000)፣ ሰሜን-ምስራቅ ኬንያ (240,000)፣ እና በሌሎች ውጭ ሀገሮች ይገኛሉ። ዋና ሃይማኖታቸው ሱኒ እስልምና ነው።

ሶማልኛ ቋንቋ ኩሺቲክ ተብሎ በሚታወቀው የቋንቋ መደብ የአፍሮ-እስያ ቤተሰብ የሚካለል ቋንቋ ነው። በአፍሪካ ቀንድ በሚገኙ አገሮች፥ በኢትዮጵያ ፥ ጅቡቲ፥ ሶማሌና ኬንያ፥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ተናጋሪዎች አሉት። በ1964፥ በዚአድ ባሬ መንግስት አነሳሽነት፥ ለመጀመሪያ ጊዜ በ ላቲን ፊደል መጻፍ ጀመረ።

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time