የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት በዛሬው ዕለት በጅጅጋ ከተማ ገብቶ ስለ ወሰደው እርምጃ ህጋችን ምን ይላል? በክልሎች ጉዳይ የፌዴራሉ መንግስት ጣልቃ-ገብነትስ እስከ ምን ድረስ ነው?
በታደሰ ተክሌ የቀረበ ምልከታ፡፡
በኢትዮ-ሶማሌ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የሰብአዊ መብት ጥሰትና መፈናቀል በክልሉ አስተደደር በኩል መፍትሔ ተሰጥቶት እንዲስተካከል በፌዴራል መንግሥት በኩል የተለያዩ ጫናዎችና የሽምግልና መድረኮች ላይ የእርቅ ስምምነቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ግን የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ሲብስበት እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ነገሮችን በቸልታ እንዳያይ የሚያደርገውና ቀጥተኛ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለው የህግ ማዕቀፍ አው፡፡ ይኸውም የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገባበትን ሁኔታ የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 359/2003(95) ሲሆን በዚህ አዋጅ መሰረት የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ወሰኑ እስከ ምን ድረስ እንደሆነ በግልፅ ይደነግጋል፡፡
የፌደራል መንግሥት በክልሎች የሚፈፀሙ ህገመንግስታዊም ሆነ ሰብአዊ መብት
ጥሰተቶች ሲያጋጥሙ ከሚወስዳቸው እርምጃዎች ውስጥ አንዱ ዛሬ ያየነው የመከላከያ ሰራዊት ጣልቃ ገብነት አንዱ ነው፡፡ “ከዚህ ቀጥሎ ሊወሰዱ የሚችሉ ተግባራትስ በምን አግባብ ወደ ህጋዊነት ሊመጡ ይችላሉ?” የሚለው የዚህ ፅሁፍ ዋናውና አንኳሩ ነጥብ ነው፡፡ “የመከላከያ ሰራዊት ጣልቃ ገብቶ ያረጋጋውን ሰላምና ደህንነት ለማን አስረክቦ ይወጣል?” የሚለውም ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ የሚዳኝ ይሆናል፡፡ ለክልሉ ፖሊስ ያስረክብ የሚባል ከሆነ ከከዚህ ቀደሙ የከፋ ቀውስ ሊያጋጥመን ይችላል፡፡ እንዲሁም “ክልሉንስ ማን ያስተዳድረው?” የሚለው ሌላው መታየት ያለበት ነጥብ ነው
በአዋጁ አንቀፅ 14(2)(ለ) ስር እንደተደነገገው የፌዴራሉ መንግሥት የክልሉን ምክር ቤትና የክልሉን ከፍተኛ የህግ አስፈፃሚ አካል በማገድ ለፌዴራል መንግስቱ ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም የመወሰን ስልጣን አለው፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩም ክልሉን በበላይነት ከመምራት ጀምሮ በስልጣን ላይ የነበሩ የአስተዳደር አካላትንና የፀጥታ ክፍል ኃላፊዎችን ለፍርድ እስከማቅረብ የሚደርስ ስልጣን የሚኖረው ይሆናል፡፡ ስለሆነም የዛሬው የመከላከያ ሰራዊት ተልዕኮ ግቡን መምታቱ ሲረጋገጥ በቀጣይ የሚደረገው ተግባር ክልሉን ለጊዜያዊ አስተዳደር የማስረከብ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡
እነዚህ የሽግግር ሂደቶች ህጋዊነታቸውን ጠብቀው በመሄድ ለክልሉ ሰላም መደፍረስ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል የክልሉን ሰላምና መረጋጋት የማስቀጠል ኃላፊነት ለፌዴራል መንግስቱ የተሰጠ ስለሆነ በአንዳንድ ወገኖች እየተነሳ ያለው ትችት ህጋዊ መሰረት የለውም፡፡ የፌዴራል መንግሥት የዛሬውን እርምጃ ለመውሰድ በመዘግየቱ ቢወቀስ እንጂ አብዲ ኢሌን ጠምዝዞ ከስልጣን በማውረዱ ተጠያቂ መሆን አይችልም፡፡ የክልሉ ምክር ቤትም ቢሆን ክልሉን የማስተዳደር አቅሙ ከተሽመደመደ ከህዝብ የተሰጠውን ውክልና እስከመነጠቅ የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድብት እንደሚችል በተጠቀሰው አዋጅ ተደንግጏል፡፡
በጋምቤላ ክልል ከአስራ ሶስት አመታት በፊት ተከስቶ የነበረውን የእርስበርስ ግጭት ለማስቆም በማሰብ የወጣው አዋጅ ዛሬ ለሌላ ተግባር ተመዞ የወጣበትን ሁኔታ እያየን ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ በፌዴራል መንግስቱ የሶህዴፓን ወክለው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ ክልሉን በጊዜያዊነት ሊመሩ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ መሆኑን አንዳንድ ሹክሹክታዎች እየተሰሙ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment