Sunday, November 13, 2016

ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚዳንትነታቸው በምርጫ ቅስቀሳቸው ካስተጋቡት ይለይ ይሆን?

  
እ.ኤ.አ. በ2015 በዲሴምበር ወር ቢዝነስ ኢንሳይደር የተባለው የአሜሪካ ጋዜጣ አንድ አስገራሚ ቃለ ምልልስ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡
   በዓመቱ ዴሞክራቷ ሒላሪ ክሊንተንን በማሸነፍ በዓለም በከፍተኛ ደረጃ አነጋጋሪ የሆነ አጋጣሚ የፈጠሩት ዶናልድ ጆን ትራምፕ፣ የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካይ ሆነው ለመወዳደር ትግል የሚያደርጉበት ወቅት ነበር፡፡
  በዋና ዋና ሚዲያ ተቋማት በመጀመርያ እምብዛም ግምት ያልተሰጣቸው ትራምፕ ተቀናቃኞቻቸውን እየጣሉ ቀስ በቀስ እየገሰገሱ ነበር፡፡ ዶናልድ ትራምፕ በቅስቀሳቸው ዘረኝነትን የተላበሱ፣ የአናሳ መብቶችን የሚያጎድፉና ስደተኞችን የሚያብጠለጥሉ መሆናቸው የበርካታ ሰዎችን ቀልብ ስቦ ነበር፡፡ ይሁንና በዚህ አያያዛቸው እንኳን የአሜሪካ ፕሬዚዳነት ሆነው ሊመረጡ የሪፐብሊካን አቻዎቸውንም ያሸንፋሉ ተብሎ የተሰጣቸው ግምት ዝቅተኛ ነበር፡፡
ታዋቂውን የፊልም ባለሙያ ማይክል ሙርን ያነጋገረው ቢዝነስ ኢንሳይደር ግን አስገራሚ ትንበያ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡ ማይክል ሙር በዚህ ቃለ ምልልስ፣ ‹‹እመኑኝ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን የሪፐብሊካን አቻዎቹን ያሸንፋል፤›› የሚል የብዙዎችን ግምት የሚፃረር አስተያየት ሰጥቶ ነበር፡፡
ማይክል ሙር የፖለቲካ አስተያየት በመስጠት ከሚታወቁት የፊልም ደራሲዎች መካከል ግንባር ቀደም ሲሆን፣ በዚሁ አስተያየቱ ግን በብዙዎች ተወቅሷል፡፡
‹‹የምነግራችሁ ቀልድ አይደለም፡፡ ወደ ጨለማው ዓለም እያመራን መሆናችንን ያኔ ሰዎች ሊሰማቸው ይጀምራል፤›› የሚል ማብራርያም ነበረበት አስተያየቱ ላይ፡፡ ማይክል ሙር ባለፈው ሐምሌ ወር  ደግሞ ከቢል ማኸር ጋር በቴሌቪዥን ባደረገው ቃለ ምልልስ ዋናዎቹ ሚዲያዎች የትራምፕ መገስገስን በቸልታ ማየታቸውን ተችቶ ነበር፡፡ ለኦስካር ተሸላሚው፣ ‹‹ይቅርታ የእናንተን መንፈስ እየረበሽኩ እንዳይሆን እንጂ ትራምፕ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ይሆናል፤›› ብሎ ነበር፡፡ ማይክል ሙር የተለየ አቋም የያዘበትንና ትራምፕን በእርግጠኝነት ያሸንፋሉ ያለበትን ምክንያትም አብራርቷል፡፡ የመጀመርያው በአሜሪካ ዓበይት የሚላቸውን ክልሎች (ሚቺጋን፣ ኦሀዮ፣ ዊስኮንሲንና ፔንሲልቫንያ) ላይ ለማሸነፍ የተከተሉትን ስትራቴጂ ነው፡፡ ቢልየነሩ ትራምፕ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከፕሬዚዳንትነት ወንበር የሚጠብቁት ምንም ቁሳዊ ነገር አለመኖሩን ለማሳመን፣ መላ ቤተሰባቸውን ይዘው ቅስቀሳ ውስጥ በመግባታቸው የአብዛኛውን መራጭ ልብ ሊያሸንፍ ይችላል በማለት ገምቶ ነበር፡፡ ‹‹አሜሪካን እንደገና ትልቅ አደርጋታለሁ፤›› በሚለው ባዶ ቅስቀሳቸው የሚታለል አሜሪካዊ ቁጥር ቀላል አይሆንም ብሎም ነበር፡፡
በአራተኛ ደረጃ የማይክል ሙር ግምት አሜሪካ ውስጥ ቁጣ ያደረባቸው ነጮች ድምፅ ያገኛሉ የሚል ነው፡፡ በተለይ ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆኑ ነጭ መራጮችን ቁጥራቸው 40 ሚሊዮን መሆኑንና በምርጫው ቀን ቁጣቸውን ለመግለጽ በእርግጠኝነት በነቂስ ወጥተው ድምፃቸውን ይሰጣሉ ብሎ ነበር፡፡
አፈንጋጩ ትራምፕ
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ድላቸውን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ‹‹የሁሉም አሜሪካዊያን ፕሬዚዳንት እሆናለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል በቅስቀሳ ወቅት ሴቶች፣ ሙስሊም አሜሪካኖች፣ ጥቁር አሜሪካኖች፣ ሜክሲካኖችና በአጠቃላይ ነጭ ያልሆኑ አሜሪካዊ ስደተኞች ላይ የሰጧቸው አስፈሪ አስተያየቶች ከአሜሪካ ጀምሮ እስከ አውሮፓ፣ እስያና አፍሪካ ድረስ ሥጋት የጫሩ በመሆናቸው የሁሉም አሜሪካኖች ፕሬዚዳንት እሆናለሁ የሚለው ንግግራቸው ከቀድሞው አወዛጋቢ ዘረኛ ንግግቸው በተቃራኒ፣ አሜሪካውያንን በሙሉ በእኩልነት አስተዳድራለሁ እንደማለት ተወስዷል፡፡  የእሳቸውን መመረጥ ተከትሎ ግን አንዳንድ ክስተቶች እየተስተናገዱ ይገኛሉ፡፡ ትራምፕ ሒላሪ ክሊንተንን አሸንፈው የአሜሪካ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ በአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ከፍተኛ ተቃውሞ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ትራምፕ በአንዳንድ ቅስቀሳዎች ላይ ለተጠቀሙባቸው አስተያየቶች ማብራሪያ እንዲሰጡ እየጠየቁ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ ከበርካታ አገሮች የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክትም እየደረሳቸው ይገኛል፡፡ ከሩሲያም እንዲሁ፡፡
ትራምፕ 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ አሜሪካ ከተለያዩ አገሮች ጋር የነበራትን ወዳጅነት ከአገሪቱ ጥቅም አንፃር እንደሚከልሱት፣ ቁጥር አንድ ባላንጣ ተደርጋ ከምትታየው ሩሲያ ጋር ሳይቀር አብረው እንዲሚሠሩ፣ አሜሪካ ከመሥራቾቹ መካከል የሆነችበትን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) አባል አገሮች ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታ እንደሚኖራት ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል ግን ድርጅቱ ጊዜ ያለፈበት ነው ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
ከሩሲያ ጋር አብረው ለመሥራት እንደሚፈልጉ የተናገሩት ትራምፕ አክራሪው እስላሚክ ስቴትን (አይኤስ) ለማጥፋት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በቅስቀሳው ከኮነኗቸው ግለሰቦች መካከል ላለፉት ስምንት ዓመታት አሜሪካን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ባራክ ኦባማን አንዱ ሲሆኑ፣ አይኤስን የፈበረኩ ናቸው፣ አሜሪካ ውስጥ አልተወለዱምና የመሳሰሉ አስተያየቶች መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡
በትራምፕ ድል ማግሥት አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ተፎካካሪያቸው ሒላሪ ክሊንተን አንዷ ሲሆኑ፣ ‹‹የአሜሪካ ህልም ሁሉንም ዓይነት ሰው አቅፎ ለመያዝ ይህንን ያህል ሰፊ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የኦባማም አስተያየት ተመሳሳይ ነው፡፡
ተፎካካሪያቸው የያዙት አቋም በዘረኝነትና በፋሽስትነት የሚመደብ ቢሆንም፣ የአሜሪካ ህልም ለእንዲህ ዓይነት ሰውም ቦታ ይሰጣል የሚል ይመስላል የእነ ኦባማ አስተያየት በሲኤንኤን እንደተተነተነው፡፡
ዘረኛው ፕሬዚዳንት?
ቮክስ የተባለው ታዋቂ ሌላ ሚዲያ ያስተናገደው አንድ ጽሑፍ፣ ‹‹የትራምፕ ማሸነፍ የማይበገርና የማይተመን የዘረኝነት ኃይልን አሳታዋሽ ነው፤›› ሲል አስፍሯል፡፡
አሸናፊው ትራምፕ እንዲህ ዓይነት አቋሞች ይዘው የአሜካውያንን ድምፅ ያሸነፉበት ምክንያት የተለያዩ ትንታኔዎች እየሰጡበት ይገኛሉ፡፡ ትራምፕ በአንዳንድ ጋዜጠኞች ከዘረኝነት ጋር በተያያዘ ለሚቀርቡባቸው ጥያቄዎች በምላሻቸው፣ ‹‹የሚገርማችሁ እኔ በዚህ ዓለም ካለው ዘረኛ ዝቅተኛው ነኝ፤›› በማለት ያስተባብላሉ፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ ባሰባሰበው መረጃ መሠረት ግን፣ ዶናልድ ትራምፕ እ.ኤ.አ. ከ1970ዎቹ ጀምሮ እስከ 2011 ከአሥር በላይ የዘረኝነት ንግግሮችና ድርጊቶች ተመዝግቦባቸዋል፡፡ የመጀመሪያው እ.ኤ.አ. በ1973 በሪቻርድ ኒክሰን አስተዳዳር ዘመን የተፈጸመ ሲሆን፣ የትራምር ኩባንያ ለጥቁር ቤት አላከራይም በማለቱ ክስ ተመሥርቶባቸው ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ሌላው እ.ኤ.አ. በ1990 ጆን ኦዶኔል በተባለው ደራሲ (የትራምፕ ፕላዛ ሆቴል ፕሬዚዳንት) የተጻፈው መጽሐፍ እንዳሰፈረው፣ ትራምፕ በጥቁር አካውንታንት ላይ የሰጡት አስተያየት ነው፡፡ ‹‹ጥቁር ሰዎች ገንዘቤን እየቆጠሩት ነው! በጣም ያስጠላል፡፡ ገንዘቤን እንዲቆጥሩት የምፈልገው ልቅም ያለ ሙሉ ልብስ የለበሱ አጭር ነጮች እንዲሆኑ ነው፤›› በማለት ጥቁሮች ሰነፎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡  ትራምፕ ይህን መጀመሪያ ክደው የነበሩ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. በ1997 በፕለይ ቦይ ኢንተርቪው አምነዋል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በተመሳሳይ በሌላ ጥቁርና ሴት ሠራተኛ ላይ በፈጸሙት የዘረኝነት ድርጊት 200 ሺሕ ዶላር ካሳ መክፈላቸው ተረጋግጧል፡፡
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ምርጫውን ለማሸነፍ ሲሉ ነው የሚል አቋም አላቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በአዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት የካቢኔ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፣ ምርጫው የአሜሪካ ሕዝብ ፍላጎት እስከሆነ ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጤቱ ደስተኛ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ዶ/ር ነገሪ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ታሪካዊና ሥር የሰደደ በመሆኑ፣ በእንዲህ ዓይነት ንፋስ የሚነቃነቅ አይሆንም፡፡
በተለያዩ የዓለም ሕዝቦች ላይ መደናገጥ መፈጠሩን የገለጹት ዶ/ር ነገሪ፣ የምርጫ ቅስቀሰቸው ትንሽ ወጣ ያለና ፍርኃት መፍጠሩን ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ‹‹የግሌ›› በሚሉት አስተያየት፣ ትራምፕ ምርጫውን ለማሸነፍ የተጠቀሙበት መንገድ እንደሆነ፣ በተለይ ባራክ ኦባማና ፓርቲያቸው ዴሞክራቲክ ፓርቲ እስከዛሬ የገነቡትን ገጽታ ከሥር መሠረቱ ለማፍረስ ታክቲክ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ዶ/ር ነገሪ ትራምፕ በቅስቀሳ ጊዜ የተናገሩዋቸው አንዳንድ አስተያየቶች በሥልጣን ዘመናቸው ተግባራዊ ይሆናሉ ብለው አያምኑም፡፡ ‹‹የአሜሪካ ሥልጣን በሕግ ነው የሚመራው፤›› ብለዋል፡፡ የሴኔቱ አባላትና ሌሎች የመንግሥት ተቋማት በጣም ጠንካራ የሥልጣን ማዕከላት መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡
አሜሪካውያን የልባቸውን የሚናገርላቸው አግኝተው ይሆን?
መስከረም መባቻ ላይ ዘ ኢኮኖሚስት “The Art of Lie” በሚል ርዕስ ያቀረበው ጽሑፍ፣ አንድ ፖለቲከኛ ሥልጣን ለመያዝ ምን ያህል ውሸት ሊደረድር እንደሚችል ያትታል፡፡ ትራምፕ የሒላሪ ክሊንተን ቤተሰቦች ከጆንኤፍ ኬኔዲ ግድያ ጀርባ እጃቸው እንዳለበት፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ የአሜሪካዊ ዜግነታቸውን በተጭበረበረ ሰነድ ያገኙ መሆናቸውን ወዘተ. በመዘርዘር የመራጮችን ድምፅ ለማግኘት መዋሸታቸው እንደሚቀጥሉበት ይተነትናል፡፡ ጽሑፉ ከዚህ በፊት በዚህ መንገድ ወደ ሥልጣን የመጡ አገር አፍቃሪ የሚመስሉ ውሸታም ሌሎች መሪዎችን ለአብነት ይጠቅሳል፡፡
ዘ ኢኮኖሚስት  ለአቋራጭ ማሸነፊያ ‹‹ስሜት ቀስቃሽና እውነትን የረገጡ ንግግሮችን ማድረግ ነው የሚያስፈልገው፤›› ይላል፡፡ እውነትን አጣመውና ውሸትን አጣጥመው የሚወዳደሩ ፖለቲከኞች አደገኞች ናቸው የሚለው ዘ ኢኮኖሚስት፣ በምርጫ ቅስቀሳ የሚወሩ ነገሮች እምብዛም በሕግ የማያስጠይቁ መሆናቸው ይህንን ለመሰለ አቀራረብ የሚጋብዝ እንደሆነ ይደመድማል፡፡
በቅስቀሳ ወቅት በውሸት የተገባ ቃል በተለያዩ መንገዶች እንደሚጋለጥ ግልጽ ይሁን እንጂ፣ በውሸት ቅስቀሳ ወደ ሥልጣን መምጣት ግን ለዘመናት ወደኋላ ወስዶ ለጭቆና ሊዳርገን ይችላል ይላል፡፡ ‹‹ትራምፕ በውሸት ቅስቀሳዎች ለማሸነፍ ይበቃሉ፤›› ሲልም አትቷል፡፡ ይህንን በመቃረን የነጭ አሜሪካውያን ድምፅ ችላ ተብሎና ሰሚ አጥቶ ቆይቷልና ትራምፕ ትክክለኛ ስትራቴጂ መከተላቸውን የሚናገሩት ደግሞ ማይክል ኮትል የተባሉ ጸሐፊ ናቸው፡፡
‹‹በእርግጥ ትኩረት የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነበሩ፡፡ የተለየ ቀለም ስላላቸው ሳይሆን የአገሪቱ ኢኮኖሚ ጫፍ ሆነው ቆይተዋል፤›› ብለዋል፡፡ ትራምፕ በክርክራቸው የተሟገቱላቸው ነጭ አሜሪካውያን በተለያዩ መጤዎችና ጥቁር አሜሪካውያን ምክንያት ተጎጂ መሆናቸውን ኮትል ይገልጻሉ፡፡
ኢትዮጵያዊው ሀብቶም በርሀ ዶናልድ ትራምፕ እንደሚያሸንፉ ያምን ነበር፡፡ ‹‹ሌሎች የሪፐብሊካን ተፎካካሪዎችን በሚያሸንፉበት ወቅት ተሸናፊ ፖለቲከኞች ሊናገሩት ያልፈለጉትን፣ ግን ውስጣቸው የነበረን ነገር ትራምፕ አውጥቶ ተናግሮታል፤›› ይላል፡፡ ‹‹ተወደደም ተጠላም ነጭ አሜሪካውያን ለዘመናት በተገነባው ሥርዓት ደስተኞች አይደሉም፡፡ አሁን የልባቸውን የሚናገርላቸው ተገኝቶላቸዋል፤›› ይላል፡፡
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ግን ትራምፕን የመረጡ ነጭ አሜሪካውያን በኢኮኖሚ ከሌሎች የተሻሉ እንጂ የወረዱ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ አንድ ጥናት የአንድ መካከለኛ ነጭ አሜሪካዊ ገቢ 72 ሺሕ ዶላር መሆኑን፣ ትራምፕን ያልመረጠ የአንድ መካከለኛ ዓመታዊ ገቢ 62 ሺሕ ዶላር ነው ይላል፡፡
ኤዲሰን ሪሰርች የተባለ በኤቢሲ ኒውስ፣ በአሶሼትድ ፕሬስ፣ በሲቢኤስ ኒውስ፣ በሲኤንኤን፣ በፎክስ ኒውስና በኤንቢሲ ኒውስ ጥምረት የተቋቋመ ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ የሁለቱን ተወዳዳሪዎች የድጋፍ መሠረት አሳይቷል፡፡ በዚህ መረጃ መሠረት ለዶናልድ ትራምፕ 53 በመቶ ወንዶች ድምፅ ሲሰጡ፣ ለሒላሪ ክሊንተን 41 በመቶ ናቸው ድምፅ የሰጡት፡፡ 58 በመቶ ነጭ ወንዶች ትራምፕን ሲመርጡ 37 በመቶ ብቻ ሒላሪን መርጠዋል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ስምንት በመቶ ብቻ የጥቁሮችን ድምፅ ሲያገኙ፣ ሒላሪ ክሊንተን በተቃራኒው 88 በመቶ ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ ትራምፕ 29 በመቶ ድምፅ ከስፓኒሽ ተናጋሪዎች ሲደርሳቸው፣ ሒላሪ 65 በመቶ ድምፅ አግኝተዋል፡፡ ከ120 ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምፅ በሰጡበት በዚህ ምርጫ፣ በናሙናነት የተወሰደው የ25 ሺሕ መራጮች መሆኑን ኤዲሰን ሪሰርች አስታውቋል፡፡ ይህ በፆታ፣ በዘርና በዕድሜ ላይ የተሠራ መረጃ 53 በመቶ የሚሆኑ ነጭ ሴቶች ትራምፕን ሲመርጡ፣ 43 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ለሒላሪ ክሊንተን ድምፅ ሰጥተዋል ይላል፡፡ በምርጫው በሕዝብ ድምፅ ሒላሪ 60,274,974 ሲያገኙ፣ ትራምፕ ደግሞ 59,937,338 ድምፅ አግኝተዋል፡፡ ይሁንና ‘ኤሌክቶራል ቮት’ በሚባለው የምርጫ ሥርዓት መሠረት ትራምፕ 290 በማግኘት 228 ያገኙትን ሒላሪን ማሸነፍ ችለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር አቶ ናሁሰናይ በላይ ግን ዶናልድ ትራምፕ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ስሜት አጥንተው ጥቅም ላይ አውለውታል ብለው ያምናሉ፡፡ ፋሺዝም እንደገና ይመለስ እንደሆነ አመላካች አድርገው የተመለከቱት አቶ ናሁሰናይ፣ የኢኮኖሚ ችግር ቢኖርም እንደዚህ ዓይነት እልም ያለ የዘረኝነት አስተሳሰብ ችግሩን ወደ ውጭ ለመግፋትና ሌሎች ላይ ለማላከክ መዋል እየተለመደ ነው ይላሉ፡፡ የትራምፕ ቅስቀሳም ሆነ የምርጫው ውጤት የነጭ አሜሪካውያንን  የበላይነት ለማንሰራራት መሠረት እየያዘ ለመምጣቱ አመላካች ነውም ይላሉ፡፡
በቅርቡ እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት እንድትወጣ የተደረገው እንቅስቃሴ፣ በዴንማርክ፣ በፈረንሣይና በስዊዘርላንድ ተመሳሳይ አዝማሚያዎች ማሳየቱን ለዚህ እንደ አብነት አቶ ናሁሰናይ ይጠቅሳሉ፡፡
ሌላው ለየት ያለ ጉዳይ ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ1789 እስከ 2016 ድረስ ባሉት 227 ዓመታት አሜሪካን በፕሬዚዳንትነት ከመሩት ጆርጅ ዋሽንግተን እስከ ባራክ ኦባማ በፖለቲካዊና ወታደራዊ ልምዳቸው መታወቃቸው ነው፡፡ የአሁኑ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ከሁለቱም የሌሉበት የመጀመሪያ መሪ መሆናቸው አነጋግሯል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ከአወዛጋቢነታቸውና ከነውጠኝነታቸው ጋር ሥልጣን ላይ ሲወጡ፣ በምርጫ ቅስቀሳቸው  ጊዜ ያስተጋቡዋቸውን ተግባራዊ ያደርጋሉ? ወይስ በሲስተሙ ይዋጣሉ? የሚለው ለጊዜው የዓለም መነጋገሪያ የሆነ የወቅቱ ጉዳይ ነው፡፡   Read more here

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time