Sunday, November 13, 2016

አዋሽ ባንክ በአዲስ ዓርማ ሊመጣ ነው

ስያሜውንም ያሻሽላል
ከደርግ ውድቀት በኋላ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለግል ዘርፉ ሲከፈት የመጀመሪያው የግል ባንክ በመሆን ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ነው፡፡ ከአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ በኋላ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀሉት አብዛኛዎቹ ባንኮች ከዋናው ስያሜያቸው ቀጥሎ ‹‹ኢንተርናሽናል›› የሚለውን በማከል እየተጓዙ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ወደ ስድስት የሚሆኑ ባንኮች ከዋና ስያሜያቸው ቀጥሎ ‹‹ኢንተርናሽናል›› የሚል ቅጥያ እየሰጡ ኢንዱስትሪውን ተቀላቅለዋል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ከስያሜያቸው ጋር ተያይዞ ኢንተርሽናል የሚል ቅጥያ ማከል ብዙም ትርጉም ያለው አይደለም እየተባለ ነው፡፡ በዓለም ላይ የሚታወቁ የፋይናንስ ተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየሠሩ ኢንተርናሽናል የሚል ቅጥያ የላቸውም፡፡ በቀደመው ጊዜ ኢንተርናሽናል የሚል ቅጥያ የነበራቸው ሳይቀሩ ይህንን አውጥተው ስያሜያቸውን በአጭር እየገለጹ መምጣታቸው፣ የንግድ ሥራቸውን እያቀላጠፈላቸው ስለመሆኑ በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
እንደ ሲቲ፣ ኮሜርስና ሌሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ባንኮች ዓርማና ስያሜ እንደ ምሳሌ በማንሳትም የስያሜና ዓርማዎች ግልጽና አጭር መሆናቸውን በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ኩባንያዎች ይመክራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ስያሜዎችና ተቋማቱ የሚገለገሉባቸው ዓርማዎች ከጊዜው ጋር መራመድ ያለባቸው ካልሆኑ፣ ተወዳዳሪነታቸውን ይገድበዋል ወደሚል አስተሳሰብ እየተገባም ነው፡፡
ከዚህ አንፃር የስያሜና የዓርማ አመራረጥ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ብዙም የሚተኮርበት ባይሆንም፣ አንዳንዶች ጠቀሜታውን በመረዳት በጥናት ላይ የተመሠረተ ስያሜና የዓርማ ቀረጻዎች እያደረጉ ነው፡፡ ለምሳሌ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ሲጠቀምበት የነበረውን ዓርማ መለወጡ ይታወሳል፡፡ ቀድሞ የነበረውን ዓርማ በአዲስ ለመለወጥ ያስፈለገበት ምክንያት፣ በቀላሉ ሊያዝ የሚችልና ጊዜው የሚጠይቀው ዓርማ በማስፈለጉ ነው፡፡
አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክም ባንኩን በተሻለ ይገልጽልኛል ወዳለው የዓርማ ለውጥ ውስጥ ገብቷል፡፡ ባንኩ ባለፉት 22 ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን ዓርማ ብቻ ሳይሆን አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ የሚለውን መጠሪያ ‹‹አዋሽ ባንክ›› በሚል በማሳጠር፣ ኢንተርናሽናል የሚለውን በማውጣት በቅርቡ በአዲስ ዓርማና ‹‹አዋሽ ባንክ›› በሚለው መጠሪያ ገበያውን ይቀላቀላል፡፡
ከባንኩ የተገኘው መረጃ ባንኩ በዚህን ያህል ደረጃ ዓርማን ለመለወጥና መጠሪያውንም ለማጣጣር ውሳኔ ላይ የደረሰው፣ የባንኩን የወደፊት አቅጣጫና ግብ ለማሳካት በቀረበ ጥናት መሠረት ነው፡፡
ባንኩ ‹‹ቪዥን 2025›› በሚል የያዘውን ውጥን ለማሳካት በአማካሪነት የተቀጠረው ኬፒኤምጂ፣ ባንኩ መለወጥ አለባቸው ብሎ ካቀረባቸው በርካታ አሠራሮችና ትግበራዎች ውስጥ አንዱ የባንኩን ዓርማና መጠሪያ ጊዜው በሚጠይቀው መልክ መቀረጽ አለበት የሚል ነው፡፡
ዓርማውን መለወጡና ስያሜውን ማሳጠሩ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሚሆንና ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ለመግባትም ያለውን ዕድል በሚያሳይ በዝርዝር ያቀረበው ጥናት፣ በባንኩ አመራር ተቀባይነት በማግኘቱ አዋሽ ዓርማውን ለመለወጥና ስያሜውንም ለማሳጠር እንዲወስን አድርጎታል፡፡
አማካሪ ድርጅቱ የዓርማ ለውጡን በተመለከተ በቀረበው ጥናት አዋሽ ባንክ በምሥራቅ አፍሪካ ከአሥሩ ምርጥ የግል ባንኮች አንዱ ለመሆን የቀረጸውን ራዕይ ለማሳካት፣ ዓርማውን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን የሚያመለክት ነበር ተብሏል፡፡
ባንኩ በአገር ውስጥ ትልቅ ቢሆንም የውጭ ገበያን ካሰበ የዓርማ ለውጡ አስፈላጊነት ላይ በዝርዝር ካቀረቡት ሐሳብ ጎን ለጎን፣ አሁን ያለው ዓርማ ከውጭ ካለው ጋር የሚሄድ አለመሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ዓርማ ወይም ብራንድ በአንድ ቢዝነስ ውስጥ ያለው ኃይል ከፍተኛ መሆኑንም አማካሪው ጠቅሶ፣ ተስማሚ ዓርማ ለገበያ ዕድገት ያለውን ጠቀሜታ በማያያዝ ጭምር ዓለም ወዳለበት ደረጃ ዓርማውንም ማሳደግ እንደሚገባ መክሯል፡፡
እስካሁን የሚጠቀሙበት ዓርማ በወቅቱ በነበረው ደረጃ የተሠራ ቢሆንም፣ የተሻለ እንዲሆን ማድረግ ግድ መሆኑ በመታመኑ ወደ ለውጡ ተገብቷል፡፡ እንደተባለውም ተስማሚ የሆነ ዓርማ ለመቅረጽ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓርማ ቀረጻ ልምድ ያላቸውን በማሳተፍ በተካሄደ ጨረታ የኬንያ ብራንድ ኢንተግሬትድ ኮንሰልቲንግ የተባለ ኩባንያ አሸንፎ አዲሱን የአዋሽ ባንክ ዓርማ ቀርጿል፡፡
የቀድሞው ዓርማ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ የሚለውን የእንግሊዝኛ መጠሪያ (AIB) በምፃረ ቃል የያዘ ሲሆንም፣ አዲሱ ዓርማ ግን ምንም ዓይነት ፊደላት የሌሉበት በክብ ቅርጽ የተሠራ ነው፡፡ ዓርማው ዓለም አቀፋዊ አገልግሎትን ይገልጻል በተባለ ደረጃ የተሠራ መሆኑንም የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ አዲሱ ዓርማ ከቀለም መረጣ ጀምሮ ለባንኩ ተወዳዳሪነት አጋዥ የሆኑ ትርጓሜዎችን የያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የባንኩን የወደፊት ራዕይ ለማሳካት ይረዳል የተባለው ይህን ዓርማ የሠራው ኩባንያም በአፍሪካ ውስጥ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማትን ዓርማ የሠራ ነው ተብሏል፡፡ ይህ ኩባንያ የኬንያው ባንክ ኦፍ ኬንያና የደቡብ አፍሪካውን ባንክ ኦፍ አፍሪካን ዓርማዎችን መሥራቱ ተገልጿል፡፡ የአዋሽ ባንክ አዲሱ ዓርማ በአዕምሯዊ ንብረት ከተመዘገበ በኋላ ሥራ ላይ ይውላል ተብሏል፡፡
አዋሽ ባንክ በአሁኑ ወቅት ከግል ባንኮች በከፍተኛ አትራፊነት የሚጠቀስ ሲሆን፣ በ2008 በጀት ዓመት ከታክስ ከአንድ ቢሊዮን ብር በማትረፍ ከግል ባንኮች የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘ ነው፡፡
በ2009 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከታክስ በፊት ከ244 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም በተጠቀሰው ጊዜ ከግል ባንኮች ከፍተኛው ትርፍ ነው ተብሏል፡፡  Read more here

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time