Monday, August 14, 2017

የሀገሪቱ ከአንድ ሚሊየን በላይ መሬት በጫት ተሸፍኗል - የኢትዮጵያ ወጣቶች ጫት ጋር ተላምደዋል

Image result for Ethiopian khat
ጫት በአማራ ክልል ከሳምንታት በፊት ኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የአፍሪካ የጥናት ተቋምን እና ከአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የምርምር ተቋም ባጠናቀረው መረጃ ግማሽ ያህሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች ጫት ጋር እንደተላመዱ ገልጧል፡፡
ከብዙ የዓለም ሀገራት የሚበልጠው መሬትም የጫት ማሳ ሆኗል፡፡በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የወጣ መረጃ እንደሚጠቁመው አሁን የሀገሪቱ ከአንድ ሚሊየን በላይ መሬት በጫት ተሸፍኗል፡፡ ጫት ከቡና ቀጥሎ ሁለተኛው የውጭ ምንዛሪ አስገኝ ተክል እንደሆነም ተገልጧል፡፡የጫት ተፈላጊነት እስከበዛ ድረስ ፣ጫት የጤፍ ማሳዎችን ሁሉ መያዙ አይቀርም፡፡
ጫት እንደ አማራ ክልል!!
ያማራው ክልል ሰፊ የለም መሬት እና የውሃማ አካላት ባለቤት ነው፡፡በዚህ በግብርና ምርት የሀገሪቱን ከፍተኛውን ምርት ይሸፍናል፡፡ አሁን አሁን አርሶአደሩ ፊቱን ክፉኛ ወደ ጫት ምርት አዙሯል፡፡ የጣና ዳርን ተከትሎ የባህርዳር ዙሪያ፣የደራ ፣የፎገራ ወዘተ አርሶአደሮች ጫትን የጓሮ አትክልታቸውን እየተው እያለሙት ነው፡፡የጎጃም ለምለም መሬቶችም በጫት ተሸፍነዋል፡፡በአዴት የጫት ገበያው ደርቷል፡፡
በሞጣ የጫት ገበያው ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮት፣ጫት በየቦታው እንዳይቃም ተከልክሏል፡፡በምስራቁ የአማራው ክፍል ጫት ሲበዛ ይቃማል፡፡ ኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣ፣ጫት በአማራ ክልል በተለይም በጎንደር እና በባህርዳር ባልተለመደ ሁኔታ ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡ ከክርስትና እና ከእስልምና ሀይማኖት አባቶች ባገኘሁት መረጃ ጫት እንዲቃም የሚደግፍ አንድም የእምነት አስተምህሮ የለም ብለውኛል፡፡
በእርግጥ ጫት መቃም በዓለም የጤና ድርጅት ከ 1980 ዓ/ም ጀምሮ እንደ ጎጂ ዕፅ ከተፈረጀ በኋላ የዓለም ገበያ እየተዘጋበት ነው፡፡በሳውዲ ጫት መቃም አደገኛ እፅ የመጠቀም ያህል ያስቀጣል፡፡በአሜሪካ እንደዚሁ፡፡እንግሊዝም ከሶስት ዓመት በፊት ጫት ወደ ሀገሯ እንዳይገባ ከልክላለች፡፡ የመን፣ጂቡቲ፣ሶማሊያ እና ኬኒያ ጫት በመቃም ይታወቃሉ፡፡ የየመን 90 በመቶ ወንድ ጫት ቃሚ ነው፡፡ጫት ለእነዚህ ሀገራት ውድቀት ሚናው የጎላ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡የመን ለመከልከል ብትሞክርም አልቻለችም፡፡
የኢትዮጲያ ጫት መዳረሻው ወደነዚህ አካባቢዎች ነው፡፡ግን እነዚህ ሀገራትም ቢሆንም ገባያቸውን ለመዝጋት እየተቃረቡ ስለሆነ የጫት ንግድ በሀገር ውስጥ መገደቡ አይቀርም፡፡ አማራ ክልል ከጫት ገቢ ምን ያህል ያገኛል? የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን እንደሚለው በአማራ ክልል ከሚመረተው ጫት 80% ለሀገር ውስጥ እና ለአካባቢ ፍጆታ ይውላል፡፡20% ብቻ ለውጭ ገበያ ይውላል፡፡ያ ሆኖም መደበኛ የገበያ ስርዓት ስለሌለው ከጫት በዓመት 10 ሚሊየን ብር እንኳ በቅጡ ማግኘት አይችልም፡፡
በ 2004 ዓ/ም የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን ጫት መቃም እንዳይበረታታ በጫት ላይ ተጨማሪ ታክስ 5% (excise tax) እንዲጣል ወስኗል፡፡ ነገር ግን ክልሉ ይህን ተግባራዊ እንኳ ማድረግ አልቻለም ከሰሞኑ ከመሞከሩ በስተቅር እርግጥ ሙከራው ጥሩ ነው፡፡ጫት በክልሉ ቃሚ እንጂ በጥፋቱ ልክ የስራ ዕድል አልፈጠረም፡፡ የጫት ገበያ በዘፈቀደ መሆኑ ለቁጥጥር አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ጫት ላይ ተጨማሪ ታክሱን ከመተግበር ባለፈ፣ጫት በየቦታው እንዳይሸጥ እገድባለሁ ብሎ በ 2008 ዓ/ም ለአማራ ቴሌቪዝን ተናግሮ ነበር፡፡ግን እስካሁን ያለውን አላደረገም፡፡ጫት በየቦታው ተመርቶ፣በየቦታው እየተሸጠ ነው፡፡
የክልሉ የግብርና ቢሮ ጫት እንደተስፋፋ ቢገልፅም፣በምን ያህል ሄክታር መሬት ምን ያህል አርሶአደሮች እያመረቱት እንደሆነ የተጠናከረ መረጃ የለውም፡፡ብቻ ጫት በከፍተኛ ሁኔታ ውሃም ስለሚፈልግ የመስኖ ምርትን እየተሻማው ነው፡፡
ለአባይ ና ጣናም ጫት ስጋት ሆኗል፡፡ በጎንደር ዮኒቨርሲቲ የህክምና መምህር የሆኑት ዶክተር ብርሌው ተሾመ፣ እንደሚሉት ጫት በቅፅበት አነቃቅቶ ለድብርት ስለሚጋብዝ ለአዕምሮ ህመም መነሻ ነው ብለዋል፡፡ለሌሎች ሱሶችም ገፊ ነው፡፡ በአማኑኤል ሆስፒታል ካሉ የአዕምሮ ህሙማን ውስጥ 70% በጫት እና ተያያዥ ደባል ሱሶች እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ጫት በጊዜ ና በገንዘብ ላይ የሚያመጣው ጫናም ቀላል አይደለም፡፡
በመሆኑም ክልሉ ጫት ላይ የንግድ ስርዓቱን መገደብ፣የሚቃምበትን እና የሚመረትበትን ቦታ መወሰን እስካልቻለ ድረስ ወጣቶች ውሏቸውን ሁሉ ጫት ማሳ ላይ ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ስራ አጥነትን ለመቀነስ፣አማራጭ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን መንግስት ቀጠሮ ሳይሰጥ ሊሰራ ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ጫት ተስፋ የመቁረጥ መደበቂያ ሆኖ መዝለቁ አይቀርም፡፡የሀይማኖት አባቶችም ማህበረሰባዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ሁኔታው ያስገድዳቸዋል፡፡
በየሺሀሳብ አበራ
ባህር ዳር፡ ነሀሴ 8/2009 ዓ/ም (አብመድ)
ለህብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት
አማራ ቴሌቪዥን ፣በአማራ ራዲዮ እና በኤፍኤም ባህር ዳር 96.9 ዜናዎች እና ዝግጅቶች ዙሪያ ለሚኖርዎት ጥቆማና አስተያየት ለአማራ ቴሌቪዥን(ATV)፣ ለአማራ ራዲዮ(AR)፣ ለኤፍኤም ባህር ዳር 96.9 (FM) እና ለበኩር (AB) በማስቀደም በ8200 ማድረስ ይችላሉ፡፡

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time