Monday, February 20, 2017

‹‹የምርጫ ቦርድ አካሄድ የተለመደ በመሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም›› ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት

- ‹‹በፓርቲው አባላት መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም››  አቶ የሺዋስ አሰፋ
ላለፉት አራት ወራት ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ ሕጋዊ መሪ (ሊቀመንበር) እኔ ነኝ እኔ ነኝ›› በማለት ሲወዛገቡ በከረሙት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትና አቶ የሺዋስ አሰፋ ላይ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የካቲት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ውሳኔውን አሳወቀ፡፡
ቦርዱ ውሳኔውን ያስታወቀው የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 10(6)ን በመጥቀስ፣ እነ አቶ የሺዋስ አሰፋ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን በኩል፣ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት ምርጫ ማካሄዱንና አቶ የሺዋስን ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡን ያሳወቀበትን ሪፖርት መርምሮ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሰው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ እንደሚያስረዳው፣ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጣም ብሎ ካመነ፣ ብሔራዊ ምክር ቤቱ የመተማመኛ ድምፅ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን ብሔራዊ ምክር ቤቱ የመተማመኛ ድምፅ ከነፈገው፣ በኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን በኩል አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት ችግሩ እንዲፈታ ማድረግ እንደሚችል ያብራራል፡፡ በመሆኑም ቦርዱ እነ አቶ የሺዋስ ያደረጉት የምርጫ ሒደትን ሲመረምር፣ በሕጉና በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት መፈጸማቸውን በማረጋገጥ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ፣ በቦርዱ ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን፣ በቦርዱ ጸሐፊና የጽሕፈት ቤቱ ዋና ኃላፊ በአቶ ነጋ ዱፊሳ ፊርማ ወጪ የተደረገው ደብዳቤ ያሳያል፡፡
ምርጫ ወይም ጠቅላላ ጉባዔው የተደረገው ኮረም ሳይሟላ፣ ታዛቢዎች በሌሉበትና የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ተጥሶ መሆኑን በመጥቀስ የፓርቲው ሕጋዊ ሊቀመንበር መሆናቸውን በመግለጽ ሲከራከሩ ስለነበሩት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ቦርዱ በውሳኔው ላይ ያለው ነገር የለም፡፡
ቦርዱ በውሳኔው እሳቸውን አስመልክቶ ምንም አለማለቱን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት እንደተናገሩት፣ የምርጫ ቦርድ አካሄድ የተለመደ ነው፡፡ ‹‹አንድና ሁለት በመቶ ያህል ተስፋ ያደረግነው ሕዝቡን አስበው እውነተኛ ውሳኔ ይሰጣል የሚል ነበር፡፡ በመሆኑም የሚያስደንቅ አይደለም፡፡ እኛ የመጀመሪያ ሳንሆን በቅንጀት፣ በኦብኮ፣ በአንድነትና በመኢአድ ላይ የተፈጸመው በእኛም ላይ በመድረሱ አያስገርመንም፤›› ብለዋል፡፡
የመሠረቱት ፓርቲ እንደ ሌሎቹ ፓርቲዎች በሁለትና በሦስት አባላት መቀለጃ ሆኖ እንዳይቀጥል በሕግ ወይም ጠቅላላ ጉባዔው በሚወስነው ሁኔታ ለመታገል፣ የካቲት 11 እና 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚያደርጉት ስብሰባ ለሕዝብ እንደሚያሳውቁ አስረድተዋል፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ውሳኔ ተከትሎ ሰማያዊ ፓርቲ ዓርብ የካቲት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ 15 ቀናት በማይፈጅ የውሳኔ ሐሳብ ከአራት ወራት በላይ ቦርዱ ሳያሳውቅ በመቅረቱ አላስፈላጊ ውጣ ውረዶች መከሰታቸውን አዲሱ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ ተናግረዋል፡፡ ቦርዱ ዘግይቶም ቢሆን የሰጠው ውሳኔ ሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንቡንና የፓርቲዎች የምርጫ ሕግን በማክበር የሚሠራ መሆኑን ያረጋገጠ በመሆኑ፣ ‹‹የቀድሞ አመራሮችና አንዳንድ አባላት እየፈጠሩት በነበረው ሁከት ግራ ለተጋቡ ደጋፊዎቻችን ጥሩ ምላሽ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በፓርቲው ውስጥ መከፋፈል ስለነበር አባላትና ደጋፊዎች ግራ ተጋብተው መክረማቸውንና በፓርቲው ህልውና ላይ መተማመኛ ስለመኖሩ የተጠየቁት አቶ የሺዋስ፣ በፓርቲው ውስጥ መከፋፈል ያለ ለማስመሰል መሞከሩን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን አራቱም አካላት ማለትም ጠቅላላ ጉባዔው፣ ብሔራዊ ምክር ቤቱ፣ ሥራ አስፈጻሚውና የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽኑ በሙሉ እንዳሉ መሆናቸውን አክለዋል፡፡  
በሁሉም ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ በፓርቲ አባላት መካከል ምንም ዓይነት ክፍተትም ሆነ ልዩነት እንደሌለ አቶ የሺዋስ ገልጸዋል፡፡
ሌላው አቶ የሺዋስ የተናገሩት በገዢው ፓርቲና 22 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያደረጉትን ድርድር በሚመለከት ነው፡፡
በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንና የኅብረተሰብ ክፍሎች ‹‹ውይይትና ክርክር›› እየተደረገ እንደሆነ የሚናገሩት ስህተት መሆኑን የገለጹት አቶ የሺዋስ፣ ኢሕአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁን እየተዘጋጁ ያሉት ‹‹ድርድር›› ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ውይይት የሚዲያ ተግባር ሲሆን፣ ክርክር ደግሞ በምርጫ ወቅት የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ‹‹በእርግጥ ድርድር በሁለት ወገኖች መካከል የሚደረግ ቢሆንም እኛ ግን 22 ሆነን ጀምረነዋል፤›› ብለዋል፡፡
ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል ድርድር ተደርጎ እንደነበር ያስታወሱት አቶ የሺዋስ፣ አንድም ጊዜ የተገኘ ውጤት እንደሌለና አሁንም የተለየ ውጤት ይገኛል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
ኢሕአዴግን ሁሉም ፓርቲዎች ለድርድር ያልጠየቁበት ጊዜ እንዳልነበርና ምንም ምላሽ ሰጥቶ እንደማያውቅ ያስታወሱት አቶ የሺዋስ፣ የሕዝብ ጥያቄ አይሎ ሲነሳ ግን በሩን መክፈቱን አስረድተዋል፡፡ የመደራደርን ሐሳብ በቅድሚያ ያነሱት የአገሪቱን ሁኔታ የተመለከቱ አቅጣጫው ያስፈራቸው የውጭና የአገር ውስጥ ሽማግሌዎች ሆነው ሳለ፣ ኢሕአዴግ ግን ሐሳቡን ራሱ እንዳመነጨው በማድረግ ‹‹እንደራደር›› ማለቱ ተገቢ አለመሆኑንና ዕውቅናውን ለአገር ሽማግሌዎች መስጠት እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡ ኢሕአዴግ እንደ አንድ ፓርቲ መደራደር እንጂ ሰብሳቢ፣ ታዛቢም ሆነ አደራዳሪ ሊሆን እንደማይችልም አክለዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ እውነተኛ ድርድር ለማድረግና ሕዝቡ በድርድሩ እምነት እንዲያድርበት በቅድሚያ የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን መፍታት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት፣ ድርድሩን የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል ያሉ ወገኖች ሁሉ እንዲሳተፉ ክፍት ማድረግና ለግልም ሆነ ለሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ክፍት መሆን እንዳለበት እምነቱ መሆኑን እንደገለጸ አቶ የሺዋስ አብራርተዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲን ያህል አባላት የታሰሩበት አንድም ተቃዋሚ ፓርቲ እንደሌለም ገልጸው፣ ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ሊፈቱ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሁሉም ፓርቲዎች ኢሕአዴግን ጨምሮ የሕዝብን ጥያቄ በሚመልስ መንገድ ድርድር ማድረግ እንዳለባቸው ያስታወቁት አቶ የሺዋስ ሕዝቦች ባነሱት ጥያቄ ምክንያት የሞቱ፣ የተፈናቀሉ፣ ወጥተው የቀሩ፣ የታሰሩ ለምሳሌ ዶ/ር መራራ ጉዲና፣ ሁለት ጋዜጠኞች ኤልያስ ገብሩና አናንያ ሶሪ ሌሎችም መፈታት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ድርድሩ ሙሉ የሚሆነውም ይኼ በተግባር ከተፈተጸመ እንደሆነም አክለዋል፡፡
አሁን ገና ድርድር እንዳልተጀመረና በቀረቡት አጀንዳዎችም ላይ መስማማት እንዳልተቻለ የገለጹት አቶ የሺዋስ፣ አደራዳሪ ማን ይሁን? ታዛቢ ማን ይሁን? የአጀንዳዎች ቅደም ተከተል እንዴት ይሁን? እና ድርድሩ ለየትኛው ሚዲያ ክፍት ይሁን? የሚለው ጥያቄ የካቲት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ምላሽ ሊያገኝ ባለመቻሉ እሳቸውን ጨምሮ ሰባት አባላት ያሉበት ኮሚቴ ተመርጦ፣ የተጠጋጋ ሐሳብ እንዲያቀርብ ለየካቲት 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ መያዙን አሳውቀዋል፡፡
ውጤታማ ድርድር ለማድረግና የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት የሕዝብ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችና በተቃውሞ ጎራ በያለበት ተሠልፈው የሚገኙ አካላትንና የመንግሥትን ፈቃደኝነት ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን አቶ የሺዋስ አስረድተዋል፡፡ Read more here

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time