ላለፉት 10 ቀናት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ ያለበትን ባለማወቅ በጭንቀት የሠነበቱት ቤተሰቦቹ፤ ትናንት ለጥቂት ደቂቃዎች በዝዋይ ማረሚያ ቤት ያገኙት ሲሆን ማረሚያ ቤቱ ‹‹ጋዜጠኛው ህግና ደንብ በመጣሱ ጠያቂ እንዳያገኝ ታግዷል›› ብሏል፡፡
‹‹የፍትህ›› ጋዜጣ የ‹‹ፋክት›› እና የ‹‹አዲስ ታይምስ›› መፅሄቶች አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ ደሣለኝ በተለያዩ ህትመቶች ላይ ባሠፈራቸው ፅሁፎች ምክንያት የተፈረደበትን የ3 ዓመት እስራት በዝዋይ ማረሚያ ቤት እያገባደደ የሚገኝ ሲሆን ላለፉት 10 ቀናት ቤተሰቦቹ ሊጠይቁት ወደ ታሰረበት ማረሚያ ቤት ቢመላለሱም እንደ ወትሮው ሊያገኙት እንዳልቻሉ በመግለፅ ሲያማርሩ ሰንብተዋል፡፡
ወላጅ እናቱም ልጃቸው የት እንዳለ ባለማወቃቸው በጭንቀት ላይ መሠንበታቸውን ለአዲስ አድማስ የገለፁት ቤተሰቦቹ ትናንት ጠዋት ከ10 ቀናት ፍለጋ በኋላ ታናሽ ወንድሙ አላምረው ደሳለኝ በዝዋይ ማረሚያ ቤት አግኝቶት ለ3 ደቂቃ ብቻ እንዲያወራው እንደተፈቀደለት አብራርቷል፡፡
ከዝዋይ ማረሚያ ቤት በተጨማሪ በሌሎች ማረሚያ ቤቶች ጋዜጠኛውን ሲፈልጉት እንደነበር የሚገልፁት ቤተሰቦቹ፤ በሄዱበት ሁሉ በቂ መረጃ ሣያገኙ ሲመላለሱ መክረማቸውን ይናገራሉ፡፡
በጉዳዩ ላይ ለአዲስ አድማስ ማብራሪያ የሠጡት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ መሃመድ ሠኢድ፤ ጋዜጠኛው ቢዲሲፒሊን ቅጣት ምክንያት ከእሁድ በስተቀር ለ15 ቀናት ጠያቂ እንደማያገኘው ለቤተሰቦቹ ተነግሯቸዋል ብለዋል፡፡
ታናሽ ወንድሙ አላምረው በበኩሉ ‹‹ ማንም እንዲህ አይነት መረጃ አልነገረንም፤ ቢነገረን ኖሮ ለምን በፍለጋ እንንከራተታለን፡፡ ሲል ቤተሰቡ መረጃ እንዳልነበረው አስረድቷል
‹‹ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ፤ ባለፉት 10 ቀናት ለምንድን ነው ቤተሰቦቹን እንዳያገኝ የተደረገው›› ስንል የጠይቅናቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ መሃመድ ሲመልሱ፤ ‹‹ከማረሚያ ቤት አስተዳደር ባገኘሁት መረጃ መሰረት ጋዜጠኛው የማረሚያ ቤቱን ህግና ደንብ በመጣሱ ጠያቂ እንዳያገኝ ስለተወሰነበት ነው›› ብለዋል፡፡
ጋዜጠኛው ፈፅሟቸዋል የተባሉት የህግ ጥሠቶችን በተመለከተ የተጠየቁት ሃላፊው ‹‹ታራሚዎች ለመናፈስ ከወጡ በኋላ ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ሲጠየቁ፤ እሱ ቶሎ በሠአቱ አለመግባቱና ሌሎች ታራሚዎች ጭምር በሠዓቱ እንዳይመለሱ የማነሳሳትና የማሳመፅ ዝንባሌ ማሳየቱ፤ እንዲሁም የሌሎችን ታራሚዎች መብት በመጣሱ እንደሆነ ጠቁመው ከዚህ ጥፋቱ እንዲታረም በተደጋጋሚ ቢነገረውም ባለመታረሙ የተነሳ ቅጣቱ ሊተላለፍበት እንደቻለ አስረድተዋል፡፡
ትናንት ጠዋት በዝዋይ ማረሚያ ቤት ያገኘው ታናሽ ወንድሙ፤ ከሠላምታ ውጪ ብዙም መነጋገር እንዳልቻሉ ተናግሯል፡፡
No comments:
Post a Comment