- በባህር ዳር በአበባ እርሻዎችና በሌሎች ንብረቶች ውድመት ደርሷል
- የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አሳስቦኛል አለ
በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ደብረ ታቦር ማረሚያ ቤት በደረሰ ቃጠሎ በእስረኞች ላይ ጉዳት ደረሰ፡፡ የመከላከያ ሠራዊት እስረኞች እንዳያመልጡ ዙሪያውን ከቦ እንደነበርና ሊያመልጡ የነበሩ በርካታ እስረኞች መሞታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የእሳት አደጋው የተከሰተው ሐሙስ ነሐሴ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ መሆኑን የገለጹት ምንጮች፣ እስረኞቹ ከአደጋው ለማምለጥ መሞከራቸውን አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አካባቢውን በፍጥነት የከበበው የመከላከያ ሠራዊት እስረኞቹ እንዳያመልጡ ሲተኩስ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በእሳት አደጋው ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት በማረሚያ ቤቱ ላይ መድረሱንና ሊያመልጡ በነበሩ እስረኞች ላይም ጉዳት እንደደረሰ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ጎንደር ማረሚያ ቤቶች መምርያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር መንጌ ከበደ ቃጠሎው የተነሳው በኤሌክትሪክ መስመሮች መገናኘት መሆኑን ገልጸው፣ ሊያመልጡ የነበሩ ሁለት እስረኞች መገደላቸውንና ከእስረኞች ደግሞ ሁለት መቁሰላቸውን አስረድተዋል፡፡
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እየተስፋፋ የሚገኘው አመፅ፣ ከመንግሥት ጋር ቁርኝት አላቸው በተባሉ የግል ባለሀብቶች ንብረቶችና የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጉዳት እያደረሰ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ኢስመራልዳ (Esmeralda Farms) የተባለው በባህር ዳር የሚገኘው የኔዘርላንድ ባለሀብቶች የአበባ እርሻ በእሳት ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡
መቀመጫውን በኔዘርላንድ ያደረገው የአበባ ኩባንያው ዋና ቢሮ ባወጣው መግለጫ፣ በፖለቲካ ተቃውሞው ምክንያት በባህር ዳር የሚገኘው የአበባ እርሻ (ኮንዶር ፋርም) በእሳት ሙሉ በሙሉ መውደሙንና የኩባንያው አጠቃላይ ኢንቨስትመንት አሥር ሚሊዮን ዩሮ እንደሆነም አስታውሷል፡፡
በኢትዮጵያ ከሚገኘው ቢሮ ጋር መገናኘት አለመቻሉን የሚገልጸው መግለጫው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጃችን በቀውሱ ምክንያት ከአካባቢው በመልቀቃቸው መረጃዎችን ማግኘት አልተቻለም፤›› ብሏል፡፡
በመንግሥት ላይ የተነሳው ተቃውሞ በአካባቢው በሚገኙ የአበባ እርሻዎች ላይ ጉዳት ማድረስ መቀጠሉንና አሥር ያህል የአበባ እርሻዎች መቃጠላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ኮንዶር ፋርም የተባለው የአበባ እርሻ ሲቃጠል በአካባቢው የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች የነበሩ ቢሆንም፣ ጉዳቱን ያደረሱት ከፀጥታ ኃይሎች ቁጥር በብዛት የሚበልጡ በመሆናቸው ማዳን አለመቻሉን ኩባንያው ገልጿል፡፡
መጋዘኖች፣ የማቀዝቀዣ ክፍሎች፣ ትራክተሮች፣ የጭነት ተሽከርካሪዎች፣ ኮንቴይነሮችና ማሸጊያዎች በሙሉ በእሳት መውደማቸውን አስታውቋል፡፡
‹‹ሁሉም ጠፍቷል፡፡ የአሥር ሚሊዮን ዩሮ ኢንቨስትመንትና የረጅም ዓመታት ጥረት በአንድ ቀን ወድሟል፤›› ሲል በመግለጫው የደረሰውን ጉዳት አመልክቷል፡፡
ሌላው በየመኑ ባለሀብት መሐመድ አልካሚን የተቋቋመውና ከ500 በላይ ሠራተኞች የነበረው የአበባ እርሻ ይገኝበታል፡፡
ለባህር ዳር ከተማ የውኃ አቅርቦት ምንጭ የሆነው እንፍራንዝ ከተማ አካባቢ የሚገኘው የጥቁር ውኃ የውኃ ማጠራቀሚያ ጋንም ቃጠሎ ደርሶበታል፡፡ ይህም በከተማዋና በአካባቢዋ የውኃ አቅርቦት ላይ እጥረት እንደሚያስከትል እየተነገረ ነው፡፡
በተያያዘ ዜና በክልሉ ውስጥ ያለው ተቃውሞ እየተባባሰና በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች እያሳዩ ነው፡፡
በተለይም ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለማስቆም የፀጥታ ኃይሉ ሕግ እንዲያስከብር ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ከገለጹ ጀምሮ ሰዎች መሞታቸውን፣ የዘር ጥቃት ተፈጸመባቸው የተባሉ ደግሞ ወደ ጎረቤት አገር እየተሰደዱ መሆናቸው እየተገለጸ ነው፡፡
በተለይ በአምባ ጊዮርጊስ፣ በደብረ ታቦር፣ በመተማ ዮሐንስና በአጎራባች አካባቢዎች የሰው ሕይወት መጥፋቱን የሚገልጹ ቁጥሮችም እየጨመሩ ስለመውጣታቸው መረጃዎች እየጠቆሙ ይገኛል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት በኩል እስካሁን ምንም ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልተሰጠም፡፡
ሪፖርተር ከምንጮች ማረጋገጥ እንደቻለው በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የመከላከያ ሠራዊት እየገባ ሲሆን፣ የከባድ መሣሪያ ተሽከርካሪዎች መታየታቸውን ለማወቅ ችሏል፡፡
የአማራ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ በክልሉ ምዕራባዊ አካባቢዎች ሁከት መከሰቱን ተናግረዋል፡፡ በአንዳንድ ፀረ ሰላም ኃይሎች የተነዛ መረጃ ሕዝቡን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መምራቱንና በተፈጠረው ሁከትም በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ግጭት እያሳሰበው መምጣቱን ጠቁሞ፣ ሁሉም ወገኖች ከማንኛውም ግጭት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ዓርብ ነሐሴ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹በአገሪቱ የማኅበራዊ ፖለቲካው የሰው ሕይወት ማጥፋት፣ በንብረቶች ላይ ውድመት ማስከተል፣ እንዲሁም የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት እስከማቋረጥ ደረጃ መድረሱ አሳሳቢ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሊቀመንበሯ አክለው ሁሉም ወገኖች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ በማመዘን ለሕግ መከበር እንዲተጉ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብትና የዴሞክራሲ ባህልና መርሆችን እንዲያከብሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ Read more here
No comments:
Post a Comment