ከኅዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ነውጦች አሁንም እንደቀጠሉ ነው፡፡ ለዓመታት ምላሽ ያላገኙ የሕዝብ ጥያቄዎች በሚፈለገው መንገድ ባለመስተናገዳቸውና ለመፍትሔ የሚረዱ ውሳኔዎች በመዘግየታቸው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱን አደጋ ውስጥ የሚከቱ ሥጋቶች እየተፈጠሩ ነው፡፡ የመነጋገርና የመደማመጥ ልምድ በሌለበት የአገሪቱ የውጥረት ፖለቲካ ላይ ዜጎችን ለሞት፣ አገሪቱንም ለውድመት የሚዳርጉ ችግሮች ሲፈጠሩ ዝም ማለትም ሆነ በአያገባኝም ስሜት ችላ ማለት የበለጠ ጉዳት ያመጣል፡፡ ይልቁንም የሕዝብ ጥያቄዎች በአፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙና እስካሁን የሚታዩ የተበላሹ አሠራሮች ተስተካክለው አገሪቱ ከገባችበት አረንቋ እንድትወጣ መፍትሔ መፈለግ ይጠቅማል፡፡ አገሪቱን የሚያስተዳድረው መንግሥትም ሆነ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች በሙሉ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩል ተጠቃሚነትና ለአገር ህልውና የማይጠቅሙ ነገሮች ተወግደው፣ ሁሉንም የሚያስማማ አማካይ እንዲፈጠር ያላሰለሰ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡ አሁን የተያዘው ሁኔታ ግን አደገኛ ነው፡፡
መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ የዜጎችንም ደኅንነት መጠበቅ ግዴታው ነው፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎችን በአግባቡ አስተናግዶ ምላሽ የመስጠት ኃላፊነትም የእሱ ነው፡፡ ሕግ የማስከበር ተግባሩ ተቃውሞን በማዳፈን በዜጎች ሕይወትና አካል ላይ አደጋ መፍጠር የለበትም፡፡ ሕግ በማስከበር ስም ከመጠን በላይ ኃይል በመጠቀም የሚፈጸሙ ግድያዎችና በአካል ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ድርጊቶች የበለጠ ነውጥና ግጭት ከመቀስቀስ በስተቀር ጥቅም የላቸውም፡፡ ሕግና ሥርዓት መከበር ያለበት ሕዝብን አደጋ ውስጥ ሳይከት ነው፡፡ ይልቁንም አመፁ በስፋት በሚታይባቸው ሥፍራዎች ሕዝቡ ምን እንደሚፈልግ በሚገባ ተረድቶ የሚያረካ ምላሽ ለመስጠት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ በፍጥነት ተነድፎ ወደ ሥራ መግባት ይገባል፡፡ የውጭ ኃይሎችም ሆኑ ፀረ ሰላም የሚባሉት ኃይሎች የሕዝቡን ጥያቄ ነጥቀው እጃቸው ከመንግሥት በላይ ረዝሞ ከሆነም የማስተካከል ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ የሕዝቡ ጥያቄዎች በአንድ በኩል ትክክል ናቸው እየተባለ በሌላ በኩል መፍትሔው ኃይል ሲሆን ያደናግራል፡፡ ለተሳሳተ ዕርምጃ ከመዳረግ አልፎ ከሕዝብ ጋርም ያጣላል፡፡ መንግሥት የቤት ሥራውን ሳያጠናቅቅና ውስጡን በሚገባ ሳይፈትሽ ጣቱን ወደ ውጭ ሲቀስርም መፋጠጡ ይቀጥላል፡፡ ለአገሪቱም አይበጅም፡፡ መንግሥት ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ዕርምጃዎች ራሱን ያዘጋጅ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ከተለያዩ አደረጃጀቶች ከመጡ ወጣቶች ጋር ተወያይተዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት የተነሱ መሠረታዊ ጉዳዮች ቢኖሩም፣ ከአደረጃጀቶች በተሻለ ሞጋች ጥያቄዎችን ሊያቀርቡ የሚችሉ ወጣቶች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖር ነበረባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ በተጠራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ስብሰባ ላይ፣ በአደረጃጀቶች ላይ ብቻ መንጠልጠል የሕዝብን ተሰሚነት እንዳሳጣ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ከአደረጃጀት ጋር ብቻ መነጋገር አሰልቺ መሆኑንና ሕዝቡም አላዳምጥም ማለቱን በግልጽ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ በአገሪቱ በተከሰተው ዙሪያ ገባ ችግር ላይ በነፃነት የውይይት መድረክ መኖር የሚገባው፣ ችግሮቹን በሚገባ አፍረጥርጦ መፍትሔ ለማምጣት የሚረዱ ነጥቦችን ለማግኘት ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት ለመነጋገርና ለመደማመጥ የሚረዱዋቸው በነፃነት የሚደረጉ ውይይቶች ብቻ ናቸው፡፡ ሕዝብ በትክክል ምን እንደሚፈልግና የሙቀት መጠኑን ማወቅ የሚቻለው በነፃነት በሚደረጉ ውይይቶች ብቻ ነው ሲባል፣ ለመፍትሔ የሚረዱ ግብዓቶችም በስፋት ይገኛሉ ማለት ነው፡፡ አገርን ከችግር ውስጥ ማውጣት የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው፡፡
መንግሥት ተቀበለውም አልተቀበለውም አገሪቱን ወደ አደገኛ ሁኔታ የሚከቱ ሥጋቶች በስፋት እየታዩ ነው፡፡ ሕዝቡ ውስጥ ያለው ጭንቀትና ግራ መጋባት ይህንን የተጋረጠ ሥጋት በግልጽ ያስተጋባል፡፡ አገሪቱ በፅኑ መሠረት ላይ በመገንባቷ የመፈራረስና የመበታተን ሥጋት እንደሌለ መንግሥት ቢወተውትም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ ብሔርንና ማንነትን የተንተራሱ ቅስቀሳዎችና የመሠረተ ልማት ውድመቶች መጪውን ጊዜ አስፈሪ እያደረጉት ነው፡፡ የተነሱት የሕዝብ ጥያቄዎች አቅጣጫቸውን እየሳቱ ለዜጎች ሕልፈተ ሕይወት፣ አካል ጉዳትና ንብረት ውድመት መባባስ ምክንያት እየሆኑ በሄዱ መጠን አገር ለማፍረስ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፈታት የነበረባቸው ችግሮች የበለጠ ሞትና ጉዳት ሲያስከትሉ ጉዞው ወደማያበራ ግጭት ይሆናል፡፡ አገሪቱን ከእንዲህ ዓይነቱ አደገኛ ቀውስ ውስጥ ማውጣትና ሁሉንም ወገን የሚያስማማ መፍትሔ መፈለግ የግድ ነው፡፡ ኃይል መፍትሔ አይሆንም፡፡ አገሪቱን ከመፍረስና ከመበታተን መታደግ የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡
በሌላ በኩል ከመንግሥት ጋር ጉዳይ አለን የሚሉ ወገኖች ሊያጤኑት የሚገባ አንድ መሠረታዊ ነገር አለ፡፡ ለዴሞክራሲያዊና ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና ለማኅበራዊ ፍትሕ ትግል የሚደረገው አገር በማውደም አይደለም፡፡ ሕዝብን የሚያሸብሩ ሥጋቶች በመፍጠርም አይደለም፡፡ በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ዴሞክራሲንና ሰብዓዊነትን የሚንዱ ቅስቀሳዎችን ማካሄድ ለአገር አይጠቅምም፡፡ የግለሰቦችንና የቡድኖችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመዳፈር የሚካሄዱ ቅስቀሳዎች ፈራቸውን የለቀቁ ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ሆነ በእኩልነት ላይ የሚመሠረት ኅብረተሰብ ለመገንባት አይረዱም፡፡ በተቃራኒው የአገርን ህልውና የሚያፈርሱና ሕዝብን እርስ በርሱ የሚያናክሱ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ የግለሰቦችን የመሳሳት መብት ከሚያከብሩ ዴሞክራሲያዊ መርሆች ጋር የሚጋጩ አደገኛ ድርጊቶች ናቸው፡፡ በተለያዩ ሥፍራዎች ከሰው ሕይወት በተጨማሪ፣ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ያለውም የቅስቀሳው ጡዘት እየፈጠረው ባለው ግለት ነው፡፡ አገሪቱን ወደ ባሰ ድህነት አዘቅት የሚከቱና የሕዝቡን ተስፋ የሚቀለብሱ ውድመቶችን ማለም ጤነኝነት አይደለም፡፡ ለአገርም ሆነ ለሕዝቡ አይበጅም፡፡
ሕዝብ ጥያቄ አንስቷል፡፡ የመደመጥ መብት አለው፡፡ ሕዝብ ዴሞክራሲ ያስፈልገዋል፡፡ ሰብዓዊ መብቱ ሊከበርለት ይገባል፡፡ በፍትሕ መዳኘት ይኖርበታል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሊኖረው ይገባል፡፡ በአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ በሚወስኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መሳተፍ አለበት፡፡ በገዛ አገሩ ጉዳይ ባለቤት እንጂ ባይተዋር መሆን የለበትም፡፡ በነፃና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ መሪዎቹን መምረጥ አለበት፡፡ በአገሪቱ የሥልጣን የመጨረሻው አካል ሕዝብ መሆኑ መተማመን ላይ ሊደረስ ይገባል፡፡ ይህንን ዓይነቱን የሠለጠነ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ በመከተል አገሪቱን ለመገንባት የሚያስፈልገው በጥላቻና በክፉ መንፈስ የታጠረ ሳይሆን፣ ለዴሞክራሲና ለነፃነት የሚታገል ብሩህ አመለካከት ብቻ ነው፡፡ የሕዝብን መሠረታዊ የመብት ጥያቄዎችን ማፈንም ሆነ፣ በጥያቄዎቹ ተከልሎ አገርን ማተራመስ ተቀባይነት የለውም፡፡ አገሪቱና ሕዝቧም ይህንን ዓይነቱን ድርጊት ለመቀበል ዝግጁ አይደሉም፡፡ ለዚህ ትውልድ በመከባበር ላይ የተመሠረተ አንድነት እንጂ በጥላቻ ላይ የተመሠረተ መጠፋፋት ሊደገስለት አይገባም፡፡
በአጠቃላይ አገሪቱ ያለችበት አጣብቂኝ ከመፍትሔ ይልቅ ሌላ ችግር ለማስተናገድ ይከብደዋል፡፡ የመፍትሔ ሐሳቦችን ሳይሆን የጥፋት መንገዶችን ለማስተናገድ መሞከር አገሪቷንም ሆነ ሕዝቧን የማይወጡበት አረንቋ ውስጥ ይከታል፡፡ አገሪቱን ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ለመታደግ የሚበጀው ብሔራዊ ውይይት ብቻ ነው፡፡ ለግማሽ ክፍል ዘመን ያህል የዘለቀው የተበላሸ የፖለቲካ ምኅዳር ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ አገሪቱን የማትወጣው አደጋ ውስጥ እየከተተ ነው፡፡ ከፖለቲካ ሥልጣን በላይ የአገሪቱ ህልውና አደጋ ውስጥ ሲገባ፣ ነዳጅ እያርከፈከፉ የበለጠ ለማባባስ መሞከር የእነ ሶሪያን ዓይነት ዕልቂት፣ ስደትና ውድመት መጋበዝ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በሠለጠነ መንገድ መነጋገር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ከሥልጣን በላይ ለአገርና ለሕዝብ ሲታሰብ ብቻ ነው፡፡ ከማናቸውም ዓይነት የኃይል ተግባር በመቆጠብ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትና መፍትሔ በማፍለቅ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው አገሪቱን ከጥፋት መታደግ የወቅቱ ጥያቄ የሚሆነው! Read more here
No comments:
Post a Comment