በነገረ አስተሳሰብ ወይም በአስተሳሰብ ሕግ (ሎጂክ) ትምህርት ላይ አንድ የማስታውሰው ምሳሌ አለ፤‹‹ሚስትህን መደብደብ ትተሃል ወይ?›› የሚል ጥያቄ ነው፤ ጥያቄው የሚነሣው ጠያቂው አውቃለሁ ብሎ ከያዘው እውቀት ወይም እምነት ነው፤ ስለዚህም ጠያቂው የሚፈልገው ጥያቄ ለማስተላለፍና መልስ ለማግኘት አይደለም፤ ጠያቂው የሚፈልገው በጥያቄ መልክ የራሱን ‹‹እውቀት›› ወይም እምነት ለተጠያቂው ለማስተላለፍና ተጠያቂውን የጠያቂው ደቀ መዝሙር ለማድረግ ነው፡፡
ሚስትህን መደብደብ ትተሃል ወይ? መልስ የሌለው ጥያቄ ነው፤ ‹‹አዎ›› የሚል መልስ፣ ሰውዬው ሚስቱን ሲደበድብ እንደነበረ አመነ ማለት ነው፤ ‹‹አልተውሁም›› ከአለ በራሱ ላይ መሰከረ፤ ሁለቱም መልሶች ተጠያቂውን የሚያስወነጅሉ ስለሆኑ መልስ አይደሉም፤ ከዚያም በላይ ጥያቄው ትክክል አይደለም፤ የማይረባ መጥፎ ጥያቄ ነው፡፡
‹‹ወልቃይት የማን ነው?›› የሚለው ጥያቄ ትክክል አይደለም፤ የማይረባና መጥፎ ጥያቄ ነው፤ ጠያቂው የሚፈልገው መልስ የአማራ ነው፤ የጎንደር ነው፤ የትግሬ አይደለም፤ የሚል ነው፤ ነገር የሚገባው ተጠያቂ፣ ጥያቄውን ጠያቂው በፈለገው መልክ አይመልስለትም፤ ሊመልስለትም አይገባም፡፡ ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው የሚል መልስ አይፈለግም፤ የማይፈለግበትም ምክንያት ‹‹ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው፤›› ማለት ወልቃይትን ከጎሠኛነት አጥር ስለሚያወጣ ነው፤ የትግራይ አይደለም፤ የአማራ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ነው፤ አሁን ትግራይና አማራ የኢትዮጵያ ናቸው፤ ይህ ከተባለ በኋላ ወልቃይት የትግራይ ነው? ወይስ የአማራ? የሚለውን ጥያቄ ማንሣት የጎሠኛነት ጥያቄ ነው፤ የኢትዮጵያዊነት ጥያቄ አይደለም፤ ጥያቄው የማይረባ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው፤ ሁለተኛው ምክንያት የጎሠኛ ጥያቄ በመሆኑ የወያኔን የጎሠኛ መመሪያ የሚያከብር መሆኑ ነው፡፡
ትልቁና መሠረታዊው ጥያቄ በአማራ ክልል ስር የነበረው ወልቃይት በወያኔ አገዛዝ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱ ነው፤ እዚህ ላይ ጥያቄው የወልቃይት ወረዳ ወይም አውራጃ ነው፤ በውስጡ የሚኖሩት ሰዎች የጎሣ ዓይነት ወይም የጎሣ ስብጥር አይደለም፤ የፈለገውን ዓይነት አንድ ጎሣ ወይም የብዙ የጎሣ ስብጥር ሊኖርበት ይችላል፤ ክርክሩ መሆን ያለበት የወልቃይት አውራጃ ከጎንደር ክልል ወጥቶ ወደ ትግራይ የገባበት መንገድ ትክክል አይደለም፤ የአስተዳደር ለውጡ የተፈጸመው የፌዴራል መዋቅሩን ሥርዓት በጣሰ መንገድ አንዱ ክልል (ትግራይ) በሌላው ክልል ላይ የጉልበተኛነት ወረራ አካሂዷል ነው፤ ይህ ወረራ ሕጋዊ አይደለም፤ ይህ ወረራ ሊቀለበስ ይገባል፤ዋናው መቋጠሪያ ይኸው ነው፡፡
ግን ጉዳዩን የጀመርነው ከመሀሉ ነው፤ ሲጀመር ወያኔ ከኦሮሞ ቡድኖች ውስጥ ኦነግን መረጠና አማርኛ ተናጋሪውን አለ እያለ እንደሌለ ቆጠረው፤ በዚያን ጊዜ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎቹም ኢ-ፍትሐዊነቱን አልተናገሩም፤ ዋና የፖሊቲካ ጉዳይ አድርገው አላነሱትም፤ ለምን? እነሱ በሎሌነት በመመረጣቸው በደስታ ተውጠው ስለነበረ፣ጌቶቻቸውን ለማስቀየም ፍላጎት አልነበራቸውም፤ ግን ወያኔ በእጁ ያሉትን ምርኮኞች ከአደራጀ በኋላ ኦነግ ተባረረና በኦሕዴድ ተተካ፤ የኦነግ መሪዎች አገር ውስጥ ሆነው ለመታገል የሚያስከፍለውን ዋጋ ላለመክፈል በአሜሪካና በአውሮፓ ተቀምጠው በስልክ ‹‹ትግሉን›› መምራት መረጡ፡፡ ወያኔ አነግን በብዙ መንገድ ተጠቅሞበታል፤ አንደኛና ዋናው፡- አማርኛ ተናጋሪውንና ኦሮምኛ ተናጋሪውን ለመለያየትና በቅራኔ ለማጋጠም፣ ሁለተኛ፡- የኦሮሞ መሪዎች ነን የሚሉ ሁሉ ለወያኔ ትሑት አገልጋይ ከመሆን ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው አረጋገጠላቸው፤ኦነግንና እስላማዊ ኦነግን አፋጅቶ በኦሕዴድ አጋዥነት ሁለቱንም ከትግል መድረኩ አስወጣቸው፡፡
አለ ተብሎ እንደሌለ የተቆጠረው አማርኛ ተናጋሪው፤ በእነ ታምራት ላይኔ፣ በእነ በረከት ስምዖን፣ በእነ ህላዌ ዮሴፍ፣ በእነ ተፈራ ዋልዋ፣ በእነ (ሁሉም ያለጥርጥር አማርኛ ተናጋሪዎች ናቸው፤ ነገር ግን ከየት ከየት እንደበቀሉ አጠራጣሪ ነው፤) ተወከለ፤ ከጎንደርም ይሁን ከጎጃም፣ ከወሎም ይሁን ከሸዋ የእነዚህን ሰዎች ውክልና የተቃወመ የለም፤ እንዲያውም ለአሽከርነቱ ውድድር ነበር፡፡
በሁለቱ ድርጅቶች -- በብአዴንና በኦሕዴድ -- አማካይነት ወያኔ ወደ ሰባ በመቶ የሚጠጋውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በቁጥጥሩ ስር አደረገ፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን በአገር ውስጥ ያሉት የአማርኛ ተናጋሪውና የኦሮምኛ ተናጋሪው ወኪሎች ነን ባዮቹ፣ ለፍርፋሪ ሲፎካከሩና ሲነታረኩ፣ ወያኔ የራሱን ክልል በትምህርትና በልማት ለማሳደግ እየሞከረ ነበር፡፡
ለእኔ ፍሬ ነገሩ፣ አማርኛ ተናጋሪውም ሆነ ኦሮምኛ ተናጋሪው፣ ሃያ አምስት ዓመታት ሙሉ እየተፎካከሩ ወያኔን ከማገልገል ሌላ መብትና ሥልጣን ፈልገው አያውቁም፤ ስለዚህም ከማይናገር ከብቱን፣ ከማይራገጥ ወተቱን እንደተባለው፣ወያኔም በከብቱም በወተቱም ተጠቀመበት፡፡
(ነሐሴ 2008፤ ፌስቡክ ላይ ፖስት የተደረገ)
Source: Addis admas
No comments:
Post a Comment