Monday, May 27, 2013

ከሕይወት ያልተዛመደ የትምህርት ዓለም፡ በምሕረት አስቻለው

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ለዓመታት በዩኒቨርሲቲ በሚኖራቸው ቆይታ ዋናውና ቀዳሚው ትኩረታቸው ትምህርት ላይ ቢሆንም በብዙ መልኩ ስለሕይወት ብዙ ይማራሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ የተለያየ አመለካከትና እሴት ካላቸው ሌሎች ተማሪዎች ጋር በአንድ ጣሪያ ሥር መኖር፣ ማዕድ መጋራትን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች በተማሪዎች አመለካከት ላይ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ለውጥ እንደሚያመጣ ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተመርቀው የወጡም በማኅበረሰቡ ዘንድ በትምህርት ብቻ ሳይሆን በሕይወት ተሞክሯቸውም የበቁ ተደርገው ይታሰባሉ፡፡ በዕለት ተዕለት የሕይወት ውጣ ውረድ የሚያጋጥማቸውን ችግር አመዛዝነው በቀላሉ የሚፈቱ ሕይወት የቸረቻቸውን ዕድሎችም በብልጠትና በብቃት የሚጠቀሙ ስለመሆናቸው ብዙዎች ጥርጣሬ አይኖራቸውም፡፡ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹ልጆች ዩኒቨርሲቲ ገቡ ወይም ተመርቀው ወጡ ሲባል ተአምር የመጠበቅ ነገር አለ፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ ያወቁ የበቁ ሳይሆኑ ገና የሚማሩ ለማወቅ የሚተጉ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል፤›› በማለት ከቀለም ትምህርት ባሻገር የመማር ማስተማር ሥርዓቶች ተማሪዎች በሕይወት ዓለም ሊኖራቸው የሚገባውን የሕይወት ክህሎት እንዲያዳብሩ የሚያግዝ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በመቀጠልም በከፍተኛ ተቋማት የትምህርት አሰጣጥ ለተማሪዎች የሕይወት ክህሎቶች ማዳበር የተመቻቸ አለመሆኑን በማመን በዚህ ረገድ ለውጥ ለማምጣት በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን እንደ አንድ ዕርምጃ እንደሚመለከቱት ይናገራሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በማኅበረሰቡ የሚንፀባረቀው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምሩቃንንም በትምህርትም በሕይወት ክህሎትም የበቁ አድርጐ መመልከት የተሳሳተ አመለካከት እንደሆነ ታምናለች፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አምስተኛ ዓመት የሕግ ተማሪ የሆነችው ሳምራዊት ጌታነህ፡፡ ለእሷ በትምህርት መብቃት በሕይወት ክህሎትም ተመሳሳይ ደረጃ ላይ መገኘት ማለት አይደለም፡፡ በእሷ እይታ አብዛኛው ተማሪ ከትምህርቱ ውጭ ስለሌሎች የሕይወት ገጽታዎች በጣም ውስን ዕውቀት ያለው የሕይወት ክህሎቱም ያነሰ ነው፡፡ በምክንያትነት የምታስቀምጠው ደግሞ ምንም እንኳ የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ከቀለም ትምህርት ባሻገር ስለሕይወት ብዙ ሊማሩበት አመለካከቶችም ሊቀርጹበት የሚችል ቢሆንም፣ ተማሪዎች ሙሉ ጊዜና ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ ብቻ ለማድረግ መፈለጋቸውን ነው፡፡ ‹‹በቀለም ትምህርቱ በሕይወት ክህሎቱም ይህ ነው የሚባል ነገር ይዞ የሚወጣው ተማሪ በጣም ትንሽ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ትምህርት ላይ ብቻ መበርታትና ጥሩ ውጤት ማግኘት ብቻውን ለሕይወት ዓለም በቂ አይደለም፡፡ ተማሪው የሚኖርበትን ማኅበረሰብ መረዳትና ማወቅ አለበት፡፡ ማኅበረሰቡን ለማገዝ ለመርዳት ብቻም ሳይሆን ለራሱ የሕይወት ተሞክሮና ግንዛቤ ሲል፡፡ የሚታየው ነገር ግን ተማሪዎች ላልተዘጋጁለት የሕይወት ዓለም ተመርቀው ሲወጡ ነው››፡፡ ከአምስት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ በመነሳት ከትምህርት ውጭ በግቢ ውስጥ በሚካሄዱ የተለያዩ ክንውኖች ላይ ለመሳተፍ አብዛኛው ተማሪ ፈቃደኛ አይሆንም፡፡ የሚታሰበውና የሚታመነው ለነገ የተሳካ ሕይወት ዛሬ ላይ የተቻለውን ያህል ተግቶ ማንበብና ጥሩ ውጤት መያዝ ወሳኝ መሆኑ ነው፡፡ ከቀለም ዓለም ወደ ሕይወትና ሥራ ዓለም ሲመጣ የሚታየው ነገር ደግሞ የመጀመርያ፣ ሁለተኛ ዲግሪ ከዚያም በላይ መሄድ የቻሉ ሰዎች በሕይወት ክህሎት ማነስ ከሰዎች ጋር መግባባት ከመቸገር ጀምሮ በተለያዩ የማኅበራዊ ሕይወት ጉዳዮች ሲፈተኑና ሲወድቁ ይታያል፡፡ ራስን መግለጽ አለመቻል፣ ጓደኝነት እንዲሁም የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት መቸገር ሌላም ሌላም ብዙ ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ በሕይወት ክህሎት ማነስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንና ተማሪዎች እንደሚታሰበው ሳይሆን በተቃራኒው በእነዚህና እነዚህን መሰል የሕይወት ዓለም ፈተናዎች ይንገዳገዳሉ፡፡ ትኩረቱ መንገዳገደቸው ላይ ሳይሆን የእነሱን የትምህርት ዕድል ላገኙ ሰዎች በሚፈተኑበት ደረጃ መፈተናቸው በተመሳሳይ ደረጃ ችግሩን ለመፍታት ከመሞከር በዘለለ መሄድ አለመቻላቸው ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ምሩቃን በአብዛኛው ዕውቀታቸው በቀለም ትምህርት እንዲወሰን የሕይወት ክህሎታቸውም ዝቅተኛ የሆነው ለምንድን ነው? የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሥርዓተ ትምህርት ተማሪዎች ከቀለም ትምህርት ባሻገር የሕይወት ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ የሚያስችል ነው? የመምህራንስ የማስተማር ዘዴና አቀራረብ የተማሪዎች የሕይወት ክህሎት ማዳበርን ታሳቢ ያደረገ ነው? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች በርእሰ ጉዳዩ ዙሪያ ያጠነጥናሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቼንጅ ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ፍርዲሳ ጀቤሳ እንደሚሉት፣ በጥቅሉ መምህሩም ተማሪውም ያደገው ዝግ በሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ መሆኑ ከቀለም ትምህርት ባሻገር በዩኒቨርሲቲ ቆይታ የሕይወት ክህሎትን ማዳበር አለመቻል በመሠረታዊነት የሚቀመጥ ነገር ነው፡፡ በአገራችን የትምህርት ዓላማ ምንድን ነው? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ በአብዛኛው እንደሚታየው ቤተሰብ ልጁን ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚልከው ልጁ ተምሮ ዳቦ እንዲበላ ነው፡፡ የተማሪውም የመማር ዓላማ ተመሳሳይ ነው፡፡ ትምህርትን በሚመለከት ያለው ትልቁ አስተሳሰብ ይኼ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ በአገር ደረጃ ቢታይም የትምህርት ፋይዳ ድህነትን ማጥፋት ነው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ከቀለም ትምህርት ባሻገር ለተማሪዎች የሕይወት ክህሎት መዳበር የመምህራን ድርሻ ከፍተኛ ቢሆንም መምህራኑም ያለፉት በተመሳሳይ የመማር ማስተማር ሒደት ውስጥ በመሆኑ ከኮርሶች አልፈው መሄድ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም መምህራኑ ራሳቸው በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሕይወት ክህሎት አዳብረው አላለፉምና ‹‹ፕሮፌሰርነት ደረጃ የደረሱ ሰዎችም የተለያዩ የሕይወት ክህሎቶችን ሳያዳብሩ በቀጭን መንገድ ወደላይ የመውጣት ነገር ይታያል፤›› ይላሉ፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱም ቢሆን በተቻለ አቅም የሕይወት ክህሎትን ያማከለ መሆን እንዳለበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ መምህራንም በተመሳሳይ መንገድ ባለማለፋቸው የተማሪዎችን የወደፊት ሕይወት ወይም የሥራ ዓለም ታሳቢ አድርገው የሚንቀሳቀሱ አለመሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቆይታ ለተማሪዎች የሕይወት ክህሎቶች መዳበር የተማሪዎች ሚና ከፍተኛ ቢሆንም፣ የሥርዓተ ትምህርትና የማኅበረሰቡ ሚናም ድርሻ አለው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች አቅራቢያ የጫትና የመጠጥ ቤቶች መገኘት ለተማሪዎች ሕይወት መመሳቀል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ተማሪዎችም ከቀለም ውጭ በሌላ መንገድ ዕውቀት ለማግኘት በዙሪያቸው ካለው ሁኔታ ለመማር ካልፈቀዱና በቀጭን መስመር ላይ ብቻ ወደላይ ለመሄድ ከወሰኑ የሕይወት ክህሎት አይኖራቸውም አመለካከታቸውም ሰፊ አይሆንም፡፡ ‹‹መማር፣ መመረቅ አንድ ነገር ነው፡፡ ሕይወት ግን ከዚያ የሚያልፍ ብዙ አማራጮች ያሉበት ሰፊ ነገር ነው፤›› በማለት አመለካከትን አጥብቦ መጓዝ ለተማሪዎች አስቸጋሪ እንደሚሆን ይገልጻሉ፡፡ እንደ ሥርዓተ ትምህርት ባለሙያነታቸው ካስተዋሉት በመነሳት በአገራችን የትምህርት ሥርዓት ውስጥ አብዛኛው ተማሪ ፊደል ከመቁጠርና ከኮምፖዚሽን [ድርሰት] የሚያልፍ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ ዕውቀቱ ያነበቡትን ወደ ተግባር የመቀየር ደረጃ ላይ (አፕሊኬሽን)፣ ይኼ ነገር ምንድን ነው ብሎ የመጠየቅ (አናሊስስ)፣ የመጭመቅ (ሲንተሲስ) እና ግምገማ (ኢቫሉኤሽን) የዕውቀት ደረጃዎች ላይ የሚደርስ አይደለም፡፡ የቀለም ትምህርት ለሕይወት እውነተኛ ለውጥና ስኬት ትልቅ ሚና መጫወት የሚችለው ደግሞ ከፊደል መቁጠርና ከንባብ ማለፍ ሲቻል መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታ ለተማሪዎች ከቀለም ትምህርት ባሻገር የሕይወት ክህሎቶችን አዳብሮ አለመውጣት የተለያዩ ምክንያቶች በመኖራቸው በሌላ በኩል የመምህራንም በአብዛኛው በዚያ መልኩ ማለፍ ነገሩን አዙሪት ስለሚያደርገው ተማሪውም፣ መምህሩ፣ ቤተሰብና ማኅበረሰቡ ያገባኛል በሚል መንፈስ ሊፈታው የሚገባ ችግር እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ተማሪዎች እንዲሁ የሚሰጣቸውን የሚቀበሉበት ሳይሆን ለምንና? እንዴት? የሚሉ ጥያቄዎችን የሚያነሱ እንደሆኑ የሚያደርግ ሥርዓተ ትምህርት በዩኒቨርሲቲዎች ሊዘረጋ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time