ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በተለያዩ አካባቢዎች እየተደረገ ላለው ድጋፍ ያስተላለፉት የምስጋና መልእክት
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች ሆይ
ምስጋና ከሚቀበል ሰው ይልቅ ምስጋና የሚሰጥ ታላቅ ነው፡፡ ያለ ጥርጥር ይህንን እንረዳለን፡፡ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ በሀገራችን እየታየ ያለው የለውጥ ጭላንጭል፤ አሁን የሀገራችን ህዝብ እየሰጠን ካለው ወሰን አልባ ድጋፍ እና ፍቅር ጋር የሚወዳደር እንዳልሆነ ብንገነዘብም መንግስት ይሄንን ድጋፍ ፣ ፍቅር ፣ ክብር እና አለኝታነት ለተሰሩ ስራዎች እንደተሰጠ ምስጋና ብቻ ሳይሆን በቀጣይ እንሰራቸው ዘንድ ለሚገቡን በርካታ ስራዎች ተግባራዊነት የተላለፈ የአደራ መልእክት እንዲሁም የአጋርነት ማሳያ አድርጎ በመቁጠር ከምን ጊዜውም በላይ በፍጹም ቁርጠኝነት እና ትጋት ለማገልገል በጽናት ይሰራል፡፡
እስካሁን የታየው የለውጥ ወጋገንም ሆነ ወደፊት የምናስመዘግበው ድርብ- ድርብርብ አንፀባራቂ ድል ባለቤት ህዝብ እና ህዝብ ብቻ ነው፡፡ አሁን ከጀመርነው የፍቅር ፣ የይቅርታ፣የመደመር፣ የአንድነት እና እንደ ሀገር የመለወጥ ጉዞ ሊያናቅፈን የሚችል መሠናክል - ሊያናጥበን የሚችል ስጋትአይኖርም በሚል መንፈስ ተነስተን በጽናት እየተደመርን የምንገኘውም ህዝብ ታግሎ ያላሸነፈበት ምንም የትግል አውድ የፍልሚያ ግንባር እንደሌለ እና እንደማይኖርም ጭምር በውል ስለምንገነዘብ ነው፡፡
ከምስራቅ እስከ ምእራብ፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ ያላችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ከሰራነው ስራ እጅግ ለሚልቀው እና ትርጉም- አንድምታውም ፍጹም ለሚረቀው ወሰን አልባ ድጋፋችሁ እና ፍቅራችሁ በያላችሁበት ሆናችሁ እነሆ ምስጋናችን ይድረሳችሁ፡፡ የቸራችሁን ምስጋና የኛ ብቻ ሳይሆን የናንተም ድምር ውጤት ነውና እናንተ አመስጋኞቹ ዋናዎቹ ተመስጋኞች መሆናችሁን ለአፍታም ቢሆን አንዘነጋም፤መዘንጋትም አይቻለንም፡፡ እናም ተመስጋኞቹ አመስጋኞች የለገሳችሁንን አብሮነት በፍቅር - አደራ ያላችሁንን የነገ ትግል በክብር ተቀብለን ታላቂቱን ሀገር ወደ ቀድሞ እና ከዚያም ወደላቀ ታላቅነት ከፍታዋ ለመመለስ ቃል ስንገባላችሁ በታላቅ አክብሮት እና በፍጹም የእንሻገራለን ቁርጥ ስሜት ነው፡፡
ውዶቹ የጉራጌ ምድር ፈርጦች - የኢትዮጵያዊነት ማሳያ ጌጦች - ዘርማዎች፤ ቃላችንን ሰምታችሁ እና ለሰላማችን ዘብ ለመቆም ከኛ ውጪ ማንም ስላለመኖሩ በውይይት የደረስንበትን ድምዳሜ በመቀበል በይቅርታ ቀስተደመና ደምቃችሁ የጸብን ደመና ስለገፈፋችሁ የአክብሮት ምስጋናዬ ካላችሁበት ይድረሳችሁ፡፡ በሰራችሁት አኩሪ ገድል እኔም ሆንኩ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በእናንተ እንደኮራን የምገልጽላችሁ በታላቅ ደስታ ነው፡፡ በዚህ ፍጹም የመደመር ተግባራችሁም በገጠር ከተማችሁ- በሰፈር ቀኤያችሁ ሁሉ ሰላም እና ፍቅርን ያለመናወጥ እንደምትተክሉ ፊታችሁንም ወደሃገር ግንባታና ልማት በማዞር ተጨባጭ ውጤት እንደምታመጡ እምነቴ የጸና ነው፤ ላደረጋችሁት ኢትዮጵያዊ የይቅርታ፣ የፍቅር እና የሰላም ተምሳሌታዊ ተግባርም ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡
የደቡብ ክልል የሀገራችን የሕብረብሄራዊነት - ማሳያ አንድ ሰበዝ የደግነት እና የፍቅር ምሳሌ የሆናችሁት ሲዳማዎች በቱባ ባህላዊ መገለጫዎቻችሁ ውስጥ ጉዳዬ ተብሎ በማይፃፍ ጥቃቅን ምክንያቶች መነሻነት በአካባቢያችሁ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት እና ሁከት አስወግዳችሁ እንደ አኩሪ ባህላችሁ እና እሴታችሁ መክራችሁ እና ዘክራችሁ ጥላቻን ድል ስለነሳችሁ ያለኝን አክብሮት እና አድናቆት ስገልጽላችሁ በቀጣይም ይሄንኑ አጽንታችሁ በመያዝ እንደምትጓዙ በጽኑ በማመንም ጭምር ነው፡፡ ዛሬ ላይ ከአካባቢያችሁ ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙ የወላይታ ወንድም- እህቶቻችሁን፤ ወላጅ ልጆቻችሁን እንደገና ወደነበሩበት ለመመለስ ቤት በመስራት ላይ እንደሆናችሁ መረዳት የርምጃችሁን ቁርጠኝነት አመላካች ነው፡፡ አውቃለሁ፡፡ ይህ የተቀደሰ መልካም ተግባራችሁ በልጅ ልጆቻችሁ ውስጥ ይተከል እና አብዝቶም ይበቅል ዘንድ ስለሚገባው እና በዘመናት መካከልም በናንተ ምድር ለነገሰው ፍቅር ይበልጥ ጥንካሬ፣ ውበት እና ድምቀት እንደሚደርብለት እምነቴ የጸና ነው፡፡ ለወላይታ ወገኖቻችሁ መልሳችሁ የምትገነቡላቸው ቤት ሀገራችሁን በፍቅር የመገንባት ተምሳሌታዊ ውክልና አለውና በዚህ የኢትዮጵያዊነት ቅን ተግባራችሁ ወገኖቻችሁ ሁሉ እንደሚደሰቱ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ ሲዳማዎች እና የሲዳማዎችን በጎ ተግባር በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የደገፋችሁ ወገኖቼ በሙሉ ልባዊ ምስጋናዬ እና አድናቆቴ ከተለየ አክብሮት እና ፍቅር ጋር በያላችሁበት ይድረሳችሁ፤ እያልኩ በቀሪው ጊዜ ፊታችሁንም ወደሃገር ግንባታና ልማት በማዞር ተጨባጭ ውጤት እንደምታመጡ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
በሀገራችን ከተሞች እና በአካባቢያችሁ አደባባዮች ወጥታችሁ ከሚገባን በላይ ያከበራችሁን፣ የደገፋችሁን እና በቀጣይ ጉዟችንም የአብሮነታችሁን ማረጋገጫ ኪዳን የሰጣችሁን የሀገራችን ህዝቦች ለክብር ምስጋናችሁ የሚመጥን ምንም ስጦታ ባይኖርም ልባዊ ምስጋናችን ግን በፍቅር ይድረሳችሁ፡፡ ምስጋና ድጋፋችሁ የቀጣይ ትግላችን ሀይል ነውና ያስታጠቃችሁንን የመደመር እና የፍቅር ትጥቅ ታጥቀን ለዚህች ታላቅ ሀገር እድገት እና ብልጽግና አበክረን ለመስራት ከምንጊዜውም በላይ ዛሬ ዝግጁ መሆናችንን ስገልጽላችሁ በፍጹም ክብር ነው፡፡
በአዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኛችሁ የአዲስ አበባ እና የሌሎች አካባቢም ህዝቦች፤ በያላችሁበት ሆናችሁ በሀሳብ፣ በጸሎት እና በመደመር ከጎናችን የሆናችሁ ወገኖች፤ በተለይም በወቅቱ በተፈጠረው የእኩያን ድርጊት የተጎዳችሁ እና በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የአካል እና የስነልቦና ስብራት የደረሰባችሁ ወገኖች እናንተ በዚህች ሀገር የለውጥ እና የመደመር ሂደት ውስጥ የራሳችሁን ግሩም ጡብ ያኖራችሁ ጀግኖች ናችሁና ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሀገራዊ አንድነታችን እና ለለውጥ ግስጋሴያችን ድጋፍ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን የጥረት ልፋታችንም አካል ለመሆን ስትሉ ህይወታችሁን ያጣችሁ ወገኖቻችን እናንተ ለኛ የምንጊዜም ጀግኖቻችን ናችሁ፡፡ የናፈቃችኋትን እና እውን እንድትሆንም የተጋችሁላትን ሀገር በአንድነት በመገንባት አልፋችሁም እንኳን ህያው እንድትሆኑ አበክረን በመስራት በህልፈታችሁ ላይ ያበበች ሀገር እውን በማድረግ የምናረጋግጥ ቢሆንም ክብር እና ምስጋናችን በአጸደ ነፍስ እንዲደርሳችሁ በማሰብ እናመሰግናለን ስል ግን በተለየ የሠማዕት ክብር እና ፍቅር ነው፡፡
መላ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ ስላደረጋችሁልን እና ወደፊትም ስለምታደርጉልን ድጋፍ፣ ፍቅር እና አብሮነት ከልብ እናመሰግናለን፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ እና ተከብራ ለዘላለም ትኑር
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ
አመሰግናለሁ!
Monday, July 2, 2018
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በተለያዩ አካባቢዎች እየተደረገ ላለው ድጋፍ ያስተላለፉት የምስጋና መልእክት
Sunday, July 1, 2018
የኢፌዴሪ ም/ጠ/ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ም/ሊ/መንበር ጓድ ደመቀ መኮንን ዛሬ በባህር ዳሩ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ያደረጉት ሙሉ ንግግር
የኢፌዴሪ ም/ጠ/ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ም/ሊ/መንበር ጓድ ደመቀ መኮንን ዛሬ በባህር ዳሩ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ያደረጉት ሙሉ ንግግር
ውድ የባህርዳር ከተማ እና የአካባቢዋ ነዋሪዎች
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች
ክብራትና ክቡራን
በቅድሚያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ . . . በአካል በዚህ ታሪካዊ ሰልፍ ላይ ባይታደሙም፤ በመንፈስ ግን አብረውን እንደሆኑ በመግለጽ ለባህርዳር ከተማ እና የአካባቢዋ ነዋሪዎች የከበረ ሰላምታ እና መልካም የለውጥ ምኞታቸውን በክብር አስተላልፈዋል፡፡
ውድ የዚህ ታሪካዊ ፕሮግራም ታዳሚዎች
እነሆ ዛሬ! እንደዚህ በደመቀ አብሮነት እና ባሸበረቀው ህዝባዊ ሰልፍ በመካከላችሁ ተገኝቼ ይሄን ንግግር ሳደርግ የተሰማኝ ልባዊ ደስታ እና የፈጠረብኝን ውስጣዊ ፍሰሃ ምንኛ ትልቅ እንደሆነ እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው፡፡
ይህ ታሪካዊ ቀን ቀጣዩን ጊዜ የተሻለ እና ክልላችንን እና ሀገራችንን ተመራጭና ተወዳጅ፣ የሰላምና የልማት ምድር ለማድረግ ብሩህ ዕለት የወገገበት ነው፡፡ ለዚህ ዕለት ዕውን መሆን በየፈርጁ የታገሉ፣ የደሙና የቆሰሉ፣ ከዚያም አልፎ ክቡር ሕይወታቸውን የሰው በዚህ አደባባይ ክብርና ሞገስ ለእነሱ ይሁን፡፡ እናመሰግናለን፡፡
ባህርዳር የክልላችን መናገሻ ከተማ ብቻ ሳትሆን፤ በለሱ ቀንቷቸው ጎራ ያሉ የሃገራችን እና የሌሎች ዓለም ሰዎች በፍቅር የሚማረኩላት፤ ስለውበቷና ስለምቹነቷ ደጋግመው የሚመሰክሩላት፤ የሃገራችን ከተሞች ፈርጥ ነች፡፡
ባህርዳር - ጣናን ተንተርሳ፣ ጊዮንን እንደመቀነቷ አገልድማ ታላላቅ ጥበቦችን በማህፀኗ ያቀፈች ድንቅ ሃብታችን ነች፡፡
አሁን. . .አሁን! በሃገር አቀፍ ደረጃ የዘመናዊነትና የብልፅግና ማሳያ ምልክት ከሆኑ ውብ ከተሞች መካከል አንዷ ባህርዳራችን ነች፡፡
እንኳን በዚች ውብ ከተማ በሚካሄደው ደማቅ ህዝባዊ ሰልፍ ላይ በጋራ ለመታደም አበቃችሁ፤ አበቃን፡፡
ውድ የዚህ ታሪካዊ ፕሮግራም ታዳሚዎች
ይህ ትዕይንት፣ የለውጥ ጥማት፣ የዴሞክራሲና የሠላም ፍላጐት ብቻ አይደለም፡፡ ኃይልም ነው፡፡ ጉልበትም ነው፡፡ ሁሉንም ዕውን የሚያደርግ አቅም ነው፡፡ ዛሬ እዚህ ፊት ለፊታችሁ ቆሜ በአይበገሬነትና በተስፋ የሚደልቀው ልባችን ዓለት ሲያንቀጠቅጥ፣ ድህነትን ሲንጥ ይሠማኛል፡፡ ለዓለም ሁሉም ይሰማል፡፡
ይህ አስደማሚ የጥምረታችን ኃይል የትኛውንም መሰናክል ገርስሶ፣ እንቅፋቶችን ሁሉ አፍርሶ ድህነትና ኋላቀርነትን ታሪክ እንደሚያደርግ አልጠራጠርም፡፡ ይህ እንዳለላ ሙዳይ፣ እንደ ህብር ሙካሽ የተንቆጠቆጠ ውበታችን የኢትዮጵያዊነት ፈርጥ ሆንነ፤ ሕዝቦቿን በውበት ሠድረንና ደምረን ለሀገራችን ድምቀት እንደምንሆን ይሄው ያየን ሁሉ ይመሰክራል፡፡ አብረን ቆመን አንጀታችን እንደክራር፣ ልባችን እንደከበሮ ተዋህዶ እየፈጠረ ያለው ዜማ ልዩ ኀብረ ዝማሬ ነው፡፡ ለሁሉም የሚጥም፣ ሁሉም የሚሰማው፣ ሰሞቶ የሚያበቃው ብቻ ሳይሆን አብሮ የሚደመርበት የፍቅር ቅኝት ነው፡፡ ፍቅራችን ሁሉንም ያሸንፋል፡፡
የዛሬው የምስጋናና የድጋፍ ትዕይንት እያደር በየፈርጁ የሚገለጥ የአደራ ጥራዝ የብርታት ስንቅ ነው፡፡
አደራው የሁሉም፤ አቅሙም የጋራ ነው፡፡ ይህን ለውጥ ከዳር ለማድረስ ስንበረታ እንደዛሬው ተመሰጋግነን፣ ስንሰንፍ ተወቃቅሰን፣ ተግሳፃችሁን ሰምተን ልንታረምና ልናገለግላችሁ ቃል የምንገባበት መድረክም ነው፡፡
በዘመን ቅብብሎሽ አያቶቻችን እና አባቶቻችን . . . በአገር ፍቅር የነደደው ነፍስ፤ በነፃነት ጥማት የተሞላው መንፈስ፤ ለችግር የማይንበረከክ ነፃና ኩሩ ህዝብ፤ በፈተናዎች ፊት ፀንታ ሳትበገር የምትቆይ ሃገር አቆይተውናል፡፡
ገና ከጥንቱ! አገርና ህዝብ ሲደፈር "ከራስ በላይ ንፋስ!" የሚል አስተሳሰብን አሽቀንጥረው "ከራስ በላይ ሃገር!" መኖሩን በታላቅ ጀግንነት ወድቀው፤ ተዋድቀው ክብሯን የጠበቀች እና ነፃነቷን ያስጠበቀች ሃገር በአደራ አውርሰውናል፡፡
በቀደሙት የታፈረችውን ሃገር፤ በእኛ ደግሞ . . . የለውጥ ጉዟችን ፈተና ቢበዛውም ሃገራችን ከስኬት ማማ ላይ እንድትታይ በቁጭት እና በስስት ለውጥን በምኞት ሳይሆን በተግባር ለማምጣት የምንታትርበት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡
እነሆ ዛሬ! ያለማንም ቀስቃሽ እና ጎትጓች በገዛ ፍቃዳችን በዚህ ታላቅ ስቴዲየም የተገናኘነው በተጀመረው ሃገራዊ አዲስ የለውጥ ስሜት አጋርነታችንን ለመግለፅና ይኸው ለውጥ በክልላችን ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ባለቤትነታችንን ለማሳየት ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት በአገር ደረጃም ሆነ በክልላችን ለለውጥ መነሻ የሆኑ ስራዎች ተመዝግበዋል፡፡ ነገር ግን ከሚጠበቀው ለውጥ አኳያ የሰራነው ትንሽ፤ የወቃነው ደግሞ ዕፍኝ እንደማይሞላ እንገነዘባለን፡፡
ዛሬ የሰጣችሁን ድጋፍ እና የለገሳችሁን ምስጋና የከረሙ ችግሮችን በሙሉ ጠራርገን ስላስወገድን እንዳልሆነ በሚገባ እንረዳለን፡፡ ዋናው ነገር ጅምር የለውጥ አያያዛችን "የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል!" የሚል መነሻ መሆኑን አንዘነጋም፡፡
ለውጡን በሚጠበቀው ከፍታ ለማስቀጠል በየደረጃው ያለን መሪዎች ካለፈው ጉድለታችን ተምረን ቃላችንን ለማደስና ህዝባችንን ለመካስ ከፊታችሁ ቆመናል፡፡ ንቅናቄው ጥቂቶች የሚዘውሩት፤ ብዙዎች የሚታዘቡት ሳይሆን ሁሉም በባለቤትነት ሊተውንበት የሚገባ ነው፡፡
በዚህ መስተጋብር መሪዎች ስናጠፋ እየተቆነጠጥን፤ በጎ ስንሰራ እየተበረታታን እንድንቀጥል ዛሬ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ከጎናችን ታስፈልጉናላችሁ፡፡
ህዝቡ ባልተሸበበ አዕምሮ በነፃነትና በሃላፊነት መንፈስ ድጋፍና ተቃውሞውን የመግለፅ ባህሉ መጠናከር አለበት፡፡
ህዝቡ እንደ ንስር ዓይን ችግሮችን ነቅሶ የሚያወጣበት እና እንደ ዶ/ር አዲስ አለማየሁ የተባ ብዕሩ ስንዴውን ከእንክርዳዱ የሚለይበት አቅሙን ከመቼውም ጊዜ በላይ በእጅጉ እንሻለን፡፡
በፓለቲካ አስተሳሰባችን እዚህ ወይንም እዚያ ልንቆም እንችላለን፡፡ የአንደኛው ወይም የሌላኛው አስተሳሰብ አራማጅ ልንሆን አንችላለን፡፡ የ”እኔ ሃሳብ የተሻለ ነው፣ የበለጠ ይጠቅማል“ ብለንም ልንፎካከርም እንችላለን፡፡ መሠረታዊው ጉዳይ ሁላችንም ለዚህች ሀገር ጥቅምና የተሻለ ነገር ፍለጋ የተሰማራን መሆናችን ነው፤ እርግጠኝነትና ልባዊነት የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው ፡፡
ውድ የዚህ ታሪካዊ ፕሮግራም ታዳሚዎች
ብዕራችሁ የተባ፣ አዕምሯችሁ የሰላ እንዲሁም ተሳትፏችሁ ደግሞ የነቃ መሆን ዘመኑ ራሱ ይጠይቃል፡፡ መንግስት ይሄን ድባብ እንዲፈጠር አቅሙ የፈቀደውን ጠጠር መወርወር እንጂ የዜጎች ባላጋራና የዲሞክራሲ ስርዓት ደግሞ ደንቀራ መሆን አይገባውም፡፡ ይሄ ያፈጀበት አካሄድ ነው፡፡
በምንገነባው ስርዓት በዴሞክራሲ ግንባታ እና በሰብዓዊ መብት አያያዝ ያለፉትን ስርዓቶች መርገምና መውቀሳችን ሳያንስ በዚህ ዘመንም አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊቶች ተፈፅሟዋል፡፡ ብዙ ዋጋም አስከፍለውናል፡፡
ከዚህ በኋላ ፀረ-ዴሞክራሲ በቃ ብለናል፤ እያንዳንዱን ድርጊታችንና ስራችንን በንቃት ተከታታሉ፡፡ አካሄዳችንና ሁኔታችን ከዴሞክራሲ ያፈነገጠና የዜጎችን መብት የሚጋፋ ሆኖ በተገኘበት ጊዜ ሁሉ ልትታገሉን እና አደብ ልታስገዙን ይገባል፡፡
በዚህ አያያዝ ኢትዮጵያውያን በነፃ አገራቸው፣ በነፃነት የሚያስቡባት፣ በነፃነት የሚፅፉባት፣ ያለ ገደብ የሚመረጡባትና የሚመርጡባት፣ የዴሞክራሲና የፍትህ ስርዓትን የሚመሩና የሚያስተባብሩ የጋራ ተቋማት የተገነቡቧት፤ ዴሞክራሲያዊ አገር ባለቤት ይሆናሉ፡፡
ይህ የህዝብ ጎርፍ፣ ሚሊዮኖች ያላንዳች ልዩነት በተባበረና ከፍ ባለ ድምፅ እየዘመሩለት ያለውን ኢትዮጵያን የዳበረና የተረጋጋ ዴሞክራሲ ባለቤት የሆነች አገር የማድረግ ጉዞ ነው፡፡
ነገር ግን ዕዚህ ላይ ሊጤን የሚገባው አንድ ታላቅ ቁም ነገር አለ፡፡ ዲሞክራሲ እንደፈለግን እንድንሮጥ እንደሚያስችለን፤ ሁሉ ልጓምንም ያበጃል፡፡ ልጓሙ የየግል ሩጫችንን በህግ ጥበቃ የተበጀላቸው የሌሎች የዜጎችን መብቶች እንዳይጋፋ ሲባል የተበጀ ነው፡፡ እናም የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ነፃነትንና ሃላፊነትን በሚዛኑ ያያዘ መሆን ይገባዋል ፡፡
ውድ የዚህ ታሪካዊ ፕሮግራም ታዳሚዎች
ፍቅራችንና አብሮ የመኖር ዕሴታችን ዕንዲሁ በምስጋና ቀንና በሰላሙ ጊዜ ብቻ የምናሳያቸው ሳይሆኑ በችግርና በፈታኝ ወቅትም ቢሆን ፀንተው የሚቆዩ ሃብቶች ናቸው፡፡ በዚህ የአብሮነትና የአካታችነት ባህሪያችንን የሚሸረሸሩ አዝማሚያዎችን በጽናት ማውገዝ ይጠይቀናል፡፡
የአማራ ክልል ህዝብ በአገራችን ቀደምት የገናናነት ታሪክ የበኩሉን ወሳኝ ሚና የተጫወተ ባለታሪክና ኩሩ ህዝብ ነው፡፡ አለመታደል ሆኖ ያ! የገናናነት አገራዊ ቁመና ተቀይሮ የከፋ ድህነትና ኋላቀርነት ቸነፈር ውስጥ ብዙ ዋጋ የከፈለ ነው፡፡ የአማራ ብሄር በታሪክ፣ በባህልና በቋንቋ እንዲሁም በሌሎች እሴቶች በአገር ግንባታ ሂደት ትልቅ ቦታ ያለው ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ስርዓቶች ጥቂቶች ከሌሎች አካላት ጋር በጥቅም ተሳስረው በፈፀሙት ስህተት፤ በአማራው ላይ በተካሄደ የተሳሳተ አስተምህሮ ሰፊው የአማራ ህዝብ በሌሎች ህዝቦች በዳይ፣ ዕዳ ከፋይና የተለየ ተጠቃሚ መስሎ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ በዚህ ብዙ መፈናቀል፤ ተጠርጣሪ እና ለሌሎች ችግሮች እንዲጋለጥ ሆኗል፡፡
ከዚህ አኳያ የነበሩ ስህተቶችን በማረም የብሄራችንን እና የሃገራችንን ክብር ተመልሶ ገናናነታችንን ለማረጋገጥ መረባረብ ይገባናል፡፡ "ትልቅ ነበርን፤ ትልቅም እንሆናለን!" ይለዋል እንዲህ ነው፡፡
ውድ የዚህ ታሪካዊ ፕሮግራም ታዳሚዎች
ይህን ታላቅ ክልላዊና አገራዊ ራዕይ እውን ለማድረግ መሪ ድርጅቱ ብአዴን/ኢህአዴግ ላስመዘገባቸው ጅምር ስራዎች እንደሚመሰገን ሁሉ ላጠፋውና ላጎደለው ሃላፊነቱን ይወስዳል፡፡
አሁን የተጀመረው የለውጥ ማዕበል ካለፈው ጉድለት ተምሮ በፅናት መጓዝን ይጠይቃል፡፡ ይህን የለውጥ ማዕበል በሙሉ ልብ ተቀብሎ ድርሻን መወጣት የግድ ይላል፡፡ ከዚህ ውጭ በእኔ አውቅልሃለሁ ፈሊጥ መንታ መንገድ መወጠን አይቻልም፡፡ መፍትሄው የህዝብን የለውጥ ፍላጎት አድምጦ ከእሱ ጋር በመሰለፍ ለውጡን በትክክለኛ አቅጣጫ መምራት ብቻ ነው፡፡
ኢትዮጵያ አንዳንዶቻችን የቅንጦት ህይወት የምንገፋባት እና እንዳሻችን የምንፈነጭባት፤ ሌሎቻችን ደግሞ ባይተዋር የምንሆንባት ሀገር መሆን የለባትም፡፡ እናም በእናት አገርና በጋራ ጎጇችን በእኩልንትና በፍቅር እንኖራለን፡፡
አገራችን በተያያዘችው የለውጥ መንፈስ አስቀድመው ለተፈፀሙ እኩይ ታሪኮች ዳግም እንዳይፈፀሙ ትምህርት ወስደንባቸው፤ አዲስ ታሪክ ለመስራት ደግሞ የተለኮሰውን መነሳሳት ሂደቱን በአግባቡ ልንመራውና ልንገራው ይገባል፡፡
በቅርቡ በመዲናችን አዲሳ አበባ በንፁሃን ዜጎቻችን ላይ የደረሰው ጉዳት በአገራችን የሚደረገው የዴሞክራሲ ስርዓት ምንም እንኳን በወሳኝነት በፍጥነት መጓዝ እንደሚቻል ከወዲሁ አፋችን ሞልተን ለመናገር ቢያስችለንም ሂደቱ የአልጋ ባልጋ ጉዞ እንደማይሆን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ክስተት ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ እኔና ባልደረቦቼ ክልላችንና ኢትዮጵያን የተረጋጋና የዳበረ ዴሞክራሲ ባለቤት የማድረግ የቤት ስራን ዳር ለማድረስ ከህዝባችን ጋር በመሆን በፅናት እንደምንዘልቅ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡
በታሪካችን አንዳችን በሌላችን ላይ ተነስተናል፡፡ ሲከፍም ቃታ ስበን አንዳችን የሌላችንን አካል አቁስለናል፡፡ አልያም አጉድለናል፡፡ ምንም እንኳ ትናንት የተከሰቱ መጥፎ ታሪኮችን መዘንጋት ሰዋዊው የማስታወስ ችሎታችን የማይፈቅድልን ቢሆንም ለወደፊት የጋራ ጥቅምና ጉዞ ሲባል ሆን ተብሎ እኩይ ትዝታዎችን መቀየር በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡
እናም እንደዚህ ዓይነቱን ቅስቀሳና ውትወታ የሚያስተላልፉት ሃይሎች ጆሮ ዳባ ልበስ ልንላቸው ይገባል፡፡ አማራ የሚታወቅበት መለያ ባህሪው አካታችነቱና አቃፊነቱ ነው፡፡ አማራ የሚታወቅበትን እሴቶችን ጠብቆ መቀጠል የሚገባው ሲሆን፤ ተናጥል ችግሮች እንኳ ቢያጋጥሙ ህዝብን እና ግለሰብን ለይቶ እንዲታረም እና እንዲስተካከል ማድረግ እንደሚገባ፤ ከዚህ ውጭ የጥላቻ፣ የዘረኝነት፣ የበቀል እና የጎጠኝነት አረሞችን በማስወገድ ብቻ ሳይሆን ይህው ለትውልድ እንዳይተላለፍ ተግተን መስራት ይኖርብናል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ከይቅር ባይነት በላይ የምናከብረውና ዋጋ የምንሰጠው ነገር የለም፡፡ “ ይቅርታ” በልባችንም በመሐላችንም ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ዛሬም ይህንን ቦታውን ልናሰፋ መሐላችንም ይቅርታ እርስት እንዲሆን እንውደድ፡፡ ይቅር አንባባል፡፡ ለየአካባቢው የሚታየውን ግጭትና መቃቃር ከመሠረቱ አክስመን በይቅርታችን እንደይመለስ አድርገን እንጠበው፡፡
ኢትዮጵያውያን ነንና ይሄ አያቅተንም፡፡ በትንሹም ሆነ በትልቁ ሆድ መባባስ ቀርቶ አንዳችን ለሌሎችን የፍቅር ማዕድና አውድ እንሁን፡፡
በሚሊዮኖች ተደግፎ የተቀጣጠለው ለውጥ ወደ ኋላ መመለስ ቀርቶ ማዝገምን አይታገስም፡፡ መፍትሄው በህዝብ ባለቤትነት እና በወጣቱ መሪነት በፍጥነት መጓዝ ነው፡፡ ካሁን በኋላ ሃገራችን ለሁሉም በእኩል የተመቸች፤ ዜጎቿ እኩል የሚደመጡባት፤ እኩል የሚሳተፉባት የጋራ ማዕዳችን ሆና ትቀጥላለች፡፡ ለዚህ እውን መሆን በፅናት መታገል ይኖርብናል፡፡
ከዚህ አኳያ የስራ ባልደረቦቼ እና እኔ ቴዎድሮስና ገብርዬ ሆነን ተጋግዘን፤ አለቃ እና ምንዝር ሳንሆን ፤ የአንድ አላማ ተሰላፊዎች በመሆን ህዝባችንን የሰላም፤ የዴሞክራሲ እና የልማት ፍላጎት ዳር እናደርሳለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ አበክሬ ላነሳ የሚገባ አንድ ቁም ነገር አለ፡፡ በኛ በአመራሮቹ በኩል፤ ህዝቡን በሚፈለገው ደረጃ ያለማዳመጥ፤ ያለማቀፍ፤ ያለማቅረብ፤ እና ለያይቶ ማየት ችግር አለ፡፡ እንዲሁም በምሁራኑ እና በወጣቱ እንዲሁም ባለሃብቱ የዳር ተመልካች የመሆን እና በራስ አገር ላይ ባይትርነቱ ተስተውሏል፡፡
ክልላችንም ሆነ ሃገራችን ወደ ፊት ሊገሰግሱ የሚችሉት እና በለውጡ ዘልቀው ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡት እኛ አመራሮቹ ችግራችንን ቀርፈን አቃፊና ደጋፊ ስንሆን ወጣቱ፤ ምሁሩ እና ባለሃብቱ ደግሞ ባይዋርነቱን ትቶ የሃገሬ እና የክልሌ ጉዳይ ያገባኛል ደግሞም አመራሮቹ፤ የኔ ክፋይ ናቸው ብሎ አብሮ ሲሳተፍ እና ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲገባ ብቻ ነው፡፡
እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ ከእንግዲህ እንደማንሳሳት ሳይሆን እንደምናደምጣችሁ፣ እንደከዚህ ቀደሙ ዘግይተን ሳይሆን ፈጥነን እንደምንመልስላችሁ እና በዚያው ፍጥነት እንደምንስተካከል ነው፡፡ ምስጋናችሁን ብቻ ሳይሆን ተግሳፃችሁን ከልብ ሰምተን ፈጥነን ለመታረም ዝግጁ መሆናችንን በልበ ሙሉነት አረጋግጥላችኋለሁ፡፡
በተቻለን መጠን ባለን አቅም ሁሉ በህዝባዊነት እንደምናገለግላችሁ፣ ደከመን ሠለቸን ሳንል ሃላፊነታችንን ለመወጣት ጥረት እንደምናደርግ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡
"የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ!" በሚል ዕሴት ታንፆ ለቃሉና ለማዕተቡ ታማኝና ሟች ከሆነ የታላቁ ህዝባችን ክፋዮች ነንና ይህንን ቃል እንጠብቃለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ ብአዴን በአማራው ስም በውጭ አገር የተደራጁና ለሱ የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅች፣የተለያዩ ማህበራዊ የሚዲያ ተቋማት በሰላም ለመንቀሳቀስ እስከወሰኑ ድረስ ወደ ክልላችን መጥተው እንዲቀሳቀሱ ጥሪ እያስተላለፈ እኛም ከግማሽ መንገድ ድረስ ተጉዞ ለህዝባችን ጥቅም መከበር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናችንን አረጋግጣለሁ፡፡
በመጨረሻም ለሰጣችሁን ክብርና ላሳያችሁን ፍቅር ከወገቤ ጎንበስ በማለት እጅ እየነሳሁ በሰላም ወደ የአካባቢችሁ እንድትመለሱ ከአደራ ጭምር እጠይቃለሁ፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቸ ትጋትና ቁርጠኝነት በልጽጋ ፣ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!!!
አመሰግናለሁ
Thursday, June 28, 2018
ኢትዮጵያና ኤርትራ በቅርቡ በመሪዎች ደረጃ ይነጋገራሉ
ኢትዮጵያና ኤርትራ በቅርቡ በመሪዎች ደረጃ ይነጋገራሉ። ኢትዮጵያና ኤርትራ በቅርቡ በመሪዎች ደረጃ ውይይት እንደሚያደርጉ ተገለፀ።
ባለፈው ማክሰኞ አዲስ አበባ የገባው የኤርትራ መንግስት ከፍተኛ ልዑክ ቡድን የኢትዮጵያ ቆይታውን ያጠናቀቀ ሲሆን፥ ዛሬ ይመለሳል።
በቆይታው ዙሪያ ዛሬ መግለጫ የሰጡት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ሀገራቱ በመሪዎች ደረጃ በቅርቡ ውይይት እንደሚያደርጉ ነው ያስታወቁት።
አዲስ አበባ ላይ ከኤርትራ መንግስት ከፍተኛ ልዑክ ቡድን ጋር የተደረገው ውይይት እንዲመጣ ለሚፈለገው ሰላም ምቹ እድል የፈጠረ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ዛሬ መልዕክት ልከዋል።
የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ገንቢ ውይይት የሚያደርግ ከፍተኛ ልዑኩን ወደ አዲስ አበባ መላኩ ይታወሳል።
በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ኦስማን ሳለህ የሚመራው እና የፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ አማካሪና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የማነ ገብረአብ ያካተተው ልኡክ ባሳለፍነው ማክሰኞ ነበር አዲስ አበባ የገባው ።
ለኤርትራ መንግስት ልኡካን ቡድን አዲስ አበባ ሲገቡን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በብሄራዊ ቤተ መንግስት የእራት ግብዣ አድርገውላቸዋል።
በተጨመማሪም ልኡኩ በትናንትናው እለት የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴ ለመመልከት ወደ ሀዋሳ ከተማ በማቅናት የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን መጎብኘቱም ይታወሳል።
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባሳለፍነው ሳምንት በድንበር ጉዳይ ላይ የሚነጋገር የሀገራቸውን ልዑክ ወደ አዲስ አበባ እንደሚልኩ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነበር ልኡኩ ወደ አዲስ አበባ የመጣው።
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ባካሄደው ስብሰባ የኢትዮ- ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በመገምገም፥ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብላ ለመተግበር መስማማቷን መግለጹ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ
ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረቡም የሚታወስ ነው።
በአልአዛር ታደለ
ኢትዮጵያ የድፍድፍ ነዳጅ የሙከራ ምርትን በይፋ ጀመረች
ኢትዮጵያ የድፍድፍ ነዳጅ የሙከራ ምርትን በይፋ ጀመረች። ኢትዮጵያ የድፍድፍ ነዳጅ የሙከራ ምርትን ዛሬ በይፋ ጀመረች። የቻይናው ፖሊ ሲ ጂ ኤል ኩባንያ በምስራቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሲያደርግ የቆየው የድፍድፍ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ውጤት አስገኝቶ ዛሬ በይፋ የሙከራ ምርት ጀምሯል። የሙከራ ምርቱን በይፋ የማስጀመር ስነ ሰርዓት ላይም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃሙድ እና የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ተገኝተዋል።
የሙከራ ምርት መጀመርን አስመልክቶ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት እንዳስታወቁት ከዛሬ ጀምሮ በሙከራ ደረጃ በቀን 450 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የማውጣቱ ስራ ይከናወናል።
አሁን የማውጣቱ ስራ ሀገሪቱ ያላትን አቅም ማወቅን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ አጠቃላይ አቅም ታውቆ በቀጣይ በሙሉ አቅም ድፍድፍ ነዳጁን የማውጣት ስራ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
ይህ መሆኑም ስራ አጥነትንና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍና ዘላቂ እድገትን ለማምጣት ይረዳልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ባለፈው በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ባደረጉት ጉብኝት የተፈጥሮ ሃብትን በሰላማዊ መንገድ መጠቀም እንዲቻል መግባባት ላይ መደረሱን አስታውሰዋል።
የተፈጥሮ ጋዝን በተመለከተም በሚቀጥለው መስከረም ወር ወደ ጅቡቲ መላክ የሚያስችል የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ይጀመራልም ነው ያሉት።
የማስተላለፊያ መስመሩ ዝርጋታ በሁለት አመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ በሙከራ ደረጃ ጋዝ ማስተላለፍ ሲጀምር በአመት 1 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስገኝ ጠቅሰዋል።
በቀጣይ በሙሉ አቅም ጋዝ ማስተላለፍ ሲጀምርም በአመት 8 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስገኝ ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ በርካታ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሃብት አላት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የነበረው ልዩነት ይህን ሃብት በአግባቡ እንዳንጠቀም አድርጎን መቆየቱን አውስተዋል።
ከዚህ አንጻርም የተገኘውን የተፈጥሮ ሃብት በእኩልነትና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በጋራ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።
የተፈጥሮ ሃብትን መቀራመት ትልቁ የአፍሪካውያን ችግር መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁን የተገኘውን ሃብት በሰላማዊ መንገድ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
አሁን የተገኘው ድፍድፍ ነዳጅም አዳዲስ ሃብቶችን ለማምጣት እንደሚያግዝ ጠቅሰው፥ በቀጣይም የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙ እምነቴ ነው ብለዋል።
ኩባንያው ለሰራው ስራ ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም በማውጣት ሂደቱ ውስጥ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
ህብረተሰቡም ከሃብቱ ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ለመላው ኢትዮጵያውያም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው፥ የተገኘው ሃብት ለብጥብጥ ሳይሆን ለጋራ ተጠቃሚነት እንዲውልም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
source: Fana
Thursday, June 21, 2018
የአርበኞች ግንቦት 7 መግለጫ
የአርበኞች ግንቦት 7 መግለጫ
“የሰለጠነ ፓለቲካ” የምንመርጠው፣ የምናውቀውና የምንመኘው የትግል ስልት ነው!!! የአርበኞች ግንቦት 7 ልዩ መግለጫ
================
ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ለፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡትን የሥራ ዘገባ እና ከምሀሀ ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ በአንክሮ ተከታትለናል።
ዶ/ር አቢይ በዚሁ ማብራሪያቸው የኢህአዴግ መንግሥት የፀጥታና የደህንነት ኃይሎች የአሸባሪነት ተግባራትን የሚፈጽሙ እንደሆኑ በይፋ ከመናገራቸውም ባሻገር ፤ ፓርቲና መንግሥት ተቀላቅለው ነፃ ተቋማት እንዳይኖሩ መደረጉን እና የዳኝነት ሥርዓቱ ከፍተኛ ችግር ያለበት መሆኑን ገልጸዋል። ንቅናቄዓችን ለዓመታት ሲናገር የነበረውን ሀቅ እሳቸው መናገራቸው፣ በአንድ በኩል እሳቸው በግላቸው ከእውነት ጎን ለመቆም ያላቸውን ቁርጠኝነት ሲያመለክት -በሌላ በኩል ደግሞ እሳቸው የሚመሩት የለውጥ ቡድን ለሀገራዊ መግባባት እያሳየ ያለው ዝግጁነት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ያመለክታል የሚል እምነት አሳድሮብናል። እነዚህ ቀድሞ ሲካዱ የነበሩ እውነታዎች በእርሳቸው አንደበት በምክር ቤቱ ስብሰባ መገለፃቸው፣ እስካሁን ሲፈፀሙ የነበሩ በደሎችንU
u
ለማስቀረት እና ጉድለቶችን ለማረም ብርቱ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል ብለን እናምናለን። ዶ/ር ዓቢይ እስካዛሬ በኢትዮጵያ የምክር ቤት ታሪክ ውስጥ ያልታየ ሀቀኝነት በማሳየታቸውም አድናቆቻችን ከፍተኛ ነው።
በሥራ ላይ ያለውንና ቋንቋን መሠረት ያደረገውን የክልል አስተዳደራዊ መዋቅር በተመለከተ የተናገሩትም ትኩረት የሚስብ ነው። ቋንቋን መሠረት ያደረገ ማካለል በየቦታው ለሚነሱ የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች አስተዋጽኦ ማበርከቱን፤ የሕዝብ መፈናቀልና መገፋት ማስከተሉን፤ ዘረኝነትን በማባባስ በሀገራችን ውስጥ በአስደንጋጭ ሁኔታ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ ማበርከቱን እና ክፍለ አህጉራዊ እይታን ነስቶ ዜጎች ስለመንደራቸው ወሰን አብዝተው እንዲጨነቁ ማድረጉን የሚገልጸው የንግግራቸው ክፍልም- ለአብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ የሰጠ እና የወደፊት መንገዳቸውን አመላካች ተደርጎ ተወስዷል።
አሁን ያለው የፌደራል አወቃቀር መሠረቱ ቋንቋ ነው ይባል እንጂ በተግባር የሚታየው ግን ዘር ነው። ይህ አደረጃጀት ለኢፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል፤ አድልዎ ለተሞላበት አስተዳደርና ለሚሊዮች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። ዶ/ር ዓቢይ ከቀናት በፊት ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፌደራል አወቃቀር ያስገኛቸውን ጥቅሞችና ጉዳቶችን መዝኖ አማራጭ የአደረጃጀት ንድፎችን የሚያዘጋጅ ኮሚሽን የሚዋቀር መሆኑን መግለፃቸውም- አርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄን (አርበኞች ግንቦት 7) በእጅጉ አስደስቷል። በዚህ ረገድ ንቅናቄያችን የበኩሉን ለማበርከት ዝግጁነቱን ይገልፃል።
ዶ/ር አቢይ አህመድ ህወሓትንና የትግራይ ሕዝብን ለያይቶ ስለመመልከት የተናገሩትም- ንቅናቄዓችን ከልብ የሚያምንበትና በጽናት ሲያራምደው የቆየው እምነት ነው። ህወሓት በርካታ አኩይ ተግባራትን የፈጸመ፤ የአገዛዙን የደህንነትና የፀጥታ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር የሚቃወሙትን ሁሉ እስር ቤት በማጎር በፈጸመው ሰቆቃ- በርካታ ዜጎችን ለኣካልና ለስነልቦና ጉዳት የዳረገ፤ ሺዎችን የገደለና ሚሊዮኖችን ለስደት የዳረገ፤ የመንግሥት ሥልጣንን ለሀብት ዘረፋ መጠቀምን ብቸኛ አማራጭ ያደረገ ፍጹም አምባገነንና ዘራፊ ድርጅት ነው። በዚህም ሁሉ ምክንያት ነው ህወሓትን የምንታገለው። ይህ ድርጅት በነፃ ምርጫ ሳይመረጥ የትግራይ ሕዝብ ተወካይ ነኝ ማለቱ ሳያንስ ራሱን ከትግራይ ሕዝብ ጋር እኩል አድርጎ የሚያቀርብ ትዕቢተኛ ድርጅት ነው። በዚህም ተግባሩ የትግራይን ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ አራርቆታል። ይህ መቆም አለበት። ለዚህም ነው ሕዝብንና ድርጅትን የመለየት አስፈላጊነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ መገለፁን እጅግ በጣም ጥሩ ነገር ነው ብለን ያመንነው። ይህ መልዕክት ለትግራይ ብቻ ሳይሆን በፍትሃዊና ነፃ ምርጫ ተመርጠው ሳያሸንፉ የሕዝብ ተጠሪ ነኝ የሚሉ ድርጅቶችን ሁሉ የሚመለከት ነው ብለን እናምናለን። ህወሓትን በተመለከተ ጥቂት ተጨማሪ ነገር ማውሳት የምንፈልገው-ህወሓትን የምንታገለው ከትግራይ ሕዝብ ጎን ቆመን መሆኑን ነው። ይህ ብቻ ሳይሖን በራሱ በህወሓት ውስጥም የለውጥ ኃይሎች መኖራቸውን ጠንቅቀን እናውቃለን። የኢትዮጵያን ሰቆቃ በመቀነስ ረገድ የእነዚህ ህወሓት ውስጥ ያሉ የለውጥ አራማጆች ሚና ከፍተኛ ነው ብለንም እናምናለን። ስለሆነም፣ ከእነዚህ ወገኖች ጋር ተባብረን ለመሥራት ዝግጁዎች ነን።
አርበኞች ግንቦት 7፣ ኦነግና አብነግ ከአመጽ ትግል ተቆጥበው ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲሸጋገሩ ጠቅላይ ሚኒስት ዶ/ር ዓቢይ አህመድ በፓርላማው ንግግራቸው ጥሪ አድርገዋል። በመገዳደል ሥልጣን መያዝም ሆነ በስልጣን ላይ መቆየት ጊዜው ያለፈበት “ኋላ ቀር ፓለቲካ” መሆኑን ገልፀዋል። ይህ አገላለፃቸው የአርበኞች ግንቦት 7 የቆየ እምነት ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 የመሣሪያ ትግል ዋነኛ የትግል ስትራቴጅው አድርጎ፤ በዚህ መንገድ የፓለቲካ ስልጣን የመያዝ ዓላማ ኖሮት አያውቅም። ሆኖም ግን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ገጥሞን የነበረው ባላንጣ የኋላ ቀር ፓለቲካ ቀንደኛ አራማጅ የነበረ በመሆኑ ፣ዜጎች አገዛዙ ከሚያደርስባቸው ሽብር ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ ድርጅታቸውን፣ ማኅበረሰባቸውንና ፓለቲካዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን እንዲከላከሉ ሲያበረታታ ቆይቷል። ራስን ከጉልበተኛ አጥቂ መከላከል፣ ፍትሀዊ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮዓዊ መብት ነው፤ አጥቂ ከሌለ ግን ይህ አያስፈልግም።
ዶ/ር አቢይ አህመድና የለውጥ ቡድናቸው ተስፋ እየሰጡ ባሉበት መንገድ ኢትዮጵያን መርተው ዜጎችን የሚያሸብር አገዛዝ እንዳይኖር የሚያደርጉ ከሆነ፤ የሰለጠነ ፖለቲካ እንዲካሄድ የሚያስፈልጉ እርምጃዎችን በተግባር መውሰዳቸውን ከቀጠሉ፤ የህወሓት አገዛዝ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ የሚታገሉ ኃይሎች ላይ በፓርላማ አስጸድቆ ያሳወጀውን የሽብርተኝነት ፍረጃ ካነሱ፤ ለዲሞክራሲ መስፈን እንቅፋት የሚሆኑ ሌሎች ህጎች ከተሻሩ እና ነፃ ተቋማት እንዲመሠረቱ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ከተጀመሩ አርበኞች ግንቦት 7 ራስን በመከላከል ተግባር ላይ ሕይወት፣ ጊዜና ንብረት የሚያጠፋበት ምንም ምክንያት የለውም። ምክንያቱም የሰለጠነ ፓለቲካ የምንፈልገውና ለሀገራችን የምንመኘው የትግል ስልት ነው።
የኛ እምነት ግን ከዚህም ያልፋል።
ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት መገንባት የበርካታ ዜጎችና ቡድኖች ትብብርን የሚጠይቅ፤ በአንዴ ተገንብቶ የማይጠናቀቅ፤ ጊዜና ሌሎች በርካታ ግብዓቶችን የሚጠይቅ የማኅበራዊ ልማት ውጤት መሆኑን እንገነዘባለን። ዜጎችን የማያሸብር መንግሥት በዶ/ር ዓቢይ ወይም በቡድናቸው ጥረት ብቻ የሚመጣ እንዳልሆነም እናውቃለን። የዚህ ትግል ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ብለን እናምናለን። ስለሆነም በዚህ ረገድ ዶ/ር ዓቢይና የለውጥ ቡድናቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም በሚያደርጉት ትግል አብረናቸው መሆናችንን ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን።
ዶ/ር አቢይ በመግለጫቸው ይህንን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ኃይሎች እየፈጸሙ ያለውን አሻጥር ነቅቶ መጠበቅ እንደሚገባና ቅልበሳውንም ለመከላከል የማኅበረሰቡን ሰፊ ድጋፍና ተሳትፎ እንደሚፈልግ መናገራቸው፤ እኛም እንደ ድርጅት ስናስጠነቅቅ የነበረውና እንዲህ ዓይነት ቅልበሳን ለመከላከል በኢህአዴግ ውስጥ ካሉ የለውጥ ኃይሎች ጋር ሙሉ ትብብር እንደምናደርግ ከዚህ በፊት ያሳወቅነውን አሁንም በግልጽ ደግመን እናሳውቃለን።
ይህ የለውጥ ሂደት ግቡን እንዲመታና ከዚህ ሂደት የሚወጣው የፖለቲካ ሥርዓት ሰፋ ያለ ማኅበራዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ሰፋ ያሉ የፖለቲካና የሲቪክ ማኅበረሰብ ኃይሎች የሚሳተፉበት ሀገራዊ ውይይት በቶሎ የመደረጉን አስፈላጊነት አሁንም በድጋሚ በአንክሮ ማሳሰብ እንፈልጋለን። በእንዲህ ዓይነት ውይይትም ድርጅታችንም ሆነ ከድርጅታችን ጋር ተባብረው የሚሠሩ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች የሚጠበቅብንን ሙሉና ቀና ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።
አርበኞች ግንቦት 7 ራሱ፣ በታሪካችን ውስጥ እስካሁን ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ እውነተኛ ፉክክር የታየበት የምርጫ 97 ውጤት ነው። የአርበኞች ግንቦት 7 አመራርና አባላት በምርጫ 97ቱ የሰለጠነ ፓለቲካ ተሳትፎ ያደረጉ ዜጎች መሆናቸውን ኢትዮጵያዊያን ያውቃሉ። የንቅናቄዓችን ተልዕኮም በግንቦት 7 ቀን 1997 ለአጭር ጊዜ አጣጥመን በጉልበት የተነጠቅነው የሰለጠነ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ህጋዊ የፓለቲካ ስልጣን ሽግግርና በዚህም ሂደት የሀገሪቱን አንድነትና የሕዝቡን አብሮነት ያስጠበቀ፤ የሁሉንም የሀገራችንን ዜጎች እኩልነት ያስረገጠ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሥርዓት እውን ማድረግ ነው።
ስለሆነም ዜጎች ላይ የሚደርስ ግልጽ ጥቃት እስከሌለ ድረስ ራስን በመከላከል ላይ ሕይወት፣ ጊዜ፣ ጉልበትና እውቀትን ማባከን ምርጫችን አለመሆኑ እንገልፃለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !
ሰኔ 13 ቀን 2010 ዓ ም
Recent Articles
Recent Video Uploads
Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube
Ethiopia Today
- Active a minute ago with many
- videos