በሻሸመኔ ከተማ በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥ የ3 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርከት ያሉ ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሷል
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተማ በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥ የሰዎች ህይወት እና አካል ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለፀ።
አደጋው የደረሰው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ዳይሬክተር አቶ ጃዋር ሞሃመድ እና ሌሎች የቡድኑ አባላት አቀባበል ለማድረግ በከተማዋ በተዘጋጀ ስነ ስርዓት ለይ መሆኑን የኦህዴድ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ አስታውቀዋል።
በአደጋውም የ3 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካቶች ላይ ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት መድረሱንም አቶ አዲሱ ገልፀዋል።
በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥ በደረሰው አደጋ ህይወታቸው ላለፈ እና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎችም የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል።
ከአደጋው ጋር ተያይዞም አንድ የሻሸመኔ ከተማ የፀጥታና አስተዳደር በሮ ተሽከርካሪ በእሳት መጋየቱንም አቶ አዲሱ አስታውቀዋል።
ተሽከርካሪው ፀጥታ የማስከበበር ስራ ላይ በተሰማራበት ወቅት ቦምብ ጭኗል በሚል በተሳሳተ መረጃ በእሳት መጋየቱን አቶ አዲሱ ገልፀዋል።
ሆኖም ግን በተሽከርካሪው ላይ ምንም አይነት ቦምብ እንዳልነበረ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ማረጋገጣቸውንም አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅትም አደጋው ጋር ተያይዞ ወጣቱን በመምሰል የህገ ወጥነት እንዲስፋፋ መንገድ የመዝጋት፣ የዝርፊያ እና በፍቅር አብሮ የኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች ላይ ጉዳት ለማድረስ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ምልክቶች መታየታቸውንም ገልፀዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች እና ወጣቶች ከዚህ ተግባር በመቆጠብ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
No comments:
Post a Comment