የኢፌዴሪ ም/ጠ/ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ም/ሊ/መንበር ጓድ ደመቀ መኮንን ዛሬ በባህር ዳሩ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ያደረጉት ሙሉ ንግግር
ውድ የባህርዳር ከተማ እና የአካባቢዋ ነዋሪዎች
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች
ክብራትና ክቡራን
በቅድሚያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ . . . በአካል በዚህ ታሪካዊ ሰልፍ ላይ ባይታደሙም፤ በመንፈስ ግን አብረውን እንደሆኑ በመግለጽ ለባህርዳር ከተማ እና የአካባቢዋ ነዋሪዎች የከበረ ሰላምታ እና መልካም የለውጥ ምኞታቸውን በክብር አስተላልፈዋል፡፡
ውድ የዚህ ታሪካዊ ፕሮግራም ታዳሚዎች
እነሆ ዛሬ! እንደዚህ በደመቀ አብሮነት እና ባሸበረቀው ህዝባዊ ሰልፍ በመካከላችሁ ተገኝቼ ይሄን ንግግር ሳደርግ የተሰማኝ ልባዊ ደስታ እና የፈጠረብኝን ውስጣዊ ፍሰሃ ምንኛ ትልቅ እንደሆነ እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው፡፡
ይህ ታሪካዊ ቀን ቀጣዩን ጊዜ የተሻለ እና ክልላችንን እና ሀገራችንን ተመራጭና ተወዳጅ፣ የሰላምና የልማት ምድር ለማድረግ ብሩህ ዕለት የወገገበት ነው፡፡ ለዚህ ዕለት ዕውን መሆን በየፈርጁ የታገሉ፣ የደሙና የቆሰሉ፣ ከዚያም አልፎ ክቡር ሕይወታቸውን የሰው በዚህ አደባባይ ክብርና ሞገስ ለእነሱ ይሁን፡፡ እናመሰግናለን፡፡
ባህርዳር የክልላችን መናገሻ ከተማ ብቻ ሳትሆን፤ በለሱ ቀንቷቸው ጎራ ያሉ የሃገራችን እና የሌሎች ዓለም ሰዎች በፍቅር የሚማረኩላት፤ ስለውበቷና ስለምቹነቷ ደጋግመው የሚመሰክሩላት፤ የሃገራችን ከተሞች ፈርጥ ነች፡፡
ባህርዳር - ጣናን ተንተርሳ፣ ጊዮንን እንደመቀነቷ አገልድማ ታላላቅ ጥበቦችን በማህፀኗ ያቀፈች ድንቅ ሃብታችን ነች፡፡
አሁን. . .አሁን! በሃገር አቀፍ ደረጃ የዘመናዊነትና የብልፅግና ማሳያ ምልክት ከሆኑ ውብ ከተሞች መካከል አንዷ ባህርዳራችን ነች፡፡
እንኳን በዚች ውብ ከተማ በሚካሄደው ደማቅ ህዝባዊ ሰልፍ ላይ በጋራ ለመታደም አበቃችሁ፤ አበቃን፡፡
ውድ የዚህ ታሪካዊ ፕሮግራም ታዳሚዎች
ይህ ትዕይንት፣ የለውጥ ጥማት፣ የዴሞክራሲና የሠላም ፍላጐት ብቻ አይደለም፡፡ ኃይልም ነው፡፡ ጉልበትም ነው፡፡ ሁሉንም ዕውን የሚያደርግ አቅም ነው፡፡ ዛሬ እዚህ ፊት ለፊታችሁ ቆሜ በአይበገሬነትና በተስፋ የሚደልቀው ልባችን ዓለት ሲያንቀጠቅጥ፣ ድህነትን ሲንጥ ይሠማኛል፡፡ ለዓለም ሁሉም ይሰማል፡፡
ይህ አስደማሚ የጥምረታችን ኃይል የትኛውንም መሰናክል ገርስሶ፣ እንቅፋቶችን ሁሉ አፍርሶ ድህነትና ኋላቀርነትን ታሪክ እንደሚያደርግ አልጠራጠርም፡፡ ይህ እንዳለላ ሙዳይ፣ እንደ ህብር ሙካሽ የተንቆጠቆጠ ውበታችን የኢትዮጵያዊነት ፈርጥ ሆንነ፤ ሕዝቦቿን በውበት ሠድረንና ደምረን ለሀገራችን ድምቀት እንደምንሆን ይሄው ያየን ሁሉ ይመሰክራል፡፡ አብረን ቆመን አንጀታችን እንደክራር፣ ልባችን እንደከበሮ ተዋህዶ እየፈጠረ ያለው ዜማ ልዩ ኀብረ ዝማሬ ነው፡፡ ለሁሉም የሚጥም፣ ሁሉም የሚሰማው፣ ሰሞቶ የሚያበቃው ብቻ ሳይሆን አብሮ የሚደመርበት የፍቅር ቅኝት ነው፡፡ ፍቅራችን ሁሉንም ያሸንፋል፡፡
የዛሬው የምስጋናና የድጋፍ ትዕይንት እያደር በየፈርጁ የሚገለጥ የአደራ ጥራዝ የብርታት ስንቅ ነው፡፡
አደራው የሁሉም፤ አቅሙም የጋራ ነው፡፡ ይህን ለውጥ ከዳር ለማድረስ ስንበረታ እንደዛሬው ተመሰጋግነን፣ ስንሰንፍ ተወቃቅሰን፣ ተግሳፃችሁን ሰምተን ልንታረምና ልናገለግላችሁ ቃል የምንገባበት መድረክም ነው፡፡
በዘመን ቅብብሎሽ አያቶቻችን እና አባቶቻችን . . . በአገር ፍቅር የነደደው ነፍስ፤ በነፃነት ጥማት የተሞላው መንፈስ፤ ለችግር የማይንበረከክ ነፃና ኩሩ ህዝብ፤ በፈተናዎች ፊት ፀንታ ሳትበገር የምትቆይ ሃገር አቆይተውናል፡፡
ገና ከጥንቱ! አገርና ህዝብ ሲደፈር "ከራስ በላይ ንፋስ!" የሚል አስተሳሰብን አሽቀንጥረው "ከራስ በላይ ሃገር!" መኖሩን በታላቅ ጀግንነት ወድቀው፤ ተዋድቀው ክብሯን የጠበቀች እና ነፃነቷን ያስጠበቀች ሃገር በአደራ አውርሰውናል፡፡
በቀደሙት የታፈረችውን ሃገር፤ በእኛ ደግሞ . . . የለውጥ ጉዟችን ፈተና ቢበዛውም ሃገራችን ከስኬት ማማ ላይ እንድትታይ በቁጭት እና በስስት ለውጥን በምኞት ሳይሆን በተግባር ለማምጣት የምንታትርበት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡
እነሆ ዛሬ! ያለማንም ቀስቃሽ እና ጎትጓች በገዛ ፍቃዳችን በዚህ ታላቅ ስቴዲየም የተገናኘነው በተጀመረው ሃገራዊ አዲስ የለውጥ ስሜት አጋርነታችንን ለመግለፅና ይኸው ለውጥ በክልላችን ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ባለቤትነታችንን ለማሳየት ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት በአገር ደረጃም ሆነ በክልላችን ለለውጥ መነሻ የሆኑ ስራዎች ተመዝግበዋል፡፡ ነገር ግን ከሚጠበቀው ለውጥ አኳያ የሰራነው ትንሽ፤ የወቃነው ደግሞ ዕፍኝ እንደማይሞላ እንገነዘባለን፡፡
ዛሬ የሰጣችሁን ድጋፍ እና የለገሳችሁን ምስጋና የከረሙ ችግሮችን በሙሉ ጠራርገን ስላስወገድን እንዳልሆነ በሚገባ እንረዳለን፡፡ ዋናው ነገር ጅምር የለውጥ አያያዛችን "የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል!" የሚል መነሻ መሆኑን አንዘነጋም፡፡
ለውጡን በሚጠበቀው ከፍታ ለማስቀጠል በየደረጃው ያለን መሪዎች ካለፈው ጉድለታችን ተምረን ቃላችንን ለማደስና ህዝባችንን ለመካስ ከፊታችሁ ቆመናል፡፡ ንቅናቄው ጥቂቶች የሚዘውሩት፤ ብዙዎች የሚታዘቡት ሳይሆን ሁሉም በባለቤትነት ሊተውንበት የሚገባ ነው፡፡
በዚህ መስተጋብር መሪዎች ስናጠፋ እየተቆነጠጥን፤ በጎ ስንሰራ እየተበረታታን እንድንቀጥል ዛሬ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ከጎናችን ታስፈልጉናላችሁ፡፡
ህዝቡ ባልተሸበበ አዕምሮ በነፃነትና በሃላፊነት መንፈስ ድጋፍና ተቃውሞውን የመግለፅ ባህሉ መጠናከር አለበት፡፡
ህዝቡ እንደ ንስር ዓይን ችግሮችን ነቅሶ የሚያወጣበት እና እንደ ዶ/ር አዲስ አለማየሁ የተባ ብዕሩ ስንዴውን ከእንክርዳዱ የሚለይበት አቅሙን ከመቼውም ጊዜ በላይ በእጅጉ እንሻለን፡፡
በፓለቲካ አስተሳሰባችን እዚህ ወይንም እዚያ ልንቆም እንችላለን፡፡ የአንደኛው ወይም የሌላኛው አስተሳሰብ አራማጅ ልንሆን አንችላለን፡፡ የ”እኔ ሃሳብ የተሻለ ነው፣ የበለጠ ይጠቅማል“ ብለንም ልንፎካከርም እንችላለን፡፡ መሠረታዊው ጉዳይ ሁላችንም ለዚህች ሀገር ጥቅምና የተሻለ ነገር ፍለጋ የተሰማራን መሆናችን ነው፤ እርግጠኝነትና ልባዊነት የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው ፡፡
ውድ የዚህ ታሪካዊ ፕሮግራም ታዳሚዎች
ብዕራችሁ የተባ፣ አዕምሯችሁ የሰላ እንዲሁም ተሳትፏችሁ ደግሞ የነቃ መሆን ዘመኑ ራሱ ይጠይቃል፡፡ መንግስት ይሄን ድባብ እንዲፈጠር አቅሙ የፈቀደውን ጠጠር መወርወር እንጂ የዜጎች ባላጋራና የዲሞክራሲ ስርዓት ደግሞ ደንቀራ መሆን አይገባውም፡፡ ይሄ ያፈጀበት አካሄድ ነው፡፡
በምንገነባው ስርዓት በዴሞክራሲ ግንባታ እና በሰብዓዊ መብት አያያዝ ያለፉትን ስርዓቶች መርገምና መውቀሳችን ሳያንስ በዚህ ዘመንም አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊቶች ተፈፅሟዋል፡፡ ብዙ ዋጋም አስከፍለውናል፡፡
ከዚህ በኋላ ፀረ-ዴሞክራሲ በቃ ብለናል፤ እያንዳንዱን ድርጊታችንና ስራችንን በንቃት ተከታታሉ፡፡ አካሄዳችንና ሁኔታችን ከዴሞክራሲ ያፈነገጠና የዜጎችን መብት የሚጋፋ ሆኖ በተገኘበት ጊዜ ሁሉ ልትታገሉን እና አደብ ልታስገዙን ይገባል፡፡
በዚህ አያያዝ ኢትዮጵያውያን በነፃ አገራቸው፣ በነፃነት የሚያስቡባት፣ በነፃነት የሚፅፉባት፣ ያለ ገደብ የሚመረጡባትና የሚመርጡባት፣ የዴሞክራሲና የፍትህ ስርዓትን የሚመሩና የሚያስተባብሩ የጋራ ተቋማት የተገነቡቧት፤ ዴሞክራሲያዊ አገር ባለቤት ይሆናሉ፡፡
ይህ የህዝብ ጎርፍ፣ ሚሊዮኖች ያላንዳች ልዩነት በተባበረና ከፍ ባለ ድምፅ እየዘመሩለት ያለውን ኢትዮጵያን የዳበረና የተረጋጋ ዴሞክራሲ ባለቤት የሆነች አገር የማድረግ ጉዞ ነው፡፡
ነገር ግን ዕዚህ ላይ ሊጤን የሚገባው አንድ ታላቅ ቁም ነገር አለ፡፡ ዲሞክራሲ እንደፈለግን እንድንሮጥ እንደሚያስችለን፤ ሁሉ ልጓምንም ያበጃል፡፡ ልጓሙ የየግል ሩጫችንን በህግ ጥበቃ የተበጀላቸው የሌሎች የዜጎችን መብቶች እንዳይጋፋ ሲባል የተበጀ ነው፡፡ እናም የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ነፃነትንና ሃላፊነትን በሚዛኑ ያያዘ መሆን ይገባዋል ፡፡
ውድ የዚህ ታሪካዊ ፕሮግራም ታዳሚዎች
ፍቅራችንና አብሮ የመኖር ዕሴታችን ዕንዲሁ በምስጋና ቀንና በሰላሙ ጊዜ ብቻ የምናሳያቸው ሳይሆኑ በችግርና በፈታኝ ወቅትም ቢሆን ፀንተው የሚቆዩ ሃብቶች ናቸው፡፡ በዚህ የአብሮነትና የአካታችነት ባህሪያችንን የሚሸረሸሩ አዝማሚያዎችን በጽናት ማውገዝ ይጠይቀናል፡፡
የአማራ ክልል ህዝብ በአገራችን ቀደምት የገናናነት ታሪክ የበኩሉን ወሳኝ ሚና የተጫወተ ባለታሪክና ኩሩ ህዝብ ነው፡፡ አለመታደል ሆኖ ያ! የገናናነት አገራዊ ቁመና ተቀይሮ የከፋ ድህነትና ኋላቀርነት ቸነፈር ውስጥ ብዙ ዋጋ የከፈለ ነው፡፡ የአማራ ብሄር በታሪክ፣ በባህልና በቋንቋ እንዲሁም በሌሎች እሴቶች በአገር ግንባታ ሂደት ትልቅ ቦታ ያለው ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ስርዓቶች ጥቂቶች ከሌሎች አካላት ጋር በጥቅም ተሳስረው በፈፀሙት ስህተት፤ በአማራው ላይ በተካሄደ የተሳሳተ አስተምህሮ ሰፊው የአማራ ህዝብ በሌሎች ህዝቦች በዳይ፣ ዕዳ ከፋይና የተለየ ተጠቃሚ መስሎ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ በዚህ ብዙ መፈናቀል፤ ተጠርጣሪ እና ለሌሎች ችግሮች እንዲጋለጥ ሆኗል፡፡
ከዚህ አኳያ የነበሩ ስህተቶችን በማረም የብሄራችንን እና የሃገራችንን ክብር ተመልሶ ገናናነታችንን ለማረጋገጥ መረባረብ ይገባናል፡፡ "ትልቅ ነበርን፤ ትልቅም እንሆናለን!" ይለዋል እንዲህ ነው፡፡
ውድ የዚህ ታሪካዊ ፕሮግራም ታዳሚዎች
ይህን ታላቅ ክልላዊና አገራዊ ራዕይ እውን ለማድረግ መሪ ድርጅቱ ብአዴን/ኢህአዴግ ላስመዘገባቸው ጅምር ስራዎች እንደሚመሰገን ሁሉ ላጠፋውና ላጎደለው ሃላፊነቱን ይወስዳል፡፡
አሁን የተጀመረው የለውጥ ማዕበል ካለፈው ጉድለት ተምሮ በፅናት መጓዝን ይጠይቃል፡፡ ይህን የለውጥ ማዕበል በሙሉ ልብ ተቀብሎ ድርሻን መወጣት የግድ ይላል፡፡ ከዚህ ውጭ በእኔ አውቅልሃለሁ ፈሊጥ መንታ መንገድ መወጠን አይቻልም፡፡ መፍትሄው የህዝብን የለውጥ ፍላጎት አድምጦ ከእሱ ጋር በመሰለፍ ለውጡን በትክክለኛ አቅጣጫ መምራት ብቻ ነው፡፡
ኢትዮጵያ አንዳንዶቻችን የቅንጦት ህይወት የምንገፋባት እና እንዳሻችን የምንፈነጭባት፤ ሌሎቻችን ደግሞ ባይተዋር የምንሆንባት ሀገር መሆን የለባትም፡፡ እናም በእናት አገርና በጋራ ጎጇችን በእኩልንትና በፍቅር እንኖራለን፡፡
አገራችን በተያያዘችው የለውጥ መንፈስ አስቀድመው ለተፈፀሙ እኩይ ታሪኮች ዳግም እንዳይፈፀሙ ትምህርት ወስደንባቸው፤ አዲስ ታሪክ ለመስራት ደግሞ የተለኮሰውን መነሳሳት ሂደቱን በአግባቡ ልንመራውና ልንገራው ይገባል፡፡
በቅርቡ በመዲናችን አዲሳ አበባ በንፁሃን ዜጎቻችን ላይ የደረሰው ጉዳት በአገራችን የሚደረገው የዴሞክራሲ ስርዓት ምንም እንኳን በወሳኝነት በፍጥነት መጓዝ እንደሚቻል ከወዲሁ አፋችን ሞልተን ለመናገር ቢያስችለንም ሂደቱ የአልጋ ባልጋ ጉዞ እንደማይሆን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ክስተት ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ እኔና ባልደረቦቼ ክልላችንና ኢትዮጵያን የተረጋጋና የዳበረ ዴሞክራሲ ባለቤት የማድረግ የቤት ስራን ዳር ለማድረስ ከህዝባችን ጋር በመሆን በፅናት እንደምንዘልቅ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡
በታሪካችን አንዳችን በሌላችን ላይ ተነስተናል፡፡ ሲከፍም ቃታ ስበን አንዳችን የሌላችንን አካል አቁስለናል፡፡ አልያም አጉድለናል፡፡ ምንም እንኳ ትናንት የተከሰቱ መጥፎ ታሪኮችን መዘንጋት ሰዋዊው የማስታወስ ችሎታችን የማይፈቅድልን ቢሆንም ለወደፊት የጋራ ጥቅምና ጉዞ ሲባል ሆን ተብሎ እኩይ ትዝታዎችን መቀየር በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡
እናም እንደዚህ ዓይነቱን ቅስቀሳና ውትወታ የሚያስተላልፉት ሃይሎች ጆሮ ዳባ ልበስ ልንላቸው ይገባል፡፡ አማራ የሚታወቅበት መለያ ባህሪው አካታችነቱና አቃፊነቱ ነው፡፡ አማራ የሚታወቅበትን እሴቶችን ጠብቆ መቀጠል የሚገባው ሲሆን፤ ተናጥል ችግሮች እንኳ ቢያጋጥሙ ህዝብን እና ግለሰብን ለይቶ እንዲታረም እና እንዲስተካከል ማድረግ እንደሚገባ፤ ከዚህ ውጭ የጥላቻ፣ የዘረኝነት፣ የበቀል እና የጎጠኝነት አረሞችን በማስወገድ ብቻ ሳይሆን ይህው ለትውልድ እንዳይተላለፍ ተግተን መስራት ይኖርብናል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ከይቅር ባይነት በላይ የምናከብረውና ዋጋ የምንሰጠው ነገር የለም፡፡ “ ይቅርታ” በልባችንም በመሐላችንም ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ዛሬም ይህንን ቦታውን ልናሰፋ መሐላችንም ይቅርታ እርስት እንዲሆን እንውደድ፡፡ ይቅር አንባባል፡፡ ለየአካባቢው የሚታየውን ግጭትና መቃቃር ከመሠረቱ አክስመን በይቅርታችን እንደይመለስ አድርገን እንጠበው፡፡
ኢትዮጵያውያን ነንና ይሄ አያቅተንም፡፡ በትንሹም ሆነ በትልቁ ሆድ መባባስ ቀርቶ አንዳችን ለሌሎችን የፍቅር ማዕድና አውድ እንሁን፡፡
በሚሊዮኖች ተደግፎ የተቀጣጠለው ለውጥ ወደ ኋላ መመለስ ቀርቶ ማዝገምን አይታገስም፡፡ መፍትሄው በህዝብ ባለቤትነት እና በወጣቱ መሪነት በፍጥነት መጓዝ ነው፡፡ ካሁን በኋላ ሃገራችን ለሁሉም በእኩል የተመቸች፤ ዜጎቿ እኩል የሚደመጡባት፤ እኩል የሚሳተፉባት የጋራ ማዕዳችን ሆና ትቀጥላለች፡፡ ለዚህ እውን መሆን በፅናት መታገል ይኖርብናል፡፡
ከዚህ አኳያ የስራ ባልደረቦቼ እና እኔ ቴዎድሮስና ገብርዬ ሆነን ተጋግዘን፤ አለቃ እና ምንዝር ሳንሆን ፤ የአንድ አላማ ተሰላፊዎች በመሆን ህዝባችንን የሰላም፤ የዴሞክራሲ እና የልማት ፍላጎት ዳር እናደርሳለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ አበክሬ ላነሳ የሚገባ አንድ ቁም ነገር አለ፡፡ በኛ በአመራሮቹ በኩል፤ ህዝቡን በሚፈለገው ደረጃ ያለማዳመጥ፤ ያለማቀፍ፤ ያለማቅረብ፤ እና ለያይቶ ማየት ችግር አለ፡፡ እንዲሁም በምሁራኑ እና በወጣቱ እንዲሁም ባለሃብቱ የዳር ተመልካች የመሆን እና በራስ አገር ላይ ባይትርነቱ ተስተውሏል፡፡
ክልላችንም ሆነ ሃገራችን ወደ ፊት ሊገሰግሱ የሚችሉት እና በለውጡ ዘልቀው ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡት እኛ አመራሮቹ ችግራችንን ቀርፈን አቃፊና ደጋፊ ስንሆን ወጣቱ፤ ምሁሩ እና ባለሃብቱ ደግሞ ባይዋርነቱን ትቶ የሃገሬ እና የክልሌ ጉዳይ ያገባኛል ደግሞም አመራሮቹ፤ የኔ ክፋይ ናቸው ብሎ አብሮ ሲሳተፍ እና ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲገባ ብቻ ነው፡፡
እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ ከእንግዲህ እንደማንሳሳት ሳይሆን እንደምናደምጣችሁ፣ እንደከዚህ ቀደሙ ዘግይተን ሳይሆን ፈጥነን እንደምንመልስላችሁ እና በዚያው ፍጥነት እንደምንስተካከል ነው፡፡ ምስጋናችሁን ብቻ ሳይሆን ተግሳፃችሁን ከልብ ሰምተን ፈጥነን ለመታረም ዝግጁ መሆናችንን በልበ ሙሉነት አረጋግጥላችኋለሁ፡፡
በተቻለን መጠን ባለን አቅም ሁሉ በህዝባዊነት እንደምናገለግላችሁ፣ ደከመን ሠለቸን ሳንል ሃላፊነታችንን ለመወጣት ጥረት እንደምናደርግ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡
"የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ!" በሚል ዕሴት ታንፆ ለቃሉና ለማዕተቡ ታማኝና ሟች ከሆነ የታላቁ ህዝባችን ክፋዮች ነንና ይህንን ቃል እንጠብቃለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ ብአዴን በአማራው ስም በውጭ አገር የተደራጁና ለሱ የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅች፣የተለያዩ ማህበራዊ የሚዲያ ተቋማት በሰላም ለመንቀሳቀስ እስከወሰኑ ድረስ ወደ ክልላችን መጥተው እንዲቀሳቀሱ ጥሪ እያስተላለፈ እኛም ከግማሽ መንገድ ድረስ ተጉዞ ለህዝባችን ጥቅም መከበር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናችንን አረጋግጣለሁ፡፡
በመጨረሻም ለሰጣችሁን ክብርና ላሳያችሁን ፍቅር ከወገቤ ጎንበስ በማለት እጅ እየነሳሁ በሰላም ወደ የአካባቢችሁ እንድትመለሱ ከአደራ ጭምር እጠይቃለሁ፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቸ ትጋትና ቁርጠኝነት በልጽጋ ፣ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!!!
አመሰግናለሁ
Sunday, July 1, 2018
የኢፌዴሪ ም/ጠ/ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ም/ሊ/መንበር ጓድ ደመቀ መኮንን ዛሬ በባህር ዳሩ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ያደረጉት ሙሉ ንግግር
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
Recent Articles
Recent Video Uploads
Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube
Ethiopia Today
- Active a minute ago with many
- videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies, Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time
No comments:
Post a Comment