የኢትዮጵያ አዲሱ የለዉጥ ጉዞ በሲ ኤን ኤን እይታ። ሲ ኤን ኤን ኢትዮጵያን በሚመከከት ባወጣዉ ሰፋ ያለ ትንታኔ በሀገሪቱ ታሪክ ያልተስተዋለ ፖለቲካዊ ለዉጥ እየተካሄደ መሆኑን አስነብቧል፡፡
በቅርቡ ወደ ስልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የለዉጡ መሪ ናቸዉም ብሏል፡፡ የወሰዷቸዉ ወሳኝ እርምጃዎች እና ያሳለፏቸዉ ዉሳኔዎች የፖለቲካ ካርታዉን በመቀየር እና የህዝቡን እምነት በማግኘት ረገድ ጉልህ ሚና ተጫዉተዋል፡፡
ሲኤን ኤን በትንታኔዉ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የዶ/ር አብይ አስተዳደር ካከናወናቸዉ ተግባራት መካከል የፖለቲካ እስረኞችን መፍታቱ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳቱ፤ የአልጀርስ ስምምነትን ለመቀበል መወሰኑ እና በመንግስት ስር ሲተዳደሩ የቆዩ ዘርፎችን ለባለሀብቶች ለማዛወር ማቀዱ ይጠቀሳሉ ይላል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ከሹመተ በዓላቸዉ በኋላ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር የህዝቡን ብሶት አድምጠዋል፡፡ መንግስታቸዉም ዲሞክራሲን ለማስፈን እና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ተጨባጭ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ለህዝቡ አረጋግጠዋል ሲል አስፍሯል ትንታኔዉ፡፡
የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸዉ፤ ከተቃዋሚዎች እና ከህዝቡ ጋር የለዉጥ ዉይይቶች መካሄዳቸዉ፤ ከሀገር ለተባረሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ወደ ሀገራቸዉ እንዲገቡ ጥሪ መቅረቡ፤ እንዲሁም በደህንነት፤ ፍትህ እና ሌሎች ተቋማት የአመራር ለዉጦች መደረጋቸዉ በጎ ጅማሬዎች ናቸዉ ብሏል ትንታኔዉ፡፡
ዶ/ር አብይ አዲስ የታሪክ መክፈታቸዉን እና በህዝቡ የተስፋ ጭላንጭል ማሳደራቸዉንም አስፍሯል፡፡
የኢትዮ ኤርትራ ደም አፋሳሽ ጦርነት በትንታኔዉ ተብራርቷል፡፡ መቶ ሺ የሚገመት ሰዉ የተሰዋበት ጦርነት መንስኤ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ መሆኑ በሁለቱ መንግስታት ቢቀርብም የተወሳሰበ ታሪካዊ እና ባህላዊ ስረ-መሰረት እንዳለዉ አሳይቷል፡፡
የኢትዮ-ኤርትራ ወታደረዊ ግጭትን ለማስቆም እና ማህበራዊ ብሎም ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ እ.ኤ.አ በ2000 የአልጀርሱን የሰላም ስምምነት ሀገራቱ ፈርመዋል፡፡ ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያ መንግሰት የስምምነቱን መፈጸም ሳይቀበል ቀርቷል፡፡
የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቱን ለማሻሻል የአልጀርሱን ስምምነት መቀበል እንደ ቅድመ ሁኔታ ላለፉት 16 አመታት ሲያስቀምጥ ቆይቷል ይላል ትንታኔው፡፡
የዶ/ር አብይ አስተዳደር የአልጀርስ ስምምነትን ለመቀበል መወሰኑ የኤርትራን ጥያቄ የመለሰ ነው፡፡ በዚህም የኤርትራ መንግስት ለ16 አመታት ሲያነሳው የቆየውን ምክንያት ዳግም በቅድመ ሁኔታነት ማቅረብ አይችልም በማለት ትንታኔው ያብራራል፡፡ ውሳኔውም የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያከበረ እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ብሎም በቀጠናው ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን የሚያስችል ነው ይላል የሲኤን ኤን ዘገባ፡፡
በተጨማሪ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከመንግስት ቁጥጥር ነፃ ለማድረግ የተላለፈውን ውሳኔ ተመልክቷል፡፡ ውሳኔው እንደ በረራ፣ ሀይል፣ ቴሌኮም እና ሌሎች ዘርፎችን ሙሉ በሙሉ አልያም በከፊል ለግል ባለሀብቶች ለማዘዋወር ያለመ ነው ሲል ትንታኔውን ያትታል፡፡
እንደ ትንታኔዉ ከ1997ቱ አወዘጋቢ ምርጫ በኋላ የኢህአዴግ መንግስት የልማታዊ ዴሞክራሲ ኢኮኖሚ ጽንሰ ሀሳብን በዋናነት መከተል ጀምሯል፡፡ ባለፉት አስርት አመታት ፈጣን እድገትም አስመዝግቧል፡፡ በዓለማችን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ካስመዘገቡ ሀገራት ተርታም ኢትዮጵያ ተመድባለች፡፡ ሆኖም የእድገቱን መጠን እና የአህዛዊ የመረጃዎችን ታማኝነት ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገቡ ምክንያቶች ተስተውለዋል፡፡
ለአብነትም ፍትሀዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል ተጠቃሽ ነው፡፡ ቀደም ሲል በሀገሪቱ ሲተገበር የቆየዉ ልማታዊ ዲሞክራሲ ኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም ለሙስና እና ለመሬት መሸንሸን የተጋለጠ እንዲሁም አያሌ ዜጎችን ያለ በቂ ካሳ ለመፈናቀላቸዉ መንስዔ መሆኑን ይገልጻል፡፡
የዶ/ር አብይ አስተዳደር መሰል እና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ አዲስ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አካሄድ መከተል መጀመሩን የተላለፉ ዉሳኔዎች ያሳያሉ ሲል ትንታኔዉ ያስረዳል፡፡
ትንታኔዉ በመጨረሻም አዲሱ ኢኮኖሚያዊ አካሄድ ችግሮች ሊገጥሙት አንደሚችሉ እና መንግስት ጥንቃቄ ማድረግ አንዳለበት ጠቁሟል፡፡ ለአብነት እጅግ ትርፋማዉን የበረራ ዘርፍ ለባለሀብቶች ማስተላለፍ የተፈለገበት ምክንያት ግልጽ አለመሆኑን ጠቅሶ ዉሳኔዉ የበረራዉ ዘርፍ ለሀገር የሚያስገኘዉን ገቢ ሊቀንስ ይችላል ነዉ ያለዉ፡፡
የዉጭ ባለሀብቶች ወደ ዘርፎቹ ሲሰማሩ የሀገር ዉስጥ ባለሀብቶች ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድሩ መሠራት አለበት፡፡የህዝቡ እኩል ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እና ሙስናን የመሳሰሉ ችግሮችን ለመቀነስ ጥልቅ የሆነ ጥናት እና ክትትል ያስፈልጋል በማለት ትንታኔዉን ይቋጫል፡፡
በቢኒያም መስፍን
ምንጭ፡- ሲ ኤን ኤን
Thursday, June 14, 2018
የኢትዮጵያ አዲሱ የለዉጥ ጉዞ በሲ ኤን ኤን እይታ
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
Recent Articles
Recent Video Uploads
Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube
Ethiopia Today
- Active a minute ago with many
- videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies, Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time
No comments:
Post a Comment