ለማ መገርሳ ጃዋርንና አሜሪካን መክሰሳቸዉ፣ ህወሃት በመቀሌ ደመር መቀመጡ እና ብአዴን አዉራዉ እንደጠፋበት ንብ መተራመሱ
(ሚኪ አማራ)
ለማ መገርሳ ጃዋርንና አሜሪካን መክሰሳቸዉ፡ ህወሃትና ሌሎችም
ለማ መገርሳ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የኦሮሞ ተቃዋሚዎችን ከረር ባለ ቋንቋ ሸንቁጠዋቸዋል፡፡ እኛን ትንቁናላችሁ ግን መሬት ላይ ሁነን ነጻ እያወጣናችሁ ያለነዉ እኛ ነን የሚል ግልጽ መልክት አስተላልፈዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እነ ጃዋር እነ በቀለ ገርባን እኛ ነዉ ያስፈታናቸዉ ስለሚሉ ኦቦ ለማ በነሱ ሃይል ሳይሆን በኦህዴድ ሃይል እንደተፈቱ ተናግረዋል፡፡ በተለይም የኦፌኮዉ በቀለ ገርባ ሰሞኑን ከጃዋር ጋር አባቴ ሌጄ እየተባባሉ ሽር ብትን ሲሉ ኦቦ ለማ ከህወሃት ደህንነት ጋር የተናነቁት ነገር ትዝ እያላቸዉ ሳያበሳጫቸዉ አይቀርም፡፡ ይህንም ሲያብራሩ የዛሬ ሁለት ወይም ሶስት አመት ለምን አላስፈታችሁም እኛ ከመጣን በኋላ ነዉ ይህ ሁሉ ነጻነት የመጣዉ አይነት ነገር ነዉ፡፡ እኛ በሰራነዉ ተቃዋሚ እና ጃዋር የሚመሰገንበት ምክንያት የለም ነዉ፡፡ይህ ከአሁኑ በኦህዴድና በተቃዋሚዉ ኦፌኮ መካከል ሊኖር የሚችለዉን ሁኔታም ሊያመላክት ይችላል፡፡ ከዛም በላይ ሰሞኑን የገቡት የኦነግ ሰዎች ዝም ብሎ በችሮታ እንዳልሆነ እና የኦህዴድ ትግል ዉጤት እደሆነ እንዲገነዘቡት ነዉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ኦህዴድ ከህወሃት ጋር እየተናነቀ ባለበት ጊዜ የአሜሪካኖች ዝምታ እና አግዙን የሚለዉን የነለማን ጥሪ ጀሮ ዳባ ልበስ ብለዉ መቆየታቸዉ ኦቦ ለማ እንዲኮንኑት አስገድዷቸዋል፡፡ አሜሪካኖች ኦህዴዶችን የመገንጠል ጥያቄያቸዉን እንዳያነሱ ማረጋገጫ እስኪያገኙ ለመደገፍ ተስኗቸዉ ነበር፡፡ እነ ለማ አዲስ አበባ ያለዉን ኤምባሲ ለማናገር እንኳን ፈልገዉ አልተሳካላቸዉም ነበር፡፡ ከነ ለማ ይልቅ ኤምባሲዉ ደመቀ መኮነንን ጠርቶ ስለ አገሪቱ ጉዳይ አናግሯቸዋል፡፡ ህወሀት በተደጋጋሚ የዲፕሎማሲ መስመሩን በመጠቀም አገሪቱን ሊያፈርሷት ይችላሉ ይሄም እዳዉ ለአሜሪካ ነዉ የሚል ዉትወታ በማሰማታቸዉ የአሜሪካ ዉጭ ጉዳይ ቢሮ አምኖ ተቀብሎ ነበር፡፡ ዶ/ር ቴወድሮስ ጀኔቭ ላይ የአሜሪካን ተወካይ በተባበሩት መንግስታት Nikki Haley ን ከአንዴም ሁለቴ አግኝተዉ የኦህዴድን አካሄድ ለአገር አደጋ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ህወሃት ከግርማ ብሩ የተሻለ የኔን አጀንዳ በአሜሪካ ያስፈጽምለኛል ብሎ የላከዉ ካሳ ተክለብርሃንም አዲስ ቢሆንም በስቴት ዲፓርትመንት የህወሃት ደጋፊዎችን በማግኘት የራሱን ሙከራ አድርጓል፡፡ በዶ/ር ወርቅነህ ቀስ እያለ ወደ እነ ለማ መስመር መግባቱ ያስፈራዉ ህወሃት በሱ ስልጣን ላይ ተጨማሪ የመካከለኛዉ ምስራቅና የአሜሪካ ልዩ ተወካይ በማድረግ ስዩም መስፍንንና ግርማ ብሩን ስልጣን ሰቶ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ሰወች የቆዩ እና ከአሜሪካኖች ጋር ጥሩ ግንኙነት ስላላቸዉ ህዋሀት የኔን ፓወር ለማስቀጠል ይጠቅሙኛል ብሎ ነበር የሾማቸዉ፡፡ ነገር ግን ግርማ ብሩም ቀስ በቀስ እነለማን በመደገፉ ለአሜሪካኖች ሀገር የማፍረስ ምንም አይነት ተልኮ እንደሌላቸዉ እና ለዲሞክረሲና ለዉጥ የቆሙ ናቸዉ ብሎ የራሱን ድርጅት አወዳድሶ ተናግሯል፡፡
ከዛም በላይ ዶ/ር ወርቅነህ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ከሁለት ጊዜ በላይ የአሜሪካን የመንግስት ሰወች በኒዉዮርክና ዋሽንግተን ተገኝነተዉ የኦህዴድን ፍላጎት አስረድተዋል፡አሜሪካኖችም ይህን ማረጋገጫ ፕራክቲካሊ ማየት እንደሚፈልጉ ስላስረዱ እነ ለማም ከመቸዉም በላይ ኢትዮጵያን ከፍ አድርገዉ አወደሷት፤ ስለ አገር እና የህዝቦች አንድነት አወሩ፡፡ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የአሜሪካን መንግስት ማሳመን የቻሉ ሲሆን ለዚህም መልስ የአሜሪካ መንግስት እነ ደ/ር አብይን እንደሚደግፍ በጊዜዉ የሰቴት ዲፓርትመንት የአፍሪካ ጉዳዮች ተወካይ የነበሩትን ያማማቶን ወደ አዲስ አበባ በመላክ አቋማቸዉን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ሰሞን ህወሃቶች ይህ የአገር ልዋላዊነት ጉዳይ ነዉ ብለዉ ሲጮሁ እንደነበር እናስታዉሳለን፡፡ በሚያዚያ ወር ላይ የግርማ ብሩን ኦህዴድን ጠቅሸ ጽፌ ነበር (ስክሪን ሾት ያደረኩትን ማየት ይቻላል)፡፡ በመሆኑም ቢያንስ የአማካሪነት ቦታ ይሰጠዋል የሚል እሳቤ ነበር፡፡ አሁን ምን እንደሆነ አላዉቅም፡፡ ኦህዴድ በጥርጣሬ አይን ሲያዩት የነበሩት ዶ/ር ወርቅነህ ግን ወደ መጨረሻዉ ሙሉ ለሙሉ የእነ ለማ ደጋፊ በመሆኑ እና ማገዙን ተከትሎ ያለበትን ቦታ ይዞ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ ለማንኛዉም ለማ አሁን የአለም መንግስታት እየተለማመጡን ነዉ የሚሉት እንግዲህ አሜሪካኖችንና እንግሊዞችን (እንግሊዞች ምናልባትም አንዳርጋቸዉን ለማስፈታት ስልጠየቁ ይሆናል) መሆኑ ነዉ፡፡ አሁን ባለዉ ሁኔታ አሜሪካኖች ለኦህዴዶች ማንኛዉንም ድጋፍ አንደሚያደርጉ ቃል ገብተዉላቸዋል፡፡ አሜሪካ በእርዳታ የምትሰጠዉ ገንዘብ ተመልሶ አዉሮፓ ሄዶ እንደሚቆለፍ መረጃዉ ስላላቸዉ አይዟቹህ ገንዘቡን ማስመለስ ከፈለጋችሁ ማንኛዉንም እርዳታ እናደርጋለን ማለታቸዉ ይታዉቋል፡፡
በዚህ የግንቦት 20 የለማ ንግግር ሌላ መርዶ ለህወሃት መቶለታል፡፡ ፖለቲካል ስልጣኑን ከህዋት የተረከበዉ ኦህዴድ አሁን ደግሞ የኢኮኖሚ ነጻነት ያስፈልገናል ብሏል፡፡ እንግዲህ ኦሮሚያ ዉስጥ በባለሃብቱና በወታደሩ በኩል ሰፊ የኢኮኖሚ ኢንተረሰት ያለዉ ህወሃት ሌላ ጣጣ ከፊቱ መቶበታል፡፡ ሃጎስ ቡና ብሎ አሜሪካና አዉሮፓ ወስዶ መሸጥ ብርቅ ሊሆንበት ይችላል፡፡ በቅርብ ቀን ገምሹ ቡና የሚል ብቻ ነዉ ልናይ የምንችለዉ፡፡
ህወሃት
ህወሃት በዚህ ሁለት ቀን ዉስጥ ደመር ላይ ተቀምጧል፡፡ ደመር ማለት ያዉ የሆነ ሰዉ ከሞተ በኋላ በሳምንቱ ያልደረሱት ሰወች እንዲደርሱት የለቅሶ ፕሮገራም ይያዝና ሰወች ለቅሶ ይደርሳሉ፡፡ ያዉ ህወሃት ከሞተ ሰነባብቷል ለቅሶ ያልደረሱ የብአዴን እና ደህዴን ሽማግሌዎች ደመሩ ላይ ተገኝነተዉ ሲያለቅሱ ነበር፡፡ ለቅሶዉም የእኛ ያልሆነ አስተሳሰብ ነዉ የገደለን፤ በዉስጣችን የተሰበሰቡት አፍራሽ ሃይሎች ነዉ የገደሉን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ የሚያወሩት ቢያጡ እራሱ ከእንግሊዞች ጋር በጀግንነት ተዋግቶ ለሃገሩ እራሱን የገበረዉ አጤ ቴወድሮስ ለምን በቴሌቪዥን ይታያል የሚል ወሬ ሲያወሩ ነበር፡፡ ህወሃት ምንም ሃሳብ ማመንጨት እንደማይችል የታየበትና የሃሳብ ድርቅ እዛ ሰፍር እንደተንሰራፋ በገሃድ የሚሳይ ደመር ነበር፡፡ ንጉሱ የሚባል ሰዉየ አይተ ዘራይን ለምን ቆጣ ቆጣ እያለ ተናገረዉ፤ እከሌ የሚባል እስረኛ ለምን ተፈታ ኧረ እንዲያዉም ጎንደሮች ለምን ነጭ ጤፍ እንጀራ ይበላሉ አይነት ጥያቄ ሁሉ ሳልሰማ አልቀረሁም፡፡ባጠቃላይ 27 አመት መንግስት ሁኖ ከቆየ ድርጅት የማይጠበቅ የጠላ ቤት ወሬ በቀጥታ በቴሌቪዥን ማየታችን እዛ ማዶ መንደር የሃሳብ እጥረት እና እርጅና እንደተከሰተ ያስታዉቃል፡፡ ህዋሀት የፖለቲካ ሽንፈት እንደደረሰበት አምኖ ተቀብሎ አሁን እንደምንም የኢኮኖሚ ኢንተረስቱ እንዳይነካ የሚጣጣር ይሆናል፡፡ ባጠቃላይ ግን ህወሃት የራሱን ቤዝ ወደማጠናከሩ የዞረ ይመስላል፡፡ በሌላዉ የአገሪቱ አካባቢ እና በፌደራል ደረጃ ያለዉ ተጽእኖ ቀላል እንደማይሆን የተረዳዉ ወደ ዉስጡ የዞሮ ይመስላል፡፡ብአዴን
ብአዴን እስከ 2012 እንኳን የሚቆይ አይመስለም፡፡ ምኑን ይዞ ምኑን እንደሚጨብጥ ግራ ገብቶታል፡፡ ተከፋፍሎና ተኮራርፎ መግለጫ እንኳን ለመስጠት ወኔ አቶ አይተነዋል፡፡ መቀሌ ላይ የተገኘዉ የብአዴኑ ቁንጮ ህላዊ ዮሴፍ ብአዴን በስብሷል የኛ ያልሆነ የዘቀጠ አስተሳሰብ ግብቶበታል እኔም ከዚህ መንዳ የለዉበትም ወጥቻለዉ ትምክተኛ እና ነፍጠኛ ማለት እንኳን ማለት አልቻለንም ብሎ በቴሌቪዠን የራሱን ድርጅት መቀሌ ላይ አንበላዉሶታል፡፡ እኔ ብአዴንን ብሆን እንደዚህ ዝቃጩ ነዉ የተጠራቀመበት ብሎ እየተሳደበ እዛዉ መቀሌ ሳይወጣ ሁለት መስመር ደብዳቤ ከድርጅቱ የሚያሰናብት ፋክስ አደርግለት ነበር፡፡ ግን ማን ያደርጋታል፡፡ እንደዚህ እየተባሉ ብአዴን ከመሆን እዉነት ወደ ነበሩበት የዲኤ ስራ መመለስ ይሻላል፡፡ ለማንኛዉም ብአዴን ህወሃትን ቢንከባከበዉም ከዉግዘት አልተረፈም፡፡ መቀሌ ላይ እንዲሰማ ተብሎ በአማረኛ ስብሰባ ተዘጋጅቶለት ብአዴን የሚባል ቡድን ቢስተካከል ይሻለዋል አይነት ዛቻ ተላልፎለታል፡፡ እኔ ግን የሚገርመኝ ብአዴን እንዲህ ለህወሃት እያሽቋለጠ ህወሃት ግን ሁሌም ይከሰዋል፡፡ ነገ አዲሱ የአማራ ፓርቲ ወደ ስልጣን ሲመጣ ህወሃት ምን ሊዉጠዉ ነዉ፡፡ ህወሃት በነገራችን ላይ ኦህዴድንና ደህዴንን ሲናገር ሰምቸዉ አላዉቀም፡፡ ብአዴንን እንደ ዉሽማዉ ስለሚያየዉ እንደፈለገ ነዉ የሚጫወትበት፡፡ ለማንኛዉም አዉራዉ እንደጠፋበት ንብ ብአዴን ወዲያ እና ወዲህ እየተንገዋለለ ነዉ፡፡ በተለይም ሰሞኑን ገዱ አንዳርጋቸዉ በጉብኝት እንዲሁም የባልተቤቱን ህክምና ለመከታተል ከባህርዳር አካባቢ በመጥፋቱ ብአዴን አባት እና እናት እንደሌለዉ ልጅ ተበታትኖ የት እንደሰነበተ አልታወቀም፡፡
ባጠቃላይ መቀሌ፤ አዳማ እና አዲስ አበባ ላይ እየተወራ ያለዉ የፖለቲካ ልዩነት እና ባህርዳር ላይ ያለዉን ጉምጉምታ ስናየዉ በዚህ ድርጅት ዉስጥ ያለዉ ጦርነት ገና እየተፏፏመ እንጅ እየቀነሰ አይመስልም፡፡ በዚህም ምክንያት ሃምሌ ላይ ኢህአዴግ ወደ አንድ ግንባር ያድጋል የሚለዉ ሃሳብ ዜሮ ነዉ፡፡ ህወሃት በዚህ uncertainty በበዛበት ወቅት ወደዚህ ዉሳኔ ደፍሮ ይሄዳል ተብሎ አይታሰብም፡፡
No comments:
Post a Comment