Sunday, May 27, 2018

ዶ/ር አብይ አህመድ 27ኛውን የግንቦት 20 የድል በዓል ምክንያት በማድረግ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት

የግንቦት ሀያ የድል በዓል ስናከብር ከውስጣችንም ሆነ ከውጪያችን አስታርቀውን ለራሳችንም ሆነ ለሌላው አዎንታዊ እይታን በሚያስታጥቁን መልካም ተግባራት ታጅበን መሆን አለበት
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ 27ኛውን የግንቦት 20 የድል በዓል ምክንያት በማድረግ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች፤ እንኳን ለ27ኛው አመት የግንቦት 20 ድል በአል በሰላም አደረሳችሁ! 27ኛውን የግንቦት 20 የድል በዓል ስናከብር ከውስጣችንም ሆነ ከውጪያችን አስታርቀውን ለራሳችንም ሆነ ለሌላው አዎንታዊ እይታን በሚያስታጥቁን መልካም ተግባራት ታጅበን እንዲሆን ከዚህ በፊት ከነበረው በተጨማሪ የሚከተሉትን 6 ጉዳዮች በመከወን እንዲሆን ከተለየ ፍቅርና አክብሮት ጋር ጥሪዬን አቀርባለሁ፡:
1ኛ ሀሉም ሰው ከራሱ ጋር ተፈላልጎ ለመገናኘት ግንቦት ሀያ የጥሞና ጊዜ እንዲሆን ወደራስ ተሰዶ ከራስ ጋር መገናኘትም ሆነ አለምን አነፍንፎ አጽናፋዊ መስተጋብር መፍጠር ዛሬያችንን በውል እንድንኖርም ሆነ ነጋችንን እንድናሳምር ለማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ከባቢን ለመረዳትም ሆነ ለመግራት ወደውስጣችን በመመልከት ከራስ ጋር በሚደረግ እርቅ እና የጥሞና ሰዓት ነፍሳችንን በአዎንታዊ ሀይል መሙላት እጅጉን ወሳኝ ልምምድ መሆን አለበት፡፡
የአርበኝነት፣ የድል፣ የትግል እና የአይበገሬነታችን ተምሳሌት የሆኑ ብሄራዊ በአሎቻችንን በምናከብርበት ወቅት ከክበረ-በአልንት ባሻግር የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ተላብሰን መሆን አለበት፡፡ ለራሳችን የጥሞና ጊዜ ኖሮን በዚህ መልካም የስሜት እና የመንፈስ እነጻ ልምምድ ውስጥ ራሳችንን በውል ለመረዳት እና ከራስ ጋር እርቅ ለማድረግ ምቹ መደላድል ይፈጥርልናል፤ ሰው ከምንም ነገር በፊት ከራሱ ጋር መታረቅ ይገባዋልና፡፡ ከራሱ ጋር የታረቀ ዜጋ ከየትኛውም ሃሳብ ሆነ- ከየቱም ግለሰብ ጋር ለመታረቅ በፍጹም አይቸገርም፡፡
2ተኛ ይህን ክብረ በአል ስናከበር ከጎረቤቶቻችን እና ከቅርብ ሩቅ ወዳጆቻችን ጋርም ያሉ ክፍተቶችን በእርቅ እና በይቅርታ የማከም የጋራ ባህል እንዲኖረን በጽናት መስጠትን መለማመድ ይገባናል፡፡ ይህች የምንሳሳላት እና የምንወዳት ሀገራችን ሰላም የምትሆነው፣ ጋራ ሸንተረሯ የሞት ሲላ የሚዞረው ሳይሆን የሰላም ምሳሌዎቹ እርግቦች በጣፋጭ ዜማቸው ዙሪያ ገባው የሚደምቀው፣ ከራሳችን ጋር ስንታረቅ፤ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ይቅር ስንባባል ብቻ ነው፡፡
በመሆኑም ይህ የግንቦት 20 የድል በአልን በምናከብርበት ቀን በተለያዩ ምክንያቶች የተኳረፉ ወዳጆች፣ ጎረቤታሞች፣ የትዳር አጋሮች ወዘተ.. ይቅር በመባባል ሰላም እንዲያወርዱ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡
3ተኛ ውስጣዊ እርጋታና ጽናታችን ያልተሸራረፈ- ውጫዊ አረዳድና ተግባቦታችንም ያልተዛነፈ ሆኖ ከራስ እስከ ሀገር የሚዘልቅ ፍቅር እና ሰላም ይኖረን ዘንድ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ድጋፋችንን ከሚሹ ወገኖች ጎን መቆም እና የታመሙ ሰዎችንም መጠየቅ፣ የታረዙትን የማልበስና ደካሞችን በማገዝ ግንቦት 20ን ማክበር ይገባናል፡፡
ከሀገራችን ሰማይ ስር በገጠርም ሆነ በከተማ፤ በየብስም ሆነ በውሀ፤ ከሜዳውም ሆነ ከተራራ፤ መሀልም ሆነ ዳር ላይ የሚሰፈው ሰላም የሚመነጨው ከእኛ እና በዙርያችን ካሉ ሰዎች አስተሳሰብ ውስጥ ነው፡፡ እኛ ያለነው እኛ እና ሌሎች አእምሮ ውስጥ በመሆኑ ከሁላችንም አእምሮ የሚፈልቁ መልካም ነገሮች ሁለንተናችንን መልካም ያደርጋሉ፡፡
በመሆኑም የታመሙትን ስንጠይቅ- ደጋፊ ያጡ አዛውንቶችን ስናበላ/ስናጠጣ እና ስንደግፍ ለራሳችን ያለን ክብር አድጎ እና ሌሎችም ለኛ ያላቸው ፍቅር ተመንድጎ ሰላማችንን ያበዛዋል- ይህም በተራዛሚው ሀገር ቀኤያችንን፤ ውስጥ- ውጪያችንን ሰላም ያደርገዋል፡፡ ግንቦት 20ን ስናከብር በዚህ የመልካምነት፣ የፍቅር፣ የአብሮነት፣ እና የሰላም መታገጊያ ውስጥ እንዲሆን በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
4ተኛ የሀገራችን ህዝብ የማንበብ፣ የመመርመር እና ከሚታየው ሁነት ጀርባ የሚኖረውን እውነት የማጥናት የዘመናት ልምምድ ያለው ህዝብ ነው፡፡ አሁን አሁን የሚታዩት እና ማህበረሰባችን ውስጥ የሚስተዋሉት አዝማሚያዎች ከትላንት ታሪካችን እና ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የአንባቢ- ጠያቂነት አሻራችን ጋር የሚሰምር ባለመሆኑ አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር ሁሉም ዜጋ እንደየ ዝንባሌ መሻቱ የማንበብን ክቡር ተግባር የህይወቱ አካል አድርጎ ሊይዝ ይገባል፡፡ የግንቦት ሀያ በአልን ስናከብርም በማንበብ እውቀትን በውስጣችን ለማሳባሰብ በመወሰን ቢሆን እጅጉን እናተርፋለን፡፡
5ተኛ የማወቅ መሰልጠን- የማደግ መዘመን ልካችን የሚታወቀው ወይም የሚገለጠው ለአካባቢያችን በምንሰጠው ትኩረት- እንክብካቤ እና ንጽህና ልክ ነው፡፡ ቤታችን ምን ቢያምር እና ቢጸዳም አካባቢያችን እስካልጸዳ ድረስ የቤት- ጊቢያችን ውበት እና ጽዳት የሚሰጠን ዋጋ የዜሮ ብዜት ነው፡፡ በመሆኑም የበአል አከባበራችን አንዱ መልክ ከአካባቢ ጽዳት ጋር ቢሰናሰል ጠቀሜታው ብዙ ነው፡፡
6ተኛ የዘመናዊነታችንና የስልጣኔያችን ዓይነተኛ ማሳያ ሊሆን የሚችለው ሀገራዊ እሴት ለሴቶች የምንሰጠው ክብር ነው፡፡ ማንኛውም ዜጋ እንደግለሰብም ይሁን እንደማህበረሰብ ነገን የተሻለ ለማድረግ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴ ውስጥ ለሴት እህቶቻችን የሚሰጠውን ክብር በማሳደግ መሆን ይገባል፡፡
ቀኑን በዚህ መልኩ ከላይ በተጠቀሱት ተግባራት ያሉንን ሰዓታት ሸንሽነን በአሉን በምናከብርበት ሂደትም የግንቦት 20 ውሎ የሰራናቸውን ተግባራት የሚያመላክት እለታዊ የዉሎ ማስታወሻ በመያዝ ቀናችን ምን ያህል እንደተጠቀምንበት የማስተዋል ልምምዳችንን ማዳበር እንደሚገባን እንዳንዘነጋ በአጽንኦት አሳስባለሁ፡፡
የተከበራችሁ የሀገሬ ህዝቦች፣ ከራስ ክብር እስከ ሀገር ፍቅር ሊያስታጥቁን የሚችሉ እነዚህን በጎ ልምምዶች የሁሌም መገለጫችን በማድረግ ዛሬ በጠንካራ መሰረት ላይ ማቆም ስንችል በእርግጠኝነት ነገ- ከዛሬ የተሻለች እንደምትሆን ማመን እንችላለን፡፡
ዛሬ ያሉብን ማህበራዊ እና ግለሰባዊ ክፍተቶቻችን የሁሌም መሆን እንዳይችሉ የምናክማቸው እንደዚህ ባሉ አዎንታዊ ሀይልን በሚጨምሩልን ተግባራት በመሆኑ ይህንን ልምምዳችንን አጠናክረን እንድንቀጥል አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡
"ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!" ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time