Thursday, December 14, 2017

በሊቢያ ኢትዮጵያዊ "እንደ ውሻ እንጂ እንደ ሰው አይቆጠርም"

በሊቢያ ኢትዮጵያዊ "እንደ ውሻ እንጂ እንደ ሰው አይቆጠርም"

ድሕነትን ሸሽተው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ መንገድ የገቡት ኢትዮጵያውያን በሊቢያ የቀውስ ወጥመድ ውስጥ ወድቀዋል። ኢትዮጵያውያኑ እንደሚሉት በሊቢያ በሰደፍ ጭምር ይደበደባሉ፣ ገንዘባቸውን ይዘረፋሉ ለእስርም ይዳረጋሉ።
የ21 አመቷ ራሕማ አሕመድ ከአስራ አምስት ቀናት በፊት በሊቢያ እስር ቤት ነበረች። ወጣቷ በእስር ቤት ድብደባ ገጥሟታል። እግሮቿም  መራመድ ቸግሯቸዋል። "እቃ ገዝተን ልንበላ ከታክሲ ስንወርድ የሆነ ሰው እየፈለግን ነበር ብለው ወስደው እስር ቤት አስገቡን ብር አምጥታችሁ ነው የምትወጡት ተብሎ 3,000 ዶላር ተጠየቅን። እግሬ አሁን ተመቶ ነው ያለው። ሳንቲም አስልኪ ብለው ነው የመቱኝ። እኔ ደግሞ ገንዘብ የሚልክልኝ ሰው የለኝም። እህት የለኝም። ወንድም የለኝም። ከየት ነው የማስልክላቸው?"
"እግሯ ተመቶ አሁን ከእሷ ጋር እየተሰቃየሁ ነው።"  የምትለው የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ዘይነብም ከራሕማ ጋር ታስራ ነበር። "3,000 ዶላር ተጠይቀን  የቤተሰቦቻችሁ ቁጥር ንገሩን ብለው ሲደበድቡን ወንዶቹ ከጣራ ላይ አስወጥተውን ከጣራ ላይ ወድቃ እግሯን የተሰበረችው። አሁን 15 ቀን አልሞላንም። እሷ እግሯ ተሰብሮ ተኝታለች ።አሁን አንድ ቤት ውስጥ ቁጭ ብለናል ።"
ራሕማ እና ዘይነብ ጓደኛሞች ናቸው። እንጀራ ፍለጋ ከትውልድ ቀያቸው ወደ ሱዳን ከዚያም ወደ ሊቢያ ያመሩትም አብረው ነበር። ሁለቱም በርስ በርስ ጦርነት በታመሰችው ሊቢያ ላለፉት አራት አመታት ኖረዋል። የሜድራኒያን ባሕርን ተሻግረው የተሻለ ነገር ይገኝበታል ሲባል ከሰሙት አውሮጳ ለመድረስ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ገንዘብ ከፍለው ያደረጉት ሙከራ አልሰመረላቸውም።
"እኔ የደሐ ልጅ ነኝ" የምትለው ራሕማ ከቤተሰቦቿ ጋር ግንኙነት የላትም። የእጅ ስልኳ ተወስዶባታል። "መጥፎ ሁኔታ ላይ ነው ያለሁት" ትላለች ያለችበትን ሁኔታ ስታብራራ። ራሕማ ከቤተሰቦቿ ገንዘብ አስልካ ሁሉ ታውቃለች። እርሷ እንደምትለው ግን ይኸ የእሷ እጣ ፈንታ ብቻ አይደለም።"ብዙ ልጆች እስር ቤት የሚወልዱ አሉ። ብዙ ደላላ ቤት የሚጎዱ አሉ። ብዙ ብር ከኢትዮጵያ ቤት አሽጠው የተላከላቸው ሰዎች አሉ። እንደዚህ አይነት ብዙ ሰዎች አሉ።"
Libyen Europa Migration Zustände in Flüchtlingslagern (picture-alliance/AP Photo/M. Brabo)
በሊቢያውያን ታግተው ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ከተላከላቸው መካከል "ስቃይ ውስጥ ነው ያለሁት" የሚለው ሰይፈል ሁሴን ይገኝበታል። የሰሐራ በርሐን አቋርጦ ሊቢያ የደረሰው ሰይፈል ከአንዴም ሁለት ጊዜ ታግቶ ታስሮ ያውቃል። "ከእስር ቤት ለመውጣት ወደ 8,000 ዶላር {ከኢትዮጵያአስልኪያለሁ። ድብደባ ሲበዛ ቤተሰብ ጋ ደወልኩ። በክላሽ በሰደፍ እየመቱ ነው ገንዘብ እንዲላክ የሚያስገድዱት። ቤተሰቦቼ ሳለቅስ ያላቸውን የሌላቸውን ተበዳድረው ላኩልኝ። ከወጣሁ በኋላ ትሪፖሊ ልላካችሁ አለን። ትሪፖሊ ነው የምልካችሁ ብሎ ከዛ መንገድ ላይ ተያዝን አሁንም። ከዛ በሊዎሊድ ገባን። በሊዎሊድ ገብተንም ለአንድ ሰው 5,500 ዶላር አምጡ አለን። ከዛም በኋላ አመት ሙሉ ስንቀጠቀጥ ስንቀጠቀጥ ቤተሰብ ስደውል ስደውል መጨረሻ ላይ ቤት ሸጠው ላኩልኝ።"
የቀድሞው አምባገነን ሞአመር ጋዳፊ በምዕራባውያኑ ጣልቃ ገብነት እና ሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን ከወረዱ ጀምሮ መንግሥታዊ ሥርዓቷ በፈራረሰው ሊቢያ አፈና የተለመደ ግን ደግሞ አሰቃቂ ተግባር ሆኗል። አፈናው ሊቢያን እንደ መሸጋገሪያ የሚጠቀሙ አፍሪቃውያን በታጣቂዎች እጅ  እንደ ባሪያ እንዲሸጡ አድርጓቸዋል። ድርጊቱ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ እና ውግዘት ቢገጥመውም ዘላቂ መፍትሔ የማግኘቱ ነገር አጠያያቂ ይመስላል። ሰይፈል በሊቢያ ካፈኑት ቡድኖች መካከል አንዱ በኤርትራዊ ይመራ እንደነበር ተናግሯል።
"እኛን ይዞን የነበረው ኤርትራዊው ወሊድ የሚባለው ወኪል የትም አገር አለው። ከሱማሌም አለው። በዱባይም ያስመጣል። ይኸን ስራ እስካሁን ድረስ ይሰራል። {የሚላከውን ገንዘብየሚቀበሉ ሰዎች አሉ። ሲታወቅበት ሌላ ሰው ይቀይራል።" ይላል።
በሊቢያ የሚገኙት ስደተኞች እንደሚሉት ግፍ እና መከራው በወንዶች ላይ ይበረታል። ሴቶቹ ከሰው ቤት ተቀጥረው በመሥራት የዕለት ጉርሳቸውን ማግኘት ይችላሉ። ይሁን እና ወርሐዊ ደሞዛቸው በአግባቡ አይከፈላቸውም። ቢከፈላቸው እንኳ ፖሊስን ጨምሮ በሊቢያውያኑ ተመልሶ ይዘረፋሉ። "አባታቸው ሞቶባቸው ልጆቼን አሳድጋለሁ ብዬ ነው ከአገሬ የወጣሁት። ልጆቼንም መርዳት አልቻልኩም።" የምትለው ዘይነብ ይኸው ገጥሟታል። "እዚህ በጣም ተሰቃይቼ ነው ያለሁት። በሰሐራ ስመጣ ስንት ጓደኞቼ ከአጠገቤ ሞተው እዚህ ደረስኩ። እዚህ ደርሼ አንድ አመት እንኳ ልጆቼን መርዳት አልቻልኩም። የምሰራው ይጠፋብኛል። አጠራቅሜ እልካለሁ ስል የሚላክበት መንገድ የለም። ባለፈው ደግሞ ፖሊስ ገብቶ ብዙ የሰራሁትን ብዙ ብር ወሰደብኝ። ሥራ ቦታ ደግሞ ብሬን አልከፈሉኝም።"
ራሕማ ባዶ እጇን መሆኗ አብዝቶ ቢያሳስባትም ወደ አገሯ መመለስ ትሻለች። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሳምንት በሊቢያ የሚገኙ ዜጎቹን ለመመለስ ማቀዱን ገልጦ ነበር። ካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሊቢያ የሚገኙ እና ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ለሚፈልጉ ዜጎች የተዘጋጁ ሶስት የስልክ ቁጥሮች አሰራጭቷል። ኢትዮጵያውያኑን የመመለሱ ተግባር ስለ መጀመሩ ለማረጋገጥ በተደጋጋሚ ያደረግንው ሙከራ ግን አልሰመረም።
ዘይነብ እንደምትለው ወደ ስልክ አድራሻዎቹ ላይ በተደጋጋሚ ቢደውሉም ምላሽ አላገኙም።  "የሚደርስብን መከራ ከፍቷል" የምትለው ዘይነብ እንደ ሰው አይቆጥሩንም ስትል ትናገራለች።
"ኢብን ወሊድ የሚባል ቦታ ላይ ብዙ ኢትዮጵያውያን ተሽጠው ፤ ሁለቴ ተሽጠው ብር ተጠይቀው እየተገረፉ ያሉ ልጆች አሉ። እዚህ ኢትዮጵያ ዜጋ እና ሌላ ዜጋ እንደ ውሻ ነው እንጂ እንደ ሰው አይቆጠርም። መንገድ ላይ ታርዶ ነው እንደ ውሻ የሚጣለው። እንደ ሰው አይቆጥሩንም።Read more here
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time