በስራ ጉዳይ ወደ ተለያዩ ቦታዎች የሚጓጓዘው ወንድሜነህ እንግዳ በርካታ የአፍሪካ ሃገራትን የመጎብኘት አጋጣሚ አግኝቷል። በቅርቡም ወደ ኬንያ ለሳምንት ያህል አምርቶ ነበር። በእነዚህ አጋጣሚዎችም ሃገሩ ኢትዮጵያ አልፎም መኖሪያው አዲስ አበባ ከመሰል ከተሞች ጋር ያላትን ልዩነትና ምስስል መታዘብ ችሏል።
"ከሁሉም ከሁሉም በበርካታ ሃገራት የማስተውለው የኢንተርኔት ፍጥነት እና አቅርቦት ጉዳይ ያስደንቀኛል" ይላል ወንድሜነህ። "የእነዚህ ሃገራት መንግስታት ኢንተርኔት ለአንድ ሃገር ዕድገት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የተረዱት ይመስላል" ሲል ትዝብቱን ያስቀምጣል። "አንድ ቀን ኢትዮጵያም እንደጎረቤት ሃገራት ፈጣንና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ኢንተርኔት ታቀርብ ይሆናል። ማንያውቃል. . . " ይላል ወንድሜነህ።
የቴሌኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ ዕድገት አብይ ማሳያ የሆነው የኢንተርኔት አገልግሎት አሁን አሁን አስፈላጊነቱ ከምንም ጊዜ በላይ እየጨመረ እንደመጣ አያጠራጥርም። ዓለማችን በሉላዊነት አንድ እንድትሆን ትልቅ ሚና ከተጫወቱ ቴክኖሎጂዎች መካከልም ቁንጮ ሆኖ ይቀመጣል።
የዓለም አቀፉ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ማሕበር በአውሮፓውያኑ 2016 ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በቴሌኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ ከዓለም 169ኛ ደረጃ ከአፍሪካ ደግሞ 33ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ሞሪሺየስ የምትመራው የአህጉራችን የቴሌ ዘርፍ ጎረቤት ሃገር ኬንያን 9ኛ ላይ ሲያስቀምጥ፤ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ በተከታታይ 20ኛ 22ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ታላቅ ቅናሽ
60 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳሉት የሚናገረው ኢትዮ ቴሌኮም ከእነዚህ ውስጥ 17 ሚሊዮን ያክሉ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው የኢንተርኔት አግልግሎት ተጠቃሚ ናቸው። የኢትዮ ቴሌኮም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አብዱራሂም አህመድ እንደሚናገሩት የ3ጂ ኢንተርኔት በአሁኑ ሰዓት በመላ ሃገሪቱ የተስፋፋ ሲሆን ተጠቃሚዎችም አገልግሎቱን በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኙ ይገኛሉ።
ኢትዮ ቴሌኮም ኢንተርኔት በተለይም ደግሞ በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚቀርበውን አገልግሎት በዝቅተኛ ታሪፍ ለደንበኞቹ ያቀርባል ሲሉ ይናገራሉ አቶ አብዱራሂም።
"አይሲቲ አፍሪካ የተባለ ድርጅት በሚያወጣው ደረጃ መሠረት ኢትዮጵያ በተንቀሳቃሽ ስልክ ኢንተርኔት ዋጋ በዝቅተኛው ደረጃ ላይ ትገኛለች። ይህም ማለት 0.03 ዶላር በአንድ ደቂቃ ዋጋ ላይ ትገኛለች። በተነፃፃሪ ደግሞ ኬንያ በ0.07 ዶላር የአንድ ደቂቃ ኢንተርኔት ትሸጣለች" በማለት አቶ አብዱራሂም ያስቀምጡታል።
ወንድሜነህ ግን በዚህ ሃሳብ የሚስማማ አይመስልም። "እኔ በሄድኩባቸው እንደ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ የመሳሰሉ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የተንቀሳቃሽ ስልክ ኢንተርኔት አግልግሎት በተነፃፃሪ እጅጉን ርካሽ እና ፈጣን ሆኖ ነው ያገኘሁት" ሲል ያስረግጣል።
የቴሌኮሚኒኬሽን ባለሙያ የሆነው ተክሊት ሃይሌም ሃሳቡ ተመሳሳይ ነው። "በቅርቡ ግብፅ ሄጄ የኢንተርኔት አግልግሎቱን በርካሽ ዋጋ መጠቀም ችያለሁ። ያውም እጅግ ፈጣን የሆነ አገልግሎት" ሲል ይናገራል።
ኢትዮ ቴሌኮም ለደንበኞቹ የሚያቀርበውን የኢንተርኔት አግልግሎት ዋጋ ከኬንያው ሳፋሪኮም ጋር ለማነፃፀር እንደሞከርነው የኢትዮ ቴሌኮም ኢንተርኔት አቅርቦት መጠን ባደገ ቁጥር ዋጋው እጅግ ከፍ እያለ ይመጣል።
ሳፋሪኮም ዝቅተኛውን የ5 ሜጋ ባይት ኢንተርኔት በ5 ሽልንግ ወይም አሁን ባለው የምንዛሪ ዋጋ 1ብር ከ30 ሳንቲም አካባቢ ያቀርባል። ኢትዮ ቴሌኮም ደግሞ የ25 ሜጋ ባይት ኢንተርኔት በ5 ብር ያቀርባል። በዚህ ረገድ ኢትዮ ቴሌኮም የተሻለ ሲሆን የኢንተርኔት መጠኑ ከፍ ሲል ግን ሳፋሪኮም እጅግ በተሻለ ዋጋ ኢንተርኔትን ለደንበኞቹ ያቀርባል። ለምሳሌ ኢትዮ ቴሌኮም 1ጂቢ በ165 ብር ሲሸጥ በተነፃፃሪ ሳፋሪኮም 1ጂቢ በ500 ሽልንግ ወይም አሁን ባለው የምንዛሪ ዋጋ በ130 ብር አካባቢ ይሸጣል።
ወጥ-አልባነት
ወንድሜነህም ሆነ ተክሊት በአንድ ተጨማሪ ነገር ይስማማሉ። በኢትዮ-ቴሌኮም የኢንተርኔት አቅርቦት ወጥ-አልባነት። "የዋጋው ነገር እንዳለ ሆኖ" ይላል ወንድሜነህ "አንዳንድ ወቅት ዘለግ ላለ ጊዜ የምትጠቀምበት ኢንተርኔት በሌላ ወቅት በደቂቃዎች ውስጥ ያልቅብሃል። በምን ዓይነት መስፈርት እንደሚሰራ ግልጽ አይደለም" ይላል።
በመንግስት ሥራ የምትዳደረው መክሊት የ2ጂ ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ነች። "2ጂም ሆነ 3ጂ ልዩነቱ አይታየኝም። እንደውም አንዳንዴ 3ጂ ከሚጠቀሙ ጓደኞቼ የኔ ኢንተርኔት ፈጥኖ ይገኛል" ትላለች። "አንዳንድ ጊዜ በ5 ብር የገዛሁትን ጥቅል አገልግሎት ረዘም ላለ ጊዜ እጠቀማለሁ ሌላ ጊዜ ወዲያው ያልቅብኛል" ስትል ትናገራለች።
ሞኖፖሊ
የኢትዮጵያን ቴሌኮሚኒኬሽን ዘርፍ በበላይነት የሚቆጣጠረው ኢትዮ ቴሌኮም ሌላ ምርጫ የሌላቸውን ደንበኞቹን ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ እያሳደገ ቢመጣም የኢንተርኔት ነገር ለብዙዎች አሁንም አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
ተክሊት ለዚህ ችግር መፍትሄው አማራጭን ማስፋት ነው ይላል። "እኔ ቴሌኮም ለውጭ ድርጅት ይሸጥ ወይም አክሲዮን ይሰጥ የሚል እምነት የለኝም። ነገር ግን ለሃገር ውስጥ ድርጅቶች ዘርፉን ክፍት ማድረግ ቢቻል በሚቀጥሉት ዓመታት ቴሌኮም በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም ማቅረብ እንደሚቻል አምናለሁ" ሲል ይናገራል።
"ኬንያ የሄድኩ ጊዜ ሳፋሪኮም፣ ኤይርቴል እና ቴልኮም የተባሉ አበይት አማራጮች ስላሉ ሰው እንደፍላጎቱ አማርጦ ሲጠቀም ተመልክቻለሁ። እኛ ሃገር ስትመጣ ግን ያለህ አማራጭ አንድ እና አንድ ነው። እሱም አሰራሩ ወጥ ነው ብዬ አላምንም" ሲል ወንድሜነህ በሌሎች ሃገራት የታዘበውንና የሃገሩን ሁኔታ ይተርካል።
ጨምሮም "እንደኬንያ በመሳሰሉ ሃገራት ረከስ ባለ ዋጋ ተገዝቶ ከግለሰቦች ቤት አልፎ በሕዝብ ማመላለሻ ባሶች ውስጥ ሳይቀር የሚገጠመው 'ዋይፋይ' ኢትዮጵያ ውስጥ ከብቸኛው አቅራቢ ኢትዮ-ቴሌኮም በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የማይታሰብ ነው" ይላል።
ኢትዮ-ቴሌኮም የኢንተርኔት አገልግሎትን ከማስፋት ባለፈ ጥራት እና ፍጥነት ላይ እየሰራ እንደሆነ አቶ አብዱራሂም ይናገራሉ። "ታሪፍን በተመለከተ በተከታታይ እያየን ማሻሻያ የምናደርግበት ጉዳይ ነው። የሚቆም ጉዳይ" አይደለም ይላሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮ ቴሌኮም ከኬንያው ሳፋሪኮም ጋር በትብብር ሊሠራ ነው ተብሎ በተለያዩ ዜና ምንጮች የተነገረው መሠረተ ቢስ መሆኑን አቶ አብዱራሂም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሆኖም መክሊት እና ወንድሜነህን የመሳሰሉ ደንበኞች አሁንም ጥያቄ ያነሳሉ። "መች ይሆን ኢንተርኔት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሁም በአስተማማኝ ፍጥነት የምናገኘው?" በማለት. . . Read more here
No comments:
Post a Comment