በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሚገኙ የታዋቂው በቀለ ሞላ ሆቴሎች መካከል አንዱ የሆነውና በባሌ ዞን በሲናና ወረዳ ሮቤ ከተማ የሚገኘው ሆቴል ለሁለት መሸጡ በፍ/ቤት እያከራከረ ነው፡፡
የሆቴሉ ባለቤቶች ሆቴሉን ለሁለት ገዢዎች እንደሸጡት መሆኑን ከክስ መዝገቦቹ መረዳት የተቻለ ሲሆን 4 ግለሰቦች በጋራ በ24 ሚሊዮን ብር ሲገዙት፣ ሳናቴ ትሬዲንግ ደግሞ በ33 ሚሊዮን ብር እንደገዛው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሰኔ 18 ቀን 2008 ዓ.ም ሆቴሉን በጋራ የገዙት አቶ ንዋይ ከበደ፣ አቶ አብርሃም ጌታሁን፣ አቶ አለሙ ንጉሴና አቶ ደምስ አበበ የተባሉ ግለሰቦች ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የፍ/ብሔር ቢፒአር ችሎት ባቀረቡት ክስ፤ ሆቴሉን በ24 ሚሊዮን ብር ለመግዛት ተስማምተው የነበረ ቢሆንም በውላቸው መሰረት ሆቴሉን የራሳቸው ማድረግ አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
የግዥ ውሉን በተፈራረሙበት ቀን ቅድመ ክፍያ 4 ሚሊዮን ብር ከፍለው ቀሪውን 20 ሚሊዮን ብር ደግሞ እስከ ህዳር 30 ቀን 2009 ዓ.ም ለማስረከብና ሆቴሉም በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ ዝውውሩን እንዲያደርግላቸው ተዋውለው የነበረ ቢሆንም ተፈፃሚ ሳይሆንላቸው መቅረቱን ከክስ አቤቱታው መረዳት ተችሏል፡፡
ከሳሾች በውላቸው መሰረት፤ ሆቴሉን ባለመረከባቸው ውሉን ያፈረሰው የሆቴሉ ባለቤት የቅድመ ክፍያውን 4 ሚሊዮን ሁለት እጥፍ ማለትም 8 ሚሊዮን ብር እንዲከፍላቸው እንዲሁም ቀደም ሲል በገቡት ውል መሰረት የሀብት ዝውውር እንዲከናወንላቸውና ድርጅቱን መረከብ እንዲችሉ ይደረግላቸው ዘንድ አመልክተዋል፡፡
ተከሳሽ በቀለ ሞላ ሆቴሎች በበኩሉ፤ ለቀረበበት ክስ በሰጠው ምላሽ፤ በ24 ሚሊዮን ብር ለመሸጥ የተደረሰ ስምምነት መኖሩን በመግለፅ የተፈረመው የስምምነት ሰነድ “የውል ረቂቅ” እንጂ “ውል” ባለመሆኑ፣ ገዥዎች በረቂቅ ውሉ መሰረት በተቀመጠላቸው ቀነ ገደብ ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው የተፈጠረ ችግር መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ከሳሾች በተሰጣቸው ቀነ ገደብ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ቀሪ ክፍያ 20 ሚሊዮን ብር በመክፈል ግዴታቸውን አለመፈፀማቸውን የጠቀሰው ተከሳሽ፤ “የገዙትን ሆቴል ዋጋ በሙሉ እስከ ህዳር 30 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ መክፈል ነበረባቸው፤ ይህን ግዴታቸውን ሳይወጡ ሻጩ ግዴታውን አልተወጣም የሚል ጥያቄ ወይም ክስ ሊያቀርቡ አይችሉም” ብሏል፡፡
ከሳሾች የራሳቸውን ግዴታ ሳይወጡ ተከሳሹ ድርጅቱን ያስረክብ የሚል ክስ ማቅረብ አይችሉም ያሉት የበቀለ ሞላ ሆቴሎች፤ 8 ሚሊዮን ብር እንዲከፈላቸው የጠየቁትም ህጋዊ መሰረት ስለሌለው ውድቅ እንዲሆን ፍ/ቤቱ ጠይቋል፡፡
በሁለቱ ወገኖች ክርክር መሃል የገባው ሳናቴ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በበኩሉ፤ ሆቴሉን በ33 ሚሊዮን ብር እንደገዛው፤ ክፍያውንም ሙሉ ለሙሉ ከፍሎ የቤቱን አስፈላጊ ሰነዶች መቀበሉንና በቦታው ላይም G+2 ህንፃ ለማሰራት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የዲዛይን ስራ ውል መግባቱን የክስ መዝገቡ ያመለክታል፡፡
ኩባንያው ለፍ/ቤቱ የዳኝነት ጥያቄ ባቀረበው ማመልከቻ፤ ከአራቱ ከሳሾች በበለጠ በንብረቱ ላይ የተሻለ መብት እንዳለው ጠቅሶ፤ ከሳሾች ያቀረቡት ክስ ውድቅ ተደርጎ የተጣለበት የእግድ ትዕዛዝ እንዲነሳለት ጠይቋል፡፡ ኩባንያው በክርክሩ ምክንያት ለጠበቃ አበል፣ ለቴምብር ቀረጥ፣ ለፎቶ ኮፒና ለመሳሰሉ ያወጣውን ወጪ እንዲተኩለት ይወሰንለት ዘንድም ፍ/ቤቱን ጠይቋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክሮች እያዳመጠ የሚገኘው ፍ/ቤቱ፤ መዝገቡን ለህዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጥሮታል፡፡ Read more here
No comments:
Post a Comment