Sunday, November 13, 2016

‹‹ከአደረጃጀት ጀምሮ በፌዴሬሽኑ ክፍተቶች እንዳሉ ለይተን አውቀናል››

አቶ ጁነዲን ባሻህ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2009 ውድድር መርሐ ግብር ተጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በተለይም ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተደጋጋሚ መድረኮችን በማመቻቸት ጭምር ሁሉም የየራሱን ድርሻ አውቆ እንዲንቀሳቀስ ጠንከር ያለ ደንብና መመርያ ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ የእግር ኳሱን መሠረተ ልማት በማስፋት ረገድም የታዳጊ ወጣቶችን ውድድር በዕድሜ በመከፋፈል እንደሚያከናውን ተናግሯል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከካፍና ፊፋ ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የገንዘብና የሙያ ድጋፍ እያገኘ ከመሆኑም ባሻገር፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2025 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ከሚወዳደደሩ አገሮች አንዷ ስለመደረጓም ተነግሯል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም የእግር ኳሱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ደረጀ ጠገናው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ከሆኑት አቶ ጁነዲን ባሻህ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ተጀምሯል፡፡ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በተለይ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር የተያያዙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይቷል፡፡ አጀማመሩ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ጁነዲን፡- ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ግልጽ ነው፡፡ እንደ ፌዴሬሽን የፕሪሚየር ሊጉ የ2009 መርሐ ግብር ለማስጀመር ታስቦ የነበረው ከመስከረም 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ነበር፡፡ እንደዚህም ሆኖ የዘንድሮ ውድድር እንዳለፉት ዓመታት ተጓትቶ የክለቦችንም ሆነ የተቋሙን የፋይናንስ አቅም እንዳያፋልሱ ተገቢው ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ፌዴሬሽኑ የ2008 መርሐ ግብር እንደተጠናቀቀ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁሉም እንደሚያውቀው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በተሳካ መልኩ ተጠናቋል፡፡ መደበኛው የፕሪሚየር ሊግ ውድድርም ተጀምሯል፡፡ ከሳምንት በኋላ ደግሞ የሴቶችን ፕሪሚየር ሊግ ለመጀመር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ በመቀጠልም ከፍተኛ ሊግና ብሔራዊ ሊግ፣ እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ20 ዓመትና ከ17 ዓመት በታች ውድድሮችን ለማስጀመር ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ ይህን ስናደርግ ታዲያ የወቅቱን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በማዘውተሪያ ሥፍራዎች ለሚፈጠሩ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል መንስዔዎች ዙሪያ ውይይቶችን በማድረግ፣ ይህንኑ ወደ ሚመለከታቸው አካላት በማውረድና ጥናት በማድረግ ሁሉም የየራሱን ድርሻ እንዲወስድ የተደረገበት ስምምነት ላይ ተደርጓል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መጀመርያ የችግሩን መንስዔ ሳናውቅ ወደ መፍትሔው መሄድ ስለሌለብን ማለትም የእግር ኳስ ዳኞች፣ የክለብ አመራሮች፣ ደጋፊዎች፣ የክልል ፌዴሬሽኖችና ብሔራዊ ፌደሬሽኑ ጭምር ሁሉም ድርሻ ድርሻውን አውቆ ዝግጅት እንዲያደርግ ከሦስትና አራት ጊዜ በላይ መድረኮች ተፈጥረው ውይይት ተደርጓል፡፡ ችግሮችና አለመግባባቶች ሲፈጠሩ እንዴትና በምን አግባብ ማረምና መቆጣጠር እንደምንችል መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ምክንያቱም  እግር ኳስ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተወዳጅነት እንደተጠበቀ ሆኖ ሰዎችን ሳይጠበቅ ስሜታዊ እንደሚያደርጋቸው በማሰብና ይኽም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እግር ኳስ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰባቸው ባደጉት አገሮች ሳይቀር ያለና የሚኖርም በመሆኑ ይህንኑ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ስምምነት ላይ የደረስነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስፖርቱ የሚፈጥረው ስሜታዊነት እንደተጠበቀ፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ግን የስፖርቱን ደንብና መመርያዎች ባለማወቅ፣ ማለትም ከአቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች ሲፈጠሩ ይስተዋላል፡፡
አቶ ጁነዲን፡- ችግሮቹ እንዳሉ አይተናል፡፡ በዚህ ብቻ ሳንወሰን በእግር ኳሱ ያሉ ደንብና መመርያዎች እግር ኳሳችን ከደረሱበት የዕድገት ደረጃ አኳያ መሻሻል ያለባቸው እንዳሉ ጭምር ተመልክተናል፡፡ የባለሙያዎቻችንን አቅም ከወቅቱና ከጊዜ ጋር መራመድ ይችል ዘንድ የሙያ ብቃት ማሻሻያዎች እንዲሰጡ አድርገናል፡፡ እያደረግንም እንገኛለን፡፡ በምንፈልገው መጠን ባይሆንም እምነት ሊወሰድ ይገባል፡፡ ሌላው በደንብና መመርያዎች ዙሪያ ከወቅቱና ከጊዜው ጋር የማይሄዱ ካሉ አንቀጾች ለባለድርሻ አካላት እንዲላኩና አስተያየት እንዲሰጥባቸው ተደርጓል፡፡ ግብረ መልሶችም እየመጡልን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ግብረ መልሱ በተለይ ከደንብና መመርያው አኳያ በሚጠበቀው መልኩ መጥቷል?
አቶ ጁነዲን፡- እስካሁን ባለው ግብረ መልሱ በምንፈልገው መልኩ አልመጣልንም፡፡ ባለው ተሞክሮ ደንብና መመርያዎች ከወጡ በኋላ በርካታ ቅሬታዎችና አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡ ዕድሉ ሲገኝ ደግሞ የምንጠቀምበት በጣም ጥቂቶች ነን፡፡ ክለቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ዕድሉን እንዲጠቀሙበት እንጠብቃለን፡፡ ካልሆነ ግን በመጣው ልክ የምንሄድበት ይሆናል፡፡ በተለይ ከእግር ኳስ ዳኝነት ጋር በተያያዘ አለ የሚባለውን ክፍተት ለመድፈን ጥረት አድርገናል፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ቡናን የመሳሰሉ ክለቦች ከደጋፊዎች ጋር ሰፊና ይበል የሚያሰኝ ውይይት እያደረጉ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ ድርሻ ድርሻዎችን ወስደው መንቀሳቀስ ከቻሉ የምንፈልገውን እናሳካለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስናጠቃልለው ባለፈው ዓመት የተስተዋለው ዓይነት ችግር ዘንድሮ ቢፈጠር እነማን ይጠየቃሉ? የመፍትሔው አካላትስ እነማን ይሆናሉ? ውሳኔውስ ምን ሊሆን ይገባል? ለሚለው ሁሉም ድርሻውን ወስዷል፡፡
ሪፖርተር፡- ከፌዴሬሽኑ የውስጥ አደረጃጃት ጋር ተያይዞ የሚደመጡ ችግሮች አሉ፡፡ አሁን ያለውን አካሄድ ከማስፈጸም አኳያ የፌዴሬሽኑ አቅም እንዴት ይታያል?
አቶ ጁነዲን፡- በጥቅል ‹‹ድርሻ›› ስል ለመግለጽ የሞከርኩት ይህንኑ ነው፡፡ በተናጠል የፌዴሬሽኑን ለመናገር፣ በሁሉም ረገድ የተሟላ ነው ባይባልም የጎላ ክፍተት ያለባቸው ክፍሎች ላይ የሰዎች ምደባና ቅጥር እየተከናወነ ነው፣ ይቀጥላልም፡፡ ተቋሙ ባለው ደንብና መመርያ በቂ አገልግሎት እየሰጠ ነው ወይ? የሚለውን ጊዜ ወስደን ተመልክተናል፡፡ የፌዴሬሽኑ ባለድርሻ ለምንላቸው ክለቦች፣ ተጨዋቾች፣ ሙያተኞችና ሌሎችም ለሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን አገልግሎት ሰጥተናል ለማለት ከባድ ነው፡፡ ብቃትና ጥራት ያላቸው ሙያተኞችን ለመመደብ መዋቅር ተጠንቷል፡፡ ዲፓርትመንቶች እየተለያዩና እየተጠኑ ይገኛል፡፡ የዕቅድ አወጣጥ ባለሙያ እንደሚያስፈልግ እምነት ይዟል፡፡ በዚህ ደረጃ እንመድባለን ስንል ያንን የሚመጥን ክፍያም የግድ ነው፡፡ ለምሳሌ የዕቅድ አወጣጥ ባለሙያ የክለቦችን ጥያቄዎች ሙያው የሚጠይቀውን ደንብና መመርያ መሠረት አድርጎ መልስ እንዲሰጥ ማለት ነው፡፡ የተጨዋቾች ዝውውር፣ የዕድሜና ሌሎች መሰል ችግሮች በዚህ ሥርዓት መልስ እንዲያገኙ እንሻለን፡፡ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ እንፈልጋለን፡፡ እስካሁን ባለው አሠራር የፌዴሬሽኑ ሠራተኞች ሥራቸውን የሚሠሩት እንዴት ነው? ሲባል በጣም የሚገርም ተሞክሮ ነው ያለው፡፡ ይኼ መቀጠል አለበት ብለን አናምንም፡፡ ግጭቶች እንደሚመጡ እናውቃለን ግን ደግሞ ሥርዓት ማበጀት የግድ የሚልበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ በአጠቃላይ ከአደረጃጀት ጀምሮ በፌዴሬሽኑ ክፍተቶች እንዳሉ ለይተን አውቀናል፡፡
ሪፖርተር፡- የፌዴሬሽኑ ሠራተኞች ከመደበኛው ሥራቸው ጎን ለጎን በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ እንዳሉ ጭምር ይነገራል?
አቶ ጁነዲን፡- ለዚህ ሲባል ሠራተኞች በሰዓታቸው ሲገቡና ሲወጡ መቆጣጠር እንዲቻል መሣሪያ ገዝተናል፡፡ ይሁንና ሠራተኞችን በመቆጣጠር ብቻ ወደ ሥርዓት ማስገባት ይቻላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ዕርምጃ መውሰድ የግድ ያስፈልጋል፡፡ በፌዴሬሽኑ ባለው ተሞክሮ የአንድ መደበኛ ሠራተኛ መደበኛ የሥራ ሰዓት አይታወቅም፡፡ ከዚህ በፊት በሰዎች ግፊት ብቻ ተነሳስተን ሠራተኞች ያላግባብ እንዳይበደሉ ጥንቃቄ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ አሁን ግን ለይተናል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ጥርስ እንዲኖረው እያደረግን ነው፡፡ በዚህ በኩል የቁርጠኝነት ክፍተት እንዳለ እናውቃለን፡፡ ይኼ መቀጠል ይኖርበታል ወይ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የማብቃት ሥራቸውም ይቀጥላል፡፡ ይህንን ስል ሁሉንም ለማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ አንዳንዶች ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ በትርፍ ሰዓታቸው እየገቡ የሚሠሩ አሉ፡፡ በአጠቃላይ ያለውን ነገር ስገመግመው ግን ሠራተኛው ከሥራ ሰዓቱ ውጭ መንቀሳቀስ በተለይ እግር ኳሱ አካባቢ በግልጽ ይታያል፡፡ ከዚህ አኳያ እነማንን ብናመጣ ነው ይህንን መጥፎ የሆነ የሥራ ባህል መለወጥ የሚቻለው? የሚለው ያሳስበኛል፡፡ ስለሆነም ከዚህ መረዳት የሚቻለው ሁሉም ወደ ራሱ መመልከት እንዳለበት ነው፡፡ በአጠቃላይ ውድድር ዓመቱ በዋዛ የሚታለፍ ነገር እንደሌለው መናገር የምፈልገው፡፡
ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ በውድድር ዓመቱ የስታዲየም መግቢያ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጉ ተሰምቷል፡፡ ጥያቄው ለምን ይጨመራል ሳይሆን ተመልካቾች ለሚከፍሉት ገንዘብ ሜዳ ላይ ከሚታየው ጨዋታ ጨምሮ መፀዳጃ ቤቶች፣ የትኬት መሸጫ ሰዓቶችና ሌሎችም ጥንት በነበረው ሆኖ ሳለ ለምን የገንዘብ ጭማሪ ብቻ ታሳቢ ተደረገ የሚሉ ቅሬታዎች ይደመጣሉ?
አቶ ጁነዲን፡- እንደ ፌዴሬሽን የተመልካቹ ቅሬታ ተገቢና ትክክለኛም ነው፡፡ ግን ደግሞ ቀድሞ በነበረበት ያለ ነገር ምንድነው? ስንል መግባባት የምንችልባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ የአዲስ አበባ ስታዲየም የአገልግሎት አሰጣጥን ትተን ለጥያቄዎቹ መልስ ይሆን ዘንድ እንሞክር ቢባል እንኳ የጎላ ችግር እንደምናገኝ እንረዳለን፡፡ አንድ ለእናቱ በሆነ ስታዲየም የኃላፊነቱም ጉዳይ ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው፡፡ ገንዘብ ኖሮ እንጠግን ብንል እንኳ መቼና በምን ሰዓት የሚለው ሌላ ችግር ነው፡፡ ችግሮቹ ባሉበትም ቢሆን በስታዲየሙ የተሰባበሩ መቀመጫ ወንበሮችና መፀዳጃ ክፍሎች ዕድሳት እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ የፍሳሽ ቦታዎችም በተመሳሳይ እንዲታዩ እያደረግን ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ የሚታይ ለውጥ ለማሳየት ደግሞ ሌላ መጠባበቂያ ስታዲየም እስከሌለ ድረስ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ከባድም ነው፡፡ ሌላው ቀደም ሲል በምናውቀው ታሪፍ የምንገለገልበት እንዲሆን ጊዜው አያስገድድም፡፡ በዛሬና በነገ ሳይቀር ለውጦች ይታያሉ፡፡ ከሻይና ማኪያቶ ጀምሮ ያለውን የዋጋ ለውጥ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ይህ እውነታ ባለበት የስታዲየም መግቢያ ትኬት ብቻ በነበረበት ይቆይ ማለት የሚያስማማ አይመስለኝም፡፡ ተመጣጣኝ አገልግሎት ይኑር ያስማማናል፡፡ እግር ኳስ አክሳሪ ሆኖ የምናየው በእኛ አገር ነው፡፡ በሌላው አገር ትልቅ የኢንቨስትመንት አማራጭ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ለምንከፍለው ክፍያ በቂ አገልግሎት ስንጠይቅ ለአገልግሎቱ ማሻሻያ የሚሆን ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሰጥተን ነው አገልገሎት መጠበቅ የሚኖርብን፡፡ በአንድ ወቅት እግር ኳሳዊ ባልሆነ ቢዝነስ ወደ አውሮፓ ሄጄ በአጋጣሚ ጨዋታ እንድመለከት የተጋበዝኩበት አጋጣሚ ትዝ ይለኛል፡፡ በተለመደ (ኖርማል) ቦታ ለአንድ ጨዋታ 378 ዶላር ተከፍሎ እንደገባሁም አስታውሳለሁ፡፡ ያ ይቅር ነገር ግን ደግሞ ድሮ በነበረው አምስትና አሥር ብር ልግባ ማለት የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ ሌላውና የሚገርመው ነገር ደግሞ በነፃ መግባት አለብኝ ብሎ መግቢያና መውጫ የሚያሳጣም አለ፡፡፡ መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ ለእግር ኳሱ ደክሜያለሁ የሚል በዝቷል፡፡ ይሁንና ለእግር ኳሱ ብዙ የደከሙ ነገር ግን ተገቢው ክብር ያልተሰጣቸው ሰዎችም አሉ፡፡ እነዚህ ቢጠየቁ ምንም አይደለም፡፡ ይህንንም እየለየን ነው፡፡ ጭማሪ ለማድረግ የታሰበው አሁን ካለው በላይ ነበር፡፡ (ጭማሪው 100 ብር የነበረው ክብር ትሪቢዩን 200 ብር፣ 50 ብር የነበረው 100 ብር እያለ በየደረጃው ተቀምጧል፡፡) እግር ኳሱንና ክለቦቻችንን እናሳድግ ከተባለ የግድ ጨከን ማለት ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከስታዲየም መግቢያ ትኬት አሻሻጥ ጋር የተያያዙ ተመሳሳይ ቅሬታዎች ይደመጣሉ፡፡ ለምሳሌ ለአሥር ሰዓት ጨዋታ ዘጠኝ ሰዓት ትኬት መሸጥ የሚጀመርበት ሁኔታ እንዳለ ይነገራል፡፡ በመፍትሔነት ደግሞ ትኬቱ ለሚመለከታቸው ክለቦች ተሰጥቶ እንዲሸጥ እንደሚሻል የሚጠይቁም አሉ፡፡
አቶ ጁነዲን፡- በቅርቡ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ በነበረው ውይይት ጉዳዩ ተነስቶ ታይቷል፡፡ የስታዲየም መግቢያ ትኬት አሻሻጥ ላይ ጥናት ተደርጓል፡፡ ዘመናዊ የትኬት አሻሻጥ ሥራ ለመጀመርም አቅደናል፡፡ ምናልባትም አሠራሩ ለሁለተኛ ዙር የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ይደርሳል የሚል እምነት አለ፡፡ መሠረታዊ ችግሩ ትኬቱ በፌዴሬሽኑ ወይም በክለብ መሸጥ የሚለው አይደለም፡፡ ትኬቱ ለክለቦች ቢሰጥ የሚሸጡት ልክ እንደ ፌዴሬሽኑ ሁሉ በሰዎች ነው፡፡ ነገር ግን የአሻሻጥ ሥርዓቱ ምን መምሰል እንዳለበት ማወቁ ላይ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው በአብዛኛው ኤሌክትሮኒክስ ነው፡፡ መሣሪያው ሁለት ዓይነት አገልግሎት አለው፡፡ አንዱና ዋናው ተመልካቾች የገዙት ትኬት ትክክለኛነቱን የሚቆጣጠር ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን የአልኮል ሱሰኛ የሆኑ ተመልካቾችን ለመለየት ጭምር ይጠቅማል፡፡ ሌላው ደግሞ ፌዴሬሽኑም ሆነ ክለቦች ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበት ማስታወቂያም ሊሠራበት ይችላል፡፡ የግድ ወደ እዚህ ሥርዓት መምጣት ይኖርብናል፡፡ እየሄድንበት ስለሆነ ትዕግሥት ይጠይቃል፡፡ ትኬቱ ለክለቦች ይሰጥ አይሰጥ የሚለውን አስመልክቶ ሁሉም ክለቦች ተመሳሳይ የሆነ አቋም የላቸውም፡፡ አንዳንዶቹ በፌዴሬሽኑ እንዲቀጥል ሲጠይቁ ከፊሎቹ ደግሞ በክለቦች ይሁን በሚል እያከራከረ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለትና ሦስት ጊዜ ለማስማማት ጥረት አድርገን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በአጠቃላይ ያለመተማመን ጉዳይ አለ፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ በዚህ ዓመት እየሄደበት ካለው ጠንካራ ጎን የታዳጊ ወጣቶች ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ሒደት በተለይ ከዕድሜ ጋር ያለው መጠነ ሰፊ ችግር ለመፍታት ከምንጊዜውም በተሻለ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ሆኖም በዘላቂነቱ ላይ ግን ጥርጣሬ ያላቸው ወገኖች አሉ፡፡ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ጁነዲን፡- የታዳጊ ወጣቶች ጉዳይ በእኛ ብቻ ሳይሆን የካፍና ፊፋ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ይገኛል፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በታዳጊ ወጣቶች ላይ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚያደንቁት ገልጸውልናል፡፡ እገዛና ድጋፍም እንደሚያደርጉ ምልክቶችን እያየን ነው፡፡ እንደሚታወቀው የአገራችን ክለቦች ዋነኛ ትኩረት ፕሪሚየር ሊግ ላይ ካልሆነ የታዳጊ ወጣቶች ጉዳይ ያን ያህል ነበር፡፡ ከፕሪሚየር ሊግ እልፍ ከተባለ ደግሞ ብሔራዊ ቡድን ነው፡፡ ብዙዎች ይህን አካሄድ ጤነኛ እንዳልሆነ እየተረዱ መጥተዋል፡፡ ምክንያቱም የእግር ኳሱ መሠረት ታዳጊ ወጣቶች ናቸው፡፡ ለክለቦቻችንም ሆነ ለብሔራዊ ቡድኖቻችን የውጤት መውረድ መንስዔው የተተኪ ቡድኖች መጥፋት መሆኑ እየታመነበት መጥቷል፡፡ ስለሆነም ፌዴሬሽኑ በጀመረው መልክ ይቀጥልበታል፣ የግድም ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች በሊግ ደረጃ ውድድሩ የተጀመረው ባለፈው ዓመት ነው፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ለመጀመር የዕድሜና መሰል ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነው፡፡ ይኼ ተጠናክሮ ከቀጠለ የዕድሜ ቅብብሎሹ ማለትም የታዳጊ ወጣቶች ዕድሜ ከ17 ሲያልፍ፣ ወደ ሚቀጥለው ማለት ከ20 ዓመት በታች ወደ ተዘጋጀው ሊግ፣ ከዚያም ወደ ፕሪሚየር ሊግ እያሉ ዕድገቱን ጠብቆ እንዲመጣ ያግዛል፡፡ ሌላው በዚህ ረገድ ከኮካ ኮላ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተደርጎ የፕሮጀክት ሥራው በስፋት እየተሄደበት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ተማሪዎች ሙሉ በጋውን በትምህርት የሚያሳልፉ እንደመሆኑ ይህንኑ ግምት ውስጥ በማስገባት በክረምት እንዲከናወን ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ የስምምነቱን ኮንትራት ወደ አምስትና ከዚህም በላይ ከፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ከዚህ ፕሮጀክት በችሎታቸው ተሽለው የሚገኙ ታዳጊዎች የተሻለ ሥልጠና የሚያገኙበት ዕድልም ያገኛሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ ታዳጊ ወጣቶችን እንደየዕድሜያቸው ማለትም ከ17 እና ከ20 ከዚያም ከ23 ዓመት በታች በመከፋፈል በብሔራዊ ደረጃ እያወዳደረ ይገኛል፡፡ ይኽም ከዚህ በፊት ያልነበረ መሆኑ ግምት ሊወሰድ ይገባል፡፡ መንግሥት በዚህ በኩል ለምናደርገው እንቅስቃሴ እገዛም እንደሚያደርግልን አንዳንድ ፍንጮች እየታዩ ስለሆነ አጠናክረን የምንቀጥልበት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት በሌላው አገር በመንግሥት እንደሚሸፈን ነው የሚታወቀው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በአገሪቱ ያለው የሥልጠና ስንታንዳርድ እንዴት ነው? አቅማችንስ? የሚለውን ጉዳይም አይተነዋል፡፡ ይህንኑ የሚያጠና አንድ ቡድን ተቋቁሟል፡፡ የቡድኑ ጥንቅር ከዩኒቨርሲቲና በስፖርቱ ካለፉ አካላት የተወጣጣ እንዲሆንም ተደርጓል፡፡ ለዚህ ዋናው መነሻ በርከት ያለ ዕድሜ ያስቆጠሩ ክለቦቻችን ለአህጉር አቀፍ ውድድሮች ይበቃሉ፡፡ ነገር ግን ብዙም  ተፎካካሪ ሳይሆኑ ከሻምፒዮናው ውጭ የሚሆኑበት ጊዜ የበዛ ነው፡፡ ለምን ብለን የችግሩን መንስኤና ምንነት መለየት የግድ ያለበት ጊዜ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ለአሠልጣኞቻችን የሰጠናቸው የአሠልጣኝነት ፈቃድ (ላይሰንስ) ደረጃውን የጠበቀ ነወይ? በዚህ ረገድ መልሳችን አዎን ከሆነ ወደ ውጭ ወጥተው እንዲያሠለጥኑ ዕድሉን ለምን አጡ? በቅርቡ ወደ ዓረብ አገር ብልጭ ብሎ የነበረው የፕሮፌሽናል ዕድል ለምን ጠፋ? ራሳችንን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ትልቅ አጀንዳችንም ሊሆን ይገባል፡፡  
ሪፖርተር፡- በቅርቡ አዲስ አበባ በምታስተናግደው የአፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ ላይ የፊፋውን ፕሬዚዳንት ለመጋበዝ እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ዓላማው ምንድነው? 
አቶ ጁነዲን፡- እንደዚህ ዓይነት ግንኙነቶች በፋይዳ ደረጃ ትርጉማቸው ብዙ ነው፡፡ የበፊቱን ትተን በቅርቡ በጀመርናቸው ግንኙነቶች ብቻ በርከት ያሉ የእግር ኳስ ዳኞቻችን ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን እንዲዳኙ የሥልጠናና መሰል ዕድሎችን እንዲያገኙ በር ተከፍቷል፡፡ በርካታ ኢንስትራክተሮች እንዲፈሩ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ እንደ ባሕር ዳር፣ ሐዋሳና ድሬዳዋን የመሰሉ ስታዲየሞች በፊፋ ዕውቅና እንዲሰጣቸው ተደርጓል፡፡ ከዚህም ሲያልፉ ፊፋ በታኅሣሥ ወር ከዓለም አገሮች የተውጣጡ የእግር ኳስ ባለሙያተኞች በአዲስ አበባ ሥልጠና እንደሚሰጥ ቃል ገብቶልናል፡፡ የፕሮግራሙ አስተናጋጅ እንደመሆናቸውን የምናገኛቸው ጥቅሞች በቀላሉ የሚታዩ አይደለም፡፡ የውጭ ምንዛሪን ጨምሮ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የታዳጊ ወጣቶች አካዴሚ ለማቋቋም የጠየቁን አካላት አሉ፡፡ በሒደት ላይ ያለ ነገር በመሆኑ ዝርዝሩን መናገር ባያስፈልግም፣ ውጤቱን በዚህ ወር እንደምናውቅ እጠብቃለሁ፡፡ እነዚህ ሁሉ የግኝኙነት ውጤቶች ናቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሁን ካለው በተጨማሪ  የራሱ የሆነ ቢሮ እንዲኖረው ለፊፋ ፕሬዚዳንት ጥያቄ አቅርበናል፡፡ ፕሮፎርማ እድንናዘጋጅ ተጠይቀንም አቅርበናል፡፡ ሌላው ለፊፋ ያቀረብነው ጥያቄ አዲስ አበባ የአፍሪካ መቀመጫ እንደመሆኗ የካፍ ጽሕፈት ቤትም ወደ አዲስ አበባ የሚመጣበት ሁኔታ እንዲያመቻች ነው፡፡ የአፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ በጥር ወር ስለሚደረግ የፊፋው ፕሬዚዳንት እንዲገኙ እያመቻቸን ነው፤ ይገኛሉ ብለንም እንጠብቃለን፡፡ ሌላው በ2025 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ጥያቄ አቅርበን ከዕጩዎቹ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ እንድትሆን ተደርጓል፡፡ እንደሚታወቀው የ2020 ቻን ኢትዮጵያ እንደምታዘጋጅ ታውቋል፡፡ ክልሎቻችን እየገነቡት ያሉት ስታዲየሞችን በተመለከተ ተነሳሽነታቸው እንደተጠበቀ የስታንዳርዱን ጉዳይም አብረው እንዲያስቡበት ያስፈልጋል፡፡ Read more here

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time