Monday, November 7, 2016

የንግድ መደብሮችን የሚተናነቀው የኪራይ ዋጋ

በቻይና የተገነቡ አዳዲስ ከተሞች በተለያዩ ምክንያቶች የሚኖርባቸው እያጡ ፀጥ እረጭ ያሉ ሕይወት አልባ መንደሮች ወደ መሆን እየተቀየሩ መጥተዋል፡፡ በየከተሞቹ የተገነቡት አፓርትመንቶችና የሕዝብ መገልገያ ሕንፃዎች ተዘግተው ውለው ማደር ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ‹‹ጎሥት ሲቲ›› ወይም የጣረሞት ከተሞች የሚል ቅጽል አትርፈዋል፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 2030 ድረስ 40 በመቶ የሚሆኑት ቻይናውያን ወደ እነዚህ ከተሞች ካልተሸጋሸጉ በስተቀር የሕንፃዎቹ ዕጣ ፈንታ በዚህ መልኩ ሊቀጥል እንደሚችል ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
በቀላሉ ሊቀረፍ የማይችል የመኖሪያ ቤት ችግር ላለባት ኢትዮጵያ ይህ ዓይነቱ ክስተት መፈጠሩ የማይታሰብ ቢሆንም፣ እየተገነቡ ያሉት ሕንፃዎች ቁጥር ግን በየጊዜው እያሻቀበ ይገኛል፡፡ በአንድ ወቅት በአገሪቱ የዘመናዊነት መገለጫ ሆኖ አንደ ብርቅ ይታይ የነበረ ሕንፃ አሁን ላይ ትልቅ የገቢ ምንጭ እየሆነ ይገኛል፡፡ አዋጭነቱን የተመለከቱ በርካቶች ባለሀብቶችም ሕንፃ በማስገንባት ከኪራዩ ዳጎስ ያለ ገቢ እያገኙ ይገኛሉ፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የአገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ በየዓመቱ በ12.43 በመቶ እያደገ ይገኛል፡፡ ለሕንፃ ማስገንቢያ የሚያውሉት ብድር ፍለጋ በአገሪቱ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማትን በሮች የሚያንኳኩም በዝተዋል፡፡ የአንዳንዱ ባንኮች የብድር መዝገብ እንደሚያሳየውም፣ ለአንድ ዓመት ለብድር ተብሎ ከሚያዘው የገንዘብ መጠን ውስጥ እስከ 15 በመቶ ያህሉ ለኮንስትራክሽን በተለይም ለገበያ ማዕከላት ግንባታ እየዋለ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1997 ዓ.ም. እና 1998 ዓ.ም. ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከኪራይ ታክስ የተገኘ ዓመታዊ ገቢ 15.2 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2004 ዓ.ም. እና 2005 ዓ.ም. ግን ይህ መጠን ወደ 78.3 ሚሊዮን ብር ከፍ ሊል ችሏል፡፡ ከዘርፉ የተገኘው ዓመታዊ ገቢም 105 ሚሊዮን ብር እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዘርፉ የሚገኘው ዓመታዊ የኪራይ ገቢ የ26.8 በመቶ ዕድገት እንዳለው ይነገርለታል፡፡
ለዚህም ዕድገት ማመሳከሪያ በየመንደሩ የሚገነቡ ሕንፃዎችን ማየቱ በቂ ነው፡፡ ካለው ፍላጎት አንፃር ተገንብተው ያልተጠናቀቁ ሕንፃዎችን ተሽቀዳድመው የሚከራዩ ድርጅቶችና ግለሰቦችን ማየትም ተለምዷል፡፡ በካሬ ሜትር ተመን እየወጣላቸው በመከራየት ላይ የሚገኙት ሁለገብ ሕንፃዎች፣ የሚከራዩበት ዋጋ እንደየአካባቢው የገበያ ሁኔታ እንዲሁም እንደየሕንፃው ወለል ስፋት የተለያየ ነው፡፡
ሕንፃው የተገነባው ከፍተኛ የገበያ ፍሰት ባለባቸው እንደ መርካቶ ባሉ ቦታዎች ከሆነ፣ በካሬ ሜትር እስከ 2,500 ብር ድረስ ይከራያል፡፡ መገናኛ፣ ሲኤምሲ፣ ቦሌ አካባቢ ደግሞ በካሬ ከ400 እስከ 750  ይከራያል፡፡ በከፍተኛ ዋጋ የሚከራዩት በሕንፃው ታችና የመጀመርያው ወለል ላይ የሚገኙ ክፍሎች ሲሆኑ፣ ወደ ላይ ከፍታ በጨመረ ቁጥር ዋጋውም እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ አብዛኛዎቹ በተለይም ዓይነተኛ ገበያ ባላቸው አካባቢዎች የሚገነቡ ሕንፃዎች ከመጠናቀቃቸው ወራት ቀደም ብሎ በደንበኞች ይያዛሉ፡፡ በጨረታ አወዳድረው የሚያከራዩም በርካቶች ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ የሕንፃዎች ዋጋ ውድ እየሆነ መምጣቱ ተከራዮችን የሚያማርር ሆኗል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም የሚጠይቁት ዋጋ ጭማሪ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ የምሥራች ብርሃን ትባላለች፡፡ መገናኛ አካባቢ በሚገኝ አንድ ሕንፃ ውስጥ ተከራይታ  የመዋቢያ ምርቶችን ትሸጣለች፡፡ ሕንፃው ውስጥ ያሉ ክፍሎች በካሬ ሜትር እስከ 400 ብር ይከራያሉ፡፡ ካላት አቅም አንፃር ግን የምሥራች የተከራየችው ከሕንፃው መወጣጫ ደረጃ ሥር የሚገኘውን ክፍት ቦታ ነው፡፡ በወር 3,000 ብር እንደምትከፍልበት ገልጻለች፡፡
40,000 ብር የሚገመት ዋጋ ያላቸው ዕቃዎችን ደርድራ የምትሸጠውና የምትደረድረው ከመወጣጫው ሥር ባስቀመጠቻቸው ባለመስታወት መደርደሪያዎች ነው፡፡ ሥራዋን ጨርሳ ስትወጣም መደርደሪያዎቹን በቁልፍ መቆለፍ ብቻ እንጂ ንብረቷን ከዘረፋ ለመከላከል የምትዘጋው በር የላትም፡፡ በአንድ ወቅት መደርደሪያዋ ተሰብሮ እንዳገኘችው ገልጻለች፡፡ ሌሎችም ችግሮች አጋጥመዋት ያውቃሉ፡፡ ይሁንና ከዚህ የተሻለ አማራጭ ስለሌላት ቦታውን ትታ ለመሄድ አታስብም፡፡ በዚህ መልኩ ስትሠራ ሁለት ዓመት አስቆጥራለች፡፡ ሕንፃውን ከተከራዩ ሰዎች ውስጥም ከመጀመርያዎቹ መካከል አንዷ ነች፡፡
በካሬ ሜትር ከሚጠየቀው ዋጋ በተጨማሪ በአንድ ጊዜ የበርካታ ወራት ኪራይ እንዲከፍሉ የሚገደዱበት አሠራር ተከራዮችን እያስጨነቀ የሚገኝ ነው፡፡ የተባሉትን መክፈል ካልቻሉም አፍታ ሳይቆዩ ቦታቸውን የሚረከቡ ተፎካካሪዎች በርካቶች ናቸው፡፡ ለዚህም ያላቸውን አሟጥጠው አልያም ተበድረው መክፈል ግድ ይላቸዋል፡፡
 ‹‹የ6 ወር 18,000 ብር ከፍዬ ነው የተከራየሁት፤›› የምትለው የምሥራች፣ አንዳንዴ ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው የተከራዩት ሕንፃ በቶሎ ላይለመድ፣ ገበያ ላይኖረው እንደሚችል፣ ለወራት በኪሳራ መቆየት እንደሚያጋጥም ተናግራለች፡፡
‹‹በመጀመርያዎቹ ወራት አንድ ቻፕስቲክ እንኳ ሳልሸጥ የምውልባቸው ቀናት ይበዙ ነበር፡፡ አሁንም ብዙ ለውጥ የለውም፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን የገበያው ሁኔታ ይስተካከላል፡፡ ሲስተካከል ደግሞ በካሬ ሜትር የሚከፈለው ዋጋ አብሮ ይጨምራል፤›› በማለት ጫናው ምን ያህል እንደሆነ አብራርታለች፡፡
 ‹‹አንድ ቦታ ላይ ሆኖ ገበያ ካለማመዱና ደንበኛ ካፈሩ በኋላ ኪራዩ ተወደደ ብሎ ሌላ መቀየር ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ከለመዱበት ቦታ መጥፋት  ደንበኞችን ያባርራል፤›› የሚለው የበርካታ ተከራዮች እምነት ነው፡፡ በመሆኑም ጥርሳቸውን ነክሰው የተከራዩትን ቤት ላለመልቀቅ ይጣጣራሉ፡፡
ቦሌ ከሚሊኒየም አዳራሽ አጠገብ በሚገኘው ስናፕ ፕላዛ ሕንፃ ውስጥ ሱቅ የተከራችው ቅድስት ዮሐንስ (ስሟ ተቀይሯል) እንደ የምሥራች ሁሉ በኪራይ ተማርራለች፡፡ ሱቋን የተከራየችው ከቫት በፊት በካሬ ሜትር 350 ብር ከፍላ ነው፡፡ እዚያ ከመግባቷ በፊት ቦሌ መድኃኔዓለም ፊት ለፊት ከሚገኙት ሕንፃዎች መካከል አንደኛውን ተከራይታ ትሠራ ነበር፡፡ ነገር ግን የደረሳት ሱቅ ከሕንፃው የፊት መግቢያ ዞር ያለ ስለነበር የሚከፈልበትን ያህል ገበያ አልነበረውም፡፡ ‹‹ቦሌ አካባቢ ሁሉም ውድ ናቸው ተብሎ ስለሚታሰብ ሰው አይደፍርም፡፡ ነገር ግን ርካሽ ናቸው ተብለው የሚገመቱ ቦታዎችም ላይ የዕቃ ዋጋ በጣም ይወደዳል፤›› በማለት የገበያውን አዝማሚያ ትገልጻለች፡፡
ሕንፃዎቹ የሚተዳደሩበት የየራሳቸው ደንቦች ሲኖራቸው ቅድስት በተከራየችበት ሕንፃ ያለው አሠራር ጠዋት ሦስት ሰዓት ላይ ሱቆች መከፈት እንዳለባቸው የሚጠይቅ ነው፡፡ ምሽት ሁለት ሰዓት ደግሞ ሱቆች የሚዘጉበት መውጫ ጊዜ ነው፡፡ በተከራዩና በአከራዩ መካከል የኪራይ ዋጋ ጭማሪና የመሳሰሉትን የሚገዛ ስምምነት ይፈጸማል፡፡ አንደኛው ወገን ውል ካፈረሰም በውሉ መሠረት ይጠየቃል፡፡
የማከራየት ሥራው የሚጀምረው ሕንፃዎች ቅርፅ መያዝ እንደ ጀመሩ፣ የማጠናቀቂያ ግንባታቸው ወቅት ላይ ነው፡፡ ይህ በሕንፃ ሕጉ መሠረት የማይፈቀድ አሠራር ቢሆንም ባንኮች፣ የመድን ድርጅቶች ያላለቀ ሕንፃ በመከራየት የሚወዳደራቸው ያለ አይመስሉም፡፡ እንዲህ ባለው ሒደት ግለሰብ ተከራዮች አልፎ አልፎ በጨረታ እንዲወዳደሩ ሲደረግ ይታያል፡፡ ሕንፃው ለአገልግሎት እስኪበቃ ለወራት መጠበቅም የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ በአሁኑ ወቅት እየተለወጠ ያለ ይመስላል፡፡ በከተማው እንደ አሸን እየፈሉ ካሉት በተለይም በቅርቡ ከተሠሩት ሕንፃዎች መካከል የሚከራያቸው ሳያገኙ ቀርተው አሊያም በሌላ ምክንያት ባዷቸውን ገትረው የሚታዩ አልታጡም፡፡ የገበያ ሁኔታ፣ የኪራይ ዋጋቸው መወደድ እንዲሁም የክፍሎቹ ወለልና ለተለዩ አገልግሎቶች እንዲውሉ የተዘጋጁ ሆነው ለተፈለገው ጉዳይ የሚከራያቸው ደንበኛ አለመገኘት ሊጠቀሱ የሚችሉ ምክንያቶች ናቸው፡፡
በዘፍመሸ ግራንድ ሞል የማርኬቲንግ ባለሙያ ሆነው የሚያገለግሉት አቶ ውብሸት አበራ እንደሚሉት፣ በሕንፃው ውስጥ ከሚገኙ በርካታ ክፍሎች መካከል አሥር ሱቆች እስካሁን አልተከራዩም፡፡ ይህም የሆነው የገበያ ማዕከል የሚለውን ስያሜ ለማሟላት ታስቦ ሱቆቹ ለንግድና ግብይት አገልግሎቶች የታጩ በመሆናቸው እስካሁን በተፈለገው ዘርፍ የተሰማሩ ደንበኞች ሊመጡ ስላልቻሉ ነው፡፡
አንድ ሕንፃ የሚከራይበትን ዋጋ የሚወስኑት ሕንፃው የተገነባበት ቦታ፣ ንጽህናው፣ በቂ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ያካተተ መሆኑና ከስርቆትና ከሌሎች የደኅንነት ሥጋቶች የፀዳ መሆኑ እንደሚጠቀሱ አቶ ውብሸት ይገልጻሉ፡፡
አንድ ሕንፃ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ የሚመጡ ሌሎች ተጨማሪ ወጪዎች መኖራቸውን፣ ለመንግሥት ገቢ የሚደረገው ታክስ ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ በካሬ ሜትር የሚከፈለው የኪራይ ዋጋ የተጋነነ አለመሆኑን የሚከራከሩ የሕንፃ ባለቤቶችም አሉ፡፡ ከሕንፃ ኪራይ በዓመት የሚገኘው ገቢ 7,200 ብር ከሆነ ከግብር ነፃ ነው፡፡ ከ7,201 እስከ 19,800 ባለው የገቢ ልክ የ10 በመቶ ታክስ ይከፈልበታል፡፡ ገቢው ከ19,801 እስከ 38,400 ባለው መጠን ሲወድቅ የ15 በመቶ፣ 38,401 እስከ 63,000 ሲሆን የ20 በመቶ፣ ከ63,001 እስከ 93,600 ሲሆን የ25 በመቶ፣ ከ93,601 እስከ 130,800 ሲሆን፣ የ30 በመቶ እና በዓመት የሚገኘው ገቢ ከ130,800 በላይ ሲሆን ደግሞ የ35 በመቶ የኪራይ ገቢ ግብር እንዲከፈል፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ ያስገድዳል፡፡ የ15 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ መክፈልም ግዴታ ነው፡፡
ከዚህ ባሻገር ሕንፃዎቹ ከተከራዩ በኋላ ወጣ ገባ የሚሉ ተከራዮች ስለሚበዙ እንደ ቧንቧ፣ የበር ቁልፍ የመሳሰሉት በየጊዜው መቀየር እነዚህንም ተከታትሎ ለማስተካከል ወጪዎችን ማውጣት ግድ ነው፡፡ በሌላ በኩልም ሱቆቹን ለመከራየት የሚፈልጉ ደንበኞች ካላቸው የመክፈል አቅም አኳያ አነስተኛ ቦታ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ የአብዛኛዎቹ ተከራዮች ፍላጎት ስለሆነ ነገሩን ቸል ማለት ከገበያ ውጭ ሊያደርግ ስለሚችል፣ ተከራዮች በሚፈልጉትና በአቅማቸው መሠረት የሕንፃ ክፍሎችን በመሸንሸንና በመከፋፈልና ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያወጡ አከራዮች ያብራራሉ፡፡
አቶ አብርሃም ገላው ካዛንቺስ አካባቢ የሚገኝ አንድ ሕንፃ ባለቤት ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ሕንፃው የተገነባው ከአምስት ዓመት በፊት ነው፡፡ በአንድ ወለል ላይ እስከ 20 የሚደርሱ ሱቆች አከራይተዋል፡፡ በ1,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈውን ባለ አሥር ፎቅ ሕንፃ የላይኛውን ክፍል የተከራዩት ቢሮዎች ናቸው፡፡
 ‹‹ከሕንፃው ውስጥ የተለያዩ ትንንሽ ዕቃዎች መስረቅ የተለመደ ነው፡፡ የጠፉትን ዕቃዎች ለማሟላትም በየጊዜው ትንሽ የማይባል ገንዘብ ይወጣል፤›› የሚሉት አቶ አብርሃም፣ ሽንሽን ለማዘጋጀት የሚወጣው ገንዘብ ደግሞ የበለጠ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፣ አብዛኛዎቹ ደንበኞች ከ20 እስከ 30 ካሬ ስፋት ያለው ቦታ ይፈልጋሉ፡፡ ከ100 እስከ 200 ካሬ የሚጠይቁም አሉ፡፡ ነገር ግን በቁጥር የሚበዙት 20 ካሬ የሚፈልጉት ናቸው፡፡ እነሱ በሚፈልጉት መጠን ከፋፍሎ ለማዘጋጀትም ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ለማውጣት መገደዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የአብዛኞቹ ሕንፃዎች ገጠመኝ ቢሆንም ዋጋው ግነት እንዳለበት የሚናገሩ አካላት ግን አልታጡም፡፡
የሕንፃ ዲዛይን አማካሪው አቶ ዳዊት ታምሩ፣ አንድ ካሬ ሜትር ቦታ ለመገንባት ከ5,000 እስከ 15,000 ብር እንደሚፈጅ፣ 15,000 ብር ወጪ የሚጠይቁት እንደ ሆቴል ያሉ ግንባታዎች መሆናቸውን፣ ለንግድ ማዕከላትና ቢሮዎች ግንባታ የሚወጣው ወጪ ቢበዛ ከ5,000 እስከ 6,000 ብር እንደሚሆን አቶ ዳዊት ገልጸዋል፡፡ አክለውም በሽንሽን ከፋፍሎ ለማዘጋጀት ‹‹በአሉሚኒየም የሚሠራው ውድ ፓርቲሽን ነው፡፡ ለዚህም ቢሆን ግን በካሬ 3,000 ብር ይበቃል፡፡ በፒቪሲ መሥራት ካስፈለገም በካሬ 2,000 ብር በቂ ነው፡፡ በጂፕሰም ከተሠራ ደግሞ በካሬ በ1,000 ብር አይሞላም፤›› ማለትም በአሁኑ ወቅት በካሬ ሜትር እየተጠየቀ ያለው ዋጋ ምክንያታዊ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡
እንዲህ ዝብርቅርቅ የሆነውን የኪራይ ሥርዓት ለማስተካከል መንግሥት ቸልተኛ ሆኗል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የኪራይ ዋጋ ተመንን የሚገዛ ሕግ እንደሚያወጣ ቢያስታውቅም እስካሁን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አይታይም፡፡ የንግድ ቤቶችን የኪራይ ዋጋ አነሳን እንጂ እየናረና የብዙዎችን ኢኮኖሚያዊ ሰብዕና እየተፈታተነ የሚገኘው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋም፣ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ፤›› እንደሚባለው በኑሮ ውድነት ላይ ተጨማሪ ፈተና በመሆን የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን እየተፈታተነ የሚገኝ ችግር ነው፡፡ መንግሥት ለዚህም የኪራይ ተመን እንደሚያወጣ ካስታወቀ ሰነባብቷል፡፡ ይህ ነው የሚባል ውጤት ግን እስካሁን አላመጣም፡፡   Read more here

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time