Sunday, November 20, 2016

ለባቡር አካዳሚና ለአዲስ አበባ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች የሚውል አንድ ቢሊዮን ዩዋን ብድር ተፈረመ

የቻይናው ምክትል ፕሬዚዳንት ሊ ዮዋንቻዎ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት በማድረግ፣ በአዲስ አበባ ለሚገነባው ዘመናዊ የባቡር አካዳሚና ለአዲስ አበባ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የሚውል የብድር ስምምነት መፈረማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ ከቻይና የሚገኘው ብድር አንድ ቢሊዮን ዩዋን (ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ) ነው፡፡  
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ረቡዕ ኅዳር 8 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርሱ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
የብድር ስምምነቱን ከመፈረማቸው አስቀድሞ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ጋር መወያየታቸውን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የቻይናው ምክትል ፕሬዚዳንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር በተገናኙበት ወቅት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለፉት 15 ዓመታት የሁለቱ አገሮች ትብብር ስላበረከተው አስተዋጽኦ እንዳብራሩላቸው አቶ ተወልደ ገልጸዋል፡፡
በተለይ በመሠረተ ልማት ዘርፍ የቻይና መንግሥት ላለፉት ዓመታት ሲያደርገው የነበረው ድጋፍ ጠቃሚ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ የሁለቱ አገሮች ትብብር የሁለትዮሽ ጥቅም ላይ የተመሠረተና ለአፍሪካ ምሳሌ እንደሚሆን መግለጻቸውን ቃል አቀባዩ አስረድተዋል፡፡
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የቻይና መንግሥት ድጋፍ እንዲቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጥያቄ ማቅረባቸውን፣ በተለይ የኢትዮጵያን የኢንዱስትራላይዜሽን ሒደት ለመደገፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማቋቋም የቻይና መንግሥት ትብብር እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ውይይቱን የተከታተሉት ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በሰው ኃይል ልማትና አቅም ግንባታ ረገድ የቻይናን ትብብር ኢትዮጵያ እንደምትሻ ለምክትል ፕሬዚዳንቱ መገለጹን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የቻይና ምክትል ፕሬዚዳንት ሊ ዮዋንቻዎ በበኩላቸው፣ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ካደረጓቸው ውይይቶች ጎን ለጎንም ሁለት የብድር ስምምነቶችን መፈረማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አንደኛው የአዲስ አበባ ከተማን የመጠጥ ውኃ ችግርን ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ለሚጠበቀው የገርቢ የመጠጥ ውኃ ግድብ የሚውል 100 ሚሊዮን ዩዋን ብድር መፈረማቸውን አቶ ተወልደ ገልጸዋል፡፡
ይህ ፕሮጀክት ከእንጦጦ ተራራ ጀርባ የሚገኝ ሲሆን፣ በቀን 73 ሺሕ ሜትር ኩብ የመጠጥ ውኃ እንደሚያመርትና ከ700 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ እስከ 50 ፎቅ ድረስ ውኃ ማድረስ እንደሚቻል፣ የዚህ ምክንያትም ውኃው ከከፍታ ቦታ ላይ ስለሚለቀቅ መሆኑን ከወራት በፊት ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለ ማርያም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ለዚህ ፕሮጀክት የሚያስፈልገው ሦስት ቢሊዮን ብር መሆኑንና የቻይና መንግሥት ወጪውን በብድር ለመሸፈን መስማማቱንም ተናግረው ነበር፡፡
የቻይና ምክትል ፕሬዚዳንት በሰሞኑ ጉብኝታቸው ለገርቢ የውኃ ፕሮጀክት የፈረሙት ብድር 100 ሚሊዮን የቻይና ገንዘብ (ዩዋን) ሲሆን፣ አሁን ባለው ምንዛሪ መሠረት 14.5 ሚሊዮን ዶላር ወይም 319 ሚሊዮን ብር ነው፡፡
የቻይና ምክትል ፕሬዚዳንት ሌላው የፈረሙት ብድር የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለሚያስገነባው የባቡር አካዳሚ የሚውል 924 ሚሊዮን ዩዋን መሆኑን አቶ ተወልደ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በወቅታዊ ምንዛሪ መሠረት ለአካዳሚው የተገኘው ቀላል ብድር 134.2 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ አካዳሚ በባቡር ዘርፍ የምሕንድስና፣ የጥገና፣ የባቡር ሹፍርና እንዲሁም ተጓዳኝ ዘርፎች ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ለመስጠት ያለመ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ Read more here

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time