የአማራ ክልል ውጥረት አሁንም ተባብሶ መቀጠሉን መረጃዎች እየገለጹ ነው፡፡ ውጥረቱ ወደ መተማ መሸጋገሩ የታወቀ ሲሆን፣ በስፍራውም ከንብረት መውደም በተጨማሪ የሰው ህይወት እየተቀጠፈ እንደሚገኝ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ እንደዚሁም የደብረ ታቦር ማረሚያ ቤት መቃጠሉን የአካባቢው ነዋሪዊች ገልጸዋል፡፡ ማረሚያ ቤቱ በሚቃጠልበት ወቅት የተኩስ ድምጽ ሲሰማ እንደነበር የገለጹት እነዚሁ ምስክሮች፣ ከእስረኞች ውስጥ የተጎዱ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ የአምባ ጊዮርጊስ ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ በአካባቢው የተኩስ ድምጽ ሲሰማ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
አንድ የመተማ አካባቢ ነዋሪ ‹‹በመተማ የተቃውሞ እንቅስቃሰሴውን ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በህዝብ ላይ ተኩስ ከፍተዋል፡፡ በዚህም ስምንት ያህል ሰዎች ተገድለዋል፡፡ የቆሰሉትም በርካታ ናቸው፡፡›› ብለዋል፡፡ የሟቾቹ ብዛት ከተጠቀሰው ቁጥር ሊልቅ እንደሚችል የገለጹት የዓይን እማኙ፣ የቁስለኛውንም ትክክለኛ ቁጥር መገመት አዳጋች እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በአምባ ጊዮርጊስ በተደረገው ጥቃት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ዩኒፎርም የለበሱ ጸጉረ ልውጥ ወታደሮች ከሃያ በላይ ሰዎችን የገደሉ ሲሆን፣ እነዚህ ወታደሮች የህወሓት መንግስት ከሱዳን ያስመጣቸው አልሞ ተኳሾች (ስናይፐርስ) እንደሆኑ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የህዝቡ ተቃውሞ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ በነዚህ ወታደሮች ህጻናት ሳይቀሩ መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡ የህወሓት የጦር አዛዦች በበኩላቸው ወደ ጎንደር ገብተው ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት ማቋቋማቸውን የገለጹት ምንጮች፣ የግድያውን ኦፕሬሽን እየመሩ የሚገኙትም እነሱ እንደሆኑ ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ እንደ ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ እና ፍኖተ ሰላም ያሉ የአማራ ክልል አካባቢዎች የተቃውሞ እንቅስቀሴው አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የክረምት ተማሪዎች ግቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ‹‹ይህም የተደረገው ተማሪዎቹ ተቃውሞዉን እንዳይቀላቀሉ ስላሰጋቸው ነው›› ብለዋል አንድ የአካባቢው ነዋሪ፡፡ በተለያዩ የክልሉ ስፍራዎች በምሽት መብራት እንደሚጠፋ የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ በምሽትም ሰዎች እየታፈሱ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ችግርም በስፋት እንደሚስተዋልም ያክላሉ፡፡
በዛሬው ዕለት የታጠቁ ወታደሮች መርዓዊ ከተባለ ቦታ ወደ ባህርዳር እና ጎንደር የተንቀሳቀሱ ሲሆን፣ ወታደሮቹን የጫኑት ወታደራዊ ኦራል መኪኖችም ቁጥራቸው በርከት እንደሚል ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንደዚሁም በፓትሮል የታጀቡና በአራት አውቶቡስ የተጫኑ የመከላከያ አባላት ከደብረማርቆስ ተነስተው ወደ ማንኩሳና ባህር ዳር መንቀሳቀሳቸውን የገለጹት ምንጮች፣ በባህር ዳር ደግሞ የታጣቁ ወታደሮች ሰላማዊ ዜጎችን መግደላቸውን ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ በህወሓት የተደረገባቸውን የሰላ ግምገማ የጨረሱት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ወደ ጎንደር ያመሩ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ሳይንስ ኮሌጅ ሳይንስ አምባ አዳራሽ ስብሰባ ተቀምጠው እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ወደ ስብሰባው ሲገቡ የነበሩትም አስቀድሞ ኩፖን የተሰጣቸው ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል፡፡ የስብሰባው ዓላማ እና ይዘት ምን እንደሆነ ለጊዜው አልታወቀም፡፡ Read more here
No comments:
Post a Comment