Tuesday, October 6, 2015

ኢትዮጵያ እና አዲሱ ካቢኔ - ምን ተቀየረ?

Äthiopien Kabinett
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ያቀረቡትን የአዲሱ ካቢኔ አባላትን ሹመት አፀደቀ። ዛሬ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ ካቢኔያቸውን ሲያሳውቁ አብዛኞቹ የመንግስት ባለስልጣናት በነበሩበት ሲቀጥሉ ጥቂት ለውጦች ደግሞ በሹመኞቹ ዘንድ ታይተዋል።

ካሁን ቀደም ኢህአዴግ መንግስት ሲመሰርት እንደ ተለመደው ጥቂት የማይባሉ የሚኒስቴር መስሪያቤቶች የአወቃቀርና የስያሜ ለውጦችም ተደርጎላቸዋል ። ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ጉባዔ ሚኒስትሮቻቸውን ለሹመት አቅርበዋል። ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን የ30 ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ሹመቶች ጥያቄ ሙሉ በሙሉ አጽድቋል። አቶ ደመቀ መኮንን ፤ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና ወይዘሮ አስቴር ማሞ በቀደመው የመንግስት አወቃቀር የነበራቸውን ስልጣን ይዘው ቀጥለዋል። ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማርያም ደሳለኝ ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ሹመታቸውን ካጸደቁ ሚኒስትሮች መካከል አራቱ ሴቶች ናቸው። የዓለም አቀፉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ አቶ ሐሌሉያ ሉሌ አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ ካቢኔ ነባሩን ስርዓት የማስቀጠል መልክ እንዳለው ይናገራሉ።
«መንግስት ውስጥ መሰረታዊ የሚባል ለውጥ የለም።» የሚሉት አቶ ሐሌሉያ አሁንም የመንግስት ዋና ዋና የስልጣን እርከኖች ቀድሞ በነበሩ ሰዎች እንደተያዙ መቀጠላቸውን ተናግረዋል። የዛሬውን የካቢኔ አሰያየም « አሁን ያለውን መንግስት አሰራሩንም አካሄዱንም የሚያስቀጥል አይነት።» ሲሉ ይገልጹታል።
Äthiopien Kabinett
በአዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት አወቃቀር የተወሰኑ ለውጦች ታይተዋል። በሚኒስቴር ማዕረግ የመንግስት ኮምንኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ሬድዋን ሁሴን አዲስ የተቋቋመው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ሆነዋል። የቀድሞው የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር አቶ ሱፍያን አህመድም በቀድሞው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድ ተተክተዋል። አሁንም እንደ አቶ ሐሌሉያሉሌ ከሆነ የአቶ ሱፍያን አህመድ ለውጥ አዲስ ሆንም በአቶ አብዱልአዚዝ መሐመድ ይተካሉ ብሎ ያሰበ ግን አልነበረም።
ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መፍረስ፤መጣመርና እንደ አዲስ መዋቀር የተለመደ ክስተት ነው። በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ጉባዔም የቀድሞው የግብርና ሚኒስቴር የእርሻና የተፈጥሮ ሐብት ልማት ሚኒስቴር ተብሏል። የእንስሳትና የዓሳ ሃብት ልማት ሚኒስቴር እንደ አዲስ ተቋቁሟል። እንደ አየር መንገድ፤ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንና ቴሌ ኮሙዩንኬሽን የመሳሰሉ የመንግስት ተቋማት አዲስ በተቋቋመው የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሊተዳደሩ ተወስኖ ሚኒስትር ተሾሞለታል። ተቋሙ ከሚያስተዳድራቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች አኳያ «በጣም ትልቅ ኃይል
Äthiopien Parlament
ሊኖረው የሚችል።» ይሉታል አቶ ሐሌሉያ አዲሱን ሚኒስቴር መስሪያ ቤት።
ማዕድንና ኢነርጂ ተብሎ ይጠራ የነበረው አሁን የማዕድን፣የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ተብሎ ተቀይሯል። ለውጡ የስም ብቻ ሳይሆን በሶማሌ ክልል ተገኝቷል ከተባለውና ኢትዮጵያ ከሶስት እስከ አምስት ባሉት አመታት ለውጭ ገበያ ልታቀርበው ካቀደችው የነዳጅና ጋዝ ክምችት ጋር በተገናኘ ሊሆን እንደሚችል አቶ ሐሌሉያ አስረድተዋል።
ዛሬ ሹመት ያዳብር ተብለው ቃለ መሃላ ከፈጸሙት 30 ሹማምንት አራቱ ሴቶች ናቸው። ወይዘሮ አስቴር ማሞ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ እና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትር ሆነው ከፍ ያለ ሹመት አግኝተዋል። ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ መጠነኛ ለውጥ የተደረገበት የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በቀድሞ ስልጣናቸው ቀጥለዋል። ኢንጂነር አይሻ መሐመድ አቶ አሚን አብዱልቃድርን ተክተው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነዋል። ወ/ሮ ደሚቱ ሐምቢሳ ደግሞ አዲስ የተቋቋመው የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል
Source: dw.com

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time