በመከላከያ እና ደህንነት መስሪያ ቤቶች ተጨማሪ ለውጦች እንደሚደረጉ ታወቀ። ዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በሁዋላ ነባር የመከላከያ አመራሮች እና የደህንነቱ ሹም ከስልጣን ተነስተዋል። ይህንን ተከትሎ በመከላከያ እና በደህንነቱ ተቋም የብሄር ተዋጽዖን ለመጠበቅ ሲባል የተለያዩ ከፍተኛ አመራሮች ከስልጣን እንደሚነሱ ታውቋል። ለረጅም አመታት የደህንነት ሹም በመሆን የሰሩት የህወሃቱ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ በጄ/ል አደም ኢብራሂም እንዲተኩ የተደረገ ሲሆን፣ እርሳቸውን ለመተካት ብአዴኖችና ኦህዴዶች ከፍተኛ ጫና ሲያደርጉ ከርመዋል። የደህንነት እና የመከላከያ መዋቅሩን መልሶ የማዋቀር እርምጃው በዚህ ፈጥነት ቀላል ይሆናል ተብሎ እንዳልተጠበቀ የሚገልጹት ምንጮች፣ ሳሞራን የመተካቱ እንቅስቃሴ ቀላል የነበረ ቢሆንም፣ ጌታቸውን ከሃላፊነት ለማስለቀቅ ግን ከባድ እንደነበር ይገልጻሉ። አቶ ጌታቸው ቤተሰባቸውን ወደ አሜሪካ ማውጣታቸው እንዲሁም በስራ ገበታቸው ላይ መገኘት አቁመው ነበር። አቶ ጌታቸው ከነሃሴው የኢህአዴግ አጠቃላይ ስብሰባ በፊት ይወርዳሉ ተብሎ ባይጠበቅም፣ በህወሃት በኩል የተፈጠረው መከፋፈል ለአቶ ጌታቸው ከስልጣን መውረድ ምክንያት እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል። አቶ ጌታቸውን የተኩት ጄ/ል አደም ኢብራሂም ከብአዴን የመጡ ሲሆን፣ ብአዴን የደህንነቱን ቦታ ለመያዝ ተጽዕኖ ማድረጉ ተሰምቷል። አቶ ጌታቸው እንደ ጄ/ል ሳሞራ የኑስ የሽኝኝት ስነስርዓት አልተደረገላቸውም። በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ የማይታወቁት አቶ ጌታቸው ላለፉት 27 ዓመታት በዜጎች ላይ ለደረሰው የሰብአዊ መብት ጥሰት ዋና ተጠያቄ ተደርገው ይታያሉ። ጄ/ል ሳሞራ የኑስን የተኩት አዲሱ ኢታማዦር ሹም ጄ/ል ሳዕረ መኮንን ከህወሃት ውጭ ባሉ የኢህአዴግ ድርጅት አባላት ዘንድ ተወዳጅ አይደሉም። ዶ/ር አብይ መሾማቸውን ተከትሎ የሜቴኩ ዋና ስራ አስኪያጅ ሜ/ጄ ክንፈ ዳኘው፣ የመረጃ መረብ ደህንነት ሃላፊ ብ/ጄ ተክልብርሃን ወልዳረጋይ በገዛ ፈቀዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸው ይታወቃል። አቶ ስብሃት ነጋ፣ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ አቶ ግርማ ብሩ፣ ዶ/ር ካሱ ኢላላ፣ አቶ በለጠ ታፈረ፣ አቶ ታደሰ ሃይሌና አቶ መኮንን ማን ያዘዋል በጡረታ መሰናበታቸው ይታወቃል።
Source: Esat
Source: Esat
No comments:
Post a Comment