Sunday, November 13, 2016

ከኮማንድ ፖስቱ ፈቃድ ባለማግኘቱ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት አለመቻሉን ኢዴፓ አስታወቀ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሐሙስ ኅዳር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በጊዮን ሆቴል ሊያደርገው የነበረውን ጋዜጣዊ መግለጫ ከኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት እውቅና ባለማግኘቱ መሰረዙን አስታወቀ፡፡ የኢዴፓ መሥራችና የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጋዜጣዊ መግለጫው እንደማይከናወን የተሰጠ ምክንያት የለም፡፡ ‹‹ነገር ግን ሆቴል ለመከራየት ባመራንበት ወቅት የሆቴሉ አስተዳደር ጋዜጣዊ መግለጫም ቢሆን እኛ ሳናውቅና ፈቃድ ሳንሰጥ እንዳታስተናግዱ ተብለናልና የፈቃድ ደብዳቤ አምጡ አሉን፤›› በማለት የተፈጠረውን ችግር ገልጸዋል፡፡
አቶ ልደቱ የኮማንድ ፖስቱ ጽሕፈት ቤት በመሄድ ማመልከቻ አስገብተው እንደነበር ጠቁመው፣ ‹‹ምንም እንኳን መልስ እንሰጣችኋለን ጠብቁ ቢሉንም ከረቡዕ ጠዋት መግለጫው እስከሚሰጥበት ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ድረስ ምንም ነገር አልደረሰንም፤›› ብለዋል፡፡
መግለጫውን ለመስጠት ያስፈለገበት ዓብይ ምክንያት ደግሞ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 8.3 ንዑስ አንቀጽ 8.3.11 መሠረት፣ መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ለስድስት ወራት መራዘሙን ለማሳወቅና አገሪቱ ስለምትገኝበት ሁኔታ ለመግለጽ እንደነበር ፓርቲው በጊዮን ሆቴል ቅጥር ግቢ ተሰብስበው ለነበሩ ጋዜጠኞች ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ከስድስት ወራት በኋላ ይካሄዳል የተባለው ጉባዔ ፓርቲውን ወደ አንድ የላቀ የጥንካሬ ደረጃ እንዲያሸጋግረው ለማድረግ አምስት አባላት ያሉት የጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ መቋቋሙም በመግለጫው ተመልክቷል፡፡
ፓርቲው የሚቀጥሉትን ስድስት ወራት በአግባቡ በመጠቀምና በቂ ዝግጅት በማድረግ ተጠናክሮ ለመውጣት የሚያስችለውን ጥረት እንደሚያደርግም እንዲሁ ተገልጿል፡፡
ከዚህ አንፃር የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነው ሕዝብ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ያለድርጅታዊ አመራር የሚያካሂደው ትግል የትም ሊደርስ እንደማይችል ተገንዝቦ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዙሪያ እንዲሰባሰብና አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ፣ እንዲሁም መንግሥት የጠንካራ ፓርቲዎች አለመኖር በአገራችን እያስከተለ ያለውን የፖለቲካ ቀውስ በአግባቡ በመገንዘብና ያለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚና ሊገነባ የሚችል የብዙኃን ፓርቲ ሥርዓት አለመኖሩን በመረዳት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥር ጠይቋል፡፡
በተጨማሪም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጣዊ ድክመታቸውን በሀቅ በመገምገም ጥራት ባለው ሐሳብና ድርጅታዊ መዋቅር ራሳቸውን ማጠናከር፣ እርስ በርስ ከመጠላለፍና ከመናቆር ይልቅ ጠንካራ ኅብረትና ውህደት በመፍጠር የሕዝቡን ትግል ማቀናጀትና ማስተባበር እንደሚጠበቅባቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡ የአገሪቱ ምሁራን የሕዝቡን ትግል ዳር ቆሞ ከመታዘብና ከመተቸት ይልቅ፣ በሚያምኑባቸው ፓርቲዎች ውስጥ ተሰባስበው ትግሉን በዕውቀታቸውና በገንዘባቸው የማጠናከር ሚና እንዲጫወቱ ጥሪውን ለማስተላለፍ የተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደነበር በመግለጫው ተመልክቷል፡፡   Read more here

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time