ባቡር መንገድ (የመኪና መንገድ) አዲስ አበባ ላይ የተጀመረው በ1894 ዓ.ም. ቢሆንም፣ በእንጦጦ ዳገት ላይ ባቡር መንገድ የተሠራው በ1897 ዓ.ም. ነው፡፡ መንገዱ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በእንጦጦ ዳገት ላይ እየተጥመዘመዘ እስከ ማርያም ቤተክርስቲያን ድረስ በመሐንዲሱ በሙሴ ካስተኛ ተቀይሶ ዳገቱ እየተቆፈረ መደልደሉን ብላታ መርስኤ ሐዘን ወልደቂርቆስ ‹‹የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ›› በሚለው መጽሐፋቸው አስፍረውታል፡፡ ‹‹ባቡር መንገድ›› የሚባለው ለመኪና ማስኬጃ እንደሚስማማ ተደርጎ ከመሠራቱ ባለፈ ባህር ዛፍም ተተክሏል፡፡ ከዚህ ቀደም በ1878 ዓ.ም. እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን የታነፀች ሲሆን፣ አፄ ምኒልክም በሥራዎቹ ላይ ይገኙ ነበር፡፡
አፄ ምኒልክ እንጦጦን ከተማ ካደረጉበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ሃይማኖታዊና መንግሥታዊ እንዲሁም የግል ተቋማት ሥፍራውን ለማልማት ቢረባረቡም፣ እንጦጦ ከአዲስ አበባ ቀድማ የመቆርቆሯን ያህል አልለማችም፡፡ ከቱሪስት የምታስገኘው ገቢም እንደ ጥንታዊነቷ አይደለም፡፡ በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእንጦጦ አረንጓዴ መቀነት የሚያርፍ፣ የጉለሌና የየካን ተራሮች የሚያካትትና ለአዲስ አበባ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚቆጠር ትልቅ ፕሮጀክት ለእንጦጦ ልማት አቅዷል፡፡ ዕቅዱም የእንጦጦ፣ የጉለሌና የየካ ሰንሰለታማ ተራራዎችን ያከተተ 4,200 ሔክታር መሬትን የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ ነው፡፡
እንጦጦና አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ ስትራቴጂ ዕቅድ ተዘጋጅቶም ሰኔ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በሰኔ 2009 ዓ.ም. አጋማሽ መገባደጃ ላይ የእጦጦና አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ፕሮጀክት አስመልክቶ ወደ ትግበራ ከመገባቱ በፊት፣ ከታሪክ ምሁራን፣ ከሥነ ሕንፃ ባለሙያዎች በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከተሰማሩ ተቋማትና ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ተደርጎ ሐሳቦች እንዲካተቱ እንደሚደረግ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባና የከተማዋ ቱሪዝም ትራንስፎርሜሸን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ድሪባ ኩማ ተናግረው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት አዲስ አበባ ከቱሪስት መስህብ የምታገኘውን ገቢ ያሳድጋል የተባለውንና በእንጦጦ ጥብቅ ደን፣ በየካ ዋሻ ሚካኤልና ጉለሌ የዕፅዋት ማዕከልን ይዞ በተራራማው 4,200 ሔክታር መሬት ላይ በሚያርፈው ፕሮጀክት ረቂቅ ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ የተለያዩ አስተያየቶችና ግብዓቶች ተሰጥተዋል፡፡
በአረንጓዴው የእንጦጦ ሰንሰለት የሚያርፍ የፈረስ መጋለቢያ ሥፍራ፣ የቱሪስት ማረፊያ ቦታዎች፣ የቱሪስት መረጃ መስጫ ማዕከል፣ የአዕዋፋት ዕይታ ሥፍራዎች፣ አፀደ እንስሳት፣ የአየር ላይ የኬብል መኪና ኢኮሎጂና ሪዞርቶች በስፍራው የሚገነቡ የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ናቸው፡፡
የባህል ማዕከል ግንባታ ከዕቅዶቹ አንዱ ሲሆን፣ በዚህ ሥር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዕውቅና የሰጣቸውን 76 የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚወክል የባህል ማዕከል ይኖራል፡፡ የዕደ ጥበባት ማሠልጠኛ፣ ማሳያና መሸጫ ማዕከል እንዲሁም የአዲስ አበባ ማማ ይገነባል፡፡
ፕሮጀክቱ የስፖርቱን ዘርፍ ያካተተ ሲሆን፣ የመሮጫ መም፣ የመዋኛ ገንዳ፣ የአትሌቶች ዌልነስ ማዕከልና ካምፕም ይኖሩታል፡፡
የአካባቢን ተፈጥሯዊ ሀብት በመጠቀም፣ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ፣ ቅርሶችን በመጠበቅና በማልማት መካከልም ሚዛናዊ መስተጋብርን የሚፈጥር ፕሮጀክት መሆኑ ተነግሯል፡፡
አዲስ አበባ ከያዘቻቸው ስድስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነውን እንጦጦና አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ ፕሮጀክት፣ በረቂቅ ደረጃ በተቀመጠው መሠረት 4.8 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር የሚፈጅ ሲሆን፣ ግንባታውም ከአምስት እስከ አሥር ዓመት ይወስዳል፡፡ ሥራ በጀመረ በስድስት ዓመት ውስጥ ወጪውን ይሸፍናል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፣ በአሥር ዓመት ውስጥ ደግሞ 63 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በእንጦጦ አረንጓዴ ሰንሰለት ውስጥ በሚገኙት ጉለሌና የካ ክፍለ ከተሞች፣ በስተሰሜን ሴፕቴምበር 11፣ በስተደቡብ አዲስ አበባ ከተማ፣ በስተምዕራብ ፍተሻ በስተምሥራቅ የካ አባዶ ወሰኑን አድርጎ የሚሠራው የቱሪዝም ልማት፣ ለቱሪዝም ዘርፍ ቅድሚያና ትኩረት በመስጠት ከዓለም በ118ኛ፣ በመሠረተ ልማት 134ኛ፣ በተወዳዳሪነት 118ኛ፣ (ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም 2016) የምትገኘውን ኢትዮጵያ፣ ደረጃ ያሻሽላል፣ በአፍሪካም በ2013 ዓ.ም. ከአምስቱ የቱሪስት መዳረሻ አገሮች አንዷ ለማድረግ ለተጀመረው ሥራ ግብዓት ይሆናል፡፡
የእንጦጦና አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በ2009 ዓ.ም. ባደረገው ዳሰሳ፣ በፕሮጀክቱ በተያዙ ሥፍራዎች ጥንቸል፣ ቀበሮ፣ ሚዳቋ፣ ጦጣ፣ ጅብና ጃርት የሚገኙ ሲሆን፣ ከአዕዋፋት አቢሲኒያን ካትበርድና የሎው ፍሮንትድ ፓሮት (ብርቅዬ ዝርያዎች ናቸው)፣ 11 ብርቅዬ ሊሆኑ የተቃረቡ እንዲሁም አራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥጋት ውስጥ ያሉ አዕዋፋት ይገኛሉ፡፡
ከአዕዋፋትና ከዱር እንስሳት በተጨማሪ የእንጦጦ አብዛኛው ክፍል በባህር ዛፍ ቢሸፈንም፣ የፕሮጀክት ሥፍራው በሚያርፍባቸው ስፍራዎች የአበሻ ጥድ፣ ወይራ ዛፍ፣ አልፎ አልፎ የኮሶ ዛፍ፣ የዝግባ ዛፍ፣ ባዝራ ግራር፣ አጋምና ቀጋም ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ስፍራው ዛፍ የሞላበት ቢመስልም ውስጡ የተራቆተ በመሆኑ ፕሮጀክቱ የተጎዱ ስፍራዎችን መልሶ የማልማት፣ ባህር ዛፎችን በአገር በቀል የመተካትና አካባቢውን በደን የማልበስ ዕቅድ አለው፡፡
በአረጓዴ ሰንሰለት (በፕሮጀክቱ) ውስጥ የሚገኙት ክፍለ ከተሞች ጉለሌና የካ ሲሆኑ፣ በጉለሌ ሦስት፣ በየካ ስምንት ወረዳዎች ላይ ፕሮጀክቱ ያርፋል፡፡ በየካ 8,291 የግል ይዞታ (አባዎራ) 99 መንግሥታዊና ሃይማኖታዊ ተቋማት እንዲሁም 38 የቀበሌ ቤቶች በአጠቃላይም 8,428 ስፍራዎች በይዞታ ሥር ያሉ ሲሆን፣ በጉለሌ የግል 388፣ መንግሥታዊና ሃይማኖታዊ ተቋማት አራት እንዲሁም የቀበሌ ቤቶች 85 በአጠቃላይ 477 ይዞታዎች አሉ፡፡ ፕሮጀክቱም ይህንን ታሳቢ አድርጎ የሚተገበርና በመልሶ ልማቱ የሚነሱ ይዞታዎችንና ነዋሪዎን ጥቅም የሚያስጠብቅ ይሆናል፡፡
ከ12 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል የተባለው ፕሮጀክት፣ ለልማት ተነሺዎች ቅድሚያ የሥራ ዕድሎች የሚያስገኝ ሲሆን፣ በተራራው ዙሪያ ያሉ አጎራባች ማኅበረሰቦች በሁለተኛ ደረጃ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ የፕሮጀክቱን ማኅበራዊ ዘላቂነት ለማረጋገጥም ልማቱ ከአካባቢው እሴቶች ጋር ተስማሚ ይደረጋል፡፡
አምፊቲያትርን ጨምሮ የተለያዩ ሙዚየሞችን በሚያካትተው በዚህ ፕሮጀክት፣ ከተለያዩ ተቋማት የተሰባሰቡ ባለሙያዎች በቢሾፍቱ በተካሄደው ውይይት ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፕሮጀክቱ መልካም መሆኑን ገልጸው፣ ፕሮጀክቱ ከመነሻው የሚያካትታቸው ስፍራዎች እንጦጦና አካባቢው የሚል እንደነበር በማስታወስ የኦሮሚያን ወሰን መካለሎች ታሳቢ ያደረገ እንደማይመስልና ግልጽ ያልሆኑ የኦሮሚያና አዲስ አበባ ግንኙነት ባለበት ፕሮጀክቱ መፈጸሙ ችግር እንዳይፈጥር ዳግም ቢታይ የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ጋር ያለው የወሰን ግንኙነት ሰፊ በመሆኑም ይህን ቢያገናዝብ፣ ቱሪዝም ለፍትሐዊነት ሀብት ክፍፍል ጥሩ ሚና ቢኖረውም፣ በግልጽ ፍትሐዊ የሚያስብለው የቱ ጋር ነው? ብዙ ነገሩ ከባለሀብት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ይህ ማኅበረሰቡን በሰፊው የሚነካ ስለሆነ በዚህ መልኩ ብናየውም ብለዋል፡፡
ባህላዊ ሙዚየሙ የታሰበው የብሔር ብሔሰቦች መንደር ነው፡፡ ነገር ግን የፌዴራል ድርሻ ምንድነው? ይህ ቢታይ የሚል ሐሳብም አቅርበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የፕሮጀክቱ የቦርድ አባል ዶ/ር ሙሉጌታ ፍሰሃ፣ በተራራው ዙሪያ በአጎራባች አካባቢዎች የአካባቢ ማኅበረሰብ በልማቱ ተሳታፊ እንዲሆንና በፕሮጀክቱ ዕቅድ ከተካተቱት ኢንቫይሮመንትና ኢኮኖሚ ቀጣይነት ጎን ለጎን የባህል ቀጣይነት ወሳኝ ስለሆነ ይህ እንዲታሰብ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበርን ወክለው የተገኙት ዶ/ር ቴድሮስ አጥላባቸው፣ ዕቅዱን ወደ ተግባር መወለጥ መልካም ቢሆንም፣ ሥራው ትልቅ ከመሆኑ አንፃር አንዴ ከመተግበሩ በፊት ኢኮሎጂውን እያዩ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በአንድ ጊዜ ስንት ሰው ያስተናግዳል? ምን ዓይነትን አገልግሎት ይሰጣል? ሆቴል ከሆነ ይህን ያህል መኝታ፣ መዋኛ ከሆነ መተንተን አለበት ብለዋል፡፡
አካባቢውን እንደ አንድ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግም በስፍራው የፖሊስ፣ የጤና ፖስት፣ የባንክ አገልግሎትና ሌሎችም ከማስፈለጋቸው በተጨማሪ የሙዚቃ ጋለሪ አምፊቲያትሩ ውስጥ ሊኖር ቢችልም፣ የሙዚቃ ጋለሪ ለብቻ ያስፈልጋል፣ ቴሌስኮፕ ተደርጎ ከዋከብት የሚታይበት ስፍራም ወሳኝ ነው ተብሏል፡፡
በአካባቢ ያሉት ፕሮጀክቶች ማለትም ሔሪቴጂ ትረስት ሴቴምበር 11፣ የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከልና ሌሎቹም ስፍራውን ለማልማት እየሞከሩ መሆኑ ተገልጾም፣ የአዲስ አበባው ፕሮጀክት ከነዚህም ጋር ተጣምሮ መሥራት እንዳለበት ሐሳብ ተሰንዝሯል፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተገኙት ቀሲስ ሰለሞን ቶልቻ፣ ቤተክርስቲያኒቷ በፕሮጀክቱ አካባቢ አራት ቤተክርስቲያናት እንዳሏት፣ ቤተክርስቲያኒቷ ከምትሰጠው አገልግሎት ውስጥ በእንጦጦ ማርያም ምዕመኑ ከመቶ ዓመት በፊት አገልግሎት የሚያገኝበት የፀበል ቦታና የቀብር ስፍራ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ቦታው የቱሪስት መዳረሻ ሲደረግ ዘመናዊ የቀብር ቦታ እንዲገነባና በፀበል ቦታውም የመፀዳጃ አገልግሎት ታሳቢ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡ በደርግ ጊዜ የተሠራው የእንጦጦ ሙዚየም ጠባብ ቢሆንም ብዙ ቅርሶች እንዳሉት ጠቁመው፣ እንጦጦ ማሪያም ሙዚየም በአንዴ 50 ሰው መያዝ እንደማይችል፣ የቱሪስት መስህቦችም በመጋዘን ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ እነዚህ መኖራቸውንም አውቆ ከቤተክርስቲያኒቷ ጋር ቢሠራ፣ ቤተክርስቲያኒቷ ለመተባበር ፍላጎት እንዳላትም አክለዋል፡፡
አረንጓዴውን የተፈጥሮ ሀብት ከመጠበቅ አኳያ የከተማውን መሬት ያጥለቀለቀው የፌስታልና የፕላስቲክ ውኃ መያዣ አደብ ሊበጅለት ይገባል ያሉት ቀሲስ ሰለሞን፣ ኬንያ ፌስታል ምርት ለአገር ጠንቅ ነው በሚል ማገዷን በማስታወስ፣ በአገራችን የውኃ ፕላስቲኮች ተመልሰው ጥቅም ላይ ካልዋሉ በስተቀር ፕሮጀክቱ ቢሠራ በፌስታልና በውኃ ፕላስቲክ ይበከላል፣ ለዚህ ምን ታስቧል? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ቤተክርሰቲያኒቷ ለፕሮጀክቱ ድጋፏን እንደምትሰጥ፣ ፕሮጀክቱም ቤተክርስቲያኒቷ ከምትሰጠው አገልግሎት ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ እንጠይቃለንም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የስፔስ ሶሳይቲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብነት እዝራ በበኩላቸው፣ የስፔስ ሶሳይቲው ያለውን ኦብዘርቫቶሪ ቱሪስቶች ለመጎብኘት እንደሚመጡ በማስታወስ፣ አዲሱ ፕሮጀክት የተረሳውን ሳይንስና ቴክኖሎጂ በተለይ ስፔስ ሳይንስን እንደ ቱሪስት መዳረሻ ቢጠቀመውና ሳይንስና ቴክኖሎጂን የሚወክል ሙዚየም ቢሠራ መልካም ነው ብለዋል፡፡
የቱሪስት መስህብ ባህል ብቻ ከሚሆንና ዓለምም ሳይንስና ቴክኖሎጂን እየተጠየቀመው ስለሆነ፣ ፕሮጀክቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሙዚየም ቢኖረው፣ ገቢውን በ40 እና 50 በመቶ ይጨምረዋል የሚል አስተያየትም ሰንዝረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወንዞች ጽሕፈት ቤት የተገኙት አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ ፕሮጀክቱ የቀረው ነገር እንዳለ ነው የተገለጹት፡፡ የፕሮጀክት አዋጭነት መልካም መሆኑን ገልጸው፣ ከከተማ ፕላንና ከኢንቫይሮመንት አንፃር ፕሮጀክቱ ምን ማለት ነው? የሚሉት እንዲታዩ የሚከተሉትን አንስተዋል፡፡
እንደ አቶ ዋለልኝ አዲሱ የከተማ መዋቅራዊ ፕላን 22 ሺሕ ሔክታር መሬት ለኢንቫይሮመንት ብሎ ትቷል፡፡ በዚህ ውስጥ ለአረንጓዴ ብቻ ሳይሆን ወንዝና ሌሎችም አሉ፡፡ አሁን ፕሮጀክቱ የሚያርፍበት በፕላኑ ከሰው ንክኪ ጥብቅ ተብሎ የተቀመጠ ነው፡፡ የቀረበው ፕሮፖዛል ደግሞ ጥብቅ ከተባለው ሥፍራ ሁለት በመቶ ያህል ይሸፍናል፡፡ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የሚዘልቀው የእንጦጦ አረንጓዴ ቀበቶ ተራራ በብዛት ከኢንቫይሮመንት አገልግሎት ውጪ እየዋለ ነው፡፡
ቦታው የከተማዋ መተንፈሻና ከተማዋን ከጎርፍ ለመጠበቅ የሚውል መሆኑን፣ መለስ ፋውንዴሽን፣ ሔሪቴጅ ትረስትና ሌሎችም፣ ከ8,000 በላይ ነዋሪዎች በውስጡ መኖራቸውን በመጥቀስ ‹‹ይህ ፕሮጀክትና ሌሎችም ለምን እንጦጦ ላይ ብቻ ይሆናሉ? ከተማዋ በተራራ የተከበበች ነች፡፡ ለምን ሌሎች ተራሮች አይታዩም? የእንጦጦ ተራራ ለምን በፕሮጀክቶች ይታጠራል?›› የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል፡፡
በፕሮጀክቱ የተለያዩ ዓይነት የመኝታ ክፍሎ ያሏቸው ሞቴል ወይም ሆቴልስ፣ የተራራ ሪዞርትና ኢኮ ሎጅ እንደሚኖሩ የተቀመጠ ሲሆን፣ አቶ ዋለልኝ መኝታ ክፍሎች እዚያው መኖራቸውን አልደገፉትም፡፡ በሰጡት አስተያየትም፣ ቱሪስቶች ተራራው ላይ ደርሰው፣ መስህቦችን ዓይተው መመለስ አለባቸው እንጂ አዚያው ማደር የለባቸውም፣ ሌሎች አገሮችም ይህንን ይከተላሉ ብለዋል፡፡
በአካባቢው ከዚህ ቀደም ያሉ ፕሮጀክቶች ከአዲስ አበባው ጋር እንዲተሳሰሩ፣ ሱሉልታ የአትሌቲክስ መንደር እያለ በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት እጦጦ ላይ መገንባቱ አዋጭ ያደርገናል ወይ? የሚልም ተነስቷ፡፡ ጎልፍ የለንም፣ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች የሚፈልጉት ነው፡፡ ከዓለም አቀፍ ደረጃ አንፃር አንድ ያለንም በቂ አይደለም፡፡ ይህ ቢታይም ተብሏል፡፡ ከኦሮሚያ ባህል ማዕከል የተወከሉት ባለሙያ ደግሞ፣ አዲስ አበባ እንደ ከተማ መስተዳደር ክልሎችን ወክሎ ነው የባህል ማዕከልን የሚሠራው? ወይስ ከክልል ጋር ተቀናጅቶ? የፌዴራል ሚና ውስጥ የገባ ይመስላል ብለዋል፡፡
በፕሮጀክቱ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የኢትዮጵያ ቅርሶች ይገነባሉ የሚለውንም፣ በየክልሉ ቅርሶቹ በአካል እያሉ የክልሎችን ሀብት አይሻማም ወይ? ለምሳሌ ኮንሶን፣ አክሱምንና ፋሲልን እዚህም ማምጣት መገንባት ምን ያህል አዋጭ ነው? ቱሪስቱ ቦታው ድረስ ሄዶ ማየት የለበትም ወይ? እንዴት ታዩታላችሁ?ም ብለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማኅበር የተወከሉ ባለሙያም፣ አዲስ አበባ የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲና ከመሆኗ አንፃር በፕሮጀክቱ የሚሠሩ ሪዞርቶችና ሌሎችም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሉ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የአገሪቱ ሆቴሎች ኢትዮጵያዊነት ስለማይታይባቸው ቱሪስቶቹ የሚገኙት በመሸታ ቤቶችና በዝቅተኛ ስፍራ መሆኑን መታዘባቸውን በመግለጽ፣ የእንጦጦው ፕሮጀክት ፈጠራ በተሞላበት እንዲሠራ፣ ተቆርቋሪነት እንዲፈጠርና ኅብረተሰቡ ለቱሪስቱ የሚናገረው ወግ መኖር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ200 በላይ ባህላዊ ስፖርቶች እንዳሏት በማስታወስም፤ ከእነዚህ ለፕሮጀክቱ አመቺ የሆኑ እንዲካተቱ፣ የኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክም ቢቃኝ የሚል ሐሳብ ተሰንዝሯል፡፡
በፕሮጀክቱ እንደ ፈረንሣዩ ኤፍል ታወር ያለ የአዲስ አበባ ማማ ተራራው ላይ ለመገንባት የታቀደ ሲሆን፣ ይህ ለገሃር አካባቢ ቢሆን የሚል አስተያየት ተሰጥቷል፡፡
ከጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞችና ጀግኖች ማኅበር የተገኙት ሻምበል ዋኘው ዓባይ፣ ‹‹የአርበኞች ታሪክ የታሪክ ማኅደር ነው፡፡ ይህ በፕሮጀክቱ በሚሠራው ሙዚየም ላይ አልተካተተም፡፡ አንድ አገር ከመነሻው ማሰብ አለበት፡፡ ለቱሪዝም መስክ ገቢ የሚያስገኙ መሣሪያዎችም አሉ፤›› በማለት የጀግኖች አርበኞች ታሪክ ያለበት ሙዚየም በፕሮጀክቱ እንዲካተት ጠይቀዋል፡፡
ውይይቱን የመሩት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው፣ ‹‹ረቂቅ ስትራቴጂ ዕቅዱ ላይ የተለያዩ አካላትን ጨምረን ያወያየነው ያላየነውን እንድታሳዩን፣ የረሳነውን እንድታስታውሱንና ማካተት ያለብንን እንድትነግሩን ነው፤› ብለዋል፡፡ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች መልስ የሰጡት የእንጦጦና አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ህያብ ገብረፃዲቅ፣ ፕሮጀክቱ አዲስ አበባ ክልል ውስጥ ብቻ እንደሚያርፍ እስከ ሱሉልታ የሚደርሰውን የኦሮሚያ ቱሪዝም ቢሮ ቢያለማው የሚል ሐሳብ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር እንጦጦ፣ የካና ጉለሌ ላይ እንደሚሠራና ኃላፊነቱም በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ሥፍራዎች መሆኑን አክለዋል፡፡
የባህል ማዕከሉን በተመለከተም፣ አዲስ አበባ ቢሠራውም የሚያለሙት ክልሎች መሆናቸውንና በዚህ ላይ ከክልሎች ጋር ውይይት እንደሚኖር አክለዋል፡፡
በአካባቢው ላይ እየሠሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶችም ወደ ልማቱ እንደሚገቡ፣ አብረው እንደሚሠሩና ከአካባቢ ጥበቃ ጋርም የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ዝግጅት መኖሩን ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው ያሉ ሃይማኖታዊ ተቋማት ሀብቶች በመሆናቸው፣ በስፍራው ዘመናዊ መቃብር ለማድረግ ውይይት ላይ መሆናቸውን ከቤተክርስቲያን ጋር አብረው እንደሚሠሩም አክለዋል፡፡
የሳይንስ ሙዚየም እንዲኖር ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ አቃቂ አካባቢ ዘመናዊ የሳይንስ ሙዚየም ስላለ ተደጋጋሚ እንዳይሆን መተውን፣ ጎልፍ በቦሌ አካባቢ ለመሥራት በከተማዋ ማስተር ፕላን ስላለም በእንጦጦው የታሰበው መሰረዙን ተናግረዋል፡፡
የአትሌቲክስ ልዩ ሙዚየም፣ ዓባይ ልዩ ሙዚየምና ቡና ልዩ ሙዚየም እንደሚኖር፣ ተረስቶ የነበረው የአርበኞች ሙዚየምም በጥናት እንደሚገባ፣ በፕሮጀክቱ ላሊበላ፣ ጢያና ሌሎችን ቅርሶች የሚመስል መሠራቱ ታሪኩን ለማሳየትና የቱሪስቱን ፍላጎት ለማነሳሳት እንጂ የክልሎችን ድርሻ ለመሻማት ወይም ቅርሶችን ደግሞ ለመሥራትና ለመተካት እንዳልሆነ፣ ፕሮጀክቱም ሌሎችን የመተካት ሳይሆን እንደ ማነሳሻ የማሳየት እንደሆነ አክለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ልዩ መለያ የሚሆን 500 ሜትር ርዝመት ያለው ማማ የሚገነባ ሲሆን፣ አናቱም የኦዳ ቅርፅ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ በኦዳና በገዳ መካከል ልዩነት መኖሩ በውይይቱ በመነሳቱ፣ ይህን ባለሙያዎች አይተውት የሚስተካከል ይሆናል ተብሏል፡፡
የመጀመሪያ ዙር ዲዛይን ሲቀርብና ሲተች፣ የጎደሉ ሙሉ እንደሚሆኑ ለዲዛይን ሥራውና ጥናቱ ብዙ ጊዜ እንደሚሰጥና የማያዳግም ሥራ እንደሚሠራም ታክሏል፡፡
የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረፃዲቅ ሐጎስ፣ በበኩላቸው፣ ከኦሮሚያ ድንበር ጋር ያለውን ሁኔታ አስመልክተው፣ ጥናቱ በዓለም ባንክ ድጋፍ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር መጠናቱን፣ ለዚህም በቱሪዝም ዙሪያ ለውጥ ለማምጣት በተመረጡ አካባቢዎች ማለትም ላሊበላ፣ አክሱም፣ አዲስ አበባና አካባቢዋ በሚል መጠናቱን፣ ቢሮውም አዲስ አበባ ላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብሎ የተነሳበትን እንጦጦን እንደሚያለማና በቀጣይ ሌላ ሠርተው ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ጥናቱ በአገር ደረጃ ሲሠራ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ኦሮሚያ ጋር የሚገናኙ የእንጦጦ አካባቢዎች ተያይዘው ተሠርተው የነበረ ቢሆንም፣ ረቂቅ ስትራቴጂክ ዕቅዱ የተዘጋጀው በጥናቱ መሠረት ሳይሆን እንጦጦ ዋሻ ሚካኤል፣ የካ አካባቢና ከጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል አካባቢ ያሉትና አዲስ አበባ ክልል ውጥስ ብቻ የሚገኙ መደረጋቸውን፣ ገልጸዋል፡፡ ወደፊት ከወሰን ጋር ያለው መስመር ሲይዝ በሱሉልታና በሌላም በኩል ያለውን ከኦሮሚያ ክልል ጋር በጋራ ለማልማት የሚከለክል ነገር እንደሌለ በመጥቀስም፣ ከአዲስ አበባ ጀምረን ወደፊት ከኦሮሚያ የሚዋሰኑት ላይ አብሮ ለመሥራት ይቻላል ብለዋል፡፡
ከማስተር ፕላኑና ከአካባቢ ጥበቃ አንፃርም ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ደን የሚጋፉ እንደማይሆን፣ 98 በመቶውን ደን በጠበቀ መልኩ የሚሠራ እንደሆነና በጥንቃቄ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
ዲዛይኑን በሚመለከት ከህዳሴ ግድብ ተለይቶ እንደማይታይ፣ ብዙ መታየት የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉና ለዲዛይኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጨረታ እንደሚወጣ ተናገረዋል፡፡
የባህል ማዕከሉን በተመለከተ አዲስ አበባ የብሔር ብሔረሰቦች መቀመጫ፣ ትንሿ ኢትዮጵያ እንደመሆኗ ይህንን የሚያሳይ የባህል ማዕከል በአገሪቱ አለመኖሩ፣ ከተማዋ በየቦታውም ለምን የባህል ማዕከል የላትም? ከተማዋ ያስፈልጋታል የሚል አስተያየት ሲሰጥ በመክረሙ የፕሮጀክቱ አንዱ አካል ተደርጓል፡፡
በማዕከሉ የሚሠሩት የቅርስ ናሙናዎች ክልሎችን የሚሸፍኑ ሳይሆኑ፣ ወደ ከተማዋ የሚገባ ቱሪስት የባህል ማዕከሉን ሲጎበኝ ሌሎች ክልሎች ያለውን ፀጋ ዓይቶ ስፍራው ለመሄድ እንዲነሳሳ የሚያደርግና የክልሎችን ተጠቃሚነት የሚደግፍ እንጂ የሚሻማ አይሆንምም ብለዋል፡፡
ይዘቱን በሚመለከት ከክልሎች ጋር በጋራ የሚመከርበት ሲሆን፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር ምክክር ተጀምሯል፡፡ ፕሮጀክቱ የሁሉም ኅብረተሰብ የጋራ አጀንዳ ከተደረገ በኋላም ወደ ትግበራ እንደሚገባ አክለዋል፡፡
ኬብል ካር ውድ ነው፣ ለውጭ ሰው ነው የታሰበው፣ አገሬውስ ውድ አይሆንበትም ወይ? ተብሎ ለቀረበው ጥያቄም፣ አገሬውም የውጭውም የተሻለ መዝናኛ አካባቢ እንዲያገኝ ታስቦ የሚሠራው ነው ተብሏል፡፡
አቶ አባተ በበኩላቸው፣ ቱሪዝም ሲታሰብ ተባብሮና ተመጋግቦ እንደሆነ ገልጸው፣ ሲንጋፖር ላይ የኢትዮጵያ መስህብ እንዳለ በመጠቆም፣ ፕሮጀክቱ ለአንድ አገር ለአንድ ዓላማ ተብሎ የሚሠራ መሆኑን፣ ከወሰን ጋር ያለውን አዲስ አበባና ኦሮሚያ ተነጋግረው በጋራ እንደሚፈቱት፣ በዋናነት ተደጋግፈን ብናለማው ምንኛ አካባቢውንና አገራችንን ይጠቅማል፣ ውብ ብናደርገው መልካም ነው ብሎ ማሰብ እንደሚገባና ወሰኑ እንደማያስጨንቅ፣ ሊያስጨንቅ የሚገባው በጋራ እንዴት አልምተን፣ አካባቢውን ውብ እናድርገው፣ እንዴትስ ሕዝቡንና አገሪቷን ተጠቃሚ እናደርግ? ለሚለው መሆን እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
እንጦጦ በደን የተሸፈነ ቢመስልም ውስጡ ሲገባ 60 በመቶው የተራቆተ መሆኑን በመናገርም፣ ሥፍራውን በአረንጓዴ መሸፈን፣ የተራቆተውን ማልማት የፕሮጀክቱ አካል እንደሆነ፣ ግንባታው በሙሉ ባህላዊ እንደሚሆንና ዲዛይኑ በጥልቀት እንደሚሠራና ውይይት እንደሚደረግበት ተናግረዋል፡፡
ውይይቱን የዘጉት ከንቲባ ድሪባ ኩማ፣ ‹‹ፕሮጀክቱ ተፈጥሮ የለገሰችንን ፀጋ ወደ ተጨባጭ ጥቅም ለመቀየር የተጀመረ ነው፤›› በማለት፣ አዲስ አበባ በተራሮች የተከበበች ብትሆንም ተራሮቿና ወንዞቿ የውበትና የሥልጣኔ ምንጭ መሆን ሲገባቸው ተበክለው ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱንም ይህንን የሚቀለብስ፣ አዲስ አበባንና ኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻ የሚያደርግና ለውጥ የሚታይበት ብለውታል፡፡ Read more here