Sunday, May 27, 2018

ደ/ር አብይን ከሰሜን አሜሪካ የስፖርት ዝግጂት አትምጣ ማለት ፈጣሪም ልምጣ ቢል ተመሳሳይ ጥያቄ የሚያነሱ ይመስለኛል።

ሙግትና ሽሽት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ፣ በ35ኛው የሰሜን አሜሪካ የስፖርትና የባህል ዝግጅት ላይ ለመገኘት ጥያቄ ማቅረባቸውን ፌዴሬሽኑ አረጋግጧል። ጥያቄው የቀረበው በኤምባሲው በኩል ነው።
ከትናንት ጀምሮ የተወራ ነገር በመሆኑ እንደዜና ከ24 ሰዓት በኋላ ማቅረብ ላያስፈልግ ይችላል። አስተያየት ግን ቢሰጥበት አይከፋም። በተለይ “ይምጡ፣ አይምጡ” የሚሉ ሁለት የማይመጣጠኑ ጎራዎች መኖራቸው የሚታይ ነውና። በነገራችን ላይ “ፈጣሪም ልምጣ ብሏል” ቢባል፣ “ባይመጣ ይሻላል” ብሎ የሚከራከር ሰው አለ ብል ማጋነን ይሆናል እንጂ፣ ውሽት ግን ሊሆን አይችልም።
በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ህዝብ ልብ ውስጥ በአጭር ጊዜ በመግባት ቀዳሚው ዶክተር ዐቢይ ናቸው። ከመሬትና ከገንዘብ፣ ከሥልጣን እና ከክብር በላይ የዜጎቻቸው ጉዳይ ግድ የሚላቸው መሪ ዶክተር ዐቢይ ናቸው። በሁለት ወር ውስጥ አሥራ ምናምን ዓመት የታሰሩትን በአገር ቤት ፈተዋል። በሁለት ወር ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ በባዕድ አገር እስር ቤት የነበሩትን አስፈትተዋል። የታመሙትን የሚችሉትን ያህል በስልክም በአካልም ጠይቀዋል፣ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ዜጎቻቸውን እየሰበሰቡ ችግርና ብሶት አዳምጠዋል፣ ህልማቸውን ፣ ዕቅዳቸውን ነግረውናል። ኢትዮጵያዊነት ጠፋ፣ አለቀለት ሲባል ፣ ማንም ባልሰጠው አስደማሚ ትርጉም ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ኢትዮጵያ መሆናችንን ነግረውናል። ኢትዮጵያ ማለት ሁላችንም መሆናችንን ነግረውናል።
ብቀላ፣ ጥላቻ፣ ቂም፣ ለማንም እንደማይጠቅም፣ ወደፊት እንጂ ወደኋላ ማየት እንደማይኖርብን ነግረውናል። ይህ ንግግራቸው “ለማንዴላ ሲሆን የሚያስጨበጭብ፣ ለዐቢይ ሲሆን የሚያስኮርፍ” እንዳይሆን እንጠንቀቅ። ማንዴላ ዛሬ በጥቁሩም በነጩም ክብር ያገኙት፣ በዚሁ “ወደፊት እንጂ፣ ወደኋላ አንይ” አቋማቸው እኮ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ማንም ሳያስገድደው፣ ማንም ሳያዘው፣ በቀበሌና በወረዳ ግዳጅ ሳይጣልበት ፣ በገንዘቡ እየገዛ ምስላቸውን በየመኪናው ለጥፎ የሚታየው፣ በኪሱ ይዞ የሚዞረው፣ ፣ ዶክተር ዐቢይ ሊናገሩ ነው ሲባል፣ ቲቪ ለመክፈት የሚሽቀዳደመው፣ ያየውና የቀመሰው ነገር ስላለ ነው።
ርግጥ ነው፣ ፍጹም ናቸው፣ እንከን አልባ ናቸው፣ ያልሰሩት ሥራ ፣ ያልጨረሱት ፕሮጄክት የለም ማለት አይደለም። ራሳቸውም ቢሆን “እኔ ሰው እንጂ እግዚአብሔር አይደለሁም፣ ልሳሳት እችላለሁ፣ በአንድ ጀንበር የምትፈልጉትን ሁሉ ላላደርግ እችላለሁ፣ ግን አግዙኝ” ሲሉ የተናገሩት ይህንኑ አውቀው ነው። አንድ ሚስማር ሳናቀብል፣ ፎቁ ለምን አላልቀም የምንል ካለን ተሳስተናል። ሂደቱን ሳናግዝ፣ በውጤቱ ልንበሳጭ አንችልም።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከኢትዮጵያ እና ፕሮፌሰር አልማርያም ከአሜሪካ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን ምስክርነት ከገጾቻቸው ላይ ማየት የበለጠ እኔ ያልኩትን ያብራራል። እነዚህ ጉምቱ፣ ግራና ቀኙን ማየት የሚችሉ፣ ለማሞገስ የማይቸኩሉ ምሁራን አገናዝበው የሰጡት ምስክርነት ብዙ ነገር ያብራራል።
በሰሜን አሜሪካው ፌዴሬሽን ዝግጅት ላይ ልገኝ ማለታቸው እውነት ከሆነ፣ ለፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን በውጭ ለሚገኘው ኢትዮጵያዊም ክብር ነው። አስቡት፣ ተጠይቀው ሳይሆን ራሳቸው ጠይቀው ነው ልምጣ አሉ የተባለው። የትኛው መሪ እንዲህ ብሎ ያውቃል? ሰው እኮ በባህላችን እንኳን የሚወደውና የሚፈልገው ሰው ቤት ለመሄድ ጥሪ አይጠብቅም፣ ድግስ ቢኖር፣ ማህበር ቢኖር፣ ሠርግ ቢሆን፣ “የርሱን ድግስማ እንዴት እቀራለሁ” የሚለው የሚወደው ሰው ዘንድ ነው። ለሌላውማ ቢሆን፣ ተጠርቶም ላለመሄድ ያልተመመ ዘመዱ ታመመ፣ ያልሞተ ዘመዱን ሞተ ብሎ ይቀራል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰው መሃል የወጡ ሰው ናቸው፣ የቤተሰብ ሃላፊ፣ አገርንም እንደ አባት በይቅርታ፣ በመፍታት፣ በፍቅር ለመምራት የቆረጡ መሆናቸውን እስከዛሬዋ ቀን ድረስ አሳይተዋል። ባለፉት ሁለት ወራት ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው አይደለም ይህን ሁሉ ያደረጉት። ዛሬ አይምጡ የሚል ሃሳብ ያላቸው ወገኖች የሚሰጡትን ምክንያት ሳየው፣ .. እደግመዋለሁ .. ፈጣሪም ልምጣ ቢል ተመሳሳይ ጥያቄ የሚያነሱ ይመስለኛል።
ፌዴሬሽኑ ባለፉት 35 ዓመታት ብዙ ነገር አሳልፏል፣ ተነገዳግዷል፣ ተወቅሷል፣ አትሂዱበት ተብሎ ዘመቻ ተከፍቶበታል፣ ተለጣፊ ተቋቁሞበታል፣ ግን ምንም አልሆንም። ነገም ምንም አይሆንም። ዶክተር ዐቢይ በራሳቸው ጥያቄ ልምጣ ማለታቸው ደግሞ ይበልጡኑ የፌዴሬሽኑን ሚዛን ከፍ ያደርገዋል፣ ክብሩን ያሳድገዋል። ፌዴሬሽኑን እንደተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅት ከሚቆጥሩ ሰዎች መካከል የወጡ ሰው በአዲስ ሃሳብ፣ በአዲስ አቀራረብ መጥቼ ልያችሁ ሲሉ፣ ከዚህ የበለጠ አዲስ ነገር ምን አለ?
ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚቃወሙም ፣ ፊት ለፊት ሲያገኟቸው በሃሳብ መሞገት፣ በጥያቄ ማፋጠጥ፣ የቀረው እንዲቀጥል፣ የጎደለው እንዲሟላ ሚዛን ደፊ ነጥቦችን ማንሳት፣ “እኛ ከርስዎ ይህን ይህን እንፈልጋለን፣ እርስዎስ ከኛ ምን ይፈልጋሉ?” ብሎ እንደ አንድ አገር ህዝብ መነጋገር እንጂ፣ አንያቸው ብሎ መሸሽን ምን አመጣው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ እንደማይፈሩም ሆነ የማንንም ሃሳብና ጥያቄም ለማዳመጥ ደከመኝ የማይሉ እንደሆኑ በአገሪቷ እየዞሩ ያደረጉትን አይተናል።
ደፋርና በራሱ የሚተማመን ሰው ፊት ለፊት ይሟገታል፣ የማይተማመን ደግሞ “ላየው አልፈልግም” ብሎ ይሸሻል። የምንሟገት እንጂ የምንሸሽ አንሁን።
By Tedy from Atlanta
Add caption

No comments:

Post a Comment