Monday, December 5, 2016

ጥራቱን ያልጠበቀ የጨው ምርት ገበያውን ማጥለቅለቁ ጥያቄ አስነስቷል



የምርት ጥራት ደረጃውን ያልጠበቀ፣ የአዮዲን ይዘቱ አነስተኛ የሆነና ከነአካቴው አዮዲን የሌለው የጨው ምርት ከአፋር ክልል አፍዴራ ወደ መሀል አገር ገበያ በብዛት እየባ እንደሆነ ተገለጸ፡፡ ይህም ድርጊት ጥያቄ አስነስቷል፡፡
ለአገሪቱ ለምግብ ፍጆታ የሚውለው ጨው በአብዛኛው የሚመረተው በአፋር ክልላዊ መንግሥት አፍዴራ ሐይቅ በባህላዊ ጨው አምራቾች ማኅበር ነው፡፡ የአገሪቱ ወርኃዊ የጨው ፍጆታ 360,000 ኩንታል ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 310,000 ኩንታል የሚሆነው በአፍዴራ በባህላዊ መንገድ እየተመረተ በጨው ነጋዴዎች አማካይነት ለማዕከላዊ ገበያ ብሎም በመላ አገሪቱ ይከፋፈላል፡፡ ጨው ለሰው ልጆች ጤና አስፈላጊ የሆነውን አዮዲን የተሰኘውን ንጥረ ነገር ሊኖረው የሚገባ በመሆኑ ለምግብነት የሚውል ጨው ከአዮዲን ጋር እንዲደባለቅ ይደረጋል፡፡ አዮዲን ለሕፃናት አዕምሮ ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ የአዮዲን እጥረት የአዕምሮ ዝግመት፣ የእንቅርት በሽታንና ውርጃን እንደሚያስከትል የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
መንግሥት ለምግብነት የሚውል የጨው ምርት ከአዮዲን ጋር እንዲደባለቅ የሚያስገድድ ሕግ አውጥቷል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሕፃናት መርጃ ድርጅት ጋር በመተባበር ባህላዊ የጨው አምራቾች ማኅበራት አቅማቸውን እንዲገነቡና የአዮዲን ንጥረ ነገር በምርታቸው ውስጥ እንዲጨምሩ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
መጋቢት 16 ቀን 2003 ዓ.ም. የሚኒስትሮች ምክር ቤት የምግብ ጨው አዮዲን እንዲኖረው የሚያስገድድ ደንብ አውጥቷል፡፡ ደንቡ ማንኛውም ሰው አዮዲን የሌለው ጨው ለሰው ምግብነት አገልግሎት እንዲውል ማዘጋጀት፣ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፣ ማከማቸት፣ ማከፋፈል፣ ማጓጓዝ ወይም መሸጥ እንደማይችል ይደነግጋል፡፡ ማንኛውም ለሰው ምግብነት የሚውል አዮዲን ያለው ጨው አግባብ ባለው አካል በሚያወጣው የጨው ደረጃዎች መሠረት የጥራት ደረጃ መመዘኛ ማሟላት እንዳለበት ይጠቅሳል፡፡ ‹‹ማንኛውም ሰው ይህን ደንብ ወይም ደንቡን ለማስፈጸም የወጡትን መመርያዎች ተላልፎ ቢገኝ አግባብ ባላቸው የአዋጅ ድንጋጌዎች መሠረት ይቀጣል፤›› ይላል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ፡፡
ይህን ደንብ የማስፈጸም ሥልጣን በአዋጅ የተሰጠው የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአገሪቱን ሕግ በመተላለፍ የጥራት ደረጃውን ያልጠበቀ፣ ዝቅተኛ የአዮዲን ይዘት ያለው ወይም ከነጭራሹ አዮዲን የሌለው የምግብ ጨው ለገበያ እየቀረበ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአፍዴራ የሚገኙ የጨው አምራቾች ማኅበራት የአመራረት ጥራት ብቃት ላይ የሚነሳው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከነአካቴው አዮዲን ያልተቀላቀለበት የጨው ምርት በስፋት ወደ ገበያ እየገባ እንደሆነ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለኅብረተሰቡ አዮዲን የሌለው ጨው እየቀረበለት ነው፡፡ ልጆቻችንን አዮዲን የሌለው ጨው እየመገብን ሊሆን ይችላል፡፡ ጉዳዩ እንደ አገር አሳሳቢ ነው፤›› ብለዋል ምንጮች፡፡ እንደ ማሳያ የሚጠቅሱት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጨው የጫኑ ተሽከርካሪዎች በሰመራ ከተማ ኬላ በኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን መያዛቸውን ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ባለሥልጣኑ ደረጃውን ያልጠበቀ የጨው ምርት የጫኑ 40 ተሽከርካሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያካሄደ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ጉዳዩ ያሳሰበው የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በአፋር ክልል በሚገኙ መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ የሚያደርገውን የጨው ምርት ጥራት ቁጥጥር ማጠናከሩን አስታውቋል፡፡ የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን አብረሃም መሥሪያ ቤታቸው በጥራት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ላይ እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ባለሥልጣኑ በአፍዴራና በሌሎችም ጣቢያዎች ያሰማራቸው ኢንስፔክተሮች ፈጣን የመመርመሪያ መሣሪያ እንዳላቸውና ጥብቅ ፍተሻ እንደሚያደርጉ አቶ ሳምሶን ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አዮዲን ያልተቀላቀለበት ጨው ለኅብረተሰቡ ፍጆታ እንዲውል ለሽያጭ ሊያቀርቡ ሲሉ እየተያዙ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ጨው የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከላይ የተጫኑት ጆንያዎች አዮዲን ያለው ጨው የያዙ ሆነው ከታች ግን አዮዲን ያልተቀላቀለበት ጨው የያዙ ጆንያዎች ተጭነው እንደተገኙ አስረድተዋል፡፡ ለፋብሪካዎች በግብዓትነት የሚቀርበው ጨው አዮዲን ያልተደባለቀ እንደሆነ፣ አምራቾችና ነጋዴዎች ለፋብሪካዎች አዮዲን የሌለው ጨው ማቅረብ እንደሚችሉ የገለጹት አቶ ሳምሶን፣ ይህን ለማድረግ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የድጋፍ ደብዳቤ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ የድጋፍ ደብዳቤውን በፍተሻ ኬላዎች ላይ እያሳዩ ለፋብሪካዎች ምርታቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ለፋብሪካ በጥሬ ዕቃነት የሚቀርብ በማስመሰል ለምግብነት ፍጆታ የሚውል ጨው (አዮዲን የሌለው) ለገበያ ለማቅረብ ጥረት ሲደረግ እየተያዘ እንደሆነ አቶ ሳምሶን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይህን ችግር ለመፍታት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከንግድ ሚኒስቴርና ከሌሎች የዘርፉ መሥሪያ ቤቶች ጋር ሆነን የመቆጣጠር ሥራ እያከናወንን ነው፤›› ብለዋል፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት 40 ተሽከርካሪዎችም አስፈላጊው የምርመራ ሥራ ተካሂዶ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡
ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ባህላዊ የጨው አምራቾች ጨውን ከአዮዲን ጋር የሚያደባልቁበት መንገድ ነው፡፡ አምራቾቹ አዮዲኑን በጨው ላይ በነሲብ የሚረጩት በመሆኑ አዮዲኑ ከጨው ጋር በአግባቡ በሚፈለገው መጠን አይዳረስም፡፡
‹‹በባህላዊ መንገድ የሚመረተው ጨው የማቀላቀል ሁኔታ ላይ ችግር ይከሰታል፡፡ የአዮዲን ይዘት የማነስና የመብዛት ሁኔታዎች እንዳሉ በቁጥጥር ሥራ ወቅት አይተናል፤›› ብለዋል አቶ ሳምሶን፡፡
አዮዲን ለጤና አስፈላጊ የመሆኑን ያህል ከሚፈለገው (በደረጃ ከተቀመጠው) መጠን በላይ ሲገኝ ደግሞ ለሰውነት መርዛማ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ዘመናዊ የገበታ ጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ሊበረታቱ እንደሚገባ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ፡፡
በባህላዊ አምራቾች በኩል የታየውን አዮዲን የመቀላቀል ድክመት ለማረም የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ከሕፃናት መርጃ ድርጅትና ማይክሮ ኒዩትረንት ኢንሼቲቭ ተራድኦ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ባህላዊ የጨው አምራቾች ማኅበራት የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ሆነን ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየሠራን ነው፡፡ ነገር ግን የአዮዲን መጠኑ ከፍና ዝቅ የማለት ሁኔታ አሁንም እያየን ነው፤›› ብለዋል፡፡
በተቻለ መጠን አዮዲን የተቀላቀለበት ምርት እንዲያቀርብ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሆነ፣ ይህን ለማረጋገጥ በመግቢያና በመውጪያ ኬላዎች በመሣሪያዎች የታገዙ ጥብቅ ፍተሻ በማድረግ ላይ መሆኑን ባለሥልጣኑ ይገልጻል፡፡ የጨው ምርት ዋና ሥራ በሚካሄድበት አፍዴራ ባለሥልጣኑ ክትትል ያደርጋል ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሳምሶን፣ በአፍዴራ የጨው ምርት ሒደት ላይና የማከማቸት ሒደት ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
‹‹የምርት ሒደት እናያለን፡፡ አዮዲን እንዴት እንደሚቀላቅሉ ከደኅንነት አኳያ እናያለን፡፡ ምርቱን እንዴት እንደሚያከማቹ እናያለን፡፡ ነገር ግን ቁጥጥራችን የተሟላ ነው ማለት አይቻልም፡፡ እኛ እያንዳንዱ ምርት ላይ በየጊዜው በየሰዓቱ እዚያው ቆይተን መመርመር አንችልም፡፡ ያን ማድረግ ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን በተወሰነ ጊዜ የፍተሻ ሥራ እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ማኅበራቱ ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱ ከክልሉ መንግሥት ጋር የተለያዩ ውይይቶች እየተካሄዱ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ‹‹የእኛ ሚና አዮዲን የተቀላቀለበት ጨው አስመልክቶ በወጡ ደንቦች ላይ ማብራሪያ መስጠት፣ የተመጠነ የአዮዲን ይዘት የሌለው ጨው የሚፈጥረውን ጉዳቶች ማስረዳት፣ በምርት ሒደትና በአከመቻቸት ላይ የሚታዩ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ ማድረግ፣ የአቅም ችግር ካለ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ድጋፍ መስጠት ነው፤›› ብለዋል፡፡
ዘመናዊ የገበታ ጨው ማምረቻ ፋብሪካዎች መቋቋም እንደሚበረታታ የገለጹት አቶ ሳምሶን የጨው ጥራትን ከፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ከጥራት ባሻገር በጨው ምርትና ንግድ ዙሪያ ያለው ሥጋት ከገበያው ፍላጎት በላይ የማምረት ጉዳይ ነው፡፡ በአፍዴራ ሐይቅ ዙሪያ በርካታ የጨው አምራች ማኅበሮችንና ነጋዴዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በሚደረገው የገበያ ሽሚያ ከአገሪቱ ዓመታዊ የጨው ፍጆታ በላይ ከሐይቁ እየተመረተ ጥቅም ላይ ሳይውል በሐይቁ አቅራቢያ ተከማችቶ እንደሚታይ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
አላቂ የተፈጥሮ ሀብት በመሆኑ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው፡፡ ፌዴራል መንግሥት ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር ለጉዳዩ እልባት ሊያበጅለት ይገባዋል ብለዋል፡፡ በአማካይ 25 ሜትር ጥልቀት ያለው የአፍዴራ ሐይቅ በ116.8 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ የተንጣለለ ነው፡፡ በሐይቁ ውስጥ የሚገኘው የጨው ክምችት 290 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ይገመታል፡፡  Read more here

No comments:

Post a Comment