Monday, December 5, 2016

የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ አመራሮቹን እያወዛገበ ነው

‹‹የሰማያዊ ፓርቲ ሕጋዊ ሊቀመንበር እኔ ነኝ››  ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት
‹‹ጉባዔው የምርጫ ቦርድ ተወካይ ባለበት የተካሄደና ሕጋዊ ነው››  አዲስ የተመረጡት የፓርቲው ሊቀመንበር
ሰማያዊ ፓርቲ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን አድርጎ ቀድሞ የነበሩ የፓርቲውን ሥራ አስፈጻሚዎች በመሻር አዲስ ሥራ አስፈጻሚዎች መመረጣቸው ቢገለጽም፣ ነባር የፓርቲው አመራሮች ደግሞ ድርጊቱ ሕገወጥና ምርጫው የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ የጣሰ መሆኑን በመግለጽ እየተወዛገቡ ነው፡፡
በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ወይም የኦዲት ምርመራ ኮሚሽኑ ሊጠራ እንደሚችል በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መደንገጉን፣ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የተጠራው ጠቅላላ ጉባዔ በኦዲት ምርመራ ኮሚሽኑ የተጠራ ቢሆንም ሕገወጥ መሆኑን ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ይናገራሉ፡፡
የጠቅላላ ጉባዔው ሕገወጥ መሆን የሚጀምረው ከአካሄድ ጀምሮ መሆኑን የሚናገሩት ኢንጂነሩ፣ ጉባዔው መካሄድ ያለበት የምክር ቤቱ አባላት ሲሟሉ ወይም ከግማሽ በላይ ሲገኙና ኮረም መሟላቱ ተረጋግጦ ነው፡፡ ነገር ግን አዲስ አመራር ነኝ የሚለው አካል ከግማሽ በታች ማለትም ከ226 የምክር ቤት አባላት ውስጥ የምርጫ ቦርድ ታዛቢና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችን ጨምሮ በ75 ሰዎች ስብሰባው መካሄዱን ኢንጂነር ይልቃል ገልጸዋል፡፡
ኮረም ካልሞላ የምርጫ ቦርድ ተወካይ እንዴት ተቀምጦ ምርጫውን ሊያስፈጽም እንደቻለ ሲጠየቁ፣ ‹‹እኔንም የገረመኝ እሱ ነው፡፡ ሊቀመንበሩ ባልፈረመበት የጥሪ ደብዳቤ መገኘት እንደማይቻል ቦርዱ እያወቀ፣ ሌላ አካል ሲጠራው እንዴት ሊገኝ እንደቻለ የሚገርም ከመሆኑም በላይ የሚያጠያይቅም ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሌላው ጉባዔ ሲደረግ ወጪ እንዳለው የሚናገሩት ኢንጂነሩ፣ ወጪ የሚያፀድቀው የፓርቲው ሊቀመንበር (እሳቸው) ቢሆኑም፣ ጉባዔው በምን ወጪና ማን እንዳፀደቀው ጭምር ሁሉንም ማብራሪያ በማከል ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ ማቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡
ጠቅላላ ጉባዔው ሕጋዊ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ለምን እንደሚናገሩ ያስረዱት ኢንጂነር ይልቃል፣ ጉባዔውን አካሂደናል የሚሉት አካላት ሕጋዊ ከሆኑ ለምን በቢሮአቸው እንዳላደረጉና የመኢአድን ቢሮ እንደመረጡ ጥያቄ እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡
በፓርቲው አመራሮች መካከል ያለው ዋናው ችግርና ልዩነት ምን እንደሆነ የተጠየቁት ኢንጂነሩ፣ እሳቸው እስከሚያውቁትና እስከ 2008 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡ ለፓርቲው ሥራ ወደ ውጭ በሄዱበት ወቅት በዚያው ይቀራሉ ብለው ያሰቡ አባላት ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ ሲዘጋጁ በመድረሳቸው፣ ሁሉንም ነገር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሪፖርት በማድረጋቸው ጉባዔው እንዲራዘም መደረጉን ገልጸዋል፡፡ አባላቱ ያሰቡት ነገር ባለመሳካቱ ቢሮ መስበርና ንብረቶችን መውሰድ የመሳሰሉትን ከአንድ የፓርቲ አባል የማይጠበቅ የወረደ ተግባር በመፈጸማቸው ጉዳዩን ወደ ሕግ (ፖሊስ ጣቢያ) በመውሰድ ሥራቸውን የቀጠሉ ቢሆንም፣ በድጋሚ ኅዳር 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ሌሊቱን የቢሮውን ጥበቃ በማባረር ቢሮአቸውን በወረራ መያዛቸውን አስረድተዋል፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር ደብዳቤ ሳይጽፍለት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ምንም ማድረግ የሌለበት ቢሆንም፣ የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ግን አዲሱ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ትክክል እንደሆነ ለመገናኛ ብዙኃን እየገለጹ ያለበት ሁኔታ በድጋሚ ሕገወጥና ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃናን አነጋግረዋቸው፣ አዲሱ አመራር ያቀረበውን የጉባዔ ሪፖርትና እሳቸው ያቀረቡትን አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ እንደሚሰጡ ስለገለጹላቸው ውሳኔውን እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ግን ከሥልጣኑ ውጪ የቦርዱን መሪ ሐሳብ የሚያስለውጥ አቅጣጫና ጫና ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት ተገቢ አለመሆኑን አክለዋል፡፡
የሕጋዊነት ጥያቄ እሳቸው ስለፈለጉ ወይም ስላልፈለጉ የሚመጣ ጉዳይ ሳይሆን፣ ‹‹የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይልቃል ጌትነት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ነው ብሎ የሰጠውን ዕውቅና መሻር የሚችለውም እሱና እሱ ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ይኼ ሒደት ሳይጠናቀቅ ማንም ተነስቶ ሊቀመንበር ነኝ ሊል እንደማይችልም ተናግረዋል፡፡
ሕግ ካለ ድርጊቱ ሁሉ (የአዲሱ አመራር አካሄድ) ሕገወጥ እንደሆነ መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆናቸውን የተናገሩት ኢንጂነሩ፣ ከዚህ በፊት ብዙ ጉድ ስለታየ ውጤቱን ቀድሞ መተንበይ ቢያስቸግርም እሳቸውም ሆኑ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና አመራሮች እየጠበቁ የሚገኙት የቦርዱን ውሳኔ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ቦርዱ አዲሱን አመራር የሚቀበል ከሆነ ምን ለማድረግ እንዳሰቡ የተጠየቁት ኢንጂነር ይልቃል፣ በአገሪቱ ፓርቲ እንደ አሸን በፈላበት ሁኔታ ፈጥነው ፓርቲ ወደማቋቋም ባይሄዱም፣ ከአባላቱ ጋር ሆነው ሊሠሯቸው የሚችሉ ብዙ አማራጮች እንዳሏቸው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የቦርዱ ውሳኔ ሕጉን ተከትሎ ከተፈጸመ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበርና አባላት እሳቸውና እሳቸው የሚመሩት አካል እንደሆነ በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡ የታሰሩ ሰዎችና በስብሰባው ላይ ያልተገኙ ከአምስት በላይ የሚሆኑ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የቀረቡበት የጠቅላላ ምርጫ ሒደት፣ ተቀባይነት ይኖረዋል የሚል ምንም ዓይነት ጥርጣሬ እንደሌላቸው ደጋግመው ተናግረዋል፡፡
ኢንጂነር ይልቃል 154 ሺሕ ብር ይዘው ጠፍተዋል ስለመባሉ ተጠይቀው፣ ‹‹አንድ የፓርቲ መሪ ፓርቲውን የመሠረተና ብዙ ልምድና ዕውቀት ያለው ይኼንን ተግባር ይፈጽማል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ለእኔ ልጄ ነው፤›› ብለው፣ ሰማያዊ ፓርቲ አሁን ላለው ተቀባይነትና ለደረሰበት ደረጃ ብዙ አስተዋጽኦ ያደረጉት እሳቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስላገራቸው እንዲያስቡ፣ ትግል ውስጥ ገብተው በመታገላቸው እንዲታሰሩ በማድረጉ ኃላፊነት ያለበትን ሰው 154 ሺሕ ብር ወስዷል ብሎ ለመወንጀል መሯሯጥ፣ ራስን ትዝብት ላይ መጣል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የእሳቸው ራዕይ ከአባላትና ከተለያዩ ደጋፊዎች የተገኘን ገንዘብ መውሰድ ሳይሆን፣ የቆሙለትን ፖለቲካዊ ዓላማ ጫፍ ማድረስና የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ማሟላት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡ የፓርቲ አባላትን ሽኩቻ መስማት ስለሰለቸው የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመጨረስ ከማሰብ እንጂ፣ አንዳንድ አባላት እየፈጸሙ የሚገኘውን ሕገወጥ አካሄድ ምላሽ መስጠት አቅቷቸው እንዳልሆነም አክለዋል፡፡ በቀጣይ በሕግ አግባብ እንደሚሄዱበትም ገልጸዋል፡፡
መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ሰማያዊ ፓርቲ ያደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ሕጋዊና ትክክለኛ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ፣ በጉባዔው የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው እንደተመረጡ የሚናገሩት አቶ የሺዋስ አሰፋ ናቸው፡፡ ‹‹ከተባረረ ወይም መባረር ከማይፈልግ ሰው ሌላ ምን ይጠበቃል?›› በማለት የኢንጂነር ይልቃልን ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር እኔ ነኝ›› ንግግርን የሚያጣጥሉት አቶ የሺዋስ፣ ማንኛውም ነገር የተደረገው የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ በጠበቀና ሕጋዊ በሆነ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውን በመኢአድ ቢሮ ያደረጉትም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት አዳራሽ መከራየት ባለመቻላቸውና የተሻለ አዳራሽ በማግኘታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ኃላፊ አቶ አበራ ገብሩ እንዳብራሩት፣ ኢንጂነር ይልቃል እንዳሉት ጉባዔው የተካሄደው ኮረም ሳይሟላ ሳይሆን ሁሉም ነገር ሕጉንና የፓርቲውን ደንብ ተከትሎ ነው፡፡ የምርጫ ቦርድ ታዛቢ በተገኙበትና ሌሎች ተጋባዥ የፓርቲ አመራሮች በተገኙበት መካሄዱን ገልጸዋል፡፡ ደብዳቤ አጻጻፍን በሚመለከት በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ሌሎች ሥራ አስፈጻሚዎችም መጻፍ እንደሚችሉና በዚያ መሠረት የጉባዔውን ታዳሚዎች መጥራታቸውን አክለው፡፡
ለጉባዔው ወጪ የተደረገውን ገንዘብ በሚመለከት በውጭ አገር የሚገኙ የፓርቲው ደጋፊ አካላት ልከውላቸው መሆኑን፣ ይኼንንም ለኢንጂነር ይልቃል በደብዳቤ እንደገለጸላቸው አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሁሉንም ነገር እንደተቀበላቸውና ግንኙነቱ ከአዲሱ አመራር ጋር እንደሆነ አቶ አበራ ገልጸዋል፡፡  Read more here

No comments:

Post a Comment