Sunday, November 13, 2016

ተቃዋሚዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ለጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ ፃፉ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ወዲህ ማናቸውንም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻልንም ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአቤቱታ ደብዳቤ ለጠ/ሚኒስትሩ መፃፋቸውን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ 

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ሰማያዊ ፓርቲ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በዕለት ተዕለት የፓርቲ ሥራቸው ላይ ችግር እንደፈጠረባቸው አዋጁን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ለጠ/ሚኒስትሩ የአቤቱታ ደብዳቤ ፃፉ መድረክ በበኩሉ፤ ለኮማንድ ፖስቱ ላቀረበው ማብራሪያ ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን ገልጿል፡፡ 

መኢአድ ለጠ/ሚኒስትሩ በፃፈው ደብዳቤ፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሀገሪቱ ለተፈጠሩት ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ያስገኛል የሚል እምነት እንደሌለው ጠቁሞ በተለይ ህዝባዊ ስብሰባ አለመፈቀዱና ፓርቲዎች ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት መከልከላቸው መደበኛ የፖለቲካ ስራ እንዳይሰሩ የሚገድብ በመሆኑ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀምና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ የተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ይሰጠን ሲል ጠይቋል፡፡ 
አዋጁ ሲወጣም በሀገሪቱ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ሃሳባቸው መጠየቅና ምክክር መደረግ ነበረበት ብሏል መኢአድ፡፡ 

ሠማያዊ ፓርቲ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሁለት ደብዳቤዎችን የፃፈ ሲሆን ለመርማሪ ቦርዱ በፃፈው ደብዳቤ፤ 3 የፖለቲካ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ 23 አባላቱ መታሰራቸው እንዳስጨነቀው በመጥቀስ ከእስር እንዲለቀቁለት ጠይቋል፡፡ የታሰሩ ሰዎች ስም ዝርዝር በአንድ ወር ጊዜ ውስት ይፋ ይደረጋል ተብሎ መዘግየቱ እንዳሳሰበውም ፓርቲው በዚሁ ደብዳቤው ገልጿል፡፡ 

ፓርቲው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፈው ደብዳቤ፤ አራት ነጥቦችን ዘርዝሮ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ 
የተያዙ ሰዎች መብትን በተመለከተ ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው የሚለው የህገ መንግስቱ አንቀፅ በዚህ አዋጅ የተሰረዘ ስለመሆኑና አለመሆኑ፤ ግጭቱ የተፈጠረው በአማራና በኦሮሚያ ክልል ሆኖ ሳለ፣ እንዴት በመላ ሀገሪቱ የሚፀና አዋጅ እንደታወጀ፣ እንዲሁም በአዋጁ ለፀጥታ ኃይሉ ስለተሰጠው ስልጣንና የፖርቲዎች የመደራጀት መብት በአዋጁ መሻር አለመሻሩን፣ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጠው መጠየቁን ጠቁሟል፡፡ 
መድረክ በበኩሉ፤ የዛሬ ሁለት ሳምንት ለኮማንድ ፖስቱ በአዋጁ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠው በደብዳቤ መጠየቁን አስታውሶ፣ እስካሁን ግን ምላሽ አልተሰጠኝም ብሏል፡፡ 

በሌላ በኩል ኢዴፓ ከትናንት በስቲያ በጊዮን ሆቴል በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሊሰጠው የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከኮማንድ ፖስቱ የፍቃድ ደብዳቤ በመጠየቁ ሊደናቀፍ እንደቻለ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡  Read more here

No comments:

Post a Comment